No summary available.
ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አደነ ንጉሴ አመልካች፡- ጠበቃ አንበርብር ዓባይነህ አልቀረቡም ተጠሪ፡ የፍትሕ ሚኒስቴር አልቀረቡም መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የቀረበው የአሁን አመልካች የጠበቆችን ስነ ምግባር ደንብ ተላልፎ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል በሚል በአዋጅ ቁጥር 199/92 አንቀጽ 24/3 መሰረት በፍድራል ፍ/ቤቶች የጠበቆች የዲስፕላን ጉባኤ ውሳኔ ተሰጥቶ በፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር የጸደቀው ውሳኔ አግባብነት በግራ ቀኙ መካከል በተደረገው ክርክር ከተረጋገጡት ፍሬ ነገሮች በመነሳት ለጉዳይ አግባብነት ካለው ከዚህ ህግ አንፃር ለማየት በሚል ነው።
የጉዳዩ መነሻ የሆነው የአሁን አመልካች በጥብቅና ተወክሎ የሚከራከርበት ጉዳይ በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ተወስኖ በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም በይግባኝ ታይቶ የፀናውን እና በፍርድ ያለቀ ጉዳይ መሆኑን እያወቀ እንደገና በዚያው በፍርድ ያለቀው ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እንደገና አቤቱታ ከማቅረብ በፊት በፍርድ ባለቀው ጉዳይ የተለየ ዳኝነት እንዲሰጥ በማድረጉ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 5 ከተወሰነው ድንጋጌ አንፃር ይኸው ተግባሩ የሙያ ጥፋት ሆኖ ስለተገኘ በአዋጅ ቁጥር 199/92 አንቀጽ 24/3/ መሰረት ጥፋተኛ ለዚህም ጥፋቱ ብር 5,000.00 /አምስት ሺህ ብር/ የገንዘብ መቃጮ እንዲቀጣ በአዋጅ መሰረት በፈድራል ጠበቆች የዲስፕላን ጉባኤ ተወሰኖ ሚኒስቴር ሚኒስትር በመጽደቁ እና ጉዳዩንም ይግባኝ ሰሚው የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በይግባኝ ተመልክቶ በማጽናቱ ምክንያት የአሁን አመልካች ይህንኑ የመጨረሻ ውሣኔ ለማስለወጥ ሲል ባቀረበው የሰበር አቤቱታ በማቅረብ ነው:: የፍትሕ ሚኒስቴርም በተጠሪነቱ በጉባኤው የተሰጠው ውሳኔ በህጉ አግባብ ስለሆነ ላፀና ይገባል በማለትም በጽሁፍ መልሱን አቅርቧል።
ከላይ በጭሩ እንደተመለከተው አሁን አመልካች ጉዳዩን በጥብቅና ይዞ ክርክር ያደረገበት የአፈፃፀም ጉዳይ ነው ለአፈፃፀም መሰረት የሆነው ዋናው ፍርድ በመ/ በቀን 09/10/2002 የተሰጠው ሲሆን የፍርዱም የተፈፃሚ ክፍል ‹‹… የሚቻል ከሆነ በዓይነት …. ይህ ሁሉ ካልተቻለ ንብረቱ በሐራጅ ተሽጦ በፍርዱ በተመለከተው የድርሻ መጠን መሰረት ይከፋፈሉ የሚል ነው።
ይህንንም ፍርድ ለማስፈፀም ሲባል ለተከፈተው በአፈፃፀም መዝገብ የሆነው የአፈፃፀም መዝገብ ፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲመለከት ቆይቶ እንደ ፍርዱ ንብረቱን በዓይነት ለማካፈል የሚቻል መሆኑን በፍርድ አፈፃፀም መምሪያ በኩል በባለሙያ ተረጋግጦ እንዲቀርብ አድርጓል።
በዚህ መሰረት ከባለሙያ በቀረበው ማረጋገጫ መሰረት ንብረቱን በዓይነቱ ለማከፋፈል አይቻልም ከሚል መነሻ ተነስቶ ንብረቱ በሐራጅ እንዲሸጥ ትዕዛዝ የሰጠበት መሆኑና በዚህም ትዕዛዝ ላይ የይግባኝ አቤቱታ ለፈድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ቀርቦ ፍ/ቤቱ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 337 መሰረት ሰርዞ ስለማሰናበቱ ያከራከረ ጉዳይ አይደለም።
እንዲሁም የፍርድ አፈፃፃም መመሪያው ከፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ንብረቱን በማየት ቦታውን በዓይነት ማካፈል የሚቻል ሲሆን ቤቱን በተመለከተ ግን ከቤቱ አተማመን አኳያ እኩል በእኩል ለማካፈል እንደማይቻል ሆኖም ትንሹንም ድርሻ ቢሆን አሁን አመልካች የወከሐቸው በአፈፃፀም መዝገቡ ላይ 1ኛ የፍርድ ባለዕዳ የነበሩት ጠይቀዋል። በዚሁ መሰረት ማስፈፀም ይቻል እንደሆነ ማብራሪያ ይሰጥበት በሚል ገልፆ እያለ አፈፃፀሙን የያዘው ፍርድ ቤት ግን ከዚሁ ከፍርድ አፈፃፀም መመሪያ የተሰጠን ሙያዊ መግለጫ ከደረሰው በኋላ እንደ ፍርዱ ንብረቱን በዓይነት ለማካፈል የልቻል አይደለም ከሚል መደምደሚ ደርሶ በመጨረሻው የፍርድ አማራጭ መሰረት ንብረቱ በሐራጅ እንዲሸጥ በሚል ትዕዛዝ የሰጠበት ስለመሆኑም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በዚህ በሐራጅ ይሸጥ በተባለው ትዕዛዝ ላይ የይግባኝ አቤቱታ ቀርቦ ተቀባይነት ካጣ በኋላ አሁን አመልካች አፈፃፀሙን በመጀመሪያ ደረጃ ለያዘው ፍ/ቤት ደንበኛቸው ንብረቱ በሐራጅ ከሚሸጥ ይልቅ በፍርድ አፈፃፀም መምሪያ በኩል እንደተረጋገጠው ቢጎዳም አነስተኛው ድርሻ ይሰጠኝ በማለት ጠይቀዋል ስለሆነም በዚሁ መሰረት እንዲፈፀም ይታዘዝልኝ በማለት በመጠየቃቸው ፍ/ቤቱ እንደጥያቄው ተቀብሎ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አፈፃፀሙን የያዘው ፍ/ቤት በዚህ አኳኋን ቀድሞ ሰጥቶት የነበረውን የሐራጅ ሸያጭ አማራጭ ትቶ አመልካች እንዳቀረበው አቤቱታው በዓይነት ይካፈሉ ብሎ ካዘዘ በኋላ እንደገና መዝገቡን አንቀሳቅሶ ከዚህ በፊት በሐራጅ ተሸጦ ይከፋፈሉ በሚል የሰጠው ዳኝነት በይግባኝ ታይቶ የጸና መሆኑን የ1ኛ ፍርድ ባለዕዳ እያወቀ እንደገና በፍርዱ ባለቀ ጉዳይ ላይ አዲስ ጥያቄ በማቅረብ የተለየ ዳኝነት እንዲሰጥ አስደርጓል። ይህም አግባብ አይደለም በማለት በዓይነት ክፍያውን አማራጭ አንስቶ የአሁን አመልካች ፍ/ቤቱን በማሳሳት ለፈፀመው ተግባር ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው አመልካች የጥብቅና ሙያ ስነ ምግባር ከሚያዘው ውጭ በፍርድ ባለቀ ጉዳይ ላይ አቤቱታ በማቅረብ በሚል ጉዳይ ላይ መጉላላቱንአስከትሐል። ይህም አድርጊቱ ከፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 5 አንፃር ሲታይ ሙያዊ ጥፋት መፈፀሙን ያረጋግጣል በማለት ጥፋተኛ ብሎ የገንዘብ መቀጮ የቀጣው ስለመሆኑ ሁሉ የተረጋገጡ ጉዳዮች ሆነው አግኝተናቸዋል።
እንግዲህ የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ ባጭር ባጭሩ የተጠቀሰው ሲሆን እኛም የጉባኤውን ውሳኔ አግባብነት እንደሚከተለው መረምረናል።
በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 5 ተፈፃሚነቱ ከታች ወደ ላይ የተዋቀሩት ፍ/ቤቱ ዋናውን ጉዳይ አከራካሪው ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ ብቻ የተወሳነ ስለመሆኑ ከአፈፃፀም ቢመለስ በመጀመሪያ ደረጃ እና በይግባኝ የቀረቡት ጉዳዮች አካሄድ የሚመሩበት ስነ ስርዓታዊ ድንጋጌዎች ያላቸውን የተፈፃሚነት ውሰን በሚደነግገው በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 32 ተመልክቷል።
ይህ ለዚህ ሰበር ክርክር ምክንያት የሆነው ጉዳይ የአፈፃፀም እንደመሆኑ መጠን ይኸው በቁጥር 5 የተመለከተው ስነ ሰርዓታዊ ድንጋጌ በዚህ ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚነት ያለው አይደለም።
ይልቁንም የተፈረደ ፍርድን በማስፈፀም ሂደት የጉዳዩ አካሄድ የሚጣራው ስለፍርድ አፈፃፀም በተመለከቱት እራሳቸውን ችለው በተዘረጉት ስነ ስርዓታዊ ድንጋጌዎች መሰረት ነው በዚህም የአፈፃፀም ጉዳይ የሚመለከትን ስርዓት አስመልክቶ በተደረገው ስነ ስርዓታዊ ዝርዝር የህግ ክፍል ማየት እንደሚቻለው የአፈፃፀም ጉዳዩን የያዘ ፍርድ ቤት እንደ ፍርዱ በማስፈፀም ረገድ ከፍርዱ ይዘት ሳይወጣ እንደፍርዱ ተቋጭቶ መዝገቡ እስኪዘጋ ድረስ በተለያዩ ጊዜ የተለያዩ ፍርድ የማስፈጸሚያ ስልትና ዘድ በመከተል የተለያዩ ትዕዛዞችን ለመስጠት ስልጣን ተሰጥቶታል በዚህ ጉዳይ በአፈፃፀም መዝገቡ ላይ አፈፃፀሙን የያዘው ፍ/ቤት በመጀመሪያ ንብረቱ በሀራጅ ተሸጦ እንዲከፋፈሉ ይደረግ ብሎ ካዘዘበት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩ በይግባኝ ሰሚ ችሎት ደርሶ ከፀናና እንደገና አሁን አመልካች እንደገና የአፈፃፀም ችሎት ቀደም ሲል ንብረቱ ተሸጦ ይከፋፈሉ በሚል የተሰጠው ትዕዛዝ አግባብነቱ እንደገና ይታይልኝ በማለት እስከጠየቀበት ድረስ ፍርዱ ፍፃሜ ያገኘ ጉዳይ ስለመሆኑ የተካደ ጉዳይ አይደለም።
ከዚህ በላይ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጡትን ጉዳዮች በተጠቀሰበት በዚህ ፍርድ ላይ እንደተገለፀው ፍርድ አፈፃፀም መምሪያ የሰጠው ሙያዊ ማረጋገጫ ይዘት ንብረቱን በዓይነት ለማካፈል የሚቻል አይደለም በሚል ሳይሆን አንደኛውን ወገን ጠቅሞ ልላኛውን ወገን ካልጎዳ በቀር ማካፈል ይቻላል በዚህም መሰረት 1ኛ የፍርድ ባልዕዳ ቢጎዳም ልጎዳ በማለት እነስተኛው ድርሻ ተሰጥቷቸው ክፍፍሉ በዓይነት እንዲደረግ ጠይቀዋል ይኸው ታይቶ አስፈላጊው ዳኝነት ይሰጥበት የሚል ሆኖ እያለ ፍ/ቤቱ በዘፈቀደ ንብረቱ በሐራጅ ይሸጥ በማለት ማዘዙ ስህተት የፈፀመ መሆኑን ያስገነዘበው ጉዳዩም ፍፃሜ አግኝቶ ባለጉዳዮች የተሰናበቱ እስካልሆነ ድረስ ፍርድን ተገቢ በሆነ መንገድ በማስፈፀም ረገድ ለአፈፃፀም ፍ/ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የተስተካከለ ዳኝነት እንዲሰጥ የአሁን አመልካች ለደንበኛው ተገቢን ሙያዊ ድጋፍ ማሰጠት ካለበት ግድታ አንፃር ለፍ/ቤቱ አመልክቷል ከሚባል በቀር የፈፀመው መያዊ ጥሰት አልተሰተዋለበትም።
በፍርዱ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው የ1ኛ የፍርድ ባለዕዳ ድርሻ ግማሽ ቀሪው የልሎች ተከራካሪዎች እንደመሆኑ መጠን ንብረቱን በዓይነት ለማካፈል ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለውን ለመለየት ይኸው የፍርድ ባለዕዳ ግማሽ ድርሻ መነሻ ከሚሆን በቀር የቀሪውን ግማሽ ድርሻ ቀሪ ተከራካሪዎች በዓይነት ላከፈሉ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ነጥብ ላሆን አይገባም በዚህም ምክንያት ግማሹ ድርሻ ለቀሪ ሶስት ወገኖች የሚከፈፈል የመሆኑ ጉዳይ የአፈፃፀሙን አካሄድ ላያስቀይረው የሚችል ሆኖም አላገኘነውም።
በዚህ ሁሉ ምክንያት የዲስፕላን ጉባኤ ለጉዳዩ አግባብነት ከልለው ድንጋጌ አንፃር እንጂ ፍርድን እንደ ፍርዱ በተገቢው መንገድ በሚስፈጽም ረገድ ፍ/ቤቱ ላከተለው ከሚገባው ስርዓት አንፃር ባለማየቱ ምክንያት የአሁን በአመልካች ሙያዊ ጥፋት ፈጽሟል ሲል የሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ እና ቀጠይ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ባለማግኘታችን የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል ፍ/ቤቶች ጠበቆች የዲስፕላን ጉባኤ በሰጠው ውሳኔ መነሻ ይግባኝ ሰሚው የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/ቁ ጳጉሜ 01 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ተሽሯል።
የአሁን አመልካች በወሰነበት መሰረት የገንዘብ መቀጮውን ክፍያ ፈፅሞ ከሆነ ለገንዘብ መቀጮው ምክንያት የሆነው ውሳኔ የተሻረ ስለሆነ ገንዘቡ እንዲመሰለት ታዟል። ለሚመለከተው ክፍል ይፃፍ
በዚህ ሰበር ክርክር ምክንያት የወጣውን ወጭና ኪሣራ ሁለቱም ወገኖች ለየራሳቸው ይቻሉ። መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.