No summary available.
መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ሰንደቁ አበበ - ጠበቃ ወንድአወክ አየለ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ሐብታሙ ቃበቶ - አልቀረቡም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ኑዛዜን መሰረት አድርጎ የቀረበውን የውርስ ንብረት ይለቀቅልኝ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በባህርዳር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት መጋቢት 21 ቀን 2002 ዓ/ም በአቀረቡት ክስ መነሻ ነው። ተጠሪ በመሰረቱት ክስም ተጠሪውና የአሁኑ አመልካች በሞግዚትነት የሚያስተዳድሯት እህታቸው ስመኝ ቃበቶ የአንድ እናትና አባት ልጆች መሆናቸውን፣ከእናታቸው ከሟች ወ/ሮ ነጠር አስፋው የተላለፈላቸው መኖሪያ ቤት በባህርዳር ከተማ ቀበል 06 ክልል ውስጥ እንደሚገኝና አመልካች፣ ተጠሪውና እህቱ ህፃን መሆናቸውን ተገን በማድረግ እንደ አንድ ወራሽ በመሆን በመኖሪያ ቤቱ ላይ የውርስ ማስረጃ በማውጣት ከ1989 ዓ/ም ጀምሮ ባለድርሻ ሁነው የቤቱን ኪራይ ተካፋይ ሲሆኑ መቆየታቸውን፣ተጠሪም ይህንኑ የአሁኑ አመልካች ድርጊት በመቃወም ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ያገኘውን የውርስ ማስረጃ እንዲሰረዝ፣የእህታቸው ሞግዚትነትና አስተዳዳሪነት እንዲነሳ ለፍርድ ቤት አመልክተው ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤት የአሁኑ አመልካች የያዘውን የውርስ ማስረጃ ሕግ በሚደግፈው መንገድ ያልተገኘ ስለሆነ ተሸሯል፣ነገር ግን የሞግዚትነት ስልጣንን በተመለከተ ግን የሟች ኑዛዜ ቃል ላከበር የሚገባው በመሆኑ ህፃኗ አካለ መጠን አድርሳ የበኩሐን መብት እስከምታስጠብቅ ድረስ የጸና ነው በማለት መወሰኑንና በይግባኝም ውሳኔው ያለመለወጡን ዘርዝረው አመልካች በተሳሳተ የውርስ ማስረጃ ለአስራ ሶስት አመታት የተጠቀሙበትን የገንዘብ መጠን ብር 139,900.00 መሆኑን በመዘርዘርና የተጠሪውን የድርሻ መጠን በመለየት በጠቅላላው ብር 23,316.20 እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስም የመጀመሪያ ወራሽነት ማስረጃ እንዲሰረዝ በተሰጠው ውሳኔ ቅሬታ አድሮባቸው ጉዳዩ በይግባኝ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን፣ስመኝ ቃበቶን በተመለከተ የውክልና ስልጣን ስለልላቸው ክስ ለማቅረብ የማይችሉ፣ጉዳዩ ከዚህ ቀድሞ በፍርድ ያለቀ በመሆኑ በድጋሚ ላቀርብ እንደማይገባ፣ክሱ በይርጋ የታገደ በመሆኑ ክሱ ላቀጥል እንደማይገባ፣የአመልካች የወራሽነት ማስረጃ የተሰረዘው የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ላሆኑ አይችሉም በሚል እንጂ የኑዛዜ ወራሽነትን በሚመለከት ያለመሆኑን የሚመለከቱ ነጥቦችን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገር ክርክር ረገድ ደግሞ ተጠሪ በክሱ ላይ የጠቀሱት ገንዘብ ብር 139,900.00(አንድ መቶ ሰላሳ ዘጠኝ ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር)፣የተጠሪ ድርሻ ተብሎ የተገለፀውን ብር 23,316.60 ለብቻቸው ያልተጠቀሙበት በመሆኑ ላከፍሉ የማይገባ መሆኑን፣ከ1989 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር1998 ዓ/ም ድረስ ቤቱ ተከራይቶ ይገኝ የነበረውን የተለየ መጠን ያለውን የኪራይ ገቢ ተጠሪ በየወሩ ድርሻቸውን እየተረከቡ ምግባቸውን ከአመልካችና ከስመኝ ቃበቶ ጋር ሁነው ሲጠቀሙ የነበረ መሆኑን፣ተጠሪ በ1996 ዓ/ም የውርስ አጣሪ ይሾምልኝ አቤቱታ አቅርበው ስለነበር አመልካች ቀርበው መልስ ከሰጡ በኋላ ሽማግልዎችን መርጠው ድርድር ጀምረው ተቋርጦ ከቆየ በኋላ እንደገና ድርድሩ ጀምሮ ስምምነት ላይ ተደርሶ ድርሻቸውን ተከፋፍለው እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ዘርዝረው በክሱ ላይ የተገለፀውን ገንዘብ የመክፈል ግድታ የለብኝም በማለት ተከራክረዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የወረዳው ፍርድ ቤትም አመልካች የኑዛዜ ወራሽ መሆናቸው ስለተረጋገጠ ከተጠሪ ጋር እንደ ያለ ኑዛዜ ወራሽ ሁነው ንብረቱን እኩል የሚካፈሉ ናቸው የሚል ምክንያት ይዞ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 915(1) ድንጋጌን በዋቢነት ጠቅሶ አመልካችና ተጠሪ በክሱ የተጠቀሰውን የኪራይ ገንዘብ በጋራ የተጠቀሙ ስለሆነ አመልካች ለተጠሪ ላከፍሉ አይገባም፣የስመኝ ቃበቶ ሞግዚትነት ስልጣንን በተመለከተ ግን አካለ መጠን ያደረሰች በመሆኑ ራሷ ከምትጠይቅ በስተቀር ተጠሪ ላጠይቅ አይገባም በማለት ወስኗል።በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይገባኙን ለምእራብ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የአመልካች የኑዛዜ ወራሽነት ጥያቄ ኑዛዜው ስለግልጽ ኑዛዜ አደራረግ ሕጉ ያስቀመጠውን መስፈርት የማያሟላ ሁኖ ተገኝቷል በሚል ምክንያት ማስረጃውን ውድቅ ያደረገውና የሟች ወ/ሮ ነጠር አስፋው ሕጋዊ ወራሾች ተጠሪና እህታቸው ስምኝ ቃበቶ ናቸው ሲል የደመደመ ሲሆን ውጤቱንም በተመለከተ የቤቱን ኪራይ ገቢ አመልካች ሕጋዊ ወራሽ ነኝ በሚል እምነት ከተጠሪ ጋር በጋራ የተጠቀሙበት በመሆኑ ላከፍሉ አይገባም፣ቤቱን በተመለከተ ግን ለሟች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች ለተጠሪና ለወ/ሮ ስመኝ ቃበቶ አመልካች ላያስረክቡ ይገባል በማለት ወስኗል።በዚህ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት በድምጽ ብልጫ ተሰርዞባቸዋል።
No topics extracted.
ከዚህም በኋላ የሰበር አቤቱታቸው ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ጉዳዩን ከይርጋ መቃወሚያ አንፃር ብቻ በመመልከት ጉዳዩ የጋራ የውርስ ንብረት ክፍፍል ጥያቄ ስለሆነ በማናቸውም ጊዜ ላጠየቅ የሚችል ነው የሚል ምክንያት ይዞ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አፅንቶታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ጉዳዩ ቀድሞ በፍርድ ያለቀ ሁኖ እያለ ስለኑዛዜው ሕጋዊነት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች በማንሳት በዚህ ረገድ የተሰጠውን የወረዳውን ፍርድ ቤትን ውሳኔ መሻራቸው ያላግባብ ነው የሚል ነው።አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች ወ/ሮ ነጠር አስፋው ሰኔ 03 ቀነ 1988 ዓ/ም ባደረጉላቸው ኑዛዜ የኑዛዜ ወራሽ መሆናቸውና ኑዛዜውም በወቅቱ በፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 99/89 ፀድቆ እስከ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መፅናቱ እየታወቀ ባሁኑ ተጠሪ ከሳሽነት በመ/ የተጀመረውን ክርክር በመቀበል ኑዛዜው በፍርድ ቤት መጽደቅ አይገባውም ነበር፤ኑዛዜው በሕግ የተቀመጠውን መስፈርት አያሟላም በማለት ጉዳዩን ዳግም በማየት ኑዛዜውን የመሻራቸውን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለሰበር ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪና ስመኝ ቃበቶ የሟች ወ/ሮ ነጠር አስፋው የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ መሆናቸው መረጋገጡን፣አመልካቸ የሟቿ ወራሽ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በመ/ቁጥር 99/89 መጋቢት 15 ቀን 1994 ዓ/ም ከወረዳው ፍርድ ቤት አግኝተው የነበረ መሆኑን፣ተጠሪ ይህ ማስረጃ በአመልካች የተገኘው ያላግባብ በመሆኑ ላሰረዝ ይገባል በማለት ለወረዳው ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበው የወረዳው ፍርድ ቤት በመ/ ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ አመልካች ከሟች የተወለዱ ባለመሆኑ ወይም የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ላያደርጋቸው የሚችል ልላ ሕጋዊ ግንኙነት የልለ በመሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ላሆኑ የሚችሉበት የሕግ መሰረት የለም በማለት ማስረጃውን ሰኔ 03 ቀን 2001 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰረዘው መሆኑን፣ይህ ውሳኔ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ ቀርቦም በመ/ በሆነው ግራ ቀኙ ተከራክረውበት ህዳር 21 ቀን 2002 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተቀባይነት አግኝቶ በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ አመልካች የሟቿ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ላሆኑ የሚችሉበት የህግ መሰረት የለም፣የአመልካች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽነት ማስረጃ ይሰረዝልኝ በሚል በተጠሪ ቀርቦ በታየውና በበታች ፍርድ ቤቶች በተሰጠው የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽነት ማስረጃ ይሰረዝ ዳኝነት ላይ አመልካች ስለኑዛዜ ክርክር የሚያቀርቡበት አግባብ የለም በማለት የመ/ በሆነው ሐምል 27 ቀን 2002 ዓ/ም በዋለው ችሎት የአጸናው መሆኑንና ለአሁኑ የሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው የተጠሪ ክስ በወረዳው ፍርድ ቤት የተመሰረተውም መጋቢት 21 ቀን 2002 ዓ/ም መሆኑን ነው።
ከዚህ መረዳት የሚቻለው ተጠሪና አመልካች በባህርዳር ወረዳ ፍርድ ቤት በጋራ የመ/ቁጥር 99/89 በሆነው በአስከፈቱት መዝገብ በኑዛዜው ላይ የነበሩ ምስክሮች ቀርበው መስክረው ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ኑዛዜው የሕግን ፎርማላቲ ያሟላ ነው በማለት ኑዛዜውን መጋቢት 14 ቀን 1994 ዓ/ም ያፀደቀው መሆኑን፣የበታች ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ አመልካች ኑዛዜው ቀድሞ ፀድቋል፤በፍርድ ያለቀ ነው በማለት ያቀረቡትን ክርክር ውድቅ ያደረጉት ኑዛዜው በፍርድ ቤት መፅደቁንና ተጠሪ የክርክሩ ተካፋይ የነበሩ መሆኑን በማመን ኑዛዜው ቀድሞውንም የሕጉን መስፈርት የማያሟላ ሁኖ እያለ በፍርድ ቤት መጽደቁ ያላግባብ ነው በሚል ምክንያት መሆኑን ነው።
ከላይ እንደተጠቀሰው ሟች ያደረጉት ኑዛዜ ግልፅ ኑዛዜ መሆኑ ያላከራከረ ጉዳይ ነው።ግልጽ ኑዛዜ ላያሟላ የሚገባቸው ስርዓቶች በፍ/ሕ/ቁ.881 ሥር ተዘርዝረዋል።ይኸውም 1ኛው ኑዛዜው በአራት ምስክሮች ፊት መነበብ ያለበት መሆኑ፣ይህም ስርዓት መፈፀሙና የተፃፈበት ጊዜ በኑዛዜው ላይ መመልከቱ፣ተናዛዥና ምስክሮቹ በኑዛዜው ላይ ወዲያውኑ ፊርማቸውን ወይም ያውራ ጣት ምልክታቸውን ማድረጋቸው መረጋገጡ አስፈላጊ መሆኑ ነው።በሟች ተሰጠ የተባለው ኑዛዜም ሰነዱ ሲታይ አራት ምስክሮች ያልፈረሙበት፣ኑዛዜው በምስክሮች እና በተናዛዡ ፊት ስለመነበቡ የማይገልጽ መሆኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ በቀረበው ክርክር ያረጋገጠው ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበናል።በመሆኑም ሟች ያደረጉት ኑዛዜ በፍ/ሕ/ቁ. 881 ሥር የተመለከቱትን ስርዓቶችን ያላሟላ ነው ተብሎ ውሳኔ የተሰጠው አመልካችና ተጠሪ ቀድሞ በመ/ቁጥር 99/89 በቀረበው ክርክር ከተከራከሩና ኑዛዜው ሕጋዊ ነው ተብሎ በፍርድ ቤት ከፀደቀ በኋላ ነው።
ፍርድ ቤቱ ኑዛዜው ፈራሽ ነው በማለት የወሰነው ቀድሞውኑም ስርዓቱን ሳያሟላ ፍርድ ቤቱ በመ/ቁጥር 99/89 ማፅደቁ ተገቢ አልነበረም በሚል ምክንያት ነው።ይሁን እንጂ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ የሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በፍርድ ቤት ኑዛዜው የፀደቀ ነው ተብሎ ሲወሰን ልሎች ሰዎች በሰነዱ ላይ ተቃውሞ ካላቸው ይህንኑ ከማቅረብ የማይከለከሉ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን የኑዛዜውን ሕጋዊነት መሰረት አድርጎ ተከራክሮ ተቀባይነት ያጣና ኑዛዜው በፍርድ ቤት የፀደቀበት ሰው በልላ ጊዜ ስለኑዛዜው ሕጋዊነት ክስ መመስረት ወይም መቃወሚያነት ማቅረብ የሚችል መሆኑን የሚያሳይ አንድምታ የልለው ነው።በመሆኑም በሕግ አግባብ የተደረገን ኑዛዜ በፍርድ ቤት ማስጸደቅ ያስፈልጋል? ወይስ አያስፈልግም? የሚል ጭብጥ ተይዞ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠበትን የሰ/መ/ ጉዳይ መሰረት አድርገን ጉዳዩን ስንመለከተው አንድ በፍርድ ቤት ሕጋዊነቱ ተረጋግጦ የፀደቀ ኑዛዜ ቀድሞውንም መፅደቅ አልነበረበትም ተብሎ ፈራሽ እንዲሆን የሚደረግ የሕግ ምክንያት የለውም።አግባብነት ያላቸው ተከራካሪ ወገኖች ስለኑዛዜው ሕጋዊነት ክርክር አቅርበው ኑዛዜው ሕጋዊ መሆኑ ተረጋግጦ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በጉዳዩ ላይ በድጋሚ ክስ ማቅረብና ፍርድ ቤቱም መቀበል በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ የሚጥስ ነው።በዚህ ድንጋጌ አግባብ ጉዳዩ በፍርድ ቀደሞ ያለቀ ነው ተብሎ ተቀባይነት እንዲያገኝ ካልተደረገ በስተቀር ክርክሮች መቋጫ እንዳይኖራቸው የሚያደርግና ተከራካሪ ወገኖችን ለአላስፈላጊ የገንዘብ፣ጊዜና ጉልበት ብክነት የሚዳርግ፣ከስነ ስርዓት ሕጉ መሰረታዊ አላማም ውጪ ነው።አንድ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ዳኝነት መስጠት የሚገባውም በስርዓቱ መሰረት የቀረበለትን ይግባኝ መሰረት አድርጎ ነው እንጂ ቀድሞ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ተገቢ አልነበረም በሚል ምክንያት እንዳልሆነ ስለይግባኝ ስርዓት ከተደነገጉት ድንጋጌዎችና ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 212 ድንጋጌ ጣምራ ንባብ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።ተጠሪ የኑዛዜን ወራሽነት አስመልክቶ አመልካቸ የሚያቀርቡትን ክርክር በመ/ቁጥር 99/89 ያልተካሄደ ነው ወይም በወቅቱ በጉዳዩ ላይ ክርክር ለማቅረብ የማያስችሉ ሕጋዊ ምክንያት የነበራቸው ስለመሆኑ ገልፀው ያልተከራከሩ ከመሆናቸውም በላይ አመልካች የሟች ነጠር አስፋው የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ አይደሉም ተብሎ ማስረጃው እንዲሰረዝ በቀረበው ክርክር አመልካቹ ስለኑዛዜው ሕጋዊነት እስከ ክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ክርክር አቅርበው ችሎቱ በመ/ ሐምል 27 ቀነ 2002 ዓ/ም በሰጠው ውሳኔ በመዝገቡ የተያዘው ክርክር ስለመጀመሪያ ደረጃ ወራሽነት እንጂ ስለኑዛዜ ተጠቃሚነት ያለመሆኑን ጠቅሶ በዚህ ነጥብ ላይ ዳኝነት ሳይሰጥበት ማለፉ በዚህ ረገድ አመልካች ወደፊት የሚያቀርቡትን ክርክር ያልገደበው መሆኑን የሚያሳይ ነው።በአንድ ጉዳይ በጭብጥነት ተይዞ እልባት ያላገኘ ነጥብ ደግሞ ቀድሞ በፍርድ አልቋል ለማለት የማይቻል መሆኑን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌ ይዘት ያስገነዘባል።ስለሆነም አመልካች ኑዛዜውን አስመልክቶ የሚያቀርቡት ክርክር የመጨረሻ ፍርድ ያላገኘ ሲሆን የተጠሪ ግን በመ/ቁጥር 99/89 በተሰጠው ፍርድ መሰረት የመጨረሻ ዳኝነት ያገኘ ሁኖ አግኝተናል።
ሲጠቃለለም አመልካች በፍርድ ቤት የፀደቀው ኑዛዜ ተጠቃሚነትን መሰረት አድርገው ጉዳዩ ቀድሞ በፍርድ ቤት ያለቀ ነው በማለት ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የታለፈው ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ውጪ በመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል።በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በምእራብ ጎጃም ዞን መስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 01-32078 ሰኔ 29 ቀን 2003 ዓ/ም፣በክልሉ ሰበር ሰሚ ጥቅምት 22 ቀን 2004 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሐል።
ሟች ወ/ሮ ነጠር አስፋው አደረጉት የተባለው ኑዛዜ የሕጉን መስፈርት ያላሟላ በመሆኑ ፈራሽ ነው ተብሎ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ ቀድሞ በፍርድ ባለቀ ጉዳይ የተሰጠ በመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌንና በፍርድ ቤት በጸደቀ ኑዛዜ ተቃውሞ የሚቀርብበትን አግባብ ያላገናዘበ ነው ብለናል።
በባህርዳር ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር በ19749 መስከረም 24 ቀን 2003 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል፤አመልካች ሟች ወ/ሮ ነጠር አሰፋው ሰኔ 03 ቀን 1988 ዓ/ም ባደረጉት ኑዛዜ ተጠቃሚነታቸው በወረዳው ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 99/89 በተሰጠ ውሳኔ የተረጋገጠ ነው ብለናል።
ተጠሪ እና ስመኝ ቃበቶ በአከራካሪው ቤት ላይ ከአመልካች ጋር እኩል መብት አላቸው ብለናል።አመልካች ለተጠሪ የሚከፍሉት የኪራይ ገንዘብ የለም ተብሎ መወሰኑ ተገቢ ነው ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ።