No summary available.
ሰኔ 18 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ሙሉ ኤልክሮኒክስ ኢንጂነሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጠበቃ ታደሰ ጉርሙ ቀረቡ መልስ ሰጪ፡- ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል /አ.አ/ ነ/ፈጅ ዳንኤል ጥላሁን ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ከውል አፈፃፀም ጋር ተያይዞ የተነሳውን የክፍያ ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመስረተው ክስ መነሻ ነው። የተጠሪ ክስ ይዘትም የአሁኑ አመልካች ለልብ ሕመማን አገልግሎት የሚውል ECLO car diagram ultra sound GE modele VIVID of system የተባለ የልብ ህክምና መመርመሪያ መሳሪያ ለተጠሪ ለማስረከብ ውል ተዋውሎ ቅድሚያ ክፍያ 30% ብር 702,000.00 /ሰባት መቶ ሁለት ሺ ብር/ ተቀብሎ መሳሪያውን ላያቀርብ ያለመቻሉን ገልፆ መሳሪያውን በአስቸኳይ እንዲያቀርብ ካልሆነም በቅድሚያ የወሰደውን ገንዘብ እጥፍ አድርጎ ብር 1,404,000.00 ከነወለዱ እንዲከፍለን ይወሰንለት ዘንድ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው። የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም ከተጠሪ ጋር ውል መዋዋሉንና የቅድሚያ ክፍያ መቀበሉን ሳይከድ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን መሳሪያ ለተጠሪ ያላስረከበው መሆኑን ገልፆ መሳሪያውን ለማምጣት ኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን የግዥ ውል ከጠቅላላ ሰነድ ጋር ቀርቦለት እንዲፀድቅ መጠየቅ እንዲሁም መሳሪያው ከውጪ እንደሚመጣ በመሆኑ ባንክ ምንዛሬ እንዲፈቅድ መጠየቅ ስለነበረበት ተጠሪም ትብበር እያደረገ ስምምነቱ ከተደረገበት ባንክ እስከ ተፈቀደበት ሚያዚያ 12 ቀን 2002 ዓ/ም ድረስ አስራ አንድ ወራቶች መቆጠራቸውን መሳሪያው ወደ አገር እንዲገባ የሚፈቅደው አካል ደግሞ ያልፈቀደለት በመሆኑ እየተጠባበቀ የሚገኝ መሆኑንና በዚህ ችግር ምክንያት ውሉን ያልፈጸመ ስለመሆኑ ገልጾ መሳሪያውን እንዲያስረክብ እንዳደረግ ይህ የማይፈቀድ ከሆነ ተጠሪ የቅድሚያ ክፍያ እጥፍ እንዲከፈለው ያቀረበው ጥያቄ በውሉ ከተቀመጠው ግድታ ውጪ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው። የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከተሰማ በኋላ አመልካችን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ በውሉ በተመለከተው ግድታ መሰረት መሳሪያውን ማስረከብ ከሚገባበት ከሐምል 12ቀን 2002 ዓ/ም ጀምሮ ሲታሰብ 437 ቀናት ማለፋቸውንና ለእያንዳንዱ ቀን 0.1% መቀጮ የግዥ ዋጋ ከሆነው ብር 2,340,000 .00 ሲታሰብ ብር 999, 180. 00 /ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺ አንድ መቶ ሰማንያ ብር/ የሚመጣው ገንዘብ በመቀጮነት አመልካች ለተጠሪ ላከፈል የሚገባው መሆኑን ገልፆ ይህንኑ ገንዘብ እንዲከፍል እንዲሁም የቅድሚያ ክፍያ ብር 702,000.00 /ሰባት መቶ ሁለት ሺህ ብር/ ክሱ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍል በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፈድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አጽንቶታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች ሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በተጠሪ የተጠየቀውን ዳኝነት ይዘት ያላገናዘበና በጉዳዩ ላይ ላመሰረት ይገባው የነበረውን ጭብጥ በአግባቡ ያልለየ መሆኑን ዘርዝሮ ውሳኔው እንዲለወጥ ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው። የሰበር አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።፡ የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም አመልካች ብር 999,180.00 በመቀጮነት እንዲከፈል የተወሰነው በተጠሪ የዳኝነት ጥያቄ ቀርቦ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ አግኝቶታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ ከአመልካች ጋር ተደርጓል በሚለው ስምምነት አከራካሪውን እቃ በወቅቱ አመልካች ያላስረከበ መሆኑን ገልጾ እንዲወሰንለት ዳኝነት የጠየቀው የህክምና መሳሪያውን በአስቸኳይ እንዲያስገባ መስሪያውን በውሉ መሰረት ማስገባት ካልቻለ በቅድሚ የወሰደውን ገንዘብ በእጥፍ አድርጎ በድምሩ 1,404,000.00 /አንድ ሚላዮን አራት መቶ አራት ሺ ብር/ መሳሪያውን ማስገባት ከነበረበት ቀን አንስቶ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር ገንዘቡን እንዲከፍልና ወጪና ኪሳራም ዝርዝር የማቅረብ መብቱ እንዲጠበቅለት መሆኑን ጥቅምት 02 ቀን 2004 ዓ.ም ተጠሪ ያቀረበው የክስ ማመልከቻ የሚያሳይ መሆኑን አመልካች ለተጠሪ ክስ በሰጠው መልስም ውሉ መኖሩንና ከተጠሪ ቅድመ ክፍያ መቀበሉን ሳይክድ ለውሉ አለመፈጸም ሕጋዊ ምክንያት ናቸው ያላቸውን ምክንያቶችን አንስቶ መከራከሩን ነው።
No topics extracted.
በመሰረቱ አመልካች ውሉን ለመፈፀም አላስቻለኝም በማለት አጥብቆ የሚከራከርበት ነጥብ የልብ መመርመሪያ መሳሪያውን ለማስመጣት ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ያለማግኘቱን ጠቅሶ ነው ይሁን እንጂ ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረበው ማስረጃ ያለመኖሩንና እቃውን ሳያስገባ ያለፉት ቀናት ብዛት ሲታዩ ፈቃድ ያለማግኘቱን ያሳያል ወይም ውሉን ለመፈፀም ተገቢውን ጥረት አድርጓል ለማለት የሚቻል አለመሆኑን ደምድመዋል። በመሆኑም ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ የበታች ፍርድ ቤቶች የልብ መመርመሪያ መሳሪያው ወደ አገር ውስጥ ያልገባው ፈቃድ ከሚሰጠው አካል ፈቃድ ሳይገኝ መቅረቱን አረጋግጠዋል በማለት የተያዘው ፍሬ ነገር ድምዳሜ በበታች ፍርድ ቤቶች የተደረገውን የግራ ቀኙን ክርክርና የማስረጃ ይዘት ያላገናዘበ በመሆኑ ይህ ችሎት የሚቀበለው ሁኖ አልተገኘም። አመልካች መሳሪያውን ለማስገባት የሚመለከተው አካል የከለከለው ስለመሆኑ በማስረጃ ያለማስደገፉ ከተረጋገጠ ደግሞ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1792 ድንጋጌን ጠቅሶ የሚያቀርበው ክርክር ተቀባይነት የሚገኝበት አግባብ የለም።
ወደ ዋናው ጭብጥ ስንመለስም ከላይ እንደተገለፀው በተጠሪ ከተጠየቁት ዳኝነቶች መካከል አንዱ የቅድመ ክፍያ ገንዘብ እጥፍ ሁኖ እንዲመለስ ሲሆን የስር ፍርድ ቤት ዳኝነት የሰጠው ግን አመልካች እቃውን ማስገባት ከነበረበት ከሐምል 12 ቀን 2002 ዓ/ም ጀምሮ በሚታሰብ 427 ቀናት ማለፋቸውንና ለእነዚህ ቀናትም የውሉን ጠቅላላ ዋጋ ብር 2, 340,000. 00 0.1% ሲታሰብ የሚመጣውንና ከውሉ ዋጋ 10% ያልበለጠውን መቀጮ አመልካች በውሉ አንቀጽ 2.3/ለ/ እና በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1731 ለመከፈል ይገደዳል የሚል ምክንያት ይዞ ሲሆን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም አመልካች የቅደም ክፍያ የከፈለ ሁኖ እያለ ቀብድ አድርጎ እጥፍ መጠየቁ ስህተት መሆኑን አምኖ ክሱ ላመሰረት የጠየቀው ዳኝነት የቅድመ ክፍያ እጥፍ ቢሆንም ክሱ በተሰማበት ወቅት የመቀጫ ገንዘብ መጠየቁ ተረጋግጧል በሚል ምክንያት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ማጽናቱን ተገንዝበናል።
በመስረቱ ክርክር የሚመራውና ዳኝነት የሚሰጠው በህጉ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ነው። በህጉ ከተዘረጋው የክርክር አመራርና የዳኝነት አሰጣት ስርዓት ውጪ ክርክር የመምራትና ዳኝነት የመስጠት አካሄድ የዳኝነት ሰጪ አካሉን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑ የሚታመን ነው። አንድ ፍርድ ቤት ዳኝነት የሚሰጠው በተከራካሪ ወገን የተጠየቀ ሁኖ በሕጉና በውሉ የተፈቀደ መሆኑን በጥንቃቄ አረጋግጦ ሲሆን ተከራካሪ ወገን በሕጉ ወይም በውሉ የተፈቀደለትን መፍትሕ ለማግኘት በግልጽ ዳኝነት መጠየቅ የሚገባው መሆኑን ስለክስ አመሰራረትና የመከላከያ መልስ አቀራረብን የሚደነግጉት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 222፣234፣235፣236 እና 83 ድንጋጌዎች ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 224 እና 182 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ጋር ተዳምረው ሲታዩ የምንረዳው ጉዳይ ነው። እነዚህ ድንጋጌዎች የዳኝነት ጥያቄ አይነትና መጠኑን በክሱ ማመልከቻ በግልጽ መስፈር ያለበት መሆኑን ያሳያል ከፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 224 ድንጋጌ ጠቅላላ ይዘቱ ሲታይም ከሳሹ በጉዳዩ ላይ የሚጠይቀው ዳኝነት ጠቅላላ ፍርድ ቤቱ የክሱን ጭብጥና የማስረጃውን አከባቢ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ትክክለኛ መስሎ የታየውን ፍርድ ላሰጥ እንደሚችል ያስገነዝባል። የፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 241 ድንጋጌ መሰረታዊ አላማ ተከራካሪ ወገኖች/ በጽሑፍ ያቀረቡትን ክርክር ለማብራራትና በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 246-248 ድንጋጌች አግባብ ጭብጥ ለመመስረት እንዲያገዝ ሲሆን በጽሑፍ ማመልከቻው ላይ ያልሰፈረን ዳኝነት ለመጠየቅ የሚስችል ያለመሆኑን የድንጋጌው ይዘትና መንፈስ ያስረዳል። ተከራካሪ ወገኖች ከመጀመሪያው ክረክር ላይ ካቀረቡት በቀር ልላ ተጨማሪ ሙግት ወይም ልላ ማስረጃ ማስቀረብና መመርመር የሚያስፈልግ ከሆነ ወይም ቀድሞ የተያዘው ጭብጥ የሚሻሻል ወይም ተጨማሪ ጭብጥ የሚያዝ መሆኑ ከታመነም በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 255 እና 251 አግባብ የሚፈፀም እንጂ ያለህጋዊ ምክንያት በማናቸውም የክርክር ደረጃ የቀረበ ክርክር ሁሉ ተቀባይነት የሚያግኝበት የክርክር አመራር የለም።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስ ተጠሪ የጠየቀው ዳኝነት ቅድመ ክፍያ አጥፍ ሁኖ እንዲከፈል ሲሆን በውሉ በተመለከተው አግባብ መቀጫ እንዲከፈለው በግልጽ አልጠየቀም የቅድመ ክፍያው እጥፍ ሁኖ እንዲከፈለው ጥያቄ ያቀረበው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1883 እና ተከታይ ድንጋጌዎች የተቀመጠውን የቃብድ መሰረተ ሐሳብ ይዞ ስላለመሆኑ የክስ ማመልከቻው ያሳያል እንዲህ ከሆነ አመልካች ለተጠሪ የቅድመ ክፍያውን እጥፍ አድርጎ ለተጠሪ የሚከፍልበት አግባብ መኖር ያለመኖሩ በጭብጥነት ተይዞና የክሱን ጭብጥና የማስረጃውን አካባቢ ሁኔታ መሰረት አድርጎ ዳኝነት ከሚሰጥበት በስተቀር የመቀጫ ገንዘብ በጭብጥነት የሚያዝበት አግባብ የለም። የፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስለቀብድ የያዘው ጭብጥ ተገቢነት ያልነበረው ሲሆን ውጤቱ ሲታይ ተጠሪ በውሉ አለመፈፀም ከአመልካች የሚጠይቀውን ኪሳራ ከመጠየቅ ላከላከለው የማይገባ መሆኑን ያሳያል። ምክንያቱም ተጠሪ አመልካችን የጠየቀው የቅድመ ክፍያ እጥፍ ክፍያ ለጉዳቱ ተገቢ ነው ብሎ ያሰበውና ጠቅላላ አገላለጽ ነው ተብሎ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 224 መሰረት ግንዛቤ የሚወሰድበት ነውና። ይህ የተጠሪው የክስ ዳኝነት ጥያቄ ዝርዝር ይዘት ደግሞ ግራ ቀኙ በውሉ ከአቋቋመበትና በማስረጃ ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር በመነሳት ምላሽ ላያገኝ የሚገባው ነው።
ይሁን እንጂ በውሉ የተጠቀሰው ስልት መሰረት ተደርጎ የሚመጣው መጠን በማናቸው ምክንያት ተጠሪ በግልጽ መጠኑን ለይቶ ከአቀረበው የዳኝነት ጥያቄ ላበልጥ የሚችልበት የዳኝነት አሰጣጥ ላኖር አይችልም። በመሆኑም ተጠሪ የቅድመ ክፍያውን እጥፍ ሲጠይቅ በውሉ የተቀመጠው መሆኑን ገልፆ ባለመሆኑና አመልካችም የቅድመ ክፍያውን መወስዱን ያልካደው በመሆኑ አመልካች ለተጠሪ ላገደድ የሚገባው የክፍያ መጠን ቅድመ ክፍያውንና ተጠሪ በመቀጫነት ላታሰብ ይገባል ያለው የዚሁ ገንዘብ መጠን ነው። ተጠሪ ውሉን መሰረት አድርጎ ስልቱን ቢሰራ ኖሮ የመቀጫው ገንዘብ የሚመጣው ብር 999, 180.00 ሲሆን ይህን ባለማድረጉና ቅደመ ክፍያው እጥፍ ነው ላከፈል የሚገባው ብሎ ዳኝነት በመጠየቁ የመቀጫ ገንዘቡ ከብር 702,000.00 /ሰባት መቶ ሁለት ሺ ብር/ ላበልጥ የሚችልበት አግባብ የለም በመሆኑም የተጠሪ ክስ ማመልከቻ ጠቅላላ ይዘት ሲታይ ለውሉ ያለመፈፀም የጠየቀው የመቀጫ ገንዘብ ነው ወደሚለው ድምዳሜ ያደረሰን በመሆኑ መጠኑን በተመለከተ ግን ተጠሪ በግልጽ ያስቀመጠ በመሆኑ የመቀጫ ገንዘቡ 999,180. 00 ተብሎ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ ከቅድመ ክፍያ ገንዘብ ጋር ተዳምሮ ሲታይ አመልካች በግልጽ ከጠየቀው ከብር 1, 404,000.00 / አንድ ሚላዮን አራት መቶ አራት ሺ ብር/ የብር 297,180. 00 /ሁለት መቶ ዘጠና ሰባት ሺ አንድ መቶ ሰማንያ ብር/ ብልጫ ያለው ሁኖ ተገኝቷል። ይህ ደግሞ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 182/2/ ድንጋጌን በግልጽ የሚጻረር በመሆኑ ከዚህ አንጻር ሲታይ የበታች ፍርድ ቤቶች የውሳኔ አሰጣጥ ከተጠየቀው ዳኝነት በላይ በመሆኑ ከላይ የተጠቀሱትን የስነ ስርዓት ሕግ ድንጋጌዎችን ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተኝቷል።
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ የካቲት 20 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ ተሻሽሐል።
ተጠሪ አመልካች በውሉ ላይ በተመለከተው መሰረት የመቀጫ ገንዘብ እንዲከፈለው ዳኝነት ያልጠየቀ በመሆኑ በውሉ በተመለከተው ስልት መሰረት መቀጫውን አመልካች ለተጠሪ ላከፈል አይገደድም ብለናል። ይሁን እንጂ አመልካች የቅድመ ክፍያውን አጥፍ መሰረት አድርጎ የመቀጫ ገንዘቡ እንዲከፈል የተጠየቀ በመሆኑ ለመቀጫ ብር 702,000.00 /ሰባት መቶ ሁለት ሺ/ ለተጠሪ ላከፍል ይገባል ብለናል።
አመልካች የቅደመ ክፍያው ብር 702,000. 00 /ሰባት መቶ ሁለት ሺ/ በተመለከተ ክስ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጋር ለተጠሪ እንዲከፍል የተሰጠው ውሳኔ ከፍል በሙሉ ጸንቷል። ይሁን እንጂ አመልካች ይህንኑ ገንዘብ ለተጠሪ ክፍሎ ከሆነ በአፈፃፀም ጊዜ እንዲታይለት ከማድረግ ይህ ውሳኔ አያግደውም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል። ይፃፍ።
ሐ/አ