No summary available.
ጥቅምት 19 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- የኢትዩጵያ መድን ድርጅት ነ/ፈጅ ሰናይት በዳሣ ቀረቡ ተጠሪ፡- የሟች ዘካሪያ ኢብራሂም ባለቤት ሳዲያ ኢብሮሽ /ጠበቃ ወረደ ፀሐይ ወ/ዮሐንስ - ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ በመድን ውሉ መሰረት የተከፈለ ገንዘብ ይተካልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ እና በአቶ ቶፊቅ ኡስማን ላይ በጅጅጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው።የአመልካች ክስ ይዘት፡-ንብረትነቱ የአቶ ዘነበ ተካን፤የአመልካች ደንበኛ የሆነውንና በሰልዳ ቁጥር 3-52129 የሚታወቀው ሚኒባስ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ጅጅጋ አስር ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ ንብረትነቱ የአሁኑ ተጠሪ የሆነውና የሰልዳ ቁጥሩ 3-00947 ሐረር በሚል የሚታወቅ መኪና በስር ሁለተኛ ተከሳሽ በነበሩት አቶ ቶውፊቅ ኡስማን ሲሽከርከር ከመንገድ በመውጣት በ23/11/2003 ዓ/ም በመግጨት ጉዳት ያደረሰበት መሆኑንና በጉዳቱም በተሳፋሪዎች የመቁሰል አደጋ ከመድረሱም በተጨማሪ መኪናው ከስራ ውጪ የሆነ መሆኑን፣ለተሳፋሪዎች የተከፈለውንና መኪናው ከስራ ውጪ በመሆኑ በድምሩ የብር 287,003.40 (ሁለት መቶ ሰማንያ ሰባት ሺህ ሶስት ብር ከአርባ ሳንቲም) ጉዳት የደረሰበት መሆኑን፣ከዚህ ገንዘብ ውስጥ የመኪናውን ሳልቬጅ በብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺ ብር) የሸጠ እና ገቢ ያደረገ መሆኑን ጠቅሶ ቀሪውን ብር 187,003.40 ግን ተጠሪና የተጠሪን መኪና ሲያሽከርክር የነበሩት ግለሰብ አቶ ቶፊቅ ኡስማን እንዲከፍሉ ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው።ለማስረጃነትም የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቧል።የሥር ሁለተኛ ተከሳሽ የነበሩት አቶ ቶውፊቅ ኡስማን በልሉበት ጉዳዩ የታየ ሲሆን የአሁኗ ተጠሪ ግን ቀርበው በሰጡት የመከላከያ መልስ ክሱ በይርጋ የሚታገድ መሆኑን፣ለአደጋው መድረስ የተጠሪ መኪና ጥፋት ያለበት መሆኑ አለመረጋገጡን፣የጉዳቱን መጠን ለማስረዳት የቀረቡት ደረሰኞችም ስርዝ ድልዝ ያለባቸው በመሆኑ በሕጉ ተቀባይነት የልላቸው መሆኑን፣ስለመከፈሉ ያስረዳል ተብሎ በቀረበው የሰነድ ማስረጃም የጉዳቱ መጠን በአኅዝና በፊደል የተቀመጠው የተለያየ በመሆኑ ላወሰድ የሚገባው የፊደል መሆኑን በመዘርዘር ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ለጉዳቱ ምክንያት የሆነው አደጋ ያደረሰው የተጠሪ መኪና መሆኑ ያለመረጋገጡን ጠቅሶ ለጉዳቱ መድረስ ሁለቱም ተሸከርካሪዎች የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደነበር በመደምደም ሁለቱም ተሸከርካሪዎች በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2084(3) ድንጋጌ መሰረት የጋራ ኃላፊነት አለባቸው በማለት የወሰነ ሲሆን የጉዳቱን መጠን በተመለከተ ደግሞ በአመልካች በኩል ከቀረቡት የተወሰኑት ደረሰኞች እምነት የማይጣልባቸው መሆኑን ለይቶ ውድቅ አድርጎ በድምሩ ብር 245,588.25 (ሁለት መቶ አርባ አምስት ሺ አምስት መቶ ሰማንያ ስምንት ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም) ጉዳት መደረሱን፣ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ብር 100,000.00(አንድ መቶ ሺ ብር) ሳልቬጅ ሲቀነስ ቀሪው ብር 145,588.25 መሆኑን በመግለፅ ይኼው የጉዳት መጠን ለሁለት ሲካፈል ተጠሪ ብር 72,794.12. (ሰባ ሁለት ሺ ሰባት መቶ ዘጠና አራት ብር ከአስራ ሁለት ሳንቲም) ለአመልካች ላከፍሉ ይገባል በማለት ወስኗል።በዚህ ውሳኔ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲያቀርብ ተጠሪ ባሉበት ጉዳዩ እንዲጣራ በመደረጉ ተጠሪም በስርኣቱ መሰረት የመስቀልኛ ይግባኝ አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አፅንቶታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የተጠሪን መኪና ሲያሽከርከሩ የነበሩት አሽከርካሪ ለጉዳቱ ሙሉ ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ በወንጀል ተቀጥተው እያለና ይኼው ውሳኔ በማስረጃነት በፍርድ ቤቱ እገዛ እንዲቀርብ አመልካች ጠይቆ እያለ ማስረጃው ሳይቀርብ ጉዳቱ የደረሰው በሁለት ተሸከርካሪዎች ግጭት ነው ተብሎ አግባብነት የልለው ሕግ ተጠቅሶ ኃላፊነቱ የጋራ ተደርጎ መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው በሰጡት መልስ የተጠሪን መኪና ሲያሽከርክር የነበረው አሽከርካሪ በወንጀል ያለመቀጣቱን፣አመልካችም የወንጀል ችሎት የሰጠውን ውሳኔ አለ ከማለት ውጪ በየትኛው ፍርድ ቤትና በየትኛው መዝገብ ቁጥር ስለመሆኑ ለይቶ ባልጠቀሰበት ሁኔታ ማስረጃው ሳይቀርብ ቀርቷል በማለት የሚያቀርበው ቅሬታ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 145 ድንጋጌ አተገባበርን ያላገናዘበ መሆኑን በመጥቀስና ተጠሪ ያላግባብ ለጉዳቱ የጋራ ሃላፊነት አለባቸው ተብሎ መወሰኑ ተጠሪን የጎዳና አመልካችን የጠቀመ መሆኑን በመግለጽ ተከራክረዋል።የአሁኑ አመልካች በሰጠው የመልስ መልስም የወንጀል ውሳኔ የተባለውን ማስረጃ ውሳኔውን የሰጠውን ፍርድ ቤትና መዝገቡን ለይቶ ሳይጠቅስ የሰበር አቤቱታውን ይዘት በመድገም ተከራከሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምረናል።ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገውን የአደጋ ቦታ ፕላንና መግለጫ ይዘት ታልፎና በፍርድ ቤት እገዛ እንዲቀርብ የተጠየቀው ማስረጃ ሳይቀርብ በበታች ፍርድ ቤቶች ኃላፊነቱ የጋራ ነው ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል በመሆኑ ከእነዚህ ነጥቦች አንጻር ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች በስር ፍርድ ቤት በነበረው ክርክር አመልካች የመድን ሸፋን የሰጠው መኪና ሐምል 23 ቀን 2003 ዓ/ም በተጠሪ መኪና ግጭት የደረሰበት መሆኑን አመልካች ገልጾ ጉዳት በደረሰበት መኪና ለነበሩት ተሳፋሪዎች የተከፈለውን ወጪ፣መኪናውን ከስራ ውጪ በመሆኑ ምክንያት የታጣውን ገቢ መጠን ዘርዝሮና የሳልቤጁን ዋጋ መጠን ለይቶ በድምሩ ብር 187,003.40 ለደንበኛው የከፈለው የጉዳቱ ወጪ መሆኑን ገልፆ ይሕው ገንዘብ እንዲተካ ጥያቄ አቅርቦ የአሁኗ ተጠሪም በኃላፊነቱም ሆነ በመጠኑ ላይ የቀረቡት ክርክሮች ያላግባብ የቀረቡ ናቸው የሚል ክርክር አቅርበው የስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክሮችና ማስረጃዎችን መርምሮ በአመልካች የመድን ሽፋን የተሰጠው መኪና ከተጠሪ መኪና ጋር ሐምል 23 ቀን 2003 ዓ/ም መጋጨቱን፣ለግጭቱ ምክንያት የሆነውን ጥፋት የፈፀመው አሽከርካሪ ግን የትኛውን መኪና ሲያሽከርከር የነበረ አሽከርካሪ እንደሆነ በጉዳዩ የቀረቡት የአመልካች ማስረጃዎች እንደማያሳዩ ገልጾ በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን ክርክር በከፊል ያለፈው መሆኑን ነው።በመሆኑም የስር ፍርድ ቤት የአመልካች ደንበኛ መኪና እና የተጠሪ ንብረት በሆነው መኪና ግጭት መድረሱንና ለጥፋቱ ሙሉ ኃላፊነቱን ላወስድ የሚገባው አሽከርካሪ ግን ያለመለየቱን ፍሬ ነገሩን አጣርቶና ማስረጃን መርምሮ ድምዳሜ ላይ የደረሰበት ጉዳይ ሲሆን ይኸው የስር ፍርድ ቤት የፍሬ ነገርና የማስረጃ ምዘና ድምዳሜ በይግባኝ ሰሚው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ተቀባይነት አግኝቷል።
እንግዲህ አመልካች የመድን ሽፋን የሰጠው መኪና ከተጠሪ መኪና ጋር ተጋጭቶ ጉዳት የደረሰበት ከመሆኑ ውጪ በተጠሪ አሽከርካሪ ሙሉ ጥፋት ግጭቱ ስለመድረሱ በጉዳዩ ላይ ከቀረቡት ማስረጃዎች ይዘትና መንፈስ የስር ፍርድ ቤት መገንዘብ ያለመቻሉን ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣኑን ተጠቅሞ ያረጋገጠው ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።አሁን አመልካች ለዚህ ሰበር ችሎት በዚህ ረገድ ያቀረበው ቅሬታ የስር ፍርድ ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 145 መሰረት እንዲቀርብ የተጠየቀውን ማስረጃ ሳያስቀርብ አልፏል የሚል ነው።በእርግጥ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 145 መሰረት የተጠየቀ ማስረጃ ሳይቀርብ ፍርድ መስጠት የፍርድ ኣካሄዱ በተሟላበት ሁኔታ የተሰጠ ነው ለማለት የማይቻል መሆኑ የሚታመን ሲሆን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 145 መሰረት የፍርድ ቤቱን እገዛ በመጠየቅ ማስረጃ ማስቀረብ የሚቻለው ግን ጠያቂው ወገን እንዲቀርብ የተጠየቀውን ማስረጃ ትክክል ግልባጭ በቅርብ ጊዜ ለማምጣት የማይችልበትን ወይም ማስገልበጫ የሚያስፈልገውን ወጭ ለመክፍል የማይችል መሆኑን እንዲሁም እንዲቀርብ የተጠየቀው ማስረጃ ለክርክሩ ምን ያህል ጠቃሚነት እንዳለው፤ትክክለኛን ፍርድ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን በፅሁፍ ገልፆ ማስረዳት እንዲሚጠበቅበት የተጠቃሹ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል።በመሆኑም ተከራካሪ ወገን በፍርድ ቤት እገዛ ማስረጃ እንዲቀርብለት ሲጠይቅ በሕጉ የተመለከቱትን መስፈርቶችን በግልጽ ገልፆ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳት ያለበት መሆኑን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 145(1) እና (2) ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያሳያል።ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው አመልካች በፍርድ ቤት እገዛ እንዲቀርብለት የሚጠይቀው የፅሑፍ ማስረጃ የፍርድ ቤት ውሳኔ ሲሆን ውሳኔው በየትኛው ፍርድ ቤትና በየትኛው የመዝገብ ቁጥር እንደተሰጠ ካለመግለፁም በላይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 145 ስር የተመለከተውን የሕጉን አገላላፅ ለማስረዳት የጠቀሳቸው ምክንያቶችም የሉም።እንዲሁም አመልካች የወንጀል ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በየትኛው ፍርድ ቤትና መዝገብ ቁጥር እንደተሰጠ ያለመግለጹን፣በስር ፍርድ ቤትም ፍርድ ቤቱንና የመዝገብ ቁጥር እንዲጠቅስና ማስረጃውንም እንዲያቀርብ እድል ተሰጥቶት በእድሉ ላጠቀም ያለመቻሉን ተጠሪ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጡት መልስ በግልጽ ጠቅሰው ተከራክረውም አመልካች በዚህ ረገድ ባቀረበው የመልስ መልስ ለተጠሪ የክርክር ነጥብ ማስተባበያ ክርክር አላቀረበበትም።በመሆኑም በስር ፍርድ ቤት እድሉ ተሰጥቶ ተገቢውን ላፈፅም ያለመቻሉን አመልካች እንዳመነ የሚያስቆጥረው መሆኑን ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 235 እና 83 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ሲሆን በዚህ የሰበር የክርክር ደረጃ እንኳን አመልካች አለኝ የሚለውን የወንጀል ውሳኔ የሰጠውን ፍርድ ቤትና የመዝገቡን ቁጥር በግልጽ ጠቅሶ ያለመከራከሩ በማስረጃው አቀራረብ ረገድ የሥር ፍርድ ቤቱ ተገቢውን እገዛ እንዲያደርግ አመልካች በራሱ በኩል ተገቢውን ያለመፈፀሙን የሚያሳይ ሁኖ አግኝተናል።
አመልካች በትራፊክ መርማሪ ፖላስ ጥፋቱ የተጠሪን መኪና ሲያሽከርክር የነበረ አሽከርካሪ መሆኑ ተገልጾ እያለ በበታች ፍርድ ቤቶች ይኼው ታልፏል በማለት የሚያቀርበው ክርክር ደግሞ ማስረጃው በስር ፍርድ ቤት ተመዝኖ የታለፈ በመሆኑና ፍርድ ቤቱ ማስረጃውን መዝኖ የራሱን ድምዳሜ ከመያዝ የሚከልክል ሕግ የልለ ስለመሆኑ፣ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንደዚህ አይነት ማስረጃ እንደማንኛውም ማስረጃ ላመዝን የሚችል እንጂ ደምዳሚ ማስረጃ ያለመሆኑን ገልጾ በሰ/መ/፣43453 እና በልሎች በርካታ መዛግብት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም የሰጠበት መሆኑን ያላገናዘበ በመሆኑ የምንቀበለው ሁኖ አልተገኘም።ስለሆነም በዚህ ረገድ የቀረበው የአመልካች ክርክር የፍሬ ነገርና የማስረጃ ምዘና ክርክር ከመሆኑም በላይ በስር ፍርድ ቤት ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር ይዘት ውጪ በመሆኑ አመልካች የበታች ፍርድ ቤቶች በፍሬ ነገር ማጣራትና በማስረጃ ምዘና ሂደት ሰርተውታል የሚለውን ስህተት የማጣራትና የማረም ስልጣን ይኽ ችሎት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10 ያልተሰጠው ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ተቀባይነት ያለው ክርክር ሁኖ አላገኘነውም። ግጭቱ በሁለት ተሸከርካሪዎች የደረሰ ከሆነና ጥፋቱ የየትኛው ተሸከርካሪ እንደሆነ በማስረጃ መለየት ካልተቻለ አንዱ ባንዱ ላይ አደጋ እንደአደረሰ እንደሚቆጠር፣ለየእንዳንዱ ተሽከርካሪ ባለሃብት ወይም ለአደጋው አላፊ የሆነው ሰው በአደጋው ምክንያት ከደረሰው ጠቅላላ ጉዳት ገሚሱን መከፈል ያለበት መሆኑን ደግሞ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2084(1) እና (2) ድንጋጌዎች በግልጽ ያሳያሉ።
በአጠቃላይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 145 ድንጋጌ መሰረት እንዲቀርብ የተጠየቀው ማስረጃ በስር ፍርድ ቤት ሳይቀርብ የቀረው አመልካች በሕጉ በተመለከተው አኳኋን ማስረጃውን ለማቅረብ ያልቻለበትን ሕጋዊ ምክንያትና ማስረጃው የሚገኝበትን ፍርድ ቤትና የመዝገቡን ቁጥር ለይቶ ባለማቅረቡ ስለመሆኑ በክርክሩ ሂደት መረጋገጡን የተገነዘብን ስለሆነና በትራፊክ ፖላስ ማስረጃ ላይም አመልካች በበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተፈጽሟል የሚለው ስህተት የፍሬ ነገርና የማስረጃ ምዘናን የሚመለከት በመሆኑና ይህ ደግሞ የመሰረታዊ ሕግ ስህተት መመዘኛ ባለመሆኑ በዚህ ችሎት ተቀባይነት የሚያገኝበት አግባብ ስለልለ በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል።
በጅጅጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 940/03 ሐምል 02 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 185/2004 የካቲት 08 ቀን 2005 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
ለአደጋው የአመልካች ደንበኛ መኪና እና የተጠሪ መኪና የጋራ ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ የጉዳት መጠኑን እኩል እንዲጋሩ ተደርጎ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል።
በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ ብለናል።
ቤ/ዮ
No topics extracted.