No summary available.
ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- 1.አቶ ተሾመ አሰፋ 2.ማርሸት አሰፋ የጠበቃ ወኪል ቀረቡ 3.ፍቅረዓለም አሰፋ ተጠሪ፡- ወ/ሪት መስታወት አሰፋ/ቀረበች **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የውርስ ንብረት ይጣራልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኗ ተጠሪ ከወ/ሪት ቦንቱ አሰፋ ጋር በመሆን በሀዋሳ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአሁን አመልካቾች ላይ ባቀረቡት ክስ መነሻ ነው። የስር ከሳሾች ያቀረቡት ክስ ይዘትም የከሳሾችና የተከሳሾች ወላጅ አባት የሆኑት አቶ አሰፋ በዳሳ የካቲት 15 ቀን 1994 ዓ/ም ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውንና ንብረቶቻቸውም በተከሳሾች እንደሚተዳደሩ ገልፀው የሟቹ የውርስ ንብረቶች እንዲጣሩ ይደረግላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል። የአሁኑ ተጠሪዎች ለክሱ በሰጡት መልስም ጉዳዩ በይርጋ የታገደና ቀድሞ በፍርድ ያለቀ መሆኑን ጠቅሰው በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ክሱ ውድቅ ላደረግ ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።የስር ፍርድ ቤትም ይህንኑ መቃወሚያ መነሻ አድርጎ ጉዳዩን የተመለከተ ሲሆን ጉዳዩ ቀድሞ በፍርድ ያለቀ መሆኑ መረጋገጡን ገልጾ ክሱን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌ መሰረት ውድቅ አድርጎታል።በዚህ ብይን ከሳሾች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት ያጡ ሲሆን የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ የስር ከሳሾች በመ/ አቅርበውት የነበረው ክስ ሟች አቶ አሰፋ በዳሳ በተውት የቁም ኑዛዜ ከሰጧቸው ብር 20,000.00 ውስጥ ቀሪውን ብር 10,000.00 የአሁኑ 1ኛ አመልካች እንዲከፍል ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የጠየቁበት ሁኖ በጉዳዩ ላይ በ7/7/2004 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔም ይህንኑ ጥያቄአቸውን በመቀበል በኑዛዜው መሰረት ቀሪው ገንዘብ እንዲከፈላቸው የሚገልፅ በመሆኑና በአዲሱ ክስ ከሳሾች ክስ የመሰረቱት የውርስ ንብረት ይጣራልኝ በሚል እንጂ በኑዛዜ የተሰጣቸውን ገንዘብ እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ ባለመሆኑ፤በሁለቱ መዛግብት የተነሱት የፍሬ ነገር እና የሕግ ክርክሮች ተመሳሳይ ባለመሆናቸው ጉዳዩ ቀድሞ በፍርድ አልቋል ለማለት የሚቻል አይደለም በሚል ምክንያት የበታች ፍርድ ቤቶችን ብይን በመሻር ፍሬ ጉዳዩ በስር ፍርድ ቤት ታይቶ ተገቢው ዳኝነት እንዲሰጥበት ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ጉዳዩ ቀድሞ በኑዛዜ ክርክር ጊዜ ያለቀ ሁኖ እያለ የውርስ ይጣራልኝ ጥያቄና በኑዛዜው መሰረት ይፈፀምልኝ ጥያቄ ተመሳሳይነት የላቸውም ተብሎ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰጠቱ ያላግባብ ነው የሚል ነው። የሰበር አቤቱታው ተመርምሮም ጉዳዩ ቀድሞ በፍርድ ያለቀ አይደለም ተብሎ መወሰኑ በአግባቡ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለዚህ ሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪና ወ/ሪት ቦንቱ አሰፋ የካቲት 08 ቀን 2004 ዓ/ም ለሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት ባቀረቡት ማመልከቻ ሟች አባታቸው አቶ አሰፋ በዳሳ መስከረም 16 ቀን 1994 ዓ/ም በተውት ኑዛዜ ላይ ለእያንዳንዳቸው ብር 10,000.00 በአቶ ተሾመ አሰፋ በኩል እንዲሰጣቸው የተናዛዙላቸው መሆኑንና ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ብር 10,000.00 በአቶ ተሾመ አሰፋ ተሰጥቷቸው ቀሪው ብር 10,000.00 ያልተሰጣቸው መሆኑን ገልጸው ይኼው በኑዛዜ የተሰጣቸው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ እንዲከፈል ዳኝነት እንዲሰጣቸው የጠየቁ መሆኑንና ክርክሩም ከአቶ ተሾመ አሰፋ ጋር ብቻ ቀጥሎ አቶ ተሾመ አሰፋ በክሱ ኃላፊ ተደርገው ገንዘቡን እንዲከፍሐቸው ዳኝነት የተሰጠበት ጉዳይ መሆኑን፣እነ ወ/ሪት መስታወት አስፋ ግንቦት 28 ቀን 2004 ዓ/ም ባቀረቡት ክስ ደግሞ አቶ ተሾመንና ልሎች ሁለት እህቶቻቸውን በአንድ ላይ አድርገው፣በተከሳሽነት ሰይመው ዳኝነት እንዲሰጣቸው የጠየቁት ጉዳይ የአቶ አሰፋ በዳሳ የውርስ ንብረት እንዲጣራላቸው መሆኑን ነው።
No topics extracted.
በመሰረቱ የፍትሐ ብሕር ክርክር አንድ ደረጃ ላይ ሲደርስ መቋጫ እንዲኖረው በማሰብ ከተደነገጉ የስነ ስርዓቱ ድንጋጌዎች አንዱ የመጨረሻ ፍርድ ያገኙ ጉዳዮች /Res judicata/ የሚለው ሲሆን ይህ ጽንሰ ሀሣብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ/ 5 ስር በግልጽ ተቀምጧል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት የመጨረሻ ፍርድ ያገኙ ጉዳዮች ማለት በማናቸውም መልክ በሕግ በተቋቋመ ፍ/ቤት ቀርበው የመጨረሻ ውጤት ያገኙ ጉዳዮችን የሚሸፍኑ መሆናቸውንና በፍርድ፣ በብይን፣በውሣኔ፣በትእዛዝ፣ወይም በጊዜያዊ አገልግሎት ባለው ትእዛዝ የመጨረሻ ውጤት አግኝተው በልላ መልክ መንቀሣቀስ የማይችሉ የክርክር ነጥቦችን ሁሉ አቅፎ የያዘ፣ክርክር አንድ ቦታ ላይ እንዲቆም ታስቦ በሕግ የተዘረጋ ስርዓት ነው። በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 5 ስር በተመለከተው አኳኋን አንድ ጉዳይ አስቀድሞ በፍርድ ያለቀ ነው ለማለት መረጋገጥ ካላባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ቀደም ሲል ቀጥተኛ የፍሬ ነገር ጭብጥ የነበሩ ጉዳዮች በድጋሚ በቀረበው ክስም ላይ በቀጥታ በፍሬ ነገር ጭብጥ ሆነው መቅረባቸው፣ ቀደም ሲል የነበረውን ክርክር አሁን በክርክር ተሣታፊ በሆኑ ወገኖች ወይም ከእነሱ መብት በተላለፈላቸው ወይም ተላልፎላቸው በነበረ ወገኖች መሆኑንና እነዚህ ጉዳዮች ቀደም ሲል በተካሄደው ሙግት የመጨረሻ ፍርድ ያረፈባቸው መሆኑን ነው።
ሕጉ ቀጥተኛ የፍሬ ነገር ጭብጥ በመጨረሻ ፍርድ መቃወሚያነት ሲቀርብ ተቀባይነት የሚኖረው ይኸው ጉዳይ በድጋሚ በቀረበው ክርክር ላይ መቅረቡ ሲረጋገጥ ስለመሆኑም ያስገነዝባል። ከሕጉ ይዘትና መንፈስ ቀጥተኛ የፍሬ ነገር ጭብጥ የሚለው ሐረግ ሲታይም በመጀመሪያው ክርክር ላይ ከአንደኛው ወገን ተጠይቆ በልላኛው ወገን የተካደ ወይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የታመነና በዚሁ ላይ የፍርድ ውሣኔ ያረፈበት የክርክር ነጥብ መሆኑን ያስነዝባል።
በመሆኑም በድጋሚ በቀረበው ክስ በቀድሞው ክርክር ተሣታፊ በነበሩ ወገኖች ወይም ከእነሱ መብት በተላለፈላቸው ወገኖች የሚካሄድ መሆኑና በሁለተኛው ክስም የተያዘው ፍሬ ነገር ጭብጥ ከመጀመሪያው ጋር ተመሣሣይ ሆኖ የመጨረሻ ፍርድ ያረፈበት መሆኑ ከተረጋገጠ እንዲሁም ጉዳዩ የመጨረሻ ፍርድ አርፎበታል የሚል ተቃውሞ በተከራካሪ ወገን ከተነሣ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 5(1)እና (2) ድንጋጌዎች ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 244(2(ለ)) እና 245(2) ድንጋጌ ጋር ተጣምረው ሲታዩ የሚያስገነዝቡን ጉዳይ ነው።
የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 5/2/ ድንጋጌ በግልጽ ሲታይም በቀድሞው ክርክር ላይ የማስረጃ ወይም የመከላከያ ወይም የመቃወሚያ መሰረት መሆን ይገባቸው ነበር ወይም ለመሆን ይችሉ ነበር የሚባሉት ነገሮችና ምክንያቶች ሁሉ ለሥረ ነገሩ መሰረት በመሆን ከቀድሞው ውሳኔ ጋር ተቀላቅለው እንዳለቁ የሚቆጠሩ ናቸው በማለት አስገዳጅነት ባለው መልኩ ደንግጓል። ይህ ድንጋጌ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 216 ድንጋጌ ጋር ተዛምዶ ሲታይም ክርክሮች ተጠቃልለው እንዲታዩ የግድ የሚል መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።በመሆኑም በተከራካሪ ወገኖች በግልጽ የሚታወቁና በቀዳሚው ክርክር ላነሱ ይችሉ የነበሩት ነገሮችና ምክንያቶች ሁሉ ለልላ ክስ ምክንያት ሁነው ላቀርቡ እንደማይገባና ፍርድ ቤቱም ተቃውሞው በስርዓቱ መሰረት ሲቀርብለት በመቀበል ክርክሩ እንዲቆም ማድረግ ያለበት ጉዳይ ነው።ከላይ ከተመለከቱት ሕጋዊ ምክንያቶች በተጨማሪ በቀድሞው ክርክርና ሙግት ላይ በግልጽ ዳኝነት ተጠይቆበት ጥያቄው ተቀባይነትን ሳያገኝ የታለፈ እንደሆነ የተጠየቀው ዳኝነት እንደተከለከለ እንደሚቆጠር የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5(3) ድንጋጌ በግልጽ አስቀምጧል።በአጠቃላይ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌ ሲታይ በቀዳሚው ክርክር የተያዘው ጭብጥና የፍሬ ነገር ክርክር ተመሳሳይ መሆኑ የተከራካሪ ወገኖች አንድነት ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ከላይ የተመለከቱት መመዘኛዎች በተሟሉበት ሁኔታ የመጨረሻ ፍርድ የተሰጠ መሆኑ ከተረጋገጠ በጉዳዩ ላይ አስቀድሞ የመጨረሻ ፍርድ የተሰጠበት በመሆኑ ድጋሚ ክስ የሚቀርብበት አግባብ የልለ መሆኑን ያስረዳል።
በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ ከእህታቸው ቦንቱ አሰፋ ጋር ሁነው ቀደም ሲል በአሁኑ 1ኛ አመልካች ላይ ያቀረቡት ክስ መስከረም 16 ቀን 1994 ዓ/ም በተደረገው ኑዛዜ መሰረት ጥሬ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ሲሆን ይኸው የዳኝነት ጥያቄአቸው በስር ፍርድ ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ገንዘቡ በ1ኛ አመልካች እንዲከፈል ተወስኗል።ይህ የተጠሪና የእህታቸው የዳኝነት ጥያቄ መሰረት ያደረገው ኑዛዜውን ሲሆን ኑዛዜው ለተጠሪና ለእህታቸው ምን ያህል ገንዘብ እንደሚሰጥ በግልጽ አስቀምጦ በኑዛዜው ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን ውጪ ልላ ገንዘብም ሆነ ንብረት ላጠይቁ እንደማይችሉ ተናዛዡ መግለጹ በኑዛዜ ላይ የተቀመጠ ጉዳይና ተጠሪና እህታቸው ስለኑዛዜው ሰነድ ይዘት እውቀት የነበራቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው።ከዚህ በኋላ ተጠሪና እህታቸው ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ክስ 1ኛ አመልካችን ጨምሮ በልሎች ሁለት እህቶቻቸው(2ኛ እና 3ኛ አመልካቾች) ላይ የቀረበ ከመሆኑ ውጪ ጠቅላላ የዳኝነት ጥያቄው የውርስ ንብረት ይጣራልኝ የሚል ነው።እንግዲህ የውርስ ንብረት ይጣራልኝ ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 944 እና ተከታይ ድንጋጌዎች አግባብ የሚፈፀም ሲሆን የኑዛዜ መኖርና ያለመኖር እንዲሁም ተጠቃሚዎች የሚለዩበት አግባብ እንደሆነ ከሕጉ የምንረዳው ጉዳይ ነው።በመሆኑም ኑዛዜን መሰረት አድርጎ የሚቀርበው የኑዛዜ ተጠቃሚነት መብት ይረጋገጥልኝ ጥያቄና የውርስ ይጣራልኝ ጥያቄዎች ተመሳሳይ የሆነ የፍሬ ነገርና የህግ ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮች ናቸው።
ተጠሪና እህታቸው ከኑዛዜው ጋር ተያይዞ የሚነሱትን ማናቸውንም የሕግ ጥያቄዎች በኑዛዜው መብት ተጠቃሚነት ይከበርልኝ በማለት ክስ በመሰረቱበት ጊዜ ላያቀርቡ የሚችሉት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በኑዛዜው ላይ የተቀመጠውን የገንዘብ መጠን ብቻ ጠይቆ መውሰድ ደግሞ በኑዛዜው የተደረገውን ክልከላንም ጭምር እንደመቀበል የሚያስቆጥር ነው።ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው ተጠሪ ሟች በተውት ኑዛዜ መሰረት ጥሬ ገንዘብ እንዲከፈላቸው ክስ አቅርበው ገንዘቡ እንዲከፈላቸው ዳኝነት ከተሰጠ በኋላ የሟች ውርስ ንብረት ይጣራልኝ በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ቀድሞ በቀረበው ክስ ጊዜ ላያቀርቡ ይችሐቸው የነበሩትን ነገሮችና ምክንያቶችን ከተዉ በኋላ ያቀረቡት በመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5(2) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ መሰረት ተቀባይት ላሰጠው የሚገባው ጉዳይ አይደለም።ተጠሪ የኑዛዜውን ሰነድ ይዘቱን እንደሚያውቁም የሚታመን ሲሆን በኑዛዜው ላይ ልላ ማናቸውንም ገንዘብ ወይም ንብረት ከሟቹ እንዳይጠይቁ ክልከላ ተደርጎባቸው እያለ ይኼው የኑዛዜው ክፍል ሕጋዊ መሆን ያለመሆኑን በቀድሞው ክስ ክርክር አቅርበው እልባት ማግኘት ሲገባቸው ኑዛዜውን ተቀብለው በኑዛዜው መሰረት ተጠቃሚነታቸው ከተረጋገጠላቸው በኋላ ልላ የውርስ ንብረት መብት እንዳላቸው በመቁጠር የውርስ ይጣራልኝ ጥያቄ ማቅረባቸው በቀድሞው ክርክር ላይ የማስረጃ ወይም የመከላከያ ወይም የመቃወሚያ መሰረት መሆን ይገባቸው ነበር ወይም ለመሆን ይችሉ ነበር የሚባሉት ነገሮችና ምክንያቶች ሁሉ ለሥረ ነገሩ መሰረት በመሆን በቀድሞው ውሳኔ ጋር ተቀላቅለው እንዳለቁ የሚቆጠሩ ናቸው በማለት አስገዳጅነት ባለው መልኩ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5(2) የተደነገገውን የሚጥስ ነው።
በመሆኑም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ተጠሪና እህታቸው በቀደመው ክስ መሰረት ያደረጉት ኑዛዜ ሁኖ እያለና በኑዛዜው ደግሞ ልላ ገንዘብ ወይም ንብረት ለመጠየቅ የማይችሉ መሆኑ በግልፅ ተመልክቶ እያለ በዚህ ረገድ ተገቢው ክርክር ቀርቦ መፍትሕ ላያገኝ ይችል የነበረውን ጉዳይ ተጠሪ በኋላ ያቀረቡት ክስ የውርስ ይጣራልኝ ጥያቄ ነው በማለትና ይህ ተግባር ኑዛዜን ማፈላለግና ተጠቃሚዎችን የመለየት ስራዎችን ጭምር የሚይዝ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገባ የኑዛዜ ተጠቃሚነትና የውርስ ይጣራልኝ ጥያቄ የተለያዩ ነገሮች ናቸው በማለት የበታች ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ መሻሩ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5፣244(2(ለ)) እና 245(2) ድንጋጌዎችን እንዲሁም አጠቃላይ የስነ ሥርዓት ሕጉን ዓላማ ባላገናዘበ መልኩ በመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በደ/ብ/ብ/ሕ/ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ የከቲት 28 ቀን 2005 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1)መሰረት ተሸሯል።
በሐዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ሐምል 16 ቀን 2004 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
ተጠሪ የአባታቸውን የአቶ አሰፋ በዳሳ ኑዛዜን መሰረት አድርገው ክስ አቅርበው ተጠቃሚነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ የውርስ ንብረት ይጣራልኝ ጥያቄ ክስ የሚመሰረትበት አግባብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌ መሰረት ተቀባይነት የለውም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየረሰሳቸውን ይቻሉ ብለናል።