No summary available.
የካቲት 28 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች:- የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ነ/ፈጅ ታደሰ ታፈሰ ቀረበ ተጠሪ፡- የአስር አለቃ ደምሴ ዳምጤ ወራሾች (ሶስት ሰዎች) - ለራሣቸውና ለልሎች ወኪል - ደጀኔ ደምሴ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በአንድ የማይንሰሣቀስ ንብረት ላይ የባለቤትነት መፋለም ክስ በመደበኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከታየና የመጨረሻ ፍርድ ካረፈበት በኃላ ጉዳዩ ለአፈፃፀም ተይዞ ባለበት ሁኔታ ለፍርዱ መሰረት የሆነውና በአስተዳደር አካሉ የተሰጠ የባለቤትነት ምስክር ወረቀት በአስተዳደር አካሉ ሲመክን በፍርድ አፈፃፀም ላይ ላያስከትለው የሚችለውን ሕጋዊ ውጤት የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን በዚህ ፍርድ ቤት የተያዘውና ለአሁኑ ክርክር መነሻ በሆነው የአፈፃፀም ጉዳይ የፍርድ ባለመብቶች የሆኑት የአሁኑ ተጠሪዎች ሲሆኑ አመልካችና አቶ ክፍሉ ዮሴፍ የፍርድ ባለእዳ ነበሩ። በዚህ ፍርድ ቤት ተጠሪዎች ባሁኑ አጠራር በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበል 08 ክልል ውስጥ የቤት ቁጥር 305 የሆነውን ቤት ፍርድ ያረፈበት መሆኑን ጠቅሰው ቤቱን በፍርድ ሃይል እንዲረከቡ ትእዛዝ እንዲሰጣቸው ዳኝነት ጠይቀዋል። የአሁኑ አመልካችም በፍርድ ባለእዳነት ቀርቦ በሰጠው መልስ የቤቱ ደብተር መሰረዙን ገልፆ የሚፈፀም ውሣኔ የለም ሲል ተከራክሯል።
ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ የአመልካችን ምክንያት ባለመቀበል ቤቱን ለተጠሪዎች እንዲያስረክብ ሲል ትእዛዘ ሰጥቷል። በዚህ የፍርድ አፈፃፀም ትእዛዝ የአሁን አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀረብም አቤቱታው ተቀባይነት አላገኘም። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሣኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የተጠሪዎች የባለቤትነት ደብተርና ካርታው ተሰርዟል፣ ፍርዱ ላፈፀም የሚችል አይደለም የባለቤትነት ማረጋገጫው የተሰረዘበትን ደብዳቤ እስካላሻሩ ድረስ ቤቱን ልናስረክብ አይገባም በማለት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 280 ድንጋጌን በዋቢነት በመጥቀስ መከራከሩን የሚያሣይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮ የባለቤትነት ማረጋገጫው ደብተር ተሰርዟል እየተባለ አመልካች ቤቱን ላያስረከብ ይገባል ተብሎ የመታዘዙን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀረበው መልሣቸውን ሰጥተዋል። ተጠሪዎች በጽሑፍ በሰጡት መልስም የባለቤትነት ማስረጃውን አምክኗል የተባለው ደብዳቤ ከዚህ ቀደም በነበረው ክርክር ለሰበር ሰሚ ችሎቱ ቀርቦ ክርክር ተደርጎበት ውድቅ መደረጉን የመሬት ልማት አስተዳደር መምሪያው ማስረጃውን ያመከነው አምኖበት ሣይሆን ፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ ባስተላለፈው ትእዛዝ መሰረት መሆኑን ጉዳዩ እስከ ፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ውሣኔ ካረፈበት በኃላ ላሻር፣ ላሻሸል የሚችልበት አግባብ የልለ መሆኑን ዘርዝረው የበታች ፍርድ ቤቶች በአፈፃፀም ጉዳይ የሰጡት ትእዛዝ ላፀና ይገባል ሲል ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል እንደመረመረውም አመልካች የባለቤነት ማረጋገጫ ደብተሩ ተሰርዟል በማለት የሚያቀርበው ምክንያት እንደ ፍርዱ ላለመፈፀም የሚያስችል ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ተይዞ ምላሽ የሚያስፈልገው ሁኖ አግኝቶታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ለክርክር መሰረት የሆነው ቤት ተጠሪዎች ሕጋዊ ባለቤትነታቸው በፍርድ ቤት ውሣኔ ተረጋግጦላቸው እንዲረከቡ እስከ የአገሪቱ የመጨረሻ የዳኝነት አካል ፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደርሶ የሰበር ችሎቱ የመጨረሻ ዳኝነት ያሰረፈበት መሆኑን ተጠሪዎች ክርክሩ በዚህ አግባብ የመጨረሻ መፍትሕ ከአገኘ በኃላ የፍርድ ቤቶቹ ውሣኔ እንዲፈጸምላቸው የአፈፃፀም ማመልከቻ አቅርበው ተገቢውን መዝገብ በሕጉ አግባብ ከፍተው አመልካች እንደ ፍርዱ እንዲፈጽም የማይፈጽምበት ሕጋዊ ምክንያት ካለም ቀርቦ እንዲያስረዳ ሲደረግ አመልካች ፍ/ቤት ቀርቦ እንደ ፍርዱ ላለመፈፀም ያቀረበው ምክንያት ለፍርዱ መሰረት የሆነውና የተጠሪዎችን የባለቤትነት መብት የማያረጋግጠው ደብተር በአስተዳደር አካሉ ከፍርድ ቤቱ ውሣኔ በኃላ መክኗል የሚል መሆኑን ነው።
በመሰረቱ በሕግ አግባብ ታይቶ የተሰጠ ፍርድ እንደ ፍርዱ መፈፀም ያለበትም ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ቁጥር 378 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ያሣያሉ። በእነዚህ ድንጋጌዎች በተዘረጋው ስርዓት አግባብ በመመራት ካልሆነ በስተቀር በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሣኔ በልላ አካል ዋጋ የሚያጣበት አግባብ አይኖርም። ድንጋጌዎች በግልጽ የሚያስገንዝቡት አቢይ ነጥብ የፍርድ አፈፃፀም ስርዓት ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ በእራሱ አማካኝነት ወደ ተግባር ወይም ውጤት የሚለወጥበት ሥርዓት መሆኑን ነው። በልላ አገላለጽ የድንጋጌዎች አቀራረጽ ይዘትና መንፈስ በጥንቃቄ ሲታይም የፍርድ አፈፃፀም ስለፍርድ አፈፃፀም የተደነገጉትን ድንጋጌዎች በመከተል ፍርዱን በተግባር መተርጐም እንደመሆኑ መጠን የአፈፃፀም ስርዓቱ ሕጉን መሰረት ማድረግ ያለበት እና የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉን መሰረታዊ አላማ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአንስተኛ ወጪ ጊዜና ጉልበት በተፋጠነና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲፈፀም በሚያስችል አግባብ ሕግ አውጪው ያስቀመጣቸው መሆኑን የምንረዳው ጉዳይ ነው።
እንዲሁም በሕግ አግባብ የተሰጠ ፍርድ ዋጋ እንዳይኖው የሚደረግው የዳግም ዳኝነት ወይም የፍርድ መቃወሚያ ጥያቄ በሕጉ በተዘረጋው ስርዓት ቀርቦ ከታየና ተቀባይነት ካገኘ ብቻ ስለመሆኑ ከፍ/ብሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 6 እና 358 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። ከዚህ ውጪ አንድ የአስተዳደር አካል በፍርድ ቤት ክርክር መረታቱን ከተረዳ በኃላ በሕጉ የተሰጠውን ስልጣን መነሻ በማድረግ ለፍርዱ መሰጠት መሰረት የሆነውን ማስረጃ ዋጋ በማሣጣቱ ምክንያት የፍርድ አፈፃፀም ዋጋ እንዲያጣ የማድረግ ውጤት በኢ.ፊ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 78/1/ እና 79/1/ እና /4/ ስር የተረጋገጠውንና የተከበረውን የነፃ ፍርድ ቤት መኖርንና የዳኝነት ስልጣን ትርጉም አልባ የሚያደርገው ነው። ይህ ብቻ ሣይሆን በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 37 ሥር የተረጋገጠው የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብትም ውጤት ባለው መልኩ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ ጠባብ እንዲሆን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ክርክሮች መቋጫ እንዳይኖራቸው የሚጋብዝ የፍርድ ቤትን ጊዜ ጉልበትና በጀት ለብክነት የሚዳርግ እንዲሁም ሕዝቡ በፍርድ ቤት አመኔታ እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው። የነፃ ፍርድ ቤት መገለጫው ደግሞ የሕግ የበላይነት መኖሩና መረጋገጥ ነው። ይህ ደግሞ ውጤታማ የሚሆነው አንዱ የመንግሥት አካል ልላኛውን ሲቆጣጠረው ከመሆኑ በተጨማሪ ፍርድ ቤት የራሱን ውሣኔ ዋጋ የማያሣጣና የሕግ መሰረት የልለውን የአስተዳደር አካል እርምጃ ውድቅ ሲያደርገው መሆኑ የሚታመን ነው። ፍርድ ቤት በሕገ መንግስቱ አንዱ የመንግስት አካል እንደመሆኑ መጠን የመንግስት የስልጣን አጠቃቀም የተወሰነና የተገደበ መሆኑ ላያረጋግጥ እንደሚገባ ይህ ላከወን ከሚያስችሉት መንገዶች አንዱ ደግሞ በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሣኔ ትርጉም እንዲኖረው በማድረግ ስለመሆኑ በሕገ መንግስቱ ስለፍርድ ቤቶች ስልጣን ከተመለከቱት ድንጋጌዎች እና በአገሪቱ የሕግ አካል ከሆኑ አለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ ከሰፈሩት መርሆዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው።
በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት ከላይ እንደተጠቀሰው ሕገ መንግስቱ ከተመሰረተባቸው መርሆች አንዱ የሕግ የበላይነት ስለመሆኑ በሕገ መንግስቱ መግቢያው ላይ የሰፈረ ጉዳይ ነው። ፍርድ ቤት ለሁሉም ወገኖች እኩል ተፈፃሚነት ባለው ሕግ መመራት ያለበት ስለመሆኑም የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 25 እና 13/1/ ድንጋጌን ይዘትና መንፈስ በማየት መረዳት የምንችለው ጉዳይ ነው። በመሆኑም በሕግ አግባብ የተቋቋመ ፍርድ ቤት አከራክሮ መወሰን ብቻ ሣይሆን የወሰነው ውሣኔ ውጤት ባለው መልኩ ወደ ተግባር መለወጡን ጭምር ማረጋገጥ አብይ ሀላፊነትና ተግባር በመሆኑ ይህንኑ በሕግ የተሰጠውን ስልጣን አንድ የመንግስት አካል የሚዘረጋው አሰራር ወይም የሚወስደው እርምጃ በፍርድ ቤቶች የፍርድ ስርዓት ላይ /በዳኝነት አካሉ ላይ/ የሚያመጣው ውጤት በሕግ የተመሰረተና የሚገዛ ስለመሆኑ ማየት የግድ ይላል። ከዚህም በተጨማሪ አንድ የአስተዳደር አካል የቤት ባለቤትንት ማስረጃ በፈለገው ጊዜ ከሕግ ውጪ እንዲሰረዝ ማስቻል በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 40/1ና2/ ድንጋጌ ሥር የተከበረውን የንብረት ባለቤትነት መብት ዋጋ የሚያሣጣው ነው። የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195 እና 1196 ድንጋጌዎች አንድ ላይ ሲነበቡም የአስተዳደር አካል በባለቤትን ማረጋገጫ ማስረጃ አሰጣጥ ላይ ፍጽም የሆነ አስተዳደራዊ ስልጣን ያለው ስለመሆኑ አያሣዩም። ይልቁንም ድንጋጌዎች እርስ በእርሣቸውም ሆነ ከፍ/ሕ/ቁጥር 1198 ድንጋጌ ጋር ተዛምደው ሲታዩ የባለቤትን ማረጋገጫ ደብትር የሚሰርዘው በሕጉ በተመለከቱት ምክንያቶች ብቻ መሆኑን ከሕጉ ውጪ ተግባሩ ተከናውኖ ከተገኘም መብቱ የተነካው ሰው በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37፣78 እና 79 ድንጋጌዎች መሰረት ጉይዩን ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት አቅርቦ አቤቱታው እንዲታይለት የሚያርግበት ጉዳይ እንጂ አስተዳደር አካሉ የሰጠው ውሣኔ በፍርድ ቤት እንዳይታይ የሚገደብበት ስርዓት የልለ መሆኑን የምንገነዘበው ነው።
በአጠቃላይ አመልካች ቀድሞ በፍርድ ቤት በነበረው ክርክሩ ተሣታፊ ሁኖ በፍርድ ኃይል ከተረታ በኃላ በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሣኔ በሕጉ አግባብ እንዳይፈጽም በሚል እሣቤ በዋናው ክርክር ጊዜ የተጠሪ ባለቤትነት የተረጋገጠበትን ማስረጃ በመሰረዝ ፍርዱን አከራካሪውን ቤት አላስረክብም ማለቱ የሕግ መሰረት የልለው በመሆኑና የበታች ፍርድ ቤቶችም ይህንኑ የአመልካች ክርክር ውድቅ በማድረግ አፈፃፀሙ እንዲቀጥል የሰጡት ውሣኔ ምንም አይነት የሕግ ስህተት የልለበት ሆኖ አግኝተናል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ህዳር 25 ቀን 2001 ዓ.ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ታህሣስ 24 ቀን 2001 ዓ/ም በትእዛዝ የፀናው ብይን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሰረት ፀንቷል።
አመልካች ቀድሞ የክርክሩ ተሣትፊ ሁኖ እስከ በላይ ፍርድ ቤቶች በተደረገው ክርክር ተረቺ መሆኑ ከተረጋገጠ በኃላ ለቀድሞው ውሣኔ መሰረት የሆነውን የባለቤትነት ምስክር ወረቀት በማምከን አዲስ ክስ የሚመሰርትበት አግባብ የለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.