No summary available.
መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ ብዙነሽ ወ/ሚካኤል - ወኪል ታፈሱ አሰፋ ቀረቡ ተጠሪዎች፡- እነ አቶ ሽመልስ ቦጋለ - ጠበቃ ተስፋዬ ግዛው ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የጋራ ንብረት ክፍፍል ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪዎች በቅምብቢት ወረዳ ፍ/ቤት ባሁኗ አመልካች ላይ በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው። የተጠሪዎች ክስም በውርስ የሚገባቸውን የሟች አባታቸውን ቆርቆሮ ቤት የአሁኗ አመልካች ይዘው እንደሚገኙ ገልፀው የቤቱን ግማሽ ግምት ብር 25,000.00 (ሃያ አምስት ሺህ ብር) አመልካች እንድትሰጣቸው ወይንም ቤቱን በአይነት እንድታካፍላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው። የአሁኗ አመልካችም የቤቱ ግምት ያላግባብ ከፍ መደረጉን ቤቱ ሶስት ክፍል ሰርቪስ ቤት ቢሆንም ብር 50,000.00 አያወጣም በማለት ተከራክረዋል። የወረዳው ፍ/ቤትም አመልካች የቆርቆሮ ቤቱን የተጠሪዎች አባት ድርሻ ላያካፍሉ ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቶ በዚህ ውሳኔ ላይ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርበው ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት ስንት ብር እንደሚያወጣ በባለሙያ ተገምቶ በአማራጭ በቀረበው ክስ ግምት ላይ ተመስርቶ ውሳኔ እንዲሰጥ በማለት ጭብጥ ይዞ ለስር ፍ/ቤት ጉዳዩን መለሰለት ሲሆን የወረዳ ፍ/ቤትም የሸኖ ከተማ አስተዳደር በባለሙያ እንዲያስገምት ትዕዛዝ ሰጥቶ ይሄው አካልም በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት በባለሙያ አስምምቶ የቤቱ ግምት ብር 93,750.00 (ዘጠና ሶስት ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ ብር) መሆኑን በቁጥር 64/353/2005 በ30/01/2005 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ ገልጾለት ፍ/ቤቱ ይህንኑ ግምት ከተቀበለ በኋላ ግራ ቀኙ አስተያየት እንዲያቀርቡ አድርጎ አመልካች ግምቱ ትክክል አይደለም የሚል ተቃውሞ ያቀረቡ መሆኑን ከመዘገበ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ግምቱን የተቃሙበት ምክንያት በቂ አይደለም የሚል ምክንያት ይዞ በቀረበው ግምት መሰረት ተጠሪዎች የአመልካችን ድርሻ ከፍለው ቤቱን እንዲወስዱ ወይም ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤት እኩል መካፈል የሚቻል ከሆነ እኩል እንዲካፈሉ ወይም ሸጠው ገንዘቡን እኩል እንዲከፋፈሉ በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታቸውን ደግሞ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የተጠሪዎች የቤቱ ግምት ብር 50,000.00 ሆኖ ይህንኑ ግምት በመቃወም በይግባኝ ለዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቅሬታ ያቀረብኩ እኔ ሆኜ እያለና የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤትም በእኔ ቅሬታ መነሻ ግምቱ እንደገና እንዲከናወን እንዲደረግና ጉዳዩ እንዲወሰን ትዕዛዝ ሰጥቶ በዚሁ መነሻ በተገኘው የተጋነነ ግምት መሰረት ተቃውሞ እየቀረበ እያለ የወረዳው ፍ/ቤት ግምቱን ከፍ አድርጎ ተጠሪዎች ግምቱን ከፍለው ቤቱን እንዲያስቀሩ በማለት በቅድሚያ የሰጠው ውሳኔ ተገቢነት የለውም በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው። አቤቱታቸው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ላታይ ይገባዋል ተብሎ በመታመኑ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብና እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበውም የአመልካች ቅሬታ ዋናውን ውሳኔ መሰረት ያላደረገና በስር ፍ/ቤት ያልተነሳ አዲስ ክርክር መሆኑን ዘርዝረው የሰበር አቤቱታው ውድቅ ላሆን ይገባል ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን አመልካች በበኩላቸው የሰበር አቤቱታቸውን አጠናክረው የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም አመልካች የተጠሪዎችን ግምት በመቃወም ባቀረቡት ይግባኝ መነሻ ግምቱ እንደገና እንዲገመት ሲደረግ ከፍ በማለቱ በዚሁ ግምት መሰረት ተጠሪዎች ቅድሚያ ቤቱን የማስቀረት መብት እንዳላቸው ተገልፆ ልሎች የክፍፍል ቅደም ተከተሎች ተጠቅሰው ውሳኔ መስጠቱ ከዳኝነት አሰጣጥ ስርዓት አንፃር ተገቢ መሆን ያለመሆኑ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል።
ተጠሪዎች የሚጠይቁት የአባታቸውን ድርሻ መሆኑን አመልካች ክርክር ያላቀረቡበት ጉዳይ ሲሆን ተጠሪዎች ንብረቱን በብር 50,000.00 ገምተው ድርሻቸውን ብር 25,000.00 አመልካች እንዲሰጧቸው፣ ይህን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ደግሞ ቤቱን በአይነት እንዲከፋፈሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን ከክርክሩ ሂደት ተገንዝበናል። ጉዳዩ በመጀመሪያ ደረጃ የቀረበለት የወረዳው ፍ/ቤት የቤቱን ግምት ሳያጣራ ክፍፍሉ እንዲደረግ ውሳኔ ሰጥቶ በዚህ ውሳኔ ቅሬታ የተሰማቸው የአሁኑ አመልካች ሲሆን የቅሬታቸው መሰረታዊ ነጥብም ቤቱ ብር 50,000.00 ግምት ላያወጣ አይችልም የሚል የነበረ መሆኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን ቅሬታ መርምሮ ግምቱ እንደገና እንዲከናወን ማድረጉን፣ በዚህ ውሳኔ መሰረት ግምቱ ሲከናወን ግን ተጠሪዎች መጀመሪያ ገምተው ከአቀረቡት ግምት እጅጉን የላቀ ሆኖ መገኘቱን አመልካች በድጋሚ ግምት ትክክል አይደለም በማለት ቢቃወሙም የወረዳው ፍ/ቤት የአመልካች ምክንያት በቂ አይደለም ከማለት አልፎ ተጠሪዎች በአዲሱ ግምት መነሻ ቤቱን እንዲያሰሩ በማለት በመጀመሪያ አማራጭነት መወሰኑን ከክርክሩ ሂደት መረዳት ተችሐል።
No topics extracted.
በመሰረቱ ክርክር በሚደረግበት ንብረት ላይ የግምት ተቃውሞ ከተነሳ ግምቱ ተጣርቶ ክርክሩ መካሄድ ያለበት መሆኑን ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 250፣ 136፣ እና ከልሎች ስለማስረጃ አቀራረብ ከሚደነግጉት ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በልላ በኩል ዳኝነት ላሰጥ የሚገባው በተጠቀሰው መጠን ሆኖ አግባብነት ባለው ማስረጃ ነጥሮ በታወቀው ውጤት መሰረት ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 182(1) ድንጋጌ መረዳት የምንችለው ጉዳይ ነው። አንድን ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ የሚመለከት ፍ/ቤት በሕጉ አግባብ ክስ ተሻሽሎ ከፍ ያለ ዳኝነት ባልተጠየቀበት ሁኔታ በግምት ላይ ተቃውሞ ቀርቦ ግምቱ እንዲጣራ ሲደረግ የንብረቱ ግምት ከፍ ማለቱ በመረጋገጡ ብቻ ቀድሞ ከተጠየቀው ዳኝነት በላይ ዳኝነት የሚሰጥበት አግባብ የልለ መሆኑን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 92፣182(1) ድንጋጌዎች ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 225 እና 226 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም ተጠሪዎች አከራካሪውን ቤት ብር 50,000.00 (ሃምሳ ሺህ) ገምተው ድርሻቸውን ብር 25,000.00 በአመልካች እንዲሰጣቸው በመጀመሪያ ደረጃ የጠየቁት ዳኝነት ሲሆን ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ቤቱን በአይነት ልንከፋፈል ይገባል በማለት በሁለተኛ አማራጭ ዳኝነት ጠይቀዋል። የቤተሰብ ሕጉንና የውርስ ሕጉን መሰረት አድርገው የሚቀርቡ የንብረት ክፍፍል ጥያቄቆች ላይ ክፍፍሉን በተመለከተ ውሳኔ ሲሰጥ በሕጉ የተቀመጡ ቅደም ተከተሎች ያሉ ሲሆን ተከራከሪ ወገን ይህንኑ በመተው ክፍፍሉን ሲጠይቅ ግን ሕጉን የማይፃረር መሆኑ ተረጋግጦ በተጠየቀው መሰረት ውሳኔ መስጠት የሚቻል መሆኑን አግባብነት ካላቸው ሕጎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው። በመሆኑም የግምት ይከፈለኝ ጥያቄ በቅድሚያ አማራጭነት ከቀረበ ፍ/ቤቱ የግምቱን ትክክለኛነት አረጋግጦ በተጠየቀው ውሳኔ ቢሰጥ የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓትን የጠበቀ ነው ከሚባል በስተቀር የሚነቀፍበት አግባብ የለም። ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው ተጠሪዎች የቤቱን ግምት በግልፅ አስቀምጠው ግምቱን አመልካች ተቃውመው እንደገና እንዲገመት በተደረገበት ሁኔታ ግምቱ ከፍ ሲል ይህንኑ ከፍ ያለውን ግምት መሰረት አድርጎ ውሳኔ መስጠት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 182(1) ድንጋጌን የጣሰ ሆኖ አግኝተናል። አመልካች ግምቱ እንዲቀነስ በማሰብ ይግባኝ አቅርበው ተቀባይነት አግኝተው በይግባኙ መነሻ ግምቱ ሲከናወን ከፍ በማለቱ ብቻ ይሄው መሰረት ተደርጎ ዳኝነት የሚሰጥበት አግባብ የይግባኝ ጽንሰ ሃሳብና የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓትን የሚፃረር ነው። ምክንያቱም አንድ ተከራከሪ ወገን ይግባኝ የሚያቀርበው መብቱን ለማስፋት እንጂ መብቱን ለማጥበብ ያለመሆኑን ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የሚመለከት ፍ/ቤት ዳኝነት መስጠት ያለበት በተጠየቀውና ሕጋዊ በሆነው መጠን መሰረት ብቻ መሆኑን ከይግባኝ አቀራረብና የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓቶች የምንገነዘበው ጉዳይ ነውና። ሥለሆነም የወረዳው ፍ/ቤት በይግባኙ መነሻ የቤቱ ግምቱ ከፍ ሲል ተጠሪዎች በጠየቁት ዳኝነት መጠን ተወስኖ የክፍፍል ውሳኔ መስጠት ሲገባው ይህንኑ በማለፍ ከፍ ብሎ በቀረበው ግምት መሰረት ተጠሪዎች ግምቱን ለአመልካች ከፍለው ቤቱን እንዲያስቀሩ በመጀመሪያ አማራጭነት መወሰኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 182(1)፣ 250 እና ስለይግባኝ የተደነገጉትን ድንጋጌዎችን የጣሰ ሲሆን ይህንኑ ውሳኔ የክልሉ የበላይ ፍ/ቤቶች ሳያስተካክሉ ማለፋቸውም የህግ ስህተት መፈፀማቸውን የሚያሳይ ሆኖ ስለአገኘን በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል።
በቅምብቢት ወረዳ ፍ/ቤት በመ/ ጥቅምት 22 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ ጥቅምት 27 ቀን 2005 ዓ/ም በኦሮሚያ ከልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ህዳር 17 ቀን 2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት በትዕዛዝ ያፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሐል።
ተጠሪዎች በቅድሚያ ዳኝነት የጠየቁት ቤቱን በብር 50,000.00 (ሃምሳ ሺህ ብር) ገምተው ድርሻቸውን አመልካች እንዲከፍሐቸው በመሆኑ ግምቱ ላይ አመልካች ባቀረቡት መቃወሚያ መሰረት እንደገና በመገመቱና ከፍ በማለቱ ተጠሪዎች ከፍ ያለውን ግምት መሰረት አድርገው ለአመልካች ድርሻቸውን ሰጥተው ቤቱን ያስቀሩ በማለት መወሰኑ ያላግባብ ነው ብለናል።
አመልካች የቤቱ ግምት 50,000.00 (ሃምሳ ሺህ) መሰረት አድርገው ግማሹን ብር 25,000.00 (ሃያ አምስት ሺህ ብር) ለተጠሪዎች እንዲከፍሉና ቤቱን እንዲያስቀሩ፣ ይህንን ማደረግ የማይችሉ ከሆነ ቤቱን በአይነት እኩል እንዲከፋፈሉ፣ ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ ቤቱን በስምምነት እንዲሸጡ፣ ካልተቻለም በሀራጅ ተሸጦ የሽያጩን ገንዘብ እኩል እንዲካፈሉ በማለት ወስነናል። በዚህ ውሳኔ መሰረት አፈፃፀሙን የወረዳው ፍ/ቤት እንዲያስፈፅም ብለናል። ይፃፍ።
ተጠሪዎች በብር 93,750.00 (ዘጠና ሶስት ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ ብር) ላይ በታሪፉ መሰረት የከፈሉት የዳኝነት ገንዘብ እንዲመለስ እንዲያደርግ የስር ፍ/ቤት ታዝዟል። ይፃፍ።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።