No summary available.
ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሀመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- አቶ ፍፁም ብርሃን ገ/ክርስቶስ ተጠሪ፡- የለም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ለዚህ ችሎት የቀረበው አመልካች ፍርድ ቤትን የመድፈር የወንጀል ድርጊት ፈፅመዋል ተብሎ በፈድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 481 አግባብ የጥፋተኝነትና የአምስት ቀን ቀላል እስራት መወሰኑም ሆነ በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ይኼው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መፅናቱ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት አመልካች ስለአመለከቱ ነው።
አመልካች ሐምል 26 ቀን 2005 ዓ/ም በፃፉት ሁለት ገፅ የሰበር አቤቱታ በጉዳዩ ላይ የነበረውን ሂደትና ጉዳዩ በችሎት መድፈር የማያስጠይቃቸው መሆኑን ዘርዝረው የበታች ፍርድ ቤቶቸ ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተተ ያለበት በመሆኑ እንዲሻርላቸው ወይም የእስራት ቅጣቱ በገንዘብ መቀጮ እንዲቀየርላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል።እኛም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተተ ተፈፅሟል ለማለት ይቻላል? ወይስ አይቻልም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምረናል።
የሥር ፍርድ ቤት አመልካችን በፍርድ ቤት መድፈር የወንጀል ድርጊት እንዲቀጡ ትዕዛዝ ላሰጥ የቻለው ፍርድ እየተነበበ ባለበት ሰዓት ትዕዛዙ በተሰጠበት መዝገብ ተከሳሽ የሆነው ድርጅት ካልብ ሆቴል ጠበቃ የሆኑት የአሁኑ አመልካች ስልክ በማስጮህ እንደሁም ከሳሽ ከሆኑት ግለሰብ ከአቶ ሀብታሙ በላይ ጋር ያልተገባ ክርክር በመፍጠር ፍርድ ቤቱ ስነ ስርዓት እንዲይዙ ቢያሳውቃቸውም ስነ ስርዓት ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው፣እንዲሁም ፍርድ ቤቱ በስነ ስርዓት ያናግረን በሚል ያልተገባ ባህርይ ማሳያታቸውን፣ከዚህም በተጨማሪ በችሎት ውስጥ ስልክ ማስጮህ እንደማይቻል ተገቢው ማስታወቂያ ተለጥፎ እያለና አመልካችም የሕግ ባለሙያ ሁነው እያለ የችሎቱን ስርዓት ያወኩ መሆኑን በመግለፅ ሲሆን እነዚህ የፍሬ ነገር ነጥቦች መኖራቸውን ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያለው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሙሉ በሙሉ ተቀብሎአቸዋል።ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው አመልካች በችሎት መድፈር ወንጀል ላቀጡ የቻሉት ስልክ በማስጮሃቸው ብቻ ሳይሆን ፍርድ ቤቱ ስነ ስርዓት እንዲይዙ አሳውቆአቸው ስነ ስርዓት ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረትና ፍርድ ቤቱ በስነ ስርዓት ያናግረን በሚል ያልተገባ ባህርይ ሁሉ ለችሎቱ በማሳየታቸው መሆኑን ጭምር ነው።ትዕዛዙን የሰጡት ዳኛም በጊዜው በፍርድ ማንበብ ስራ ላይ እንደነበሩ በመዝገቡ ላይ የሰፈረ ጉዳይ ነው።
እንግዲህ ይህ ችሎት በኢ.ፍ..ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 የተሰጠው ስልጣን ፍሬ ነገርን የማጣራት ወይም ማስረጃን የመመዘን ጉዳይ ያለመሆኑ የሚታወቅ በመሆኑ ከላይ የተገለፁትን ፍሬ ነገሮችን እንዳሉ የምንቀባላቸው ይሆናል። ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው ደግሞ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ አመልካች በችሎት ውስጥ ሞባይል ስልክ አስጩኸዋል ተብለው በዚህ ድርጊት መነሻነት ከልላኛው ተከራካሪ ወገን ጋር በተደረገ የቃላት ልውውጥ መነሻነት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 449(1(ሀ)) እንዲቀጡ መደረጉ በአግባቡ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ተብሎ የተያዘው ጭብጥ በስር ፍርድ ቤት አመልካች ከችሎቱ ዳኛ ስነ ስርዓት እንዲይዙ የተነገራቸውን ትዕዛዝ ሳያከብሩ መቅረታቸውን እንዲሁም ችሎቱንም በስነ ስርዓት ያናግረን በማለት ያልተገባ ባህርይ ማሳየታቸውን የስር ፍርድ ቤት የመዘገበውን ፍሬ ነገር ባግባቡ ያላገናዘበ በመሆኑ ይህ ችሎት የሚቀበለው ሁኖ አልተገኘም።አመልካች ፍርድ ቤቱ ፍርድ በሚያነብበት ጊዜ ስነ ስርዓት እንዲይዙ የተነገራቸውን ትዕዛዝ ያለማክበራቸውንና "ፍርድ ቤቱን በስነ ስርዓት ያናግረን" በሚል ያልተገባ ባህርይ ማሳየታቸው የፍርድ ስራ በሚከናወንበት ጊዜ ፍርድ ቤቱን ማወካቸውን የሚያሳይ እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 481 አግባብ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 449(1(ሀ)) ድንጋጌ ስር ተጠያቂነት የሚያስከትል ተግባር ነው ከሚባል በስተቀር ልላ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም።በመሆኑም የአመልካች የሰበር አቤቱታ ይዘትና የሰበር አጣሪ ችሎት ጭብጥ በስር ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አሰጣጥ መነሻ የሆኑትን ፍሬ ነገሮችን ሙሉ በሙሉ መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ተገቢነት የልለው ሁኖ ተገኝቷል።ቅጣቱን በተመለከተም አመልካች በገንዘብ መቀጮ እንዲቀየርላቸው ያቀረቡት ጥያቄ የመሰረታዊ ሕግ መመዘኛን የሚያሟላ ነው ለማለት አልተቻለም።ሲጠቃለልም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ጸንቷል።
አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ፍርድ እየተነበበ ባለበት ጊዜ የችሎቱን ስነ ስርዓት ባለማክበርና ያልተገባ ባህርይ ማሳየታቸው ተረጋግጦ ፍርድ ቤቱን በመድፈር የተቀጡ በመሆኑ በውሳኔው ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል።
መዝገቡ ተዝግቷል፤ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል።
የማይነበበ የአምስት ዳኞች ፊርማ አለበት
No topics extracted.