No summary available.
መጋቢት 27 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ ሙስጠፋ አሕመድ አመልካች፡- ወ/ሮ ወርቅነሽ ውብነህ አልቀረቡም ተጠሪዎች፡-
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በፍርድ ቤት ያፀደቀው የእርቅ ስምምነት ያስረዝልኝ በሚል መንገድ የቀረበን ጥያቄ የሚመለከት ነው። ክርክሩ በመጀመሪያ የታየው በፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ቤት አመልካች የፍርድ መቃወሚያ አቅራቢ /አመልካች ተጠሪዎች የፍርድ መቃወሚያ ተጠሪዎች በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ በኮልፍ ቀራንዬ ክፍል ከተማ ወረዳ 7 ክልል ውስጥ የሚገኘው ቁጥር ያልተሰጠውን አዲስ ቤት ከሶስተኛ ተጠሪ እኔ በሕጋዊ ውል ገዝቼና ተጨማሪ ግንባታ በማካሄድ እየተገለገልኩበት እገኛለሁ። ሆኖም አንደኛ የመቃወም ተጠሪና ሁለተኛ የመቃወም ተጠሪ በመካከላቸው በፍርድ ቤት ሲያደርጉት የነበረው ክርክር ለማቋረጥና ቤቱ በሐራጅ ተሽጦ ለእዳ መክፈያ እንዲሆን በመግለጽ በመስማማት ይህንን ስምምነታቸውን ፍርድ ቤቱ እንዲያውቅና እንዲመዘግበው በማድረግ እኔ ተካፋይ ባልሆንኩበት ክርክር ንብረቴን ለማሸጥ በማንቀሣቀስ ላይ ናቸው። ስለዚህ እኔ በክርከሩ ገብቼ ውሣኔው እንዲሰረዝልኝ በማለት የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻ አቀርባለች።
ተጠሪዎች የእዳ መክፈያ እንዲሆን የእርቅ ስምምነት ያደረጉበትን ቤት፣ እኔ ከእዳና እገዳ ነፃ መሆኑን አረጋግጪ በውልና ማስረጃ ጽ/ቤት በተደረገ ውል ከሶስተኛው ተጠሪ ገዝቼ ቤቱንና ይዞታውን ተረክቤያለሁ። ቤቱን በግዥ ከተረከብኩ በኃላ በከፍተኛ ወጭ ተጨማሪ ግንባታ ሥራ ሰርቻለሁ። የሥር ፍርድ ቤት 06-04-2002 ዓ.ም በሰጠው ትእዛዝ መሰረት ቤቱ በፍርድ አፈፃም መምሪያ ላሸጥ የሀራጅ ማስታወቂያ በግድግዳው ላይ ሲለጠፍበት ሁኔታውን በማወቄ በመጀመሪያ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ/ቁጥር 418 መሰረት በአፈፃፀም ጣልቃ ገብቼ መቃወሚያየን አቅረብኩ። አፈፃፀሙን የያዘው ችሎት በመጀመሪያ የእርቅ ስምምነቱን የመዘገበው ችሎት በእርቁ መሰረት አንዲፈፀም የሰጠውን ትእዛዝ ሣይሰረዝ ጥያቄሽ ተቀባይነት የለውም በማለት መቃሚያን ውድቅ አደረገብኝ የሥር ፍርድ ቤት መዝግቦና በፍርድ ቤቱ ማህተም አረጋግጦ ያስተላለፈው በፍርድ አፈፃፀም መምሪያ በኩል እየተፈፀመ ያለውን ከፍርድ ቤቱ የፀደቀው የአፈፃፀም ስምምነት እኔ ባለሁበት ታይቶ እንዲሰረዝ የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻ አቅርቤለት ውድቅ አድርጎብኛል። ስለዚህ ውሣኔው የእኔን መብትና ጥቅም የሚነካና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምለኝ በማለት አመልክቷል።
አንደኛ ተጠሪ በበኩላቸው አንደኛ ተጠሪና 3ኛ ተጠሪ በጋብቻ ተሣስረን የኖርን ባልና ሚስት ነበረን በ1996 ዓ.ም ጋብቻችንን በስምምነት ስናፈርስ የጋራ ሃብት የሆነውን ክርክር የተነሣበትን ቤት እኩል እንድካፈል የትግራይ ክልል ማህበራዊ ፍርድ ቤት ውሣኔ ሰጥቶበታል። ከዚህ በኃላ ሁለተኛው ተጠሪ በቤቱ ላይ መብት አለኝ በማለት በመያዙ የሁከት ይወገድልኝ ክስ አቅርቤ ተጠሪዎች በስምምነትና በእርቅ ጉዳዩን በመጨረሣችን፣ የሥር ፍርድ ቤት በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 182 መሰረት የሰጠው ውሣኔ የለም። አመልካች ፍርድ ቤት ያልሰጠውን ውሣኔ አንዲሰረዝላት የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 358 ድንጋጌ ከሚያዘው ውጭ ያቀረበችው የፍርድ መቃወሚያ ውድቅ መደረጉ የሕግ ስህተት የለበትም። ሶስተኛው ተጠሪ የአንደኛ አንደኛ ተጠሪ አመልካች የፍርድ መቃወሚያ ባቀረቡበት ቤት ላይ ክርክር ተካሂዶ በዚህ ፍርድ ቤት የተሰጠ የመጨረሻ ውሣኔ የለም። መቃወሚያ ማቅረብ የሚችለው ሶስተኛው ተጠሪ እንጂ አመልካች አይደለም። ማመልከቻቸው ውድቅ ይደረግ በማለት መልስ የሰጠ ሲሆን፣ ሁለተኛ ተጠሪ ከአንደኛ ተጠሪ የተለየ ምላሽ የለኝም ብሐል። ሶስተኛው ተጠሪ መልስ አላቀረበም።
የሥር ፍርድ ቤት ቤቱን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ የሰጠው ውሣኔ የለም።
ባለመኖሩ የአመልካች የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻ የሕግ መሰረት የልለው ነው በማለት የአመልካችን የመቃሚያ ማመልከቻ ውድቅ አድርጎታል። አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ አጽንቶታል።
አመልካች ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ባልና ሚስት የሆኑት አንደኛ ተጠሪና ሁለተኛ ተጠሪ የጥቅም ተካፋያቸው ከሆነው ሁለተኛ ተጠሪ ጋር በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመዝገብ የሁከት ይወገድልኝ ክስ አቅርበው ክርክር ካደረጉ በኃላ፣ በመጀመሪያ ሕዳር 3 ቀን 2002 ዓ.ም የተፃፈ የእርቅ ስምምነት በማጽደቅ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን እንዲዘጋላቸው ጠየቁ በማስከተል ሕዳር 23 ቀን 2002 ዓ.ም የእርቅ ስምምነት በማድረግ ፍርድ ቤቱ እንዲያፀድቅላቸው ሲያቀርቡ በመዝገቡ የተያዘው ጭብጥ የሁከት ይወገድልኝ ሆኖ እያለ ቤቱ ተሽጦ የእዳ እንዲሆን በማለት ተስማምተው መቅረባቸውን በመዘርዘር የእርቅ ስምምነቱን ሣያፀድቅ ውድቅ አድርጎታል። ተጠሪዎች ለሶስተኛ ጊዜ የእርቅ ስምምነት አቅርበው ፍርድ ቤቱ 06- 04-2002 ዓ.ም በዋለው ችሎት በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 377 መሰረት መዝግቦና በፍርድ ቤቱ ማህተም አረጋግጦ ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍ ትእዛዝ ሰጥቷል።
ተጠሪዎችም በሀራጅ ተሽጦ የእዳ መክፈያ እንዲሆን የእርቅ ስምምነት ያደረጉበትን ቤት ቤቱ ከእዳና እገዳ ነፃ መሆኑ ተረጋግጦና በሶስተኛ ተጠሪ ስም የተመዘገበ መሆኑንና ሶስተኛ ተጠሪም ሚስት የልለው መሆኑን ማስረጃ አቅርቦ በሰነዶች ምዝገባ ጽ/ቤት በተደተገ የቤት ሽያጭ ውል አመልካች ገዝቼዋልሁ። ቤቱን ከሶስተኛ ተጠሪ በውል ከገዛው በኃላ ቤቱንና ይዞታውን ተረክቤ በከፍተኛ ወጭ ተጨማሪ ግንባታ አከናውኛለሁ። ተጠሪዎች ባደረጉት የእርቅ ስምምነትና የሥር ፍርድ ቤት በመዝገብ ታህሣስ 6 ቀን 2002 ዓ.ም በሰጠው ትእዛዝ መነሻ ቤቱን በአፈፃፀም በሐራጅ ለማሸጥ የሐራጅ ማስታወቂያ ተሰጥቷል። እኔም በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 ጣልቃ ገብቶ ያቀረቡኩትን መቃወሚያ የእርቅ ስምምነት የፀደቀበት ትእዛዝ ሣታሸሪ በአፈፃፀም ጣልቃ ልትገቢ አትችይም በማለት አፈፃፀሙን የያዘው ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎብኛል ስለዚህ የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ የተጠሪዎች የእርቅ ስምምነት ላይ ተቃውሞ እንዳላቀርብ የሚገድብና የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክታለች።
አንደኛ ተጠሪ ታህሣስ 1 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ ቤቱ ከሶስተኛ ተጠሪ ጋር በጋብቻ ሲኖሩ ያፈራው የጋራ ሃብት ነው ጋብቻችን ሲፈርስ ቤቱን እንድንካፈል በማሕራዊ ፍርድ ቤት ተወስኗል። ሶስተኛ ተጠሪ መደበኛ መኖሪያው መቀል ሆኖ እያለ ከባህር ዳር ሚስት የልለው መሆኑን የሚገልጽ የሐሰት ማስረጃ በማቅርብ ከአመልካች ጋር ያደረገው የሽያጭ ውል እኔ በቤቱ ላይ ያለኝን መብት የሚጎዳ ነው። የሥር ፍርድ ቤት የአመልካችን አቤቱታ በመቀበል ፍሬ ጉዳዩን በማጣራ መወሰን ነበረበት። ይህንን በማድረጉ እኔን በተጨማሪ ክርክር ማለት ባለሃብትነት የመፋለም ክስ በመዝገበ እንዳቀርብ አስገድዶኛል። ስለዚህ ጉዳዩ ተመልሶ ሁለቱ መዛግብት ተጣምረው ተጣርቶ እንዲወሰንልኝ በማለት መልስ ሰጥታለች።
ሁለተኛው ተጠሪ ታህሣስ 22 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ እኔና ሶስተኛ ተጠሪ በሶስተኛ ተጠሪ ስም ቤት በጋራ ገዝተን ለመሸጥ በነበረን ስምምነት ቤቱ በሶስተኛ ተጠሪ ስም ሲገዛ ገንዘብ አዋጥቻለሁ። ሶስተኛ ተጠሪ ከእኛ በመደበቅ ቤቱን ለመሸጥ ሲንቀሣሰቅ ስለደርስንበት አንደኛ ተጠሪና እኔ የሁከት ይወገድልኝ ክስ አቅርበንበታል። ሶስተኛው ተጠሪም በእርቅ ለመጨረስ ስለተስማማ፣ ጉዳዩ በእርቅ አልቋል ስለዚህ የአመልካች አቤቱታ የሕግ መሰረት የለውም በማለት መልስ ሰጥቷል። የሶስተኛ ተጠሪ መልስ የመስጠት መብት በብይን ተልፏል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው የጽሑፍ ክርክና ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች ያቀረበችውን የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻ ውድቅ ማድረጋቸው ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ከሥር ፍርድ ቤት በፍርድ ቤቱ ማህተም ተረጋግጦ ለሚመለከትው ክፍል እዲተላለፍ ትእዛዝ የtሰጠበትና ተጠሪዎች ሕዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም ያደጉት የእርቅ ስምምነት በይዘቱ አመልካች በሕጋዊ ውል ገዝቻዋለሁ የምትለውን በኮልፍ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት በሶስተኛ ተጠሪ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ ቁጥር ያልተሰጠው አዲስ ቤት ተጠሪዎች ባለበት ሁኔታ ሽጠው፣ ዋጋውን ለሶስት እኩል ለመካፈል ያደጉት የእርቅ ስምምነት ነወ።
የሥር ፍርድ ቤት በፍርድ ቤቱ ማህተም ተረጋግጦ ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍ ታህሣስ 6 ቀን 2003 ዓ.ም የሰጠውን ትእዛዝና ከዚሁ ትእዛዝ ጋር የተያያዘውን በሕዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም የእርቅ ስምምነት መሰረት በማድረግ አንደኛ ተጠሪና ሁለተኛ ተጠሪዎች የፍርድ ባለመብቶች ሶስተኛው ተጠሪ የፍርድ ባለእዳ ሆኖ የሚከራከሩት የአፈፃፀም መዝገብ ተከፍቶ ቤቱ በባለሙያ ተገምቶ የሀራጅ ማስታወቂያ ወጥቶበታል።
የሥር ፍ/ቤት ታህሣስ 06 ቀን 2003 ዓ.ም ተጠሪዎች ሕዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረጉት የእርቅ ስምምነት በፍርድ ቤቱ ማህተም ተረጋግጦ ለሚመለከተው ክፍል ይተላለፍ በማለት የሰጠው ትእዝዛ በይዘቱም ሆነ በሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት በፍታበሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 277 ንዑስ አንቀጽ 1 በተደነገገው መሰረት የእርቅ ስምምነቱ ሕግና ሞራልን የማይቃረን መሆኑን በመቀበልና በማረጋገጥ የመዘገበው መሆኑ የሚያሣይ ነው። የሥር ፍርድ ቤት ተጠሪዎች ሕዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረጉት የእርቅ ስምምነት በፍታብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 377 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ተቀብሎ አጽድቄዋለሁ ብሎ በዝርዝር ታህሣስ 6 ቀን 2003 ዓ.ም በሰጠው ትእዛዝ ውስጥ አለመፃፉ ፍርድ ቤቱ ተጠሪዎች ሕዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረጉትን የእርቅ ውል ተቀብሎ አላፀደቀውም፣አልመዘገበውም ከሚለው መደምደሚያ ላይ የሚያደርስ አይደለም። ስለዚህ የሥር ፍርድ ቤት ተጠሪዎች ሕዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረጉት የእርቅ ስምምነት ህጋዊ ውጤትና አስገዳጅነት በሚያገኝበት መንገድ ትእዛዝ ከሰጠ፣ ተጠሪዎች በፍርድ ቤቱ በማህተም ተረጋግጦ ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍ ትእዛዝ የሰጠበትን የእርቅ ስምምነት እንዲፈፀምላቸው መጠየቅ የሚችሉ መሆኑን ከፍታብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 277 ንዑስ አንቀጽ 2 ድንጋጌ ይዘት ለመረዳት ይቻላል።
አመልካች በክርክሩ ተካፋይ ሣልሆን የሥር ፍርድ ቤት ታህሣስ 6 ቀን 2003 ዓ.ም በሰጠው ትእዛዝ እውቅና በሰጠውና ባፀደቀው ተጠሪዎች ህዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረጉት የእርቅ ስምምነት በእኔ ንብረት ላይ የተደረገ ነወ። ክርክሬንና ማስረጃዬን አቅርቤ ፍርድ ቤቱ ለተጠሪዎች ስምምነት እውቅና ለመስጠትና ለመመዝገብ የሰጠው ትእዛዛ ላሰረዝልኝ ይገባል በማለት ያቀረበችው የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻ በፍታብሕር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ትእዛዝ ማለት ውሣኔ የተለያና በፍርድ ቤት የሚሰጥ ማናቸውም አይነት እንደ ብይን የሚቆጠር ተፈፃሚ ትእዛዝ ማለት እንደሆነ የተሰጠው ትረጓሜ የፍታብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 277 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የእርቅ ስምምነት መጽደቁ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር. 227 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤትና የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 ድንጋጌ ይዘትና መሰረታዊ ዓላማ ያገናዘበና መሰረት ያደረገ ጥያቄ ነው።
የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካች የሥር ፍርድ ቤት ለተጠሪዎች የእርቅ ስምምነት እውቅና የሰጠበትንና የመዘገበበትን ታህሣስ 6 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትእዛዝና ከዚሁ ትእዛዝ ጋር ሕጋዊ ተፈፃሚነት ያገኘው የሕዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም የእርቅ ስምምነት በመቃወም ተከራካራ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 360 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ካላስረከበች መብቷን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 ሆነ በልላ መንገድ ለማስረከብ የማትችል መሆኑን አልተረዱትም። የበታች ፍርድ ቤቶች በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 358 የሰጡት ትርጉም የጠበበ ነው። እንደዚሁም የእርቅ ስምምነት በፍርድ ቤት ትእዛዝ ተረጋግጦና ለሚመለከተው ክፍል ይተላለፍ መባሉ የፍርድ ያህል አስገጃጅነት ያለው መሆኑና አስገዳጅነቱን ለማስቀረት እርቁን ያፀደቀው ፍርድ ቤት እርቁ ለሕግና ለሞራል ተቃራኒ አይደለም እርቁን የፀደቀው ፍርድ ቤት እርቁ ለሕግና ለሞራል ተቀራኒ አይደም በእርቁ መሰረት ይፈፀም በማለት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የሰጠውን ትእዛዝ መሰረዝ አስፈላጊ መሆኑን ሣያገናዝቡ አመልካች ያቀረበችውን መቃወሚያ ውድቅ ማድረጋቸው ከላይ በዝርዝር የገለጽናቸውን የሕግ ድንጋጌዎች የሚጥስና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ የካቲት 26 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ነሐሴ 24 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠሪዎች ሕዳር 3 ቀን 2003 ዓ.ም ያደጉት የእርቅ ስምምነት በፍርድ ቤቱ እውቅና ላሰጠውና ላመዘገብ አይገባም በማለትና ፍርድ ቤቱ ታህሣስ 6 ቀን 2003 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ ላሰረዝ ይገባዋል በማለት ያቀረበችውን ማመልከቻና ማስረጃ እንደዚሁም ተጠሪዎች የሚያቀርቡትን ክርክርና ማስረጃ በመቀበልና በመመርመር በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 360 መሰረት የመሰለውን ውሣኔ አንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341/1/ መሰረት መልሰን ልከንለታል።
በዚህ ጉዳይ ያወጡትን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሣቸው ይቻሉ።
መዘገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.