No summary available.
ጥር 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ - ነ/ፈጅ ትዕግስት አሸናፊ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ገ/ሥላሴ በርሄ - የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቶአል።
ጉዳዩ በውሉ በተመለከተው መሰረት አልተከፈለም የተባለን በብድር የተሰጠ ገንዘብ ከማስመለስ ጋር የተያያዘ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ተከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ በብድር የወሰዱትን ገንዘብ ባለመክፈላቸው ከሳሽ የነበረው የአሁኑ አመልካች ያቀረበውን ክስ ተከሳሽ ቀርበው ባለመከላከላቸው የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ጉዳዩን ተከሳሽ በልሉበት አይቶ ዋናውን ገንዘብ እና ወለዱን ጨምሮ በድምሩ ብር 300,109.15 ከ 29/05/2000 ዓ.ም. ጀምሮ ከሚታሰብ ወለድ ጋር ለከሳሽ እንዲከፍሉ በ26/02/2001 ዓ.ም. ውሳኔ በመስጠት እና በ19/11/2002 ዓ.ም. ደግሞ የብር 6,294.30 የወጪና ኪሳራ ውሳኔ በመስጠት መዝገቡን ከዘጋ በኃላ ተከሳሽ ክርክሩ በልሉበት ተሰምቶ ውሳኔ የተሰጠባቸው መጥሪያው በመደበኛ መኖሪያ አድራሻቸው በአግባቡ እንዲደርሳቸው ሳይደረግ መሆኑን ገልጸው ውሳኔው ተነስቶ ክርክራቸውን ለማቅረብ እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ ውሳኔው ተነስቶ የጽሁፍ መልሳቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶአቸው የነበረ መሆኑን፣ይሁን እንጂ ተከሳሽ በቀጠሮው ዕለት መልስ ባለማቅረባቸው መብታቸው ታልፎ ክሱን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ የተያዘ መሆኑን፣ክሱን ለመስማት በተያዘው ቀጠሮም ሳይቀርቡ በመቅረታቸው ጉዳዩ በድጋሚ በልሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ የተሰጠ መሆኑን ፣ከዚህ በኃላ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ በህግ ግምት የሚሸፈን የፍሬ ነገር ክርክርን ተከራካሪ ወገኖች ባያነሱትም ግምቱን ፍ/ቤቱ በራሱ ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚገባው፣እስከ ሁለት ዓመት ያልተከፈለ የወለድ ገንዘብ እንደተከፈለ የሚቆጠር ስለመሆኑ በፍ.ሕ.ቁ. 2024(1) ስር የተመለከተው ግምት በባንክ በሚሰጥ ብድር ጉዳይም ተፈጻሚነት ያለው ስለመሆኑ የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 29181 በ20/04/2002 ዓ.ም. አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እንደሰጠ እና ይህንን የሕላና ግምት ለማፍረስ ከሳሽ በፍ.ሕ.ቁ. 2473(2) መሰረት ያቀረበው ማናቸውም ዓይነት ማስረጃ እንደልለ ገልጾ ተከሳሽ ከዋናው ዕዳ ያልተከፈለውን ብር 41,391.50 እና ለኢንሹራንስ የተከፈለውን ብር 19,586.87 ከወለድ እና ከቅጣት ወለድ ጋር ለከሳሽ እንዲከፍሉ እና የወጪና ኪሳራ መጠኑንም ከቀድሞው ዝቅ በማድረግ በ22/02/2004 ዓ.ም. ውሳኔ መስጠቱን፣በከሳሽ ጠያቂነት የይግባኝ ክርክሩን የሰማው ፍ/ከ/ፍ/ቤት በበኩሉ የስር ተከሳሽ ወደ ክርክሩ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ቢሆንም በጽሁፍም ሆነ በቃል ያቀረቡት ክርክር በልለበት ሁኔታ የስር ፍ/ቤት የቀድሞ ውሳኔውን እራሱ በመለወጥ የሰጠው ውሳኔ ስነ ስርዓታዊ አይደለም በማለት ውሳኔውን ሽሮ በቀድሞው ውሳኔ መሰረት አፈጻጸሙ እንዲቀጥል ውሳኔ መስጠቱን እና በመጨረሻም በስር ተከሳሽ ጠያቂነት የይግባኝ ክርክሩን የሰማው የፍ/ጠ/ፍ/ቤት የቀድሞው ውሳኔ የተነሳ በመሆኑ ጉዳዩን እንደገና ከመመርመር የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤትን የሚያግደው ነገር እንደልለ ገልጾ የከ/ፍ/ቤት ውሳኔ በመሻር የፍሬ ነገር ክርክሩን መርምሮ ይወስን ዘንድ ጉዳዩን በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 343(1) መሰረት ለፍከ/ፍ/ቤት በመመለስ ውሳኔ መስጠቱን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።
አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረበው የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ ተጠሪ ብር 300,109.15 ከነወለዱ እንዲከፍሉ ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ በልለሁበት የተሰጠው ውሳኔ ይነሳልኝ በማለታቸው ውሳኔው ቢነሳም ተጠሪ የጽሁፍም ሆነ የቃል ክርክር ላሰማ በተቀጠረበት ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ፍ/ቤቱ ጉዳዩን በድጋሚ በልሉበት አይቶ ተጠሪ በፍ.ሕ.ቁ. 2024(1) በተመለከተው የሕላና ግምት ተጠቃሚ ላሆኑ ይገባል በማለት የወለድ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ ዋናውን ዕዳ ብቻ እንዲከፍሉ ሲወስን ቀደም ብሎ አመልካች የወለድ አሰላሉን በተመለከተ ያያዘውን ሰነድ ሳይመለከት የማለፉን አግባብነት ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር የተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በዚህ ችሎት ምላሽ ማግኘት የሚገባው ነጥብ ተከሳሽ በልሉበት በመጀመሪያ ተሰጥቶ የነበረው ውሳኔ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 78(2) መሰረት ተነስቶ ተከሳሽ ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ትዕዛዝ ከተሰጠ በኃላ የጽሁፍ መልስ ሳያቀርቡና ክሱ ላሰማ በተያዘው በቀጠሮም ሳይቀርቡ ከቀሩ በድጋሚ በልሉበት ታይቶና ተመርምሮ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት ከሚሆን በስተቀር የተነሳው ውሳኔ ተመልሶ እንዲጸና የሚደረግበት አግባብ የለም ሲል የፍ/ከ/ፍ/ቤት ውሳኔን በመሻር የፍሬ ጉዳይ ክርክሩን መርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን ለፍ/ከ/ፍ/ቤት በመመለስ የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ነው ለማለት ይቻላል ወይስ አይቻልም? የሚል ጭብጥ መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን ከዚሁ ጭብጥ አንፃር መርምረናል።
No topics extracted.
በዚህም መሰረት አንድ ተከሳሽ በክርከሩ ላይ ቀርቦ መልስ ሳይሰጥ ወይም ተገቢውን መከራከሪያ ሳያቀርብ በመቅረቱ በልለበት አንድ ውሳኔ ወይም ትእዛዝ የተሰጠ ሲሆን ውሳኔው ወይም ትእዛዙ መሰጠቱን በተረዳው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቀርቦ ትዕዛዙ ወይም ውሳኔው እንዲነሳለት ላያመለክት እንደሚችል እና ፍ/ቤቱም የልላኛውን ወገን አስተያየት ከሰማ በኃላ የአመልካቹን አቤቱታ ተገቢ አድርጎ ከተቀበለው ውሳኔውን በማንሳት ክርክሩ እንደገና የሚሰማበትን ቀነ ቀጠሮ እንደሚሰጥ በፍ.ስ.ስ.ህ.ቁ. 78 ተመልክቶአል።በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ በልሉበት ታይቶ የተሰጠባቸው ውሳኔ ተነስቶ ክርክራቸውን ለማቅረብ እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ ውሳኔው ከተነሳ እና ክርክሩን እንደገና ለመቀጠል ቀጠሮ ከተያዘ በኃላ የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ተጠሪ በልሉበት የአመልካችን ክስ እና ማስረጃ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት የቻለው ተጠሪ በጽሁፍም ሆነ በቃል ክርክራቸውን ለመስማት በተሰጠው ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ክርክሩን በድጋሚ በልሉበት በማየት ነው።በመሰረቱ አንድ ተከሳሽ በልለበት ታይቶ የተሰጠበት ውሳኔ ተነስቶ ክርክሩን ለማሰማት እነዲፈቀድለት ጠይቆና ተፈቅዶለት ለጹፍም ሆነ ለቃል ክርክር በተያዘው ቀጠሮ በድጋሚ ሳይቀርብ ከቀረ ፍ/ቤቱ ክርክሩን መምራት የሚገባው በምን ዓይነት ስርዓት እንደሆነ የስነ ስርዓት ሕጉ በግልጽ ያስቀምጠው ነገር የለም።ይሁን እንጂ ፍ/ቤቱ ተጠሪ ክርክሩን እንደገና ለማየት የሚያስችል በቂ ምክንያት ያቀረቡ መሆኑን አረጋገግጦ የቀድሞውን ውሳኔ ያነሳው እስከሆነ ድረስ ተጠሪ ክርክራቸውን እንዲያቀርቡ በድጋሚ በተሰጣቸው ዕድል ተጠቃሚ ሳይሆኑ ከቀሩ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 70(ሀ) በተመለከተው አጠቃላይ ድንጋጌ እና ክርክሩን እንደገና ለመስማት በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት የአመልካች ክስ እና ማስረጃ እንደገና ተመርምሮ ተገቢው ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚደረግ ከሚሆን በስተቀር እንዲነሳ አስቀድሞ ትዕዛዝ የተሰጠበት የቀድሞ ውሳኔ በቀጥታ ተመልሶ እንዲፀና ላደረግ የሚችልበት የሕግ አግባብ አይኖርም።የከሳሽ ወገን ክስ እና ማስረጃ እንደገና ተመርምሮ የሚሰጠው ውሳኔ ደግሞ እንደነገሩ ሁኔታ ከበፊቱ ውሳኔ ጋር ተመሳሳይ ወይም የተለየ ላሆን ይችላል።በመሆኑም ተከሳሽ ወገን የቀድሞውን ውሳኔ ለማሰለወጥ የሚችል የጽሁፍም ሆነ የቃል ክርክር ያላቀረበ አስከሆነ ድረስ የከሳሽ ወገንን ክስ እና ማስረጃ እንደገና መመርመር ሳያስፈልግ የተነሳው የቀድሞ ውሳኔ ተመልሶ እንዲጸና መደረግ ነበረበት በማለት አመልካች ቀረበውን ክርክር ሕጋዊ መሰረት ያለው ሆኖ አላገኘነውም።
ሲጠቃለል ተጠሪ በልሉበት በመጀመሪያ ተሰጥቶ የነበረው ውሳኔ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 78(2) መሰረት ተነስቶ ተጠሪው ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ትዕዛዝ ከተሰጠ በኃላ የጽሁፍ መልስ ሳያቀርቡና ክሱ ላሰማ በተያዘው በቀጠሮም ሳይቀርቡ ከቀሩ በድጋሚ በልሉበት ታይቶና ተመርምሮ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት ከሚሆን በስተቀር አስቀድሞ የተነሳው ውሳኔ ተመልሶ እንዲጸና የሚደረግበት አግባብ አለመኖሩን ገልጾ የፍ/ከ/ፍ/ቤት ውሳኔን በመሻር እና የፍሬ ጉዳይ ክርክሩን መርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን ለፍ/ከ/ፍ/ቤት በመመለስ የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስሕተት የተፈጸመበት ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።
የስር ተከሳሽ ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ትዕዛዝ ከተሰጠ በኃላ በጽሁፍም ሆነ በቃል ያቀረቡት ክርክር በልለበት ሁኔታ የስር የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት የቀድሞ ውሳኔውን እራሱ በመለወጥ በመቁ.114956 በ22/02/2004 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ ስነ ስርዓታዊ አይደለም በማለት ውሳኔውን ሽሮ በቀድሞው ውሳኔ መሰረት አፈጻጸሙ እንዲቀጥል የፍ/ከ/ፍ/ቤት በመ.ቁ.118042 በ08/12/2004 ዓ.ም. የሰጠውን ውሳኔ በመሻር ተጠሪው ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ትዕዛዝ ከተሰጠ በኃላ የጽሁፍ መልስ ሳያቀርቡና ክሱ ላሰማ በተያዘው በቀጠሮም ሳይቀርቡ ከቀሩ በድጋሚ በልሉበት ታይቶና ተመርምሮ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሚሰጥበት ከሚሆን በስተቀር አስቀድሞ የተነሳው ውሳኔ ተመልሶ እንዲጸና የሚደረግበት የሕግ አግባብ አለመኖሩን ገልጾ የፍ/ከ/ፍ/ቤት በፍሬ ጉዳዩ ረገድ የይግባኝ ክርክሩን መርምሮ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩን በፍ.ስ.ስ.ህ.ቁ. 343(1) መሰረት ወደ ፍ/ከ/ፍ/ቤት በመመለስ የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 82803 በ21/06/2005 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 348(1) መሰረት ፀንቶአል።
የውሳኔው ግልባጭ ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል።