No summary available.
የካቲት 26 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ አየለ መኮንን /ከጠበቃ አቶ ምናሴ ዘሪሁን ጋር ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1ኛ ወ/ሮ ጦቢያው ወንድም ገዛው 2ኛ ወ/ሮ ውቢት በየነ 5ኛ ተጠሪ እና የሁሉም ጠበቃ 3ኛ አቶ ብሩክ በየነ አቶ አበበ ማስረሻ ጋር ቀረቡ 4ኛ ወ/ት ሰናይት በየነ 5ኛ ወ/ት እጥፍወርቅ በየነ 6ኛ ወ/ት መሰረት በየነ መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን መርመረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የቀረበው ግራ ቀኙን ካከራከረው ጉዳይ አንፃር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 231/1/ሀ/ የተመለከተው ስነ ሥርዓታዊ ድንጋጌ ለጉዳዩ ያለውን አግባብነት ለማየት ሲባል ነው።
የአሁን አመልካች በስር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በአሁኑ ተጠሪዎች ላይ ያቀረበው ክስ የጉዳዩ መነሻ ሲሆን የዚህም ክስ ይዘት በጉለል ክ/ከተማ ወረዳ 03 የቤት ቁጥር 696 የሆነው ቤት አካል የሆነውን ሰርቪስ ቤት ከ2ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር ከተጠቀሱት ተጠሪዎች አባት ከአቶ በየነ ወልደሚካኤል እና ከባለቤታቸው ከአሁን 1ኛ ተጠሪ ጋር ህዳር 27 ቀን 1990 ዓ.ም ባደረግነው የሽያጭ ውል ገዝቼ ተረከቢያለሁ ሻጮችም ቀደም ሲል ቤቱን የገዙበትን ውል እና የግብር ደረሰኝ አስረክበውኛል። በቤቱም ላይ ያለውን ካርታ ተከታትዬ እንዲሰጣቸው አድርጌያለሁ አስረከቢያቸዋለሁ። ሆኖም ከዚህ በፊት በሽያጭ ውሉ በገቡት ግድታ መሰረት በገዛሁት ሰርቪስ ቤት ላይ ካርታ ተዘጋጅቶ እንዲሰጠኝ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም ስለሆነም የገዛሁት ሰርቪስ ቤት ስመ ሀብትነት በስሜ እንዲዞር ተከሳሾች ስመ ሀብትነትን በሚያዛውር አካል በመቅረብ የመለያ ውል በመፈረምና አስፈላጊ ሰነዶችን ይዘው በመቅረብ ሰመ ሀብቱ እንዲዛወር ያደርጉ ዘንድ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
የአሁን ተጠሪዎችም በመካከላችን የተደረገ የሽያጭ ውል የለም። ቢኖርም እንኳ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2879 መሰረት ቤቱንና ሰነዶችን ለገዥ ማስረከብ እንጂ ውል እንድንዋዋል አንገደድም፡ ፍ/ቤቱም ውል ተዋዋሉ ብሎ ውሣኔ ለመስጠት አይችልም። ክሱ የክስ ምክንያት የለውም የሚለውን ክርክር ካስቀደሙ በኋላ ስለዋናው ጉዳዩም ዝርዝር መልስ ሰጥተዋል።
ፍ/ቤቱም ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባቱ በፊት በአሁን አመልካች አማካኝነት የቀረበው ክስ የክስ ምክንያት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ መስርቶ እና ጉዳዩን ተመልክቶ በኮ/መ/ በሆነው በቀን 25/7/2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ከሳሽ የጠየቁት ዳኝነት ተከሳሾች የሸጡልኝን ቤት ካርታ እና የሽያጭ ውሉን በክ/ከተማው መሬት አስተዳደር በማቅረብ የመለያያ ውል እንዲፈርሙ ይወሰንልኝ የሚል ነው። ሆኖም ውል በሁለት ተዋዋይ ወገኖች ፈቃድ የሚቋቋም እንጂ ሁለቱም ቀርበው ውል ላያደርጉ ይገባል በሚል ፍ/ቤት በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት የሚደረግ አይደለም። ከሳሽ በጠየቀው ዳኝነት መሰረት የሚሰጠው ውሣኔ ፍ/ቤት በሚሰጠው ውሣኔ መሰረት የሚደረግ አይደለም ከሳሽ በጠየቀው ዳኝነት መሰረት የሚሰጠው ውሣኔ ፍ/ቤት ለሁለት ወገኖች ውል የመፍጠር ያህል ውጤት የሚያስከትል ስለሆነ ጥያቄው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1679 ከተመለከተው ደንጋጌ ዓላማ ውጭ ሆኖ ስለተገኘ ክሱ የክስ ምክንያት የለውም በማለት በይኗል።
ይግባኙን የተመለከተው ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም ጉዳዩን ተመልክቶ የአሁን ተጠሪዎቹን መጥራት ሳያስፈልገው ይግባኙን ሰርዞ የአሁን አመልካችን ያሰናበተ የመጨረሻ ዳኝነት በመስጠቱ በዚህ የመጨረሻ ዳኝነት የቀረበ የሰበር ጉዳይ ነው።
ግራ ቀኙ በዚህ የሰበር ደረጃ በየፊናቸው ያላቸውን የጽሁፍ ክርክር ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱም ብይኑን በሚመለከት በየግላቸው ያቀረቡትን ክርክር የያዘ ከመሆኑም በላይ የዋናውን ጉዳይ ዝርዝር ክርክርንም ሁሉ አካቶ መያዙን የሚያሳይ ነው። እንግዲህ የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም የአሁን አመልካች በጉዳዩ ላይ ክስ ለማቅረብ የሚያስችለው መብት የለውም በሚል የስር ፍ/ቤቶች የሰጡትን ዳኝነት አግባብነት ለግራ ቀኙ ክርክርና ማስረጃ ይዘት እና ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ካላቸው ፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁ 33/2/ እና 33/3/ ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው ተመልከተናል።
አመልካቹ ባቀረበው ክስ ላይ ግራ ቀኙ ካደረጉት የቤት ሽያጭ ውል የመነጨ በተሸጠው ንብረት ላይ መብት አግኝቻለሁ በዚሁ ባገኘሁት መብት መገልገል እችል ዘንድ ሻጭ በሸጠው ነገር ላይ ያለውን የባለቤትነት መብት ለገዥው ለማስተላለፍ በህግ ይገደዳል ስለሆነም የእኔ እና የሻጩ መብትና ግድታ ታይቶ ሻጭ የሚጠበቅበትን ግድታ እንዲወጣ ይወሰንልኝ የሚል፤የአሁን ተጠሪዎችም ለአሁን አመልካች መብት ከእኛ ላይ ደግሞ ግድታ ላፈጥር የሚችል ህጋዊ ተግባር አልፈፀምንም የቤት ሽያጭ ውል አላደረግንም አድርገናል እንኳ ቢባል የእኛ የግድታ ውሉን ከሳሹ የሚለውን ሁሉ አይጨምርም በከሳሹ የተጠየቀው ዳኝነት በእኛ አማካኝነት የሚፈፀም አይደለም ከሚለው ጀምሮ በህግ ረገድ ግድታ ላፈጥር የሚችል ከከሳሹ ጋር የፈጠሩት ግንኙነት ሁሉ እንደልለ ገልፀው የተከራከሩበት ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች በየቅላቸው ያቀረቡት ክርክር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 33/2/ እና 33/3/ እንደተደነገገው ከውል ወይም ከህግ የመነጨ መብትና ግድታ ያለ መሆኑን ለማመልከት የሚያበቃ ክርክር እንዳቀርቡ አስረጂ ነው። ይህ መብትና ግድታ በእርግጥም አለ ወይስ የለም በክርክር ሂደት የሚረጋገጥ ነው የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ዓላማው በዋናው ህግ የተቀመጡትን መብትና ግድታዎች ወደ ተግባር ለመለወጥ እንዲያስችል ታስቦ የተዘረጋ ስርዓት እንደመሆኑ መጠን በከሳሽነትም ሆነ በተከሳሽነት ተሰይመው ለመከራከር በቅድሚያ ክርክሩ ቀጥሎ አንደ ክርክራቸው ሁለቱም ወገኖች በማስረጃ አስደግፈው ቢያስረዱ ለህግ ወይም ከውል የመነጨ መብትና ግደታ ያላቸው መሆኑን ለማመልከት በሚያስችል ደረጃ ክሱ ተብራርቶ እና ተዘጋጅቶ መቅረብ እንዳለበት በሚያስገነዝብ አኳኋን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ እና 33/3/ መደንገጉ እና የእነዚህ ድንጋጌዎችን መስፈርት ባላሟላ ክስ ተከሳሹን መጥራት እንደማያስፈልግ እና ክርክሩም በጅምር ደረጃ ላቋረጥ እንደሚገባ ተገልፆ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 231/1/ሀ/ መደንገጉም ክርክር ውጤት ኖሮት በመሰረተ ህጉ የተቀመጡትን መብትና ግድታ ላያስከብር መቻሉን ለማረጋገጥ ነው።
No topics extracted.
ከዚህም አንፃር አሁን በግራ ቀኙ መካከል የተነሳውን ክርክር እንዳየነው የአሁን አመልካች ካቀረበው ክስ መረዳት እንደሚቻለው ግራ ቀኛችን ካደረግነው የሽያጭ ውል የመነጨ የንብረት መብት አለኝ፤ ተከሳሾችም ከዚህ ውል የተነሣ ግድታ አለባቸው ግድታቸውም የተሸጠውን ነገር ስመ ሀብትነት በሚመለከተው ክፍል ቀርበው ለማዛወር ግድታ ገብተዋል። እንደገቡት ግድታ ይፈጽሙልኝ የሚል ነው። የስር ፍ/ቤት የአሁን አመልካችን የክስ ዝርዝር ጥቅል በማየት የክስ ምክንያቱ እና የሚጠይቀው ዳኝነት ምንድን ነው የሚለውን ከእነ ሙሉ ይዘቱ መውሰድ ሲገባው የመለያያ ውል እንዲያደርጉ የሚለውን ሐረግ ብቻ መውሰዱ በፍ/ብ/ሥ//ሥ/ህ/ቁ 222 እና 224 የተመለከቱትን ድንገጌዎች ግብና ዓላማ መሰረት ያደረገ አይደለም።
ተከሳሾችም ቀርበው በሰጡት የመከላከያ መልስ ከከሳሽ ጋር የፈፀምነው የሽያጭ ውል የለም የሚለውንና የመሳሰለውን ክርክር ያቀረቡ በመሆኑ በቅድሚያ ተለይቶ ላረጋገጥ የሚገባው ጉዳይ ለከሳሽ መብት ለተከሳሾች ደግሞ ግድታ ላፈጥር የሚችል ህጋዊ ተግባር ተከናውኗል ወይስ አልተከናወነም? የሚለው እንደመሆኑ መጠን የግራ ቀኙን ክርክር ተመልከቶ እንደ ስነ ስርዓት ህጉ ዓለማ ትርጉም እና ውጤት ያለው ዳኝነት በመስጠት ረገድ በጭብጥ አያያዝ ረገድም ስነ ስርዓታዊ ጉድለት የታየበት ዳኝነት ነው።
ስለሆነም ከሳሽ የአሁን አመልካች ያቀረበው የክስ አቤቱታ ከእነ ሙሉ ይዘቱ ሲታይ ሻጮች ስመ ሀብትነቱን በሚመለከተው ክፍል ቀርበው ሸጠውታል በተባለው ቤቱ ላይ ስመ ሀብትነት ለማዞር የሚያስችል ውል እንዲያደርጉ ሳይሆን የተሸጠውን ንብረት ስመ ሀብትነት ስልጣን ያለው አካል ወደ ገዥው ማዞር እንዲችል አስቀድመው በውሉ ላይ የገቡትን ግድታና ህጉ በሻጭ ላይ የሚጥለውን ግድታ እንዲፈፀሙ የሚል በመሆኑ ይኸው የክስ አቀራረብ እና የዳኝነት ጥያቄ ከፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 33/2/ እና 33/3/ አንፃር ሲታይ ክርክሩ ቀጥሎ በግራ ቀኙ ማስረጃ ከመለየቱ በፊት ከወዲሁ ከሳሹ ድሮውንም ቢሆን የክስ ምክንያት የለውም ብሎ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 231/1/ሀ/ መሰረት ዳኝነት ለመሰጠት የሚያስቻል አይደለም።
በመሆኑም ከግራ ቀኙ ክርክር እና ክርክራቸውን ለማስረዳት ካቀረቡት ማስረጃ እንፃር በቅድሚያ ላታዩ የሚገባቸው የክርክር ነጥቦች እያሉ የአሁኑ አመልካች ያቀረበው የክስ ምክንያትና የጠየቀውን ዳኝነት ሙሉ ይዘቱ እና ሀሳቡ ሳይታይ በስር ፍ/ቤቶች ክሱ የክስ ምክንያት ያለው አይደለም በሚል የሰጡት ዳኝነት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 33/2/፣33/3/ እና 231/1/ሀ/ ደንጋጌዎች ትክክለኛ አፈፃፀም የተከተለ ሁኖ ስላላገኘነው የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኮ/መ/ በቀን 25/7/2004 ዓ.ም የሰጠው ብይን ይግባኝ ሰሚው ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/መ/ ግንቦት 06 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ ተሽሯል።
የክርክሩን ቅደም ተከተል ጠብቆ በግራ ቀኙ መካከል የተነሱት ልሎች አከራካሪ ነጥቦች በማስረጃ እንዲለዩ በማድረግ የአሁን አመልካች በህግ ፊት ከፀና ውል ወይም ከህግ የመነጨ መብት የለውም ካልተባለ በስተቀር የግራ ቀኙ ክርክር ከደረሰበት የክርክር ደረጃ አንፃር የአሁን አመልካች የክስ ምክንያት የለውም ላባል አይችልም ብለናል ስለሆነም የተዘጋውን መዝገብ በማንቀሳቀስ ክርክሩን ቀጥሎ አስፈላጊውን ዳኝነት ይሰጥበት ዘንድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 341 መሰረት ወደ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መልስናል።
በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት የተደረገው ክርክር ላስከተለው ወጭና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ።