No summary available.
ሰኔ 3 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶልሣ ሙስጠፋ አሕመድ አመልካቾች፡-
ጉዳይ የቀረበው አመልካች የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገብ ሰኔ 4 ቀን 2004 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የውርስ ንብረት በአንደኛው ወራሽ ስም እንዲመዘገብ የቀረበን ክርክር የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በስዮ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው። በወረዳው ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሣሽ የደንቢ ዶሎ ማዘጋጃ ቤት ተከሣሽ ተጠሪዎች ደግሞ ጣልቃ ገብ ተከራካሪዎች ሆነው ቀርበው ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ያቀረበው ክስ ነው። ተጠሪ ከአባቱ በውርስ ያገኘሁት ቤት ስመ ንብረቱን እንዲያዛውርልኝ ተከሣሹ /የደንቢ ዶሎ ማዘጋጃ ቤት/ ስጠይቀው ስም ለማዛወር እንቢተኛ ስለሆነ ስመሀብቱን እንዲያዛውር ውሣኔ ይሰጥኝ በማለት ለወረዳው ፍርድ ቤት ክስ አቅርቧል። በሥር ተከሣሽ የነበረው የደንቢ ዶሎ ማዘጋጃ ቤት ግብር የተከፈለው በሟች አቶ ገመቹ ገዳም ወራሾች ስም በመሆኑና አንደኛ አመልካች ወ/ሮ አልማዝ ገመቹ/ የቤቱ ስመ ሀብት ወደ ተከሣሽ እንዳይዛወር ያመለከቱ በመሆኑና ስም አላዛወርኩም የሚል ክርክር አቅርቧል። አመልካቾች ጣልቃ ገብ ተከራካሪ ሆነው ቀርበው ቤቱ በወራሾች ስም ግብር የሚከፍልበት እና በሽማግል ዳኞች ወራሾች እንድንካፈለው በ1992 ውሣኔ የተሰጠበት እና በ1998 ዓ.ም የእርቅ ስምምነት የፈፀምንበት የሟች ወራሾች የጋራ ሀብት በመሆኑ ወደ ከሣሽ ስም ላዛወር አይገባም የሚል ክርክር አቅርበዋል።
የወረዳው ፍርድ ቤት ተጠሪና አመልካቾች በሚከራከሩበት ቤት ላይ የተጠሪዎች ጥያቄ በይርጋ ቀሪ እንደሚሆን ከዚህ በፊት ውሣኔ ተሰጥቶበታል ስለዚህ የቤቱ ስመሃብት ወደ ከሣሽ /ተጠሪ/ እንዲዛወር ለተከሣሹ ደንቢዶሎ ማዘጋጃ ቤት ይፃፍ በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል። አመልካቾች በዚህ ትእዛዝ ቅር በመሰኘት ለቄለም ወለጋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ቤቱ ያልተከፋፈለ የውርስ ንብረት እንደሆነ በመግለጽ የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ ሽሮታል።
ተጠሪ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል። ይግባኝ ሰሚው ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ የአሁን አመልካቾች ተጠሪ የያዘውን ያልተከፋፈለ የውርስ ንብረት የወረዳው ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 99/90 የካቲት 10 ቀን 1992 ዓ.ም በሰጠው ውሣኔ መሰረት እንዲያካፍለን የሚል የአፈፃፀም ክስ በመዝገብ አቅርበው ነበረ ተጠሪ በበኩሉ የአፈፃፀም ክስ ያቀረበው በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 384 የተደረገው የአስር ዓመት የይርጋ የጊዜ ገደብ ካለፈ በኃላ በመሆኑ የአፈፃፀም ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት ተከራከሯል። የወረዳው ፍርድ ቤትም አመልካቾች /ይግባኝ ባይዎችና/ እና መልስ ሰጭ /ተጠሪ/ በመዝገብ ያቀረቡትን ክርክር በመመርመር አመልካቾች ያቀረቡት የአፈፃፀም ክስ በአስር ዓመት የይርጋ ጊዜ ገደብ የሚታገድ መሆኑን ገልፆ ታህሣስ 4 ቀን 2003 ዓ.ም ውሣኔ ሰጥቷል። ይግባኝ ባዮች /አመልካች/ በዚህ መዝገብ በተሰጠው ውሣኔ ላይ ይግባኝ አላቀረቡም። ይግባኝ ባዮች በመዝገብ የተሰጠውን ውሣኔ ለማሻር የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 323/2/ በልሎች ድንጋጌዎች መሰረት ይግባኝ ሣያቀርቡ ተጠሪ የደንቢ ዶሎ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በወረዳው ፍርድ ቤት በመዝገብ ሀምል 11 ቀን 2003 ዓ.ም በሰጠው ትእዛዝ ባቀረቡት ይግባኝ በመዝገብ የተሰጠውን ውሣኔ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሻሩ የሥነ ሥርዓት ሕጉን የተከተለ አይደለም በማለት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ በመሻር የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን ትእዛዝ አጽንቶታል። አመልካች የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበዋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የልለበት ነው በማለት ወስኗል።
አመልካች ጳጉሜ 2 ቀን 2002 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ የቤቱ ባለቤትነትና ግብር ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ በወራሾች ስም የሚከፈል መሆኑን ተጠሪ በማመን ተከራክሯል። አመልካቾች በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 1060/1/ መሰረት የንብረቱ የጋራ ባለሃብት ናቸው። አመልካቾች በመዝገብ ያቀረቡት የአፈፃፀም ክስ በአስር አመት ይርጋ ቀሪ ነው መባሉ ተጠሪን ብቸኛ የቤቱ ባለሃብት እያደርገውም። አመልካቾች በፍታብሕር ሕግ ቁጥር 1168 መሰረት ለተከታታይ አስራ አምስት ዓመት ግብር የገበሩ በመሆናቸው የቤቱ ባለሃብት ናቸው። በማይንቀሣቀስ ንብረት ላይ የሚቀርብ ክስ በይርጋ ቀሪ እንደማይሆን ይኸ ሰበር ችሎት በመዝገብ ጥር 5 ቀን 2002 ዓ.ም አስገዳጅ ትርጉም ሰጥቶበታል። ስለዚህ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት የሰጡት ውሣኔ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት አመልክተዋል።
ተጠሪ ሕዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካች ቤቱን እንዲያካፍላቸው የአፈፃፀም ክስ አቅርበው ጥያቄቸው በይርጋ ቀሪ ነው ተብሎ በመዝገብ ውድቅ ተደርጎባቸዋል።አመልካቾች በሕግ በተደነገገው መሰረት ይህንን ውሣኔ በይግባኝ አላሻሩም አመልካች ይህንን ውሣኔ በይግባኝ እንዲለወጥ ወይም እንዲሻር ሣያደርጉ ቤቱ የጋራ ሃብታችን ነው በተጠሪ ስም ላዛወር አይገባም ብለው ለመከራከር የሚችሉበት የሕግ መሰረት የለም። ስለዚህ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል። አመልካቾች ታህሣስ 9 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርበዋል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና ሰበር ችሎት ግራ ቀኙ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት የአመልካቾችን ክርክር ውድቅ ያደረጉት በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካችና ተጠሪ የሟች አባታቸው የአቶ ገመቹ ገዳም የውርስ ንብረት ክፍል የሆነው ቤት የጋራ ወራሾች መሆናቸው አከራካሪ አይደለም። እንደዚሁም በሟች ወራሾች ስም በጋራ ለቤቱ ግብር ሲከፈል የቆየ መሆኑም ግራ ቀኙ አልተካካዱበትም በዚህ መዝገብ እያከራከረ ያለው ጉዳይ አመልካቾች በወራሽነታቸው በቤቱ ላይ ያረጋገጡት የወራሽነት መብት ያለ መሆኑ ወይም አለመሆኑ አይደለም። አከራካሪ የሆነው አመልካቾች በንብረቱ ላይ ያላቸውን ያልተከፋፈል የጋራ ባለሃብትነት ለማስፈፀም አቅርበውት የነበረውን የአፈፃፀም ክስና በአፈፃፀም ክሱ ላይ የተሰጠውን ውሣኔ ይግባኝ ቀርቦበት ሣይሻር ፣ሣይለወጥ ወይም ሣይሻሻል መቅረቱ አመልካቾች በቤቱ ላይ የሚያነሱት የመብት ጥያቄና ክርክር ላይ ምን አይነት ሕጋዊ ውጤት ይኖረዋል የሚለው የሥነ ሥርዓት ጉዳይ ነው።
አመልካቾች በተጠሪ ይዞታ ሥር የነበረው የማይንቀሣቀስ የውርስ ንብረት /ቤት/ የወረዳው ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 99/90 የካቲት 10 ቀን 1992 ዓ.ም በሰጠው ውሣኔ መሰረት ለሶስት እኩል እንዲያካፍላቸው ፍርድ ቤቱ የአፈፃፀም ትእዛዝ እንዲሰጥላቸው በመዝገብ የአፈፃፀም ክስ አቅርበው የነበረ መሆኑን ተረጋግጧል። ተጠሪ በዚህ መዝገብ አመልካቾች ያቀረቡት የአፈፃፀም ክስ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 384 የተደነገገው የአሥር ዓመት የይርጋ የጊዜ ገደብ ካለፈ በኃላ ነው ስለዚህ በይርጋ ቀሪ ነው የሚል ክርክር አቅርቦ የወረዳው ፍርድ ቤት አመልካቾች በመዝገብ ያቀረቡት የአፈፃፀም ክስ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት ታህሣስ 4 ቀን 2003 ዓ.ም በሰጠው ውሣኔ ዘግቶታል። አመልካቾች በህጉ በተደነገገው የጊዜ ገደብ ውስጥ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት የይግባኝ ቅሬታቸውን በማቅረብ ወደ ይኽ ውሳኔ እንዲሻር ፣እነዲለወጥ ወይም እንዲሻሻል አላደረጉም። ስለሆነም በመዝገብ ታህሳስ 4 ቀን 2003 ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ አመልካቾች በቤቱ ላይ ያላቸውን የወራሽነት መብት በፍርድ ለማስፈፀም በሕግ በተደነገገው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለማቅረባቸው ተጠሪ ቤቱን እንዲያካፍላቸው የመጠየቅ መብታቸውን በይርጋ ቀሪ የሚሆን በመሆኑ ጉዳዩ ላይ የተሰጠ የመጨረሻ አስገዳጅነት ያለው ውሣኔ ነው።
አመልካቾች በቤቱ ላይ ያላቸው መብት በፍርድ ሃይል እንዲፈፀም ለመጠየቅና ለመከራከር የማይችሉና ጥያቄያቸው በይርጋ ቀሪ እንደሆነ በመዝገብ ታህሣስ 4 ቀን 2003 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ አንቀጽ 320/1/፣ አንቀጽ 324፣ አንቀጽ 327 እና በልሎች ድንጋጌዎች መሰረት ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አቅርበው ሣያሽሩ ተጠሪ በውርስ በተገኘው ቤት ላይ በፍርድ ላፈፀም የሚችል መብት ያለኝ እኔ ብቻ ነኝ ስለዚህ የደንቢ ዶሎ ማዘጋጃ ቤት ስመ ሃብቱን እንዲያዛውር ውሣኔ ይሰጥልኝ በማለት ያቀረበውን ክስ በመቃወም ጣልቃ ገብ ተከራካሪ የሚሆኑበት በሕግ ፊት የፀናና ላፈፀም የሚችል መብትና ጥቅም የላቸውም። የወረዳው ፍ/ቤት የአመልካቾች በቤቱ ላይ አለን የሚሉት መብት በፍ/ቤት ውሣኔ /ትእዛዝ/ እንዲፈፀም ጥያቄ ላያቀርቡበት የማይችሉና የይርጋ የጊዜ ገደብ ያለፈበት መሆኑ ቀደም ሲል መወሰኑን ገልፆ የአመልካቾችን ክርክር በመዝገብ ሐምል 11 ቀን 2003 ዓ.ም ውድቅ አድርጓል።
አመልካቾች በዚህ መዝገብ የተሰጠውን ብይን መነሻ በማድረግ በውጤት ደረጃ በመዝገብ ታህሣስ 4 ቀን 2003 ዓ.ም የተሰጠው ውሣኔ በመቃወም ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ የይግባኝ ቅሬታ አቅርበዋል። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካቾች በመዝገብ የተሰጠውን ውሣኔ በይግባኝ ለማሻር ወይም ለማስለወጥ የሥነ ሥርዓት ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ይግባኝ ያላቀረቡ መሆኑን ሳያገናዝብ በመዝገብ በተሰጠው ትእዛዝ ያቀረበውን ይግባኝ መነሻ በማድረግ በመዝገብ የተሰጠውን ውሣኔ ሙሉ በመሉ የሚሽርና ውጤት አልባ የሚያደርግ ውሣኔ መስጠቱ ፍርድ ቤቶች የሰጡት ፍርድ በይግባኝ እና በሰበር ለማሣረም ላውሉ የሚገቡ አስገዳጅ ሥርዓቶችን ያልተከተለና አንድ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ በሕግ በተደነገገው ሥርዓት መሰረት በይግባኝ በልላ ሥርዓት ወይም በሰበር ካልታረመ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻና አስገዳጅነት ያለው ውሣኔ ነው የውሣኔው አስገዳጅነትና ተፈፃሚነት በባለጉዳዮች ላይ ብቻ የተወሰነ ሣይሆን በማናቸውም አስፈፃሚ አካልና ማናቸውም ፍርድ ቤት የሚመለከት እንደሆነ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 5/1/ ፣በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 79 ንዑስ አንቀጽ 2 የተካተተውን መሰረታዊ መርህ የሚጥስ ነው።
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወረዳው ፍርድ ቤት በመዝገብ በሰጠው ትእዛዝ መነሻ አመልካቾች በፍታብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 320/1/ አንቀጽ 324፣ አንቀጽ 327 እና ልሎች ድንጋጌዎች መሰረት የይግባኝ ቅሬታ ያላቀረቡበትንና በጉዳዩ ላይ የመጨረሻና አስገዳጅነት ያለውን የወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ የሰጠውን ውሣኔ በይግባኝ መዝገብ መሻሩ የሕግ መሰረት የልለው ነው። አመልካቾች በዚህ መዝገብ የጠቀሷቸውን የፍታብሕር ሕግ ቁጥር 1060፣ የፍታብሕር ሕግ ቁጥር 1168፣ እና ልሎች ድንጋጌዎች ይዘትና ትርጉም በመተንተን የይግባኝ ቅሬታ በማቅረብ ለማስለወጥ ወይም ለማሻር በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 324 በተደነገገው የጊዜ ገደብ ውስጥ የይግባኝ ቅሬታ ማቅረብ የነበራቸው የወረዳው ፍርድ ቤት በመዝገብ ታህሣስ 4 ቀን 2003 ዓ.ም በሰጠው ውሣኔ ላይ ነበር። አመልካቾች በዚህ ውሣኔ ላይ ይግባኝ በማቅረብ ውሣኔውን አላስለወጡም ወይም አላሻሩም
በመዝገቡ የተሰጠው ውሣኔ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ታይቶ ባልተሻረበት ወይም ባለተለወጠበት ሁኔታ የወረዳው ፍርድ ቤት በመዝገብ ሐምል 11 ቀን 2003 ዓ.ም የሰጠውን ትእዛዝ መነሻ በማድረግ በቀረበው ይግባኝ በመዝገብ የተሰጠው ውሣኔ ህጋዊ ውጤትና ተፈፃሚነት ላኖረው አይገባም በማለት ያቀረቡት ክርክር ከላይ የገለጽናቸውን የፍርድ ቤቶች ውሣኔ አስገዳጅነትና ተፈፃሚነት መርህንና አስገዳጅ የሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች እና የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 5/1/ የሚጥስ ነው። ስለሆነም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት ከላይ የገለጽናቸውን ሥነ ሥርዓታዊ ምክንያቶችንና መሰረታዊ የዳኝነት ሥራ አካሄድ መርሆች መሰረት በማድረግ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሣኔ መሻራቸውና የአመልካቾች ክርክር ውድቅ ማድረጋቸው መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የሰበር ችሎት የሰጡት ውሣኔ ፀንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ በየየራሣቸውን ይቻሉ።
No topics extracted.