No summary available.
መጋቢት 28 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ፕሮፍሰር አደም ዓላ አህመድ ጠበቃ አስፋ ንጉሴ ቀረቡ ተጠሪ፡- አዳማ ጠቅላላ ሆስፒታልና ሜዲካል ኮልጅ ኃ/የተ/የግል ማህበር ጠበቃ አቶ በሻዳ ገመቹ ቀረቡ ጉዳዩን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል
ጉዳዩ የቀረበው አዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን ሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው።
ጉዳዩ የዳኝነት የስረ ነገር ስልጣንን የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ እንዲሁም አመልካች የተከሳሽ ከሳሽ ተጠሪ የከሳሽ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
አመልካች በተከሳሽነት ቀርበው እኔ ብር 35,000,000 /ሰላሳ አምሰት ሚላዮን ብር/ ለመክፈል በቂ ማስረጃ አለኝ።
ስለዚህ ከሳሽ ያቀረበው ክስ ከማህበር አባልነት ይሰረዝልኝ የሚል ቢሆንም የክርክሩ መሰረታዊ ጭብጥ ተከሳሽ ብር 35,000,000 /ሰላሳ አምስት ሚላዮን ብር/ ከፍሐል ወይስ አልከፈለም? የሚለው በመሆኑ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዚህ የገንዘብ መጠን ላይ አከራክሮ የመወሰን የስረ ነገር ስልጣን የለውም በማለት ተከራክረዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ሆስፒታሉ ስራ ሲጀምር በሜድካል ዳሬክተርነት አገኝ የነበረው በወር 40,000 በ1993-2000 ዓ.ም ብር 3,360,000 እና በስራ አስኪያጅነት የሰራ ጊዜዬንና አእምሮዬን በማጥፋት ለሰጠሁት አገልግሎት አበል ብር 5,000,000 ከነወለዱ የተከሳሽ ተከሳሽ እንዲከፍል ይወሰንልኝ በሶስተኛ ደረጃ መሬቱን መካከለኛ ሆስፒታል ለመገንባት 40,600 ካሬ ሜትር በአዳማ ከተማ አስተዳደር በግል የተሰጠኝ ነው። ሆስፒታሉ እንዲገነበባት የተስማማሁት የመሬቱ ባለይዞታ በመሆኔ፣ ተገምቶ ወደ ፊት ጥቅም የማገኝ መሆኑን ተወያይተን ስለተሰማማንበት ነው። አሁን ግን እኔ ሳላውቅ የባለይዞታነት መብቴ ተገፎ ወደ ከሳሽ ተከሳሽ የተዛወረ በመሆኑ ይዞታዬ በፍታብሕር ህግ ቁጥር 1179 መሰረት እንዲለቀቅ ይወሰንልኝ በማለት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ አቅርበዋል።
ተጠሪ ማህበሩ የሚፈርሰበት ህጋዊ ምክንያት የለም። የመሬት ካርታ ይሰርዝልኝ ጥያቄ በአስተዳደር የሚታይ እንጂ በፍርድ ቤት የሚታይ ጉዳይ አይደለም። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሽ ከሳሽ የጠየቁት የገንዘብ ጥያቄ አይቶ የመወሰን ስልጣን የለውም የሚል መከራከሪያዎችን አቅርቧል።
• የተከሳሽ ከሳሽ የከሳሽ ተከሳሽ ብር 8,360,000 /ስምንት ሚላዮን ሶስት መቶ ስልሣ ሺ ብር/ እንዲከፍለው ያቀረበው ጥያቄ ፍርድ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 14 ከተሰጠው ስልጣን በላይ በመሆኑ፣ ጉዳዩን አይቶ የመወሰን ስልጣን የለኝም • ማህበሩን መፍረስ በተመለከተ ጉዳዩን አይቶ የመወሰን ስልጣን አለኝ።
• የመሬቱ ይዞታ ከተከሳሽ ወደ ከሳሽ ተከሳሽ የተዛወረ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ለተከሳሽ ከሳሽ የተሰጠው የይዞታ የምስክር ወረቀት እንዲሰረዝና በተከሳሽ ስም የይዞታ የምስክር ወረቀት እንዲሰጥ የመወሰን የዳኝነት ስልጣን የለውም። በማለት ብይን ሰጥቶ በልሎች ነጥቦች ላይ የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ለመስማት ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት አመልካች ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበዋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ አመልካች በተከሳሽ ከሳሽነት የጠየቀው ብር 8,360,000 በስር ፍርድ ቤት የሚታይ ባለመሆኑ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ትዕዛዝ መሰጠቱ ተገቢ ነው። ተጠሪ በከሳሽነት ያቀረበው ከማህበር አባልነት ይሰርዝልኝ በማለት ስለሆነ የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት የስር ነገር ስልጣን አለው። የስር ፍርድ ቤት ማህበሩ የተመሰረተበትን መሬት ጉዳይ አይቶ የመወሰን ስልጣን የለኝም በማለት የሰጠው ብይን ተገቢ አይደለም። ስለዚህ አመልካች መሬቱን በተመለከተ ያቀረበው የዳኝነት ጥያቄ ማህበሩ እንዲፈርስ ካቀረበው ጥያቄ ጋር ታይቶ ውሣኔ ይሰጥበት በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።
አመልካች መስከረም 7 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብር 35‚000‚000 የተከፈለ መሆን አለመሆኑን የክርክሩ ጭብጥ የሆነበትን ጉዳይ የማየት ስልጣን አለው መባሉ ስህተት ነው። የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመልካች በተከሣሽ ከሣሽነት ያቀረቡት የገንዘብ ጥያቄ ተነጥሎ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት እንዲቀርብ በማለት የሰጠው ውሣኔ የተሣሣተ ነው። ስለመሬቱ የሰጠውን ውሣኔም ስህተት ያለበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክተዋል።
ተጠሪ በበኩሉ ታህሣስ 26 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በስልጣኔ ሥር ናቸው ባላቸው ጉዳዮች ውሣኔ ሣይሰጥ፣ የአመልካች ክርክር በይግባኝና በሰበር መስተናገዱ ስህተት ነው። አመልካች ያቀርቧቸው ክሶች ተለይተው ላቀርቡ የሚገባቸው ናቸው ስለዚህ ጉዳዩ የመጨረሻ ውሣኔ ከማግኘቱ በፊት ያቀረበው ክርክር በሕግ የተደነገገውን ስርአት የተከተለ አይደለም በማለት መልስ ሰጥቷል። አመልካች ጥር 21 ቀን 2005 ዓ.ም የሥር ፍርድ ቤት የከሣሽን ክስና አራት ራሣቸውን የቻሉ የዳኝነት ጥያቄዎችን የያዙ የተከሣሸ ከሣሽነት ክሶች ቀርበውለታል። ከዚህ አንፃር ሲታይ የሥር ፍርድ ቤት ብይን በጉዳዩ ላይ የሚሰጠውን የመጨረሻ ውሣኔ ላይ ውጤት ያለው በመሆኑ አመልካች ያቀረበው ይግባኝ እና የሰበር አቤቱታ የሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌውን የተከተለ ነው በማለት የመልስ መልስ ሰጥቷል።
6.1. ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን፣ በመጀመሪያ ለአዳማ ልዩ ዞን ተጠሪ ያቀረበው ክስና በአመልካች በኩል የቀረበው የተከሣሽነት ክስ ተጠሪ ከአመልካች የሚጠይቀውን የመብትና የዳኝነት ጥያቄ እና አመልካች ከተጠሪው የሚጠይቀውን የመብትና የዳኝነት ጥያቄ የያዙና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዩች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ሕግ አውጭው በከሣሽ በኩል ክስ የቀረበበት ተከሣሽ፣ ክሱን ለመከላከል ከሚያቀርበው መልስ በተጨማሪ ጉዳዩን እያየ ላለው ፍርድ ቤት የተከሣሽ ከሣሽነት ክስ ማቅረብ እንደሚችል በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ አንቀጽ 30/1/ አንቀጽ 324/1/ሀ እና በአንቀጽ 215/2/ የደነገገው፣ የከሣሸ ክስና የተከሣሸ ክስ የተከሣሽ ከሣሽነት ክስ በአንድ ላይ ተጠቃልለው ጉዳዮን የመወሰን ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት መታየታቸው፣ የተከራከሪዎቹንና የፍርድ ቤቱን ጊዜና ወጭ የሚቆጥብና ትክክለኛ ፍትሕ ላይ ለመደረስ፣ ጠቀሜታ እንዳለው በመገንዘብ ነው።
ተከሣሽ የተከሣሽ ከሣሽነት ክስ ካቀረበ ፍርድ ቤት ከቀረቡለት ጉዳዮች በሥረ ነገር ስልጣኑ ሥር ያሉትን መርጦ የማየትና ክሱ ከስረ ነገር ስልጣን በላይ የሆኑትን ጉዳዮች ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይቅረብ በማለት የከሣሽ ክስና የተከሣሽ ተከሣሽነት ክስ ተነጣጥለው እንዲታዩ ትእዛዝ መስጠት አይችልም። ምክንያቱም የከሣሽን ክስ ተቀብሎ ለመወሰን የሥረ ነገር ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት ጉዳዩን በማየት ላይ እያለ ተከሣሹ የተከሣሽ ከሣሽነት ክስ ካቀረበ የፍርድ ቤቱ የሥረ ነገር ስልጣን የሚወሰነው አንደኛው ወገን ያቀረበውን ከፍተኛ የሃብት ግምት መሰረት በማድረግ እንደሆነ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ 3 አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ተደንግጓል።
በያዝነው ጉዳይ የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ያቀረበውን ክስና አመልካች ያቀረበውን የተከሣሸ ከሣሽነት ክስ አጠቃልሎ ለማየት የሚያስችለው የሥረ ነገር ስልጣን የልለው በመሆኑና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ባቀረበው የተከሣሽ ከሣሽነት ክስ ውስጥ የብር 8‚360‚000 የዳኝነት ጥያቄ የያዘውን ጉዳይ አከራክሮ የመወሰን የሥረ ነገር ሥልጣን የለኝም፡ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይቅረብ በማለት ብይን ሰጥቷል። የሥር ፍርድ ቤት አመልካች ይህንን ጉዳዩ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት ነጥሎ እንዲያቀርብ የሚያስገድድ ብይን ሰጥቷል።
አመልካች የይግባኝ ቅሬታና የሰበር አቤቱታ ያቀረበው የሥር ፍርድ ቤት በከሣሽ ያቀረበውን ክስና በተከሣሸ የቀረበውን የተከሣሽ ከሣሽነት ክስ አጠቃልሎ ለመወሰን የሚያስችለው የሥር ነገር ስልጣን ከልለው መዝገቡን ዘግቶ ማስናበት እንጂ የተጠሪ ክስ እና እኔ ያቀረብኩት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ተነጣጥለው ግማሹ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግማሹ በልላ ፍርድ ቤት እንዲታይ ትዕዛዝ መስጠት አይችልም በማለት ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ የስር ፍርድ ቤት አመልካች ካቀረባቸው የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ውስጥ የተወሰኑትን የዳኝነት ስልጣን የለኝም በማለት የሰጠው ብይንና ከሳሽ ያቀረበውን ክስና አመልካች በተከሳሽ ከሳሽነት ከጠየቃቸው የተወሰኑትን ስልጣን አለኝ ብሎ ማከራከር መቀጠሉ ተጠሪ እንዲሚለው በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 320 ንዑስ አንቀጽ /3/ መሰረት ይግባኝ የማይባልበት ጊዚያዊ አገልግሎት ያለው ትዕዛዝ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። የስር ፍርድ ቤት ብይን ክስና የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ በቀረበበት ጉዳይ የፍርድ ቤቱ ስረ ነገር ስልጣን ስለሚወሰንበት ሁኔታ የተደነገገውን አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌ የሚጥስና ጉዳዩ ተነጣጥሎ በፍርድ ከማለቁ በፊት በይግባኝና በሰበር መታረም የሚገባው የዳኝነት የስረ ነገር ስልጣንን በተመለከተ ልዩ ባህሪና ውጤት ያለው የመጨረሻ ውሳኔ ነው። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ተጠሪ የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 320 ንዑስ አንቀጽ 3ን በመጥቀስ ያቀረበውን ክርክር አልተቀበልነውም።
ተጠሪ አመልካች ብር 35,000,000 የአባልነት መዋጮ የአክሲዮን ክፍያ ያልከፈለ ስለሆነ ከማህበር አባልነት ይሰረዝልኝ በማለት ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዳኝነት ጥያቄ አቅርቧል። የከሳሽ ክስ ተከሳሽ ከአባልነት ይሰረዛል ወይስ አይሰረዝም የሚል ጭብጥ የሚያስነሳ መሆኑን በመግለጽ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት የስረ ነገር ስልጣን አለው በማለት የስር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ብይን ሰጥተዋል። በልላ በኩል አመልካች ተጠሪ ብር 8,360,000 /ስምንት ሚላዮን ሶስት መቶ ስልሳ ሺ ብር/ ላከፍለኝ ይገባል የሚልና ልሎች የዳኝነት ጥያቄዎችን የያዘ የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ አቅርቧል።
የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በዳኝነት አይቶ የመወሰን ስልጣን አለው ወይስ የለውም የሚለው ጭብጥ የሚወሰነው ከተጠሪና አመልካች ካቀረቡት የዳኝነት ጥያቄ ከፍተኛ የኃብት ግምት ያለውን ማለትም አመልካች በተከሳሽ ከሳሽነት ክሱ የጠየቀውን ብር 8,360,000 መሰረት በማድረግ መሆን እንዳለበት የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 17 ንዑስ አንቀጽ 3 ተደንግጓል።
ከዚህ አንፃር ሲታይ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተጠሪን ክስም ሆነ የአመልካችን የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ አከራክሮ ለመወሰን የሚያስችለው የዳኝነት የስረ ነገር ስልጣን የልለው መሆኑ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 17 ንዑስ አንቀጽ 3 አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌ ተደንግጎ እያለ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተጠሪውን ክስና አመልካች በተከሳሽ ከሳሽነት ካቀረባቸው የዳኝነት ጥያቄዎች የተወሰኑትን በዳኝነት አይቶ የመወሰን የስረ ነገር ስልጣን አለኝ ልሎቹን ደግሞ የስረ ነገር ስልጣን የልለኝ በመሆኑ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት አመልካች ያቅርብ በማለት የሰጠው ብይን መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው። ጉዳዩን በይግባኝ ያየው የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ የተጠሪን ክስና የአመልካችን የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ አጠቃልሎ የማየት የስረ ነገር ስልጣን እንዲቀርብ በመወሰን የስር ፍርድ ቤት የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 17 ንዑስ አንቀጽ 3ን በመጣስ የፈፀመውን ስህተት ሳያርም ማለፍ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ግንቦት 3 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ብይንና የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምስራቅ ችሎት በመዝገብ ሰኔ 14 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ ተሸሯል።
የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተጠሪ የቀረበውን ክስም ሆነ በአመልካች ያቀረበውን የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ለማየት የሚያስችለው የስረ ነገር የዳኝነት ስልጣን የለውም በማለት በፍ/ስ/ስ/ህ/ሕግ ቁጥር 17/3/ መሰረት ወስነናል።
ጉዳዩ መታየት ያለበት የተጠሪን ክስና የአመልካችን የተከሳሻ ከሳሽነት ክስ አጠቃልሎ ለማየትና ውሣኔ ለመስጠት የስረ ነገር ስልጣን ያለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሆኑ፣ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገቡን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላልፍለት በማለት ወስነናል።
አመልካች የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን መሰረት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ ሲያቀርብ የከፈለው የዳኝነት ገንዘብ በደንቡ መሰረት ተቀንሶ ተመልሶለት ከሆነ፣ በሕጉ መሰረት የዳኝነት ገንዘቡን እንዲከፍል ላደረግ ይገባል ብለናል። ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ። መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.