No summary available.
የሰ/መ/ ጥቅምት 20 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡-
ጉዳዩ በፍርድ አፈፃፀም ጊዜ በአንድ ንብረት ላይ አፈጻጸሙ ሲመራ በንብረቱ ላይ ሕጋዊ መብት አለን የሚሉ ሰዎች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 መሰረት አቤቱታ ሲያቀርቡ አቤቱታቸው ሙሉ የክርክር አመራር ስርዓትን መሰረት አድርጎ ላከናወን የሚችል መሆን ያለመሆኑን የሚመለከት ነው።የአፈፃፀሙ ክርክር የተጀመረው የአሁኗ 1ኛ ተጠሪ ባሁኗ 2ኛ ተጠሪ ላይ የጥብቅና አበል አልተከፈለኝም በሚል ያቀረቡት የዋና ክርክር ጉዳይ ታይቶ የፍርድ ባለመብት መሆናቸው በመረጋገጡ ይኼው ፍርድ ቤት እንዲፈፅምላቸው በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስከፈቱት የአፈጻጸም መዝገብ ነው።1ኛ ተጠሪ ለፍርዱ ማስፈፀሚያ ይሆንላቸው ዘንድም 2ኛ ተጠሪ በውርስ መብት አግኝተውባቸዋል ባሐቸው፤በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ አጠራር በወረዳ 3፣ቀበል 32 ክልል ውስጥ በሚገኙትና ቁጥራቸው ከ803 እስከ 805 በሆኑ ቤቶች እንዲሁም በወረዳ 5፣ቀበል 06 ክልል ውስጥ በሚገኙትና ቁጥራቸው ከ936 እስከ 953 በሚል ተመዝግቦ በሚገኙ ጋራዥ ቤቶች ላይ ለፍርድ ቤቱ የገለፁ ሲሆን የአሁኑ አመልካቾች በወረዳ 5 ቀበል 06 ክልል በሚገኙትና ቁጥራቸው ከ936 እስከ 953 ተብሎ የተመዘገቡ የመኮነን ነጋሽ የሕዝብ ማመላለሻ ድርጅትና ጋራዥ በድርጅትነት እንደሚታወቅና ሰኔ 22 ቀን 1999 ዓ/ም በተደረገ የንግድ ቤት ድርጅት ሽያጭ ውል የሟች አቶ መኮንን ነጋሽ ሚስት ወ/ሮ የሺወርቅ ግዛው ከልጆቻቸው እነ ፋሲል መኮነን ነጋሽ (ሰባት ራሳቸው) እንዲሁም 2ኛ ተጠሪ ጋር በመሆን ሽጠውላቸው ነሐሴ 08 ቀን 1999 ዓ/ም የተረከቧቸው መሆኑን ገልፀው 1ኛ ተጠሪ ያቀረቡት የፍርድ ይፈፀምልኝ ጥያቄ በንብረቶቹ ላይ ላቀጥል እንደማይገባ፣በወረዳ 3 ቀበል 32 በቤት ቁጥር 803 እስከ 805 በሚታወቁት ቤቶች ላይ አፈፃጸሙ ቀጥሎ በእነዚህ ንብረቶች ላይ የፍርድ ባለእዳዋ ድርሻ እዳውን የሚሽፈን ካልሆነ የአሁኑ አመልካቾች ሻጮች ባደረጉት ውል መሰረት ተፈጽሞ 2ኛ ተጠሪ የፍርድ ባለእዳ ቀሪ ድርሻ እንዳላቸው ቀሪውን በፍርድ ባለእዳዋ ድርሻ ልክ ይዘው ለመክፈል የሚችሉ መሆኑን ገልጸው አፈፃጸሙ በዚህ መልክ እንዲመራ አመልክተዋል።የአሁኗ ተጠሪ ለአመልካች አቤቱታ በሰጡት መልስም አመልካች አለን የሚሉት ውል ሕጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ ያልተደረገ በመሆኑ ተቀባይነት የልለው መሆኑን ጠቅሰው ጥያቄአቸው ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲሆን ያመለከቱ ሲሆን 2ኛዋ ተጠሪም አመልካቾች በወረዳ 5 ቀበል 06 ክልል ውስጥ የሚገኙትንና ቁጥራቸው 936/2/፣947 እስከ 952፣953/2/ ፣954 እና 954/2/ የሆኑትን በውል ገዝተው የተረከቧቸው መሆኑን ጠቅሰው እንደውሉ ተጠብቆ እንዲፈፀምላቸው ቢደረግ የማይቃወሙ መሆኑን፣የቤት ቁጥር 803 የተባለውን ግን እንደማያውቁት፣የቤት ቁጥር 936/3/፣938/1/፣946 እና 947/2/ ለአመልካቾች ያልተሸጡላቸው፣ገንዘብ ያልተቀበሉባቸው እና ያላስረከቧቸው በመሆናቸው የፍርድ ባለመብት ፍርዱን ላያስፈጽሙባቸው የሚችሉ በመሆኑ የአመልካቾች ጥያቄ ተገቢነት የልለው መሆኑን፣የቤት ቁጥር 937/1/፣938፣940፣941፣943፣944፣945 የሆኑት ደግሞ የመንግስት ቤቶች በመሆናቸው ፍርዱ ላፈጸምባቸውም ሆነ መቃወሚያ ላቀርብባቸው የማይችልባቸው መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል።
አፈጻጸሙን የያዘው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ አመልካቾች ያቀረቡት ውል በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1723(1) ስር እና በንግድ ሕጉ ቁጥር 127 እንዲሁም የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1432(1) ድንጋጌዎችን ይዘት የሚያሟላ አይደለም በማለት የአመልካቾችን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።በዚህ ትዕዛዝ የአሁኑ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ችሎቱ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ የአሁኑ አመልካቾች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 አግባብ ያቀረቡት በመደበኛ የሙግት ስርዓት ከግራ ቀኙ ክርክርና ማስረጃ አንፃር ተመርምሮ ውሳኔ የሚሰጥበት ባለመሆኑና ይህንኑ እድል ደግሞ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 421 ክስ አቅርቦ መጠቀም እንደሚቻል፣ይህ ስለመሆኑም ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠበት መሆኑን ዘርዝሮ የሥር ፍርድ ቤትን የአፈጻጸም ትእዛዝ ምክንያቱን ለውጦ በማፅናት የአመልካቾችን አዲስ ክስ የማቅረብ መብታቸውን ጠብቋል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ሲሆን አመልካቾች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ የፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ለፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 እና 421 ድንጋጌዎች አተገባበር የሰጠው ትርጉም የሕጉን መንፈስና አላማ ያላገናዘበና ትርጉሙ ውጤት የልለው መሆኑን እንዲሁም የሥር ፍርድ ቤት ሽያጩ በሕጉ የተዘረጋውን የሽያጭ አደራረግ ስርዓት ያልተከተለ ነው ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው ለድርጅት ሽያጭ የተመለከቱትን የሕግ ድንጋጌዎችን ባግባቡ ያላገናዘበ መሆኑን ዘርዝረው በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ተሽሮ አመልካቾች በንብረቶቹ ላይ ያላቸው መብት እንዲጠብቅላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት ጠይቀዋል።አቤቱታቸው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበውም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
No topics extracted.
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ በሚከተለው መልኩ መርምረናል።እንደመረመርነውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው አብይ ነጥብ የፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 መሰረት የሚቀርብ አቤቱታ መደበኛ የሙግት ስርዓት ተከትሎ የሚከናወን አይደለም፣አቤቱታው ውድቅ የሆነበት አካል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 421 አግባብ ልላ ክስ አቅርቦ መብቱን ማስጠበቅ ይችላል በማለት የሰጠው የሕግ ትርጉም ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ሁኖ አግኝቶታል።
ከክርክር ሂደቱ መገንዘብ እንደተቻለው የአሁኑ አመልካቾች በወረዳ 5 ቀበል 06 ክልል በሚገኙትና ቁጥራቸው ከ936 እስከ 953 ተብሎ የተመዘገቡ የመኮነን ነጋሽ የሕዝብ ማመላለሻ ድርጅትና ጋራዥ በድርጅትነት እንደሚታወቅና ሰኔ 22 ቀን 1999 ዓ/ም በተደረገ የንግድ ቤት ድርጅት ሽያጭ ውል የሟች አቶ መኮነን ነጋሽ ሚስት ወ/ሮ የሻሸወርቅ ግዛው ከልጆቻቸው እነ ፋሲል መኮነን ነጋሽ (ሰባት ራሳቸው) እንዲሁም 2ኛ ተጠሪ ጋር በመሆን ሽጠውላቸው ነሐሴ 08 ቀን 1999 ዓ/ም የተረከቧቸው መሆኑን ገልፀው 1ኛ ተጠሪ በ2ኛ ተጠሪ ያቀረቡት የፍርድ አፈጻጸም ጥያቄ በእነዚህ ንብረቶች ላቀጥል እንደማይገባ ገልፀው በሽያጭ ያገኙት መብት እንዲጠብቅላቸው ዳኝነት ጠይቀው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽያጭ ውሉ ሕጉን የማያሟላ ነው በማለት የአመልካቾችን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉና የፍደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ግን የአመልካቾች አቤቱታ በመደበኛ ሙግት አመራር ስርዓት መሰረት ላከናወን የማይችልና መብታቸውን በአዲስ ክስ ማስከበር የሚችሉ መሆኑን ዘርዝሮ የስር ፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ምክንያቱን ለውጦ በውጤት ደረጃ የተቀበለው መሆኑን ነው።
በመሰረቱ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 እና 419 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ሲታይ በፍርድ አፈፃፀም ምክንያት ንብረት እንዳይያዝ ወይም እንዳይከበር የመቃወሚያ አቤቱታ ሲቀርብ ወይም በዚሁ ንብረት ላይ ተቀዳሚ መብት አለኝ የሚል ተቃዋሚ አቤቱታ ያቀረበ እንደሆነ ፍ/ቤቱ በሚያዘው ንብረት ላይ መብት እንዳላቸው በመቁጠር የሚያቀርቡትን መቃወሚያና አቤቱታ ተቀብሎ መመርመር እንዳለበት እንዲሁም በመጨረሻ ላይም የቀረበለትን አቤቱታና ማስረጃውን ከመረመረ በኋላ ንብረቱ እንዲያዝ ወይም እንዲከበር የሚያደርግ በቂ ምክንያት ያለመኖሩን የተረዳ እንደሆነ ንብረቱ እንደሁኔታው በሙሉ ወይም በከፊል እንዲለቀቅ ወይም ንብረቱ በፍርዱ አፈጻጸም መያዙ ተገቢ ሆኖ ካገኘው ደግሞ አቤቱታውን እንደሚሰረዝ ያስገነዝባሉ።ሆኖም ግን እነዚህ ድንጋጌዎች በተለይም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 419 መሰረት ፍ/ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሣኔ ሲሰጥ የልላውን ተከራካሪ ወገን ህገ መንግስታዊ የመስማት መብቱ ሣይከበርለት እና እንዲሁም አግባብነት ባለው መሰረት የተከበሩለትን መብቶች አንስቶ መከራከሪያ ሣያደርግባቸው ላፈጸም የሚችል አይደለም።በልላ አነጋገር የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 419 ድንጋጌ ይዘት የልላውን ተከራካሪ ወገን የመስማት፤የመደመጥ እና በህጉ አግባብ ክርክሩን የማቅረብ መብቱን የሚከለክል ያለመሆኑን ከላይ በተገለጸው አግባብ በመተንተን ይህ ችሎት በሰ/መ/ በቀረበው ጉዳይ ላይ በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በየትኛውም እርከን የሚገኝ ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል።በሰ/መ/ በቀረበው ጉዳይ ይህ የመሰማትና የመደመጥ መብት የማይከበር ስለመሆኑ በግልጽ አቋም ያልተያዘበት የሕግ ትርጉም ሲሆን በዚህ መዝገብ ላይ የተሰጠው ውሳኔ የሚያሳያው የቀዳሚነት መብት አለኝ በሚል መቃወሚያ አቅርቦ ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ሰው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 421 መሰረት በድጋሚ ክስ ለማቅረብ የተፈቀደለት በአፈፃፀም ችሎቱ የንብረቱ ባለመብትነት በጭብጥነት ተይዞ በመደበኛው የሙግት ስርአት አይነት የአመልካቹ ጥያቄ ከግራ ቀኙ ክርክርና ማስረጃ አንፃር ተመርምሮ ውሳኔ የሚሰጥበት ባለመሆኑ ይህንን እድል ለመስጠት ነው በሚል ነው።ሆኖም ችሎቱ ድንጋጌው የመደበኛ ሙግት ስርዓትን በመከተል መቃወሚያ አቤቱታውን ለማስተናገድ ሕጉ በግልጽ ክልከላ አድርጓል ወደሚለው ድምዳሜ ያልደረሰ ሲሆን በሰ/መ/ የተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው።በመሆኑም በሕጉ አግባብ የቀረበን መቃወሚያ የግራ ቀኙን ክርክር በመስማት ተገቢውን ዳኝነት መስጠት የፍትሓብሄር ስነ ስርዓት ሕጉን መሰረታዊ አላማ ያሳካል ከሚባል በስተቀር ልላ አሉታዊ ውጤት በክርክር አመራር ስርዓት ላይ የሚያስከትል አይደለም።በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 መሰረት አቤቱታ ያቀረበ ወገን በሕጉ አግባብ ማስረጃ ቆጥሮ ተቃውሞውን ከአቀረበ ጉዳዩ በአፈጻጸም መዝገብ እንዲከናወን ማድረግ ጊዜን፣ጉልበትንና ወጪ የሚቆጥብ መሆኑ የሚታመን ሲሆን ክርክሩ የመደበኛ መግት ስርዓትን ተከትሎ እንዲከወን ለማድረግ የሚያስችል አቤቱታ መቅረቡ እስከተረጋገጠ ድረስ የግራ ቀኙን የመከራከር መብት ጠብቆ በጉዳዩ ላይ ዳኝነት መስጠት ተገቢ አይደለም፣የሕጉን አላማ አያሳካም ላባል የሚችልበት ሕጋዊ ምክንያትም የለም። በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 አግባብ የተሟላ ክርክርና ማስረጃ ያቀረበ ወገን አቤቱታው በመደበኛ ሙግት እንዲከናወን እንዳይጠይቅ ሕጉ ግልጽ ክልከላ ያላደረገበት ሲሆን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 421 ስር የተጠበቀው መብትም በሕጉ አግባብ የሚቀርቡ መቃወሚያዎች እንደተጠበቁ ሁነው አመልካቹ በምርጫው እንዲጠቀምበት የተቀመጠ እንጂ ይህንኑ ስርዓት እንዲከተል የግድ የሚደረግበት ያለመሆኑ ድንጋጌው በፈቃደኝነት የአቀራረፅ ስርዓት መቀመጡ አስረጂ ነው።
ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካቾች ለክርክሩ መነሻ የሆኑት ንብረቶች በአፈጻጸም ላያዙ የማይችሉበትን ሕጋዊና በቂ ምክንያት ካላቸው ይህንኑ አንስተው ሙሉ በመደበኛው የሙግት ክርክር አቅርበው መብታቸው ላከበርላቸው የማይገባበት ምክንያት የለም። በመሆኑም በእርግጥም ሽያጭ ውሉ በህጉ አግባብ የተደረገ መሆን አለመሆኑንና ወይም በንብረቶቹ ላይ አመልካቾች ያቋቋሙት መብት መኖር ያለመኖሩና አመልካቾች በሽያጭ ንብረቶቹን አስተላልፈዋል የሚሐቸው ወገኖች ተግባሩን ለመፈፀም ከሕግ ወይም ከውል የመነጨ መብት ያላቸው መሆኑና ልሎች ተያያዥነት ያላቸውን የሕግና የፍሬ ነገር ክርክሮችን በጭብጥነት ይዞና በግራ ቀኙ ማስረጃዎችም ሆነ ፍርድ ቤቱ በሚያስቀርባቸው ልሎች አግባብነት ባላቸው ማስረጃዎች በማንጠር የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካቾች አለ የሚሉት የሽያጭ ውል ሕጋዊ አይደለም በማለት የሰጠው ትእዛዝ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን የፈድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ላወስንበት የሚገባው ሁኖ ሳላ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418፣419 እና 421 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ውጪ በመውጣት ጉዳዩ በመደበኛ የሙግት ስርዓት ላከናወን የሚችል አይደለም፣አዲስ ክስ በማቅረብ መብቱን ማስከበር የሚቻልበት ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ የድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ፣ የፍታብሕር ስነ ስርዓት ሕግ አይነተኛ አላማ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተነዋል።በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በዚህ ጉዳይ ላይ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ታህሳስ 23 ቀን 2005 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክሩን በመ/ ቀጥሎ የግራ ቀኙን አስቀርቦ የአመልካቾች አቤቱታ በህጉ አግባብ በተቀመጠው ሙሉ የመስማት መብት ጠብቆ እና ጉዳዩ በግራ ቀኙ ክርክር እና አግባብነት ባለው ማስረጃ እንዲጣራ ከተደረገ በኋላ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥበት በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 341 መሰረት ክርክሩን መልሰንለታል። ይፃፍ።
የሰበር ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ ብለናል።