No summary available.
መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- እነ ወ/ሮ ኒኢማ አባድጋ አባዋጂ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ጣሐ ጀማል አደም ቀረቡ።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በውጭ አገር የተደረገ የእርቅ እና የግልግል ስምምነት በሸሪዓ ፍርድ ቤት ቀርቦ ላፀድቅ የሚችልበትን ሕጋዊ አግባብ የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ከአሁኗ አመልካች ጋር የነበራቸውን ጋብቻና ውጤቱን በተመለከተ በሽማግል ፊት ነሐሴ 01 ቀን 2002 ዓ.ም በስምምነት በሰዑዲ አረቢያ የኢ.ፍ.ዲ.ሪ መንግስት ቆንጽላ ጽ/ቤት በተረጋገጠው አግባብ መደረጉን ገልፀው ይኼው ስምምነት እንዲፀድቅላቸው ለፍድራል ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት አቅርበው የካቲት 17 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ለተጠሪ ያጸደቀላቸው ሲሆን የአሁኗ አመልካች ሰኔ 26 ቀን 2004 ዓ.ም ፅፈው ባቀረቡት ማመልከቻ የአሁኑ ተጠሪ ያቀረቡት የስምምነት ፍቺ በልሉበትና እና ሙሉ ፍላጎታቸው ሳይጠየቅ በተጠሪ ተፅፎ የቀረበ ስለመሆኑና በውጤቱም እጅጉን የጎዳቸው መሆኑን ጠቅሰው በጉዳዩ ላይ ክርክር አድርገው የመኸር ገንዘብ ብር 10,000.00 (አስር ሺህ ብር)፣ የቤት ንብረት፣የልጅ ቀለብ ላይ ውሳኔ እንዲሰጣቸው የመቃወም ማመልከቻ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት አድርጎ ጉዳዩን በመመርመር ተጠሪና አመልካች ሰኔ 01 ቀን 2002 ዓ.ም ያደረጉት የእርቅ ስምምነት አመልካች የተሳተፈበት መሆኑ የተረጋገጠ ነው በሚል ምክንያት ቀድሞ የእርቅ ስምምነቱን ያጸደቀበትን ውሳኔ ባለበት አጽንቶታል። በዚህ ውሳኔ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍደራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ጋብቻው በስምምነት የፈረሰ ቢሆንም በንብረቱና በልጅ አስተዳደግ ላይ ግን ተገቢዉና ሕጋዊ ስምምነት ባልተደረገበት ሁኔታ የበታች ፍርድ ቤቶች በስምምነት መሰረት ልትጸና ይገባል በማለት የሰጡት ውሳኔ የሸሪዓ ሕጉንም ሆነ መደበኛውን ሕግ የሚጥስ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ላታይ የሚገባው ነው ተብሎ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
እንደመረመረውም ተጠሪ ከአመልካች ጋር ነሐሴ 01 ቀን 2002 ዓ.ም የተደረገ ነው ያሉትን የእርቅ ስምምነት ለፍድራል ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት አቅርበው አመልካች በልሉበት እንዲጸድቅ ማድረጋቸው ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ አግኝተናል። ይህንኑ ጭብጥ ለመመለስም የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በሕጉ ተለይቶ የተሰጣቸውን ስልጣን ምን እንደሆነ መመልከቱ ተገቢ ይሆናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካችና ተጠሪ ባልና ሚስት የነበሩ መሆኑን፣ ባሁኑ ደረጃ ተለያይተው እንደሚገኙና በባልና ሚስትነት ሲኖሩ በሳውዲ አረቢያ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንፅላ ጽ/ቤት ነሐሴ 01 ቀን 2002 ዓ.ም በሽማግልዎች ፍቺ ተደረገ በተባለ የእርቅና የግልግል ስምምነት የሚል ርዕስ ባለው ሰነድ ጋብቻውን በፈቃዳቸው አፍርሰው ንብረቱንም ሆነ በጋብቻ ወቅት ያፈሯትን ሕጻን አስተዳደግ በተመለከተ ስምምነት ተደርጓል በሚል ምክንያት ተጠሪ ሰነዱን ለፍድራል ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም አመልካች በልሉበት ሁኔታ የካቲት 16 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎት ስምምነቱ ፀድቋል ተበሎ የተወሰነ መሆኑንና አመልካች ይህንኑ ውሳኔ ለማስነሳት የተቃውሞ አቤቱታ ማቅረባቸውን፣ ለአቤቱታቸው መሰረት ያደረጉት ምክንያትም ተጠሪ አለ በማለት ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡት ስምምነት የማያውቁትና በተጠሪ ፍላጎት ብቻ ተፅፎ የቀረበ እንዲሁም የአመልካችን የንብረት መብትም ሆነ የህጻኗን አስተዳደግ የጎዳ መሆኑን መጥቀሳቸውን የሚያሳይ መሆኑን ነው።
በመሰረቱ የኢ.ፍ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 34 (5) ስር የግልና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሀይማኖት ወይም በባሕሎች ሕጎች መሰረት መዳኘትን በሕገ መንግስቱ ክልከላ እንዳልተደረገበት በግልጽ ከማስቀመጡም በላይ ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን ያሳያል። በሸሪዓ ፍርድ ቤት የመዳኘት መብትም ምንጩ ይኼው የሕገ መንግስቱ ድንጋጌ ሲሆን የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 188/1992 መሰረት ተደራጅተዋል።
በዚሁ አዋጅም ስልጣናቸው ተለይቶ ተቀምጧል። በአዋጁ የክርክሩን የአመራር ሥርዓት ካልሆነ በስተቀር የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በስረ ነገር ስልጣናቸው ሥር የሆኑ ጉዳዮች የሚቀርብላቸውን አቤቱታና ክርክር የሚወስኑት የሸሪዓ ህግን መሰረት በማድረግ እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 188/92 በአንቀጽ 6 (1) ስር በግልፅ የተደነገገ ሲሆን አንድ ሰው ለሸሪዓ ፍርድ ቤት ክስ ወይም አቤቱታ ሲያቀርብ ሥነ ሥርዓታዊ ከሆነው ጭብጥና ጥያቄ ውጭ የሆኑት ጉዳዮች በሸሪዓ ህግ ለመዳኘት ፈቃድ የሰጠ መሆኑም ላረጋገጥ ይገባል። በመሆኑም የሸሪዓ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ዳኝነት ከመሰጠቱ በፊት በአዋጅ ቁጥር 188/1992 ዓ.ም አግባብ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የተሰጠው መሆኑን በቅድሚያ ላያረጋግጥ የሚገባ መሆኑን ከአዋጁ አንቀጽ 6 ድንጋጌና ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 9 እና 231 (1(ለ)) ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። ይህ ችሎትም በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ህግ መንግስት አንቀጽ 80 (3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 188/1992 አንቀጽ 6 ጣምራ ንባብ መሰረት ስነ ስርዓታዊ የሆነ የህግ ጥያቄን ብቻ ለማየት ስልጣን እንዳለው ግንዛቤ በመውሰድ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ስነ ስርዓታዊ ሕጎችን መሰረት አድርጎ የተሰጠ መሆን ያለመሆኑን ከጭብጡ አንጻር መርምሯል።
ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው ተጠሪ በሸሪዓ ፍርድ ቤት የእርቅ ስምምነት እንዲፀድቅላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ ያቀረቡት ሰነድ የእርቅ ግልግል ስምምነት መሆኑን በርዕሱ የሚገልፅና በይዘቱም ጋብቻንና ውጤቱን እንዲሁም የልጅ አስተዳደግን በተመለከተ ግራ ቀኙ ያደረጉትን ስምምነትን ምንነት የያዘ ነው። ይሁን እንጂ ስምምነቱ የተደረገው የሸሪዓ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ከመጀመሪያው ለማየት በቀጥታ በተከፈተለት መዝገብ ሳይሆን በውጪ አገር ተደርጎ የመጣው የእርቅ ስምምነት እንዲፀድቅ ተጠሪ አመልካች በመሆን ባስከፈቱት መዝገብ ነው። በዚሁ መዝገብ ላይ በአመልካችነት የአሁኑ ተጠሪ ስም የተመዘገበ ሲሆን በመዝገቡ ተጠሪ በሚል በተቀመጠው ቃል ትይዩ ግን የአሁኗ አመልካች ወይም ለጉዳዩ ተከራካሪ የሆነ ሰው ስም ያለመመዝገቡን የውሳኔው ግልባጭ ያሳያል።
በመሰረቱ አንድ እርቅ በፍርድ ቤት ላፀድቅ የሚችለው ጉዳዩ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት በመታየት ሂደት ላይ እያለ ተከራካሪ ወገኖች ጉዳዩን በስምምነት የጨረሱ መሆኑን ገልፀው ይኼው ስምምነታቸው ለሕግ እና ለሞራል ተቃራኒ ያለመሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ እርቁ ወይም ስምምነቱ በፍርድ ቤት ተመዝግቦ ክርክሩ እንዲቆምላቸው ሲያመለክቱ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 277 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ያሳያል። ከዚህ ውጪ ከፍርድ ቤት ውጪ በሚደረግ እርቅ ወይም ግልግል መሰረት ያለመግባባትን ያስቀሩ ወይም ለጉዳያቸው እልባት ያገኙ ሰዎች እርቁ ወይም ግልግሉ እንደተፈረደ ፍርድ ላቆጠርላቸው የሚገባ እና በውጤቱም በፍርድ ቤት ማስመዝገብ ወይም ማስፀደቅ ሳያስፈልገው ራሱን ችሎ ላፈጸም የሚችል ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 3312 እና 3324 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በመሆኑም ተጠሪ እርቁ ለሸሪዓ ፍርድ ቤት እንዲጸድቅ ያቀረቡት ማመልከቻ በሕጉ ያልተቀመጠውን ስርዓት መሰረት በማድረግና በአዋጅ ቁጥር 188/1992 አግባብም ለሸሪዓ ፍርድ ቤት ባልተሰጠው ሁኔታ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከላይ እንደተገለጸው የአሁኗ አመልካች በአካል ያልቀረቡ ከመሆኑም በላይ ተጠሪ በሕጉ አግባብ ተወክለው ጉዳዩ ያልታዬ ስለመሆኑ የክርክሩ ሂደት ያሳያል።
ይልቁንም አመልካች ያቀረቡት የእርቅ ስምምነት ይዘት አመልካች የማያውቁት እና በተጠሪ ተፅፎ የቀረበ ነው በማለት ለመቃወም አቤቱታ ማቅረቢያ መነሻ ያደረጉ መሆኑ ሲታይ ተጠሪ ነሐሴ 01 ቀን 2002 ዓ.ም ተደረገ የተባለውን ስምምነት በሸሪዓ ህግ መሰረት በሸሪዓ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ቀድመው ፈቃዳቸውን በአዋጁ አንቀጽ 2 (4)፣4 (5) እና 5 (1) ድንጋጌዎች አነጋገር መሰረት ሰጥተዋል ለማለት ሁሉ የማያስደፍር መሆኑን ከክርክሩ ሂደት ተገንዝበናል። ምክንያቱም አመልካች በሸሪዓ ፍርድ ቤት ለመዳኘት ፈቃደኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በአዋጅ ቁጥር 188/92 አንቀፅ 5 (1) እና ከአዋጁ ጋር በተያያዘው አባሪ (ፎርም) በመሙላት ማረጋገጥ እንደአለባቸው ሕጉ ያሳያል። ይህም የመከራከር መብትን በህጉ አግባብ ለማስከበርና ለማረጋገጥ የተዘረጋ ስርዓት መሆኑ የሚታመን ነው። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች በጉዳዩ ላይ ተደረገ የተባለው የእርቅ ስምምነት በልላ አግባብ ውጤት ከሚያገኝ በስተቀር በሸሪዓ ፍርድ ቤትም ሆነ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር በልለበት ሁኔታ ቀርቦ የሚጸድቅበት ሕጋዊ አግባብ የልለ በመሆኑ እርቁ መፅደቁ ከአዋጅ ቁጥር 188/1992 አንቀጽ 6 (1) እና ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 277 ድንጋጌዎች አንጻር ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለአገኘነው ተከታዩን ወስነናል።
በፍድራል ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 4595/04 የካቲት 17 ቀን 2003 ዓ.ም እና ህዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም ተሰጥቶ በፍድራል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 007/05 ታህሳስ 22 ቀን 2005 ዓ.ም በትእዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348 (1) መሰረት ተሽሯል።
በአመልካችና በተጠሪ መካከል ነሐሴ 01 ቀን 2002 ዓ.ም በውጪ አገር ተደረገ የተባለው ስምምነት በሸሪዓ ፍርድ ቤት በቀጥታ ቀርቦ የሚጸድቅበት አግባብ የለም ብለናል።
አመልካች ከተጠሪ ጋር በጋብቻ ተሳስረው የኖሩ ከሆነ ውጤቱንም ሆነ የልጅ አስተዳደግን በተመለከተ በሕጉ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ከመጠየቅና መብታቸውን ከማስከበር ተጠሪ ነሐሴ 01 ቀን 2002 ዓ.ም ተደረገ የሚሉት ስምምነት በሸሪዓ ፍርድ ቤት ጸድቋል ተብሎ ላከለከሉ አይገባም ብለናል። ተጠሪም ስምምነቱ በሸሪዓ ፍርድ ቤት ጸድቋል ከሚለው ነጥብ በመለስ ይህንኑ ስምምነት መሰረት አድርገው የሚያቀርቡትን ክርክር ይህ ውሳኔ አይከለክላቸውም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.