No summary available.
የካቲት 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካቾች፡-
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ የተጀመረው በአሁን የሰበር አመልካቾች የመቃወሚያ አቤቱታ አቅራቢነት በአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው። አቤቱታውም፡- በ04/05/1994 ዓ/ም በተደረገ የሽያጭ ውል አቶ ደሴ ተላላ ለወ/ሮ የሺ ወ/መድህን የሸጡትን ቤት ወ/ሮ የሺም በ24/07/1994 ዓ/ም በተደረገ የሽያጭ ውል ለአመልካቾች ለእያንዳንዳችን አንድ አንድ ክፍል ሽጠውልን ይዘን እያለ በመቃወም ተጠሪዎች ፍርድ ቤቱን በማሳሳትና ባዶ ቦታ በማስመሰል በውርስ የተላለፈልን ነው በሚል የወራሽነት ውሳኔ ያሰጡ ስለሆነ ውሳኔው እንዲሰረዝ ይወሰንልን ብለዋል።
ተጠሪዎች በበኩላቸው በሰጡት መልስ፡- የሚያከራክረውን ቤትና ቦታ ከሟች አባታችንና እናታችን በውርስ ያገኘነው ነው፣ ወ/ሮ የሺ ወ/መድህን ከወንድማችን ደሴ ተላላ እንደገዙና አመልካቾችም ከግለሰቧ እንደገዙ በመጥቀስ ያቀረቡት ማስረጃ የሐሰት ነው፤ማስረጃው አለ ቢባል እንኳን በህግ ፊት የሚጸና አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።
የወረዳው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ማስረጃዎች በመስማትና በመመዘን በሰጠው፡- ውሳኔ የግራ ቀኙ ምስክሮች ቤቱ የተጠሪዎች አባት እና እናት መሆኑን ያስረዱ በመሆናቸው በመቃወም አመልካቾች ወ/ሮ የሺ ወ/መደህን ከተባሉት ግለሰብ ገዝተናል ቢሉም ግለሰቧ እነዚህን ሰዎች በመወከል ላሸጡ አይችሉም፣ እንዲሁም የሽያጭ ውሉ የተመዘገበ ባለመሆኑ በህግ ፊት ተቀባይነት የለውም፣ ስለሆነም አመልካቾች ከፈለጉ ግለሰቧን በመክሰስ መብታቸውን ከሚያስጠብቁ በስተቀር ለተጠሪዎች የተሰጣቸው የወራሽ ማስረጃ ላሰረዛባቸው አይገባም በሚል የመቃወም አመልካቾች ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ አድርጓል።
በመቃወም አመልካቾችም በወረዳው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን ከፍተኛው ፍርድ ቤትም በሰጠው ውሳኔ ክርክር ያስነሳው ቤት በ1990 ዓ/ም ከመልስ ሰጪዎች እጅ መውጣቱን ከአዳማ ከተማ አስተዳደር እና ከደቤ ሶለቄ ቀበል አስተዳደር ከተጻፉት ደብዳቤዎች ከመረጋገጡም ልላ መልስ ሰጪዎች (በመቃወም ተጠሪዎች) በ26/09/2002 ዓ/ም ለወረዳው ፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ አባታቸው በ1976 ዓ/ም፣እናታቸው ደግሞ በ1990 ዓ/ም መሞታቸውን የገለጹ ሲሆን የወራሽነት ማስረጃውን የያዙት ደግሞ በመ/ቁ/38843 በቀን 28/05/2002 በመሆኑ ማስረጃውን የወሰዱት 10 ዓመት ካለፈ በኋላ ሆኖ እያለ የወረዳው ፍርድ ቤት በቀረበው የይርጋ መቃወሚያ ላይ ብይን ሳይሰጥ ማለፉ ተገቢነት የለውም በሚል መልስ ሰጪዎች የወራሽነት ማስረጃ ያወጡት በፍ/ህ/ቁ 1845 የተደነገገው 10 ዓመት ይርጋ ካለፈው በኋላ ነው ሲል የወረዳውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሽሯል።
በመቃወም ተጠሪዎች ይግባኝ ጠያቂነት ጉዳዩን የመረመረው የክልሉ ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በበኩሉ በሰጠው ውሳኔ በይግባኝ ባዮች እናት እጅ የነበረው ቤት ፈርሶ 5ኛ ይግባኝ ባይ (አቶ ደሴ ተላላ) በቦታው አራት ክፍል ቤት መስራታቸው የተረጋገጠ በመሆኑና ቤቱ ወደ መልስ ሰጪዎች የተላለፈው በ5ኛ ይግባኝ ባይ በመሆኑ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የወራሽነት ማስረጃውን ይግባኝ ባዮች ያወጡት የ10 ዓመት ይርጋ ካለፈ በኋላ በመሆኑ በይርጋ የሚታገድ ነው በሚል የጠቀሰው ምክንያት ተቀባይነት የልለው ቢሆንም በውጤት ደረጃ ግን የሚነቀፍ አይደለም ሲል አጽንቷል።
በመቃወም ተጠሪዎችም በከፍተኛው እና በክልሉ ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ችሎቱም የግራ ቀኙን ወገን ካከራከረ በኋላ በሰጠው ውሳኔ፡- ተጠሪዎች አቤቱታ ያቀረቡት በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 358 ሲሆን ይዘቱም ክርክር ባስነሳው ቤት ላይ ለአመልካቾች የተሰጠ የወራሽነት ማስረጃ እንዲሻር ሲሆን በዚሁ ድንጋጌ መሰረት መቃወሚያ የሚያቀርብ ሰው ደግሞ መብቱን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ አለበት፣ በከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኝ ቤት ደግሞ ባለንብረት ለመሆን የባለይዞታነት ማረጋጫ ማስረጃ (ካርታና ፕላን) መኖር ግድታ ነው፣ይህ በመሆኑ ግዥ እና ሽያጭ መፈጸም ብቻ የቤቱ ባለቤት ማድረግ እንደማይችል የፍ/ህ/ቁ/1185 ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻል በመሆኑ ተጠሪዎቹ መብት በልላቸው ንብረት ላይ የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/358ን ጠቅሰው ያቀረቡት የመቃወሚያ አቤቱታ ውድቅ የሚሆን ነው ሲል የከፍተኛውን እና የክልሉን ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ በመሻር የወረዳውን ፍርድ ቤት ውሳኔ አጽንቷል።
No topics extracted.
አመልካቾችም በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት የጠቀሱአቸው የቅሬታ ነጥቦችም፡- የተጠሪዎች አባት ከሞቱ ከ26 ዓመት በኋላ እንዲሁም እናታቸው ከሞቱ 12 ዓመት በኋላ ተጠሪዎች በቦታውና ቤቱ ላይ ወራሽነት ይገባናል በሚል የያዙት የወራሽነት ማስረጃ በፍ/ህ/ቁ/1000(1) እና 1845 የተደነገጉት ይርጋ ጊዜያት ካለፉ በኋላ የተሰጣቸው በመሆኑ ተቀባይነት የለውም በሚል ያቀረብነው የመከራከሪያ ነጥብ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በዝምታ ማለፉ ተገቢነት የለውም፤
ክርክር ያስነሳውን ቤትና ቦታ የተጠሪዎች ወላጆች ከሞቱ በኋላ በ5ኛ ተጠሪ እጅ ገብቶ ተጠሪውም ቀደም ሲል የነበረውን ቤት አፍርሶ በአዲስ መልክ ሰርቶ ለወ/ሮ የሺ ወ/መድህን የሸጠ ሲሆን ግለሰቧም አስፋፍታ ግንባታዎችን በማካሄድ በጽሁፍ በተደረገ የሽያጭ ውል ለአመልካቾች ሽጣ እያለ ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር ወጪ የክልሉ ሰበር ሰሚው ችሎት የፍሬ ነገር ጉዳዮችን ለማጣራት ስልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ካርታ እና ፕላን በተመለከተ ክርክር ያልተነሳውን በራሱ ጊዜ በማንሳት የከፍተኛውንና የክልሉን ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሻሩ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ነው የሚል ነው።
ተጠሪዎች በበኩላቸው በሰጡት መልስ፡- የሚያከራክረው ቤትና ቦታ የወላጆቻችን የነበረ ሲሆን ወላጆቻችን በሞት ከተለዩ በኋላ በእጃችን የሚገኝ ሆኖ እያለ አመልካቾች በሽያጭ አግኝተው በእጃቸው መግባቱን በመጥቀስ በሐሰት በተቀነባበረ ማስረጃ የሚከራከሩ ቢሆንም የሽያጭ ውሉ አመልካቾች እንደሚሉት ተፈጽሟል ቢባል እንኳን የጋራ የውርስ ንብረት አንዱ ወራሽ ብቻ አደረገ በተባለው የሽያጭ ውል መነሻ ልሎች ወራሾች የመውረስ መብታችንን የምናጣበት ህጋዊ ምክንያት አይኖርም፤እንዲሁም ተጠሪዎች የውርስ ንብረት ይለቀቅልን በሚል ያቀረብነው ክስ በልለበት የይርጋ ክርክር ላነሳ የማይችል ከመሆኑም ልላ ይርጋን መከራከሪያ ላያደረግ የሚችለው ተከሳሽ የሆነ ወገን እንጂ ከሳሽ አይደለም። በመሆኑም የሰበር አቤቱታቸው ውድቅ ላሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።
አመልካቾችም ተጠሪዎች ለሰጡት መልስ የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- አመልካቾች ያቀረቡት ክርክር በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/358 መሰረት ላቀርብ የሚገባ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
አመልካቾች ካቀረቡት ክርክር መረዳት የተቻለው ተጠሪዎች ወላጅ አባታቸውና እናታቸው በሞት የተለዩ መሆናቸውን በመግለጽ የወራሽነት ማስረጃ እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተው ወራሽ ናቸው በሚል በተሰጠ ውሳኔ መነሻ የውርስ ሀብት ነው በሚል በግዥ ያገኘነውን ቤት ስለያዙ የተሰጣቸው ማስረጃ እንዲሰረዝባቸው ሲሉ መጠየቃቸውን ነው።
በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/358 መሰረት የፍርድ መቃወሚያ ማቅረብ የሚችለው በክርክሩ ተካፋይ መሆን የሚገባው ወይም በክርክሩ ውስጥ ለመግባት የሚችልና እንዲሁም ተካፋይ ባልሆነበት ክርክር የተሰጠው ፍርድ መብቱን የሚነካበት ማናቸውም ሰው ወይም ጠበቃው ወይም ነገረ ፈጅ መሆኑን ከድንጋጌው መረዳት የሚቻል ሲሆን መቃወሚያውም ላቀርብ የሚገባው ለመቃወሚያው መሰረት የሆነው ፍርድ ከመፈጸሙ በፊት ነው። በዚህ በተያዘው ጉዳይ ተጠሪዎች የሟች እናታቸው እና አባታቸው ወራሾች መሆናቸው እንዲወሰንላቸው ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ወራሾች ናቸው በሚል በመ/ቁ/38843 በቀን 28/05/2002 ዓ/ም ፍርድ/ውሳኔ የተሰጠ መሆኑን መዝገቡ ያመላክታል። በዚህ በተጠቀሰው መዝገብ ተጠሪዎች ወራሾች ስለመሆናቸው ባቀረቡት አቤቱታም ሆነ በሚደረገው ክርክር እንዲሁም በሚሰጠው ፍርድ ወይም ውሳኔ የሚያከራክረውን ቤት ስለገዛን ፍርዱ ወይም ውሳኔው መብታችንን ይነካል በሚል ምክንያት የተጠሪዎች የወራሽነት ማስረጃ እንዲሰረዝባቸው አመልካቾች መቃወሚያ ላያቀርቡ የሚችሉበት ህጋዊ ሁኔታ አይኖርም። ምክንያቱም ተጠሪዎች የወራሽነት ማስረጃ እንዲሰጣቸው ከጠየቁት ዳኝነትም ሆነ ከተሰጠው ውሳኔ ጋር አመልካቾች የውርስ ሀብቱን በሽያጭ ውል አግኝተናል በሚል ያቀረቡት የንብረት መብት ጥያቄ የሚገናኝ ባለመሆኑ ነው። በመሆኑም አመልካቾች በሚያከራክረው ንብረት ላይ መብት አለን የሚሉ ከሆነ ተገቢውን ዳኝነት ክፍለው ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ክስ አቅርበው መብታቸውን ከሚጠይቁ በስተቀር በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/ 358 መሰረት የፍርድ/የውሳኔ መቃወሚያ ላያቀርቡ አይገባም። ይህ ሆኖ ሳለ የስር ፍርድ ቤቶች በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/358 መሰረት ላቀርብ የማይገባውን መቃወሚያ ተቀብለው በማከራከር ውሳኔ መስጠታቸው ተገቢ ባይሆንም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የዞኑ ከፍተኛው ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡትን ውሳኔ በመሻር የመቃወሚያ አቤቱታቸውን ውድቅ ያደረገው በውጤት ደረጃ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ባለማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የኦሮሚያ ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/131390 በቀን 06/09/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ምክንያቱን ለውጠን በውጤት ደረጃ በመቀበል በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት አጽንተናል።
አመልካቾች የውርስ ሀብት የሆነውን የሚያከራክረውን ቤትና ቦታ በግዥ ስላገኘን ለተጠሪዎች የተሰጣቸው የወራሽነት ማስረጃ ይሰረዝልን ሲሉ ያቀረቡት የመቃወሚያ አቤቱታ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/358 መሰረት ላቀርብ የሚገባ አይደለም ብለናል። ይህ ውሳኔ አመልካቾች ለሚያከራክረው ንብረት ተገቢውን ዳኝነት ከፍለው መብታቸውን በሚጠይቁት ወገን ላይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት በህጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ክስ አቅርበው መብታቸውን ከመጠየቅ የሚያግዳቸው አይሆንም ብለናል።
የዚህ ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ
ት/ዘ