No summary available.
መጋቢት 27 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ ከበቡሽ ሸዋረገድ / አክላሉ አበባው ቀረቡ ተጠሪዎች፡- ወ/ሮ እንዳገር ጌቱ - ጠበቃ ጌታሁን ተስፋዬ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በጋብቻ የተፈራ የጋራ ሀብት ጥያቄን የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፍድራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት ነው። በስር ፍ/ቤት ተጠሪና ወ/ሮ እብስቴ በልስቲ አመልካች የአሁን አመልካችና እነ ጤናዬ በልስቲ ተጠሪዎች በመሆን ተከራክረዋል።
ክርክሩ የተነሳው የሟች በልስቲ አወቀ ውርስ በሚጣራበት ወቅት ነው። አመልካች 1960 ዓ.ም ጀምሮ ሟች ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት ድረስ በህጋዊ ጋብቻ ተሳስረን ኖረናል። በጋብቻ ስንኖር በጉለል ክ/ከተማ ቀበል 09/15 የቤት ቁጥር 487 የሆነውን ቤት አፍርተናል። ስለዚህ ይህ ቤት ግማሹ የሟች በልስቲ አወቀ ግማሹ ደግሞ የአመልካች ማለትም የከበቡሽ ሸዋረገድ መሆኑ የጋራ ሀብት ነው ተብሎ ይወሰንልኝ በማለት ጠይቀዋል። በልላ በኩል ተጠሪ በጉለል ክ/ከተማ ቀበል 09/15 የሚገኘው የቤት ቁጥር 457 ሟች አቶ በልስቲ አወቀ ከእኔ ጋር በጋብቻ ተሳስረው በነበረበት ጊዜ ያፈሩት ንብረት ነው። ስለዚህ የቤቱ የጋራ ባለሀብት እኔ ነኝ በማለት ተከራክረዋል።
የሟች አቶ በልስቲ አወቀን ውርስ እንዲያጣራ የተመደበው ውርስ አጣሪ በጉለል ክ/ከተማ ቀበል 08/15 የቤት ቁጥር 487 ሟች አቶ በልስቲ አወቀ ከማንኛቸው ጋር እንዳፈራው አከራካሪ በመሆኑ ፍ/ቤቱ መርምሮ ውሳኔ ይስጥበት በማለት አስተያየት አቅርቧል። የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ፣ አከራከሪውን ቤት ሟች በልስቲ አወቀ ከወ/ሮ ከበቡሽ ሸዋረገድ ጋር ያፈራው ንብረት ነው።
ስለዚህ የቤቱ ግማሽ ባለሀብት ወ/ሮ ከበቡሽ ሸዋረገድ (አመልካች) ናት በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።
ተጠሪ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሸኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርባለች። ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የቤቱ ግማሽ ባለሀብት ወ/ሮ አንዳገር ጌቱ (ተጠሪ) ናት በማለት የሥር ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል። አመልካች ይህንን በመቃወም ይግባኝ ለፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርባለች። ይግባኝ ሰሚው ችሎት አመልካች (ይግባኝ ባይ) ተጠሪ (መልስ ሰጭዋ) ከሟች ጋር ከተለያየች አስር ዓመት ካለፈው በኋላ ያቀረበችው የጋራ ንብረት ጥያቄ በይርጋ ይታገዳል በማለት ያቀረብኩትን መከራከሪያ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት አላግባብ ውድቅ አድርጎብኛል። ቤቱም የጋራ ንብረቴ ሆኖ እያለ የጋራ ሀብትሽ አይደለም መባሉ ስህተት ነው በማለት ያቀረበችውን የይግባኝ ቅሬታ ለማጣራት ጭብጥ ይዞ፣ መልስ ሰጭ (ተጠሪን) በማስቀረብ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቷል። ይግባኝ ሰሚው ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ይርጋውን ክርክር አመልካች አንስተው ቢሆን እንኳን፣ ይህንን የይርጋ መከራከሪያ ሁለቱ ፍ/ቤቶች ያልተቀበሉት በመሆኑ፣ ይግባኝ ሰሚው ችሎት ለሶስተኛ ጊዜ ይህንን መከራከሪያ ላመረምር እንደማይችል በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 9 የተደነገገ በመሆኑ ይህንን መከራከሪያ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ መርምሮ የመወሰን ሥልጣን ስለልው አልፈነዋል።
ቤቱ የይግባኝ ባይ (የአመልካች) የጋራ ሀብት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በተመለከተ መልስ ሰጭ (ተጠሪ) የሟች ሚስት መሆኗን በማረጋገጥ የደብረ ኤልያስ ወረዳ ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ በማስረጃነት ቀርቧል።
ቤቱም ይግባኝ ባይ (አመልካች) ከሟች በልስቲ አወቀ ጋር በጋብቻ ስትኖር ያፈራችው ስለመሆኑ ያስረዳል ተብሎ የቀረበው ማስረጃ ቤቱን ይግባኝ ባይ ከሟች ጋር ያፈሩት መሆኑን የማስረዳት ብቃት የለውም። ስለዚህ አከራከሪው ቤት ሟች አቶ በልስቲ አወቀ ከመልስ ሰጭ( ተጠሪ) ጋር ያፈሩት ሀብት ነው በማለት የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ነው በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል።
የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡትን ውሳኔ ለማሳረም ነው።
አመልካች ነሐሴ 07 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የሟች በልስቲ አወቀ ሚስት መሆኗን አረጋግጣ ያቀረበችው የሟች መደበኛ የመኖሪያ ቦታ ባልሆነው ምስራቅ ጎጃም ዞን በሚገኘው ደብረኤልያስ ወረዳ ፍ/ቤት ነው። ይህንን ማስረጃ በመቃወም ማስረጃው ትክክለኛውን ፍሬ ጉዳይ የማያሳይ መሆኑን ያቀረብኩትን ክርክር ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት በመጀመሪያ የደብረኤልያስ ወረዳ ፍ/ቤት ውሳኔ አላሻረም በማለት ውድቅ ማድረጋቸው የሕግ ስህተት አለበት።
ተጠሪ ከሟች ጋር ከተለያየች አስር ዓመት ያለፋት መሆኑን በመግለፅ የተጠሪ ክርክር በይርጋ ይታገዳል የሚለውን ክርክር ለፍድራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት አቅርቤያለሁ። ይህ የይርጋ መከራከሪያ መታለፉ ተገቢ አለመሆኑን በመግለፅ በከፍተኛው ፍ/ቤት ተከራከሬያለሁ። ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የተጠሪ ጥያቄ በይርጋ የሚታገድ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በማጣራት እንዲወስንልኝ ያቀረብኩትን ክርክር በይግባኝ ደረጃ እንደተነሳ አዲስ ክርክር አድርጎ በመውሰድ የሰጠው ውሳኔ ስህተት ያለበት ነው። ተጠሪ ሟች በልስቲ አወቀ 1954 ቦታውን የተመራ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ከማቅረቧ ውጭ ቤቱ 1954 የተሰራ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ አላቀረበችም። ስለዚህ ቦታው የተመራበትን ጊዜ ቤቱ እንደተሰራበት ጊዜ በመውሰድ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አለበት በማለት አመልክታለች።
ተጠሪ በበኩሐ ታህሳስ 5 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ መልስ ቤቱ እኔና ሟች ከተጋባን ከአራት አመት በኋላ የተፈራ ነው። አመልካች ቤቱ ሲሰራ አልነበሩም። የይርጋ ክርክር ለስር ፍ/ቤት አላቀረቡም። የሚስትነት ማስረጃ ከሟች መደበኛ መኖሪያ ውጭ በሚገኝ ፍ/ቤት አስወስኖ በመቅረብ የጋራ ሀብት መጠየቅ የሚከለክል ሕግ የለም። ስለዚህ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ውድቅ ይደረግልኝ በማለት ተከራክረዋል። አመልካች ታህሳስ 17 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ ተጠሪ ከሟች ጋር የነበራት ጋብቻ ከሃምሳ ዓመት በኋላ ያቀረበችውን ጥያቄ በመቀበል የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት ተከራክረዋል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው የፅሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም አከራከሪው ቤት የሟች በልስቲ አወቀና የተጠሪ የጋራ ሀብት ነው በማለት የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሳኔ ግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክርክር ባህሪና ሕጋዊ ውጤት እንዲሁም አግባብነት ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎችና ይኽ ሰበር ችሎት የሰጠውን አስገዳጅ ትርጉም ያገናዘበ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭበጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ተጠሪ የሟች ሚስት መሆኗን ለማስረዳት የደብረ ኤልያስ ወረዳ ፍ/ቤት የሰጣትን የሚስትነት ማስረጃ ብታቀርብም ተጠሪ ከሟች በልስቲ አወቀ ጋር ተለያይታ የኖረች መሆኑን ለፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መጋቢት 22 ቀን 2001 ዓ.ም ፅፋ ባቀረበችው አቤቱታዋ ያመነች መሆኑን በማረጋገጥ የስር ፍ/ቤት በውሳኔው በግልፅ አስፍሮታል። ከዚህ በተጨማሪ አመልካች ተጠሪ ከሟች ጋር የነበራት ጋብቻ የፈረሰ መሆኑን ጋብቻው ከፈረሰ ከሃምሳ ዓመት በኋላ የጋራ ንብረት አለኝ በማለት የክፍያ ጥያቄ ማቅርቧ ተገቢ አለመሆኑን ለዚህ ሰበር ችሎት ነሐሴ 7 ቀን 2004 ዓ.ም ፅፋ ባቀረበችው የሰበር አቤቱታ በግልፅ በማስፈር ተከራክራለች። በአንፃሩ ተጠሪ የሟች ሚስት መሆኔ በውሳኔ ተረጋግጧል ከማለት ውጭ ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ ሟች ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩ ጊዜ ድረስ ከሟች ጋር የነበረን ጋብቻ አልፈረሰም በማለት የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 234(1) በሚደነግገው መሰረት በግልፅ ክዳ ያቀረበችው ክርክር የልለ መሆኑን ተጠሪ ለዚህ ሰበር ችሎት ታህሳስ 4 ቀን 2005 ዓ/ም ፅፋ ያቀረበችውን መልስ የዘት በማየት ለመገንዘብ ይቻላል። ይህም ተጠሪ ከሟች ጋር ከተለያየች ሃምሳ ዓመት ሆኖታል በማለት አመልካች በሰበር አቤቱታዋ ያቀረበችውን ክርክር በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 235(2) መሰረት እንዳመነች የሚያስቆጥራት ነው።
ተጠሪ የሟች ሚስት ስለመሆኗ የደብረ ኤልያስ ወረዳ የሰጣትን የሚስትነት ማስረጃ ብታቀርብም በፍሬ ጉዳይ ደረጃ አመልካችና ተጠሪ ተለያይተው የኖሩ መሆኑንና አመልካች ከሟች ጋር ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ በፀና ጋብቻ የኖረች መሆኑን ተጠሪ በክርክር ሂደት ለስር ፍ/ቤት ካቀረበችው የፅሁፍ አቤቱታና ለዚህ በሰበር ችሎት ከሰጠችው መልስ በመሸሽ መልክ ካቀረበችው ክርክር ለመገንዘብ ይቻላል።
ከላይ ከተገለፀው በተጨማሪ አከራከሪው ቤት በሟች አቶ በልስቲ አወቀና በአመልካች ስም የተመዘገበና አመልካች የቤቱ የጋራ ባለሀብት መሆኗን የሚያሳይ የባለሀብትነት የምስክር ወረቀት ያላት መሆኑን ተጠሪም የምትክደው አይደለም። ተጠሪ የምትከራከረው ቤቱ የተሰራው ሟች አመልካችን ከማግባቱ በፊት ነው በማለት ነው።
ከዚህ በተጨማሪ አመልካች ከሟች በልሰቲ አወቀ ጋር የቤቱ የጋራ ባለህበት ሆና የማይንቀሳቀሰው ንብረት መዝገብ ውስጥ መመዝገቧና አመልካች ከሟች ጋር ባለህብት መሆነኗን በአስተዳደሩ ክፍል የተመዘገበ መሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የቤቱ ባለሃብት እንደሆነች የሚያስገምት እንደሆነ ከህጉ ድንጋጌ ይዘት ለመረዳት ይቻላል። ስለዚህ አመልካች የቤቱ የጋራ ባለሀብት መሆኗ ከላይ የገለፅናቸው የሕግ ድንጋጌዎች የህላና ግምት የሚወስድበት በመሆኑ በሕጉ የተደነገገውን ግምት ተቃራኒ ማስረጃ በማቅረብ የማፍረስ ወይም የማስተባበል ግድታው ያለባት ተጠሪ ናት። ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 213/92 አንቀጽ 62(1) የተደነገገውንና በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195(1) የተደነገገውን የአመልካችን የቤቱን የጋራ ባለሀብትነት ግምት ለማፍረስና ለማስተባበል የሚያስችል ማስረጃ የማቅረብ ኃላፊነት አለባት።
ከዚህ አንፃር ስንመረምረው ተጠሪ ሟች ቦታውን 1954 ዓ.ም መመራቱን የሚያስረዳ ማስረጃ በማቅረብ ከላይ በተገለፁት የሕግ ድንጋጌዎች የተደነገገውን የአመልካችን የቤቱ የጋራ ባለህብትነት ግምት የማፍረስ ወይም የማስተባበል ግድታና ኃላፊነት ለመወጣት አትችልም። በተለይም ተጠሪ አመልካች ከሟች ጋር የቤቱ ባለሀብት መሆኗ የቤቱ ዕርስተ መዝገብ የተመዘገበች መሆኗንና በቤቱ ባለቤትነት የአስተዳደሩ ክፍል መዝገብ ላይ ስሟ በባለሀብትነት መገለፀን፣ ለማስተባበል በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1196 ከተደነገጉት ሁኔታዎች አንደኛውን በማስረጃ በማረጋገጥ የማስተባበል ኃላፊነት አለባቸው። ከዚህ አንፃር ሲታይ ተጠሪ በተሻሻለው የፍድራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 62 እና በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195(1) የተደነገገውን የአመልካችን የቤቱ የጋራ ባለህበትነት ግምት የማስተባበልና የማፍረስ ኃላፊነቷን ባልተወጣችበት ሁኔታ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት ቤቱ የተጠሪ የጋራ ሀብት ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል።
ከላይ ከተገለፀው በተጨማሪ ለፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተጠሪ የሟች ሚስት ስለመሆኗ በደብረኤልያስ ወረዳ ፍ/ቤት የተሰጣት ማስረጃ (ውሳኔ) እውነታውን የሚያንፀባርቅ አይደለም በማለት አመልካች ተቃውሞ ብታቀርብም የወረዳው ፍ/ቤት ሚስትነቷን በመግለፅ የሰጠውን ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ/ቁጥር 360(2) መሰረት ካላሰረዘ ተጠሪ የሟች ሚስት ናት ወይስ አይደለችም የሚለውን ፍሬ ጉዳይ የማጣራት ስልጣን የለኝም በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት እንዳለፈው ከውሳኔው ተረድተናል። የደብረኤልያስ ወረዳ ፍ/ቤት የተጠሪን አቤቱታና ማስረጃ ብቻ በመቀበል የሰጠው የሚስትነት ማስረጃ በማስረጃነት በቀረበበት በማናቸውም ጊዜ ተዓማኒነትና ክብደት የልለው ማስረጃ መሆኑን ለማሳየት ክርክር ላቀርብበትና ተቃራኒ ማስረጃ ተሰምቶ ውድቅ ላደረግ የሚችል (Declaratory Judgment) ነው። ይህ ሆኖ እያለ የወረዳው ፍርድ ቤት የተጠሪን ሚስትነት በመግለፅ የሰጠውን የሚስትነት ውሳኔ አመልካች ካላሻረች ውሳኔውን መቃወምም ሆነ ተቃራኒ ማስረጃ በማቅረብ እውነትነት የልለው መሆኑን መከራከር አትችልም። ይግባኝ ሰሚው ችሎትም በወረዳው ፍ/ቤት የተሰጠው የሚስትነት ማስረጃ ትክክል መሆን አለመሆኑን የመመርመርና የመመዘን ሥልጣን የለውም በማለት የተሰጠው ትርጉም ይህ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ እና የሰ.መ. የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ያላገናዘበና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው።
የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አመልካች ያቀረበችውን የይርጋ ክርክር መነሻ በማድረግ ለአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 9 የሰጠው ትርጓሜ ላታይ የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል። ስለጠቅላይ ፍ/ቤት የይግባኝ ስልጣን የሚደነግግው የአዋጅ ቁጥር 25/1988 ይግባኝ ሰሚው ችሎት የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣኑ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በይግባኝ ሰሚነት ስልጣኑ የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ከሰጠው የተለየ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች በይግባኝ የማየት ስልጣን እንዳለው በአንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 አና ንዑስ አንቀጽ 2 ደንግጓል።
በያዝነው ጉዳይ የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአመልካች የጋራ ሀብት ነው በማለት የሰጠውን ውሳኔ ከፍተኛው ፍ/ቤት በይግባኝ ስልጣኑ አይቶ በመሻር ቤቱ የተጠሪ የጋራ ሀብት ነው በማለት ወስኗል።
አመልካች ከስር ፍርድ ቤት ጀምራ የይርጋ መከራከሪያ እንዳነሳች ገልፃ የከፍተኛው ፍ/ቤት ጥያቄው በይግባኝ ደረጃ እንደተነሳ በውሳኔው የገለፀውና መከራከሪያውን ውድቅ ያደረገው ስህተት ስለሆነ በይግባኝ ታይቶ ይሻርልኝ በማለት ጠይቃለች። ይግባኝ ሰሚው ችሎት በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 9(2) አንድ ተከራካሪ ያነሳው የህግ መከራከሪያና ምክንያት በስር ፍ/ቤትና በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ከታለፉ የክርክሩ ውጤት የስር ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ቢለውጠውም በሁለቱም ፍ/ቤቶች የታለፈውን የሕግ መከራከሪያ በይግባኝ የማየት ስልጣን እንደልለው በመግለፅ የሰጠው ትርጓሜ የአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 9 ንኡስ አንቀጽ 2 ድንጋጌ ይዘት ዓላማና ተግባራዊ ተፈፀሚነት ያገናዘበ ሆኖ አላገኘነውም።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አከራካሪው ቤት የአመልካች ነው በማለት የሰጠውን ውሳኔ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመለወጥ አከራካሪው ቤት የተጠሪ ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። ይግባኝ ሰሚው ችሎት አመልካች በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 9(2) በተጠበቀላት የይግባኝ መብት ተጠቅማ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ ለማሳረም ያቀረበቻቸውን የፍሬ ጉዳይና የሕግ ክርክሮች የመመርመርና ውሳኔ የመስጠት የስረ ነገር ሥልጣን ብቻ ሣይሆን ኃላፊነትና ግድታ በአንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 2 ድንጋጌ ተጥሎበታል። በመሆኑም ይግባኝ ሰሚው ችሎት አመልካች ያቀረበችው የይርጋ መከራከሪያ በሁለቱ ፍ/ቤቶች የታለፉ በመሆኑ በይግባኝ የማየት ሥልጣን የለኝም በማለት የሰጠው የህግ ትርጉም መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል።
ከላይ በዝርዝር በገለፅናቸው የሕግ ምክንያቶች የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የፍድራል ክፍተኛ ፍ/ቤት አከራካሪው ቤት የተጠሪ የጋራ ሀብት ነው በማለት የሰጠውን ውሳኔ ማጽናቱ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ፀንቷል።
በጉለል ክ/ከተማ ቀበል 09/15 የሚገኘው ቁጥሩ 487 የሆነው ቤት የአመልካችና የሟች በልስቲ አወቀ የጋራ ሀብት ነው በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.