No summary available.
መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡-
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በጋብቻ ውጤት በሆኑ ንብረቶች ላይ በአንደኛው ተጋቢ የተደረጉ የሽያጭ ውሎች የሚፈርሱበትን አግባብ የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን በዚህ ፍርድ ቤት ከሣሽ የነበሩት የአሁኗ ተጠሪ ናቸው። ተከሣሽ ደግሞ የአሁኑ አመልካቾች ነበሩ። ተጠሪ በአመልካቾች በመሰረቱት ክስ ከአሁኑ አንደኛ አመልካች ጋር በጋብቻ ተሳስረው ቆይተው በመካከላቸው በተፈጠረው ያለመግባባት ጋብቻው እንዲፈርስ በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበው የጋብቻ ውጤት የሆኑት ንብረቶችን ለማስከበር የፍርድ ቤት ትእዛዝ ይዘው ወደሚመለከታቸው አካላት ሲሄዱ ንብረቶቹ በሶስተኛ ወገኖች ስም የሚታወቁና በሽያጭ የተላለፉ መሆኑን የእግድ ትእዛዙን ይዘውላቸው የሄዱባቸው አካላት እንደገለፁላቸው ንብረቶቹን ባል የሆኑት አንደኛ አመልካች ከሕግ ውጪ ለብቻ ልጆቻቸው ከተጠሪ እውቅና ውጪ ያስተላለፉ መሆኑንና የተላለፉትን ንብረቶችንም፡- በአዲስ አበባ ከተማ በአ/ክ/ከተማ በቀበል 19/2ዐ የቤት ቁጥር 816 በሆነው ቤት በ1ኛ አመልካችና ከወ/ሮ ብርቱካን በላይ ጋር፣ በአዲስ አበባ ከተማ በአራዳ ክፍለ ከተማ በቀበል ዐ1/ዐ2 በሚገኘውና ቁጥሩ KH-B2 B104 በሆነው ኮንዶሚኒየም ቤት ከወ/ሪት ዜኒት ኢድሪስ ጋር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ቦል ክፍለ ከተማ በወረዳ 2 የሚገኘውና ቁጥር GEB1 Co/04 ከሆነው ኮንዶሚኒየም ቤት ከአቶ አንዋር ኢድሪስ ጋር፣ የሰልዳ ቁጥር 2-52682 በሆነችው የቤት መኪና ላይ ከወ/ሪት ዜኒት ኢድሪስ ጋር፣ የሰልዳ ቁጥር 3-46778 ኢት በሆነው የጭነት መኪና ከወ/ሮ ዜኒት እንድሪስ ጋር የሰልዳ ቁጥር 2-42462 አ.አ በሆነችው የቤት መኪና ከካሜል ኤድሪስ ጋር እና የሰልዳ ቁጥር 3-ዐ6469 የሆነ ከባድ መኪና ከአቶ አንዋር ኢድሪስ ጋር በተደረጉት የማስመሰያ የሽያጭ ውል እንደተላለፉ በገዥነት የተመዘገቡት የትኞቹ የባል ልጆች እንደሆኑ ለይተው ስማቸውን ገልፀው በንብረቶቹ የተደረጉ ውሎች እንዲፈርሱና ንብረቶቹ በቀድሞው ሁኔታ እንዲመዘገቡ እና ውጪ ኪሣራ እንዲወሰንላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል። የአሁኑ 1ኛ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስም ከተጠሪ ጋር ጋብቻ መኖሩን አምነው ተፈጠረ የተባለውን ያለመግባባት ወይም ጠብ ግን እንደማያውቁትና ተጠሪ ጋብቻው እንዲፈርስ በፍርድ ቤት ክስ መሥርተው ያሉ መሆኑን ለክርክሩ ምክንያት የሆኑት ንብረቶች በሽያጭ ውሉ ለልሎች አመልካቾች ያስተላለፉት ከተጠሪ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ወደ መጥፎ ሁኔታ ከመቀየሩ በፊት ከተጠሪ በቁጥር 59ዐ4/13/2ዐዐዐ ግንቦት 25 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም በተሰጣቸው የውክልና ሥልጣን መሰረት መሆኑንና የሽያጭ ውሎቹ መደረጋቸውንም ተጠሪ ያውቁ እንደነበር ገልፀው የሽያጭ ውሎችም ላፈርሱ አይገባም በማለት ተከራክረዋል። የአሁኑ 2ኛ፣ 3ኛ እና 5ኛ አመልካቾች በጋራ በሰጡት መልስም ለክርክሩ ምክንያት የሆኑነት ንብረቶችን ተጠሪ በወኪላቸው አንደኛ አመልካች አማካኝነት በሽያጭ ውሉ ላይ ፈቃዳቸውን የሰጡ በመሆኑ የተሻሻለውን የፍድራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 68 እና 69 ድንጋጌዎችን በመጥቀስ ክርክር ላያደርጉባቸው እንደማይችሉ ጠቅሰው ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል። የአሁኑ 4ኛ አመልካች በበኩላቸው በግል የመከላከያ መልሣቸውን ያቀረቡ ሲሆን በአቀረቡት መልስም አመልካቹ ገዙ የተባለውን መኪና ከተጠሪ ሕጋዊ ወኪላቸው የአሁኑ አንደኛ አመልካች የገዙትና የሽያጭ ውሉ ገዢው የወኪሉ ልጅ በመሆናቸው ብቻ ላፈርስ እንደማይገባ ገልፀው ተከራክረዋል። ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ንብረቶቹ የጋብቻ ውጤት መሆናቸውና የአሁኑ አንደኛ አመልካች ከተጠሪ በተሰጣቸው ውክልና መነሻ ገቢና መተዳደሪያ ለልላቸው ለአሁኑ አንደኛ አመልካች የብቻ ልጆች ለሆኑት ከተራ ቁጥር ሁለት እስከ ተራ ቁጥር አምስት ድረስ ለተጠቀሱት አመልካቾች መሸጡ መረጋገጡንና አንደኛ አመልካች አንድ ወኪል በሕጉ የተጣለበትን ግድታ አክብረው ሽያጩን አከናውነዋል ለማለት የሚቻልበት አግባብ የልለ መሆኑን ከክርክሩ መገንዘቡና እንዲህ አይነት የወኪል ተግባር ደግሞ ሕጋዊ ያለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁጥር 2208፣ 2209 እና 2188 ድንጋጌዎች እንደሚያስረዱ በመጥቀስ በንብረቶቹ ላይ የተደረጉት ሽያጮች እንዲፈርሱና ወደ ነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ሲል ወስኗል። በዚህ ውሳኔ አመላክቾች ቅር በመሰኘት የአሁኑ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 4 የተጠቀሱት በይ/መ/ የአሁኗ 5ኛ አመልካች ደግሞ በይ/መ/ ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ መዝገቦችን አጣምሮ ከተመለከተና ከመመርመረ በኋላ አከራካሪ ንብረቶችን አንደኛ አመልካች ከተጠሪ ጋር ወደ አለመግባባት ከገቡ በኋላ መተዳደሪያ ለልላቸው ተማሪ ለሆኑት አንዳንዶቹ ለአቅመ አዳም እንኳን ላልደረሱ ልጆቻቸው በአፋጣኝ የሸጡ መሆናቸውን መገንዘቡን በውሳኔ ላይ ከአሰፈረና ይህም አንደኛ አመልካች ንብረቶቹን ከቅን ልቦና ውጪ ለብቻቸው ለመጠቀም በማሰብ ያደረጉት ዘድ መሆኑን ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ መሆኑን ጠቅሶ የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ተገቢ ነው ብሎ ሙሉ በሙሉ አንፅንቷል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም አንደኛ አመልካችና ተጠሪ ወደ አሜሪካ ሀገር ለመሄድ ለመኖር በማሰብ በአደረጉት ስምምነት መሰረት ተጠሪ ከአመልካቹ ውክልና ሰጥተው ንብረቶቹን አመልካች በውክልና ስልጣናቸው መሸጣቸው የማይካድ ሀቅ ሆኖ እያለ ሐቁ ተገቢው ጭብጥ ተይዞ በተገቢው የክርክር አመራርና ማስረጃ ሳይጣራ ንብረቶቹ ለአንደኛ አመልካች ልጆች በመሸጣቸው ምክንያት ብቻ የሽያጭ ውሎቹ እንዲፈርሱ መደረጉ ያላግባብ ነው የሚል ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ላታይ የሚገባው መሆኑ ታምኖበት ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው የተጠሪ ጠበቃ ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆኑት ውሳኔዎች እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም በጉዳይ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ለማለት ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሆኖ ተገኝቷል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አንደኛ አመልካችን ተጠሪ ለረዥም አመታት በባልና ሚስት ሲኖሩ በሽያጭ ውሉ ተላለፉ የተባሉትን ንብረቶችን በጋራ ያፈሩ መሆኑን፣ በመካከላቸው በተፈጠረው ያለመግባባትም ተጠሪ የፍቺ ጥያቄ ለፍርድ ቤት አቅርበው ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ እንዳለ ንብረቶችን ለማስከበር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ንብረቶቹ ከፍቃዳቸው ውጪ መሸጣቸውን አውቀው ሽያጭ ውሎቹ እንዲፈርሱላቸው ለዚህ ሰበር ክርክር መነሻ የሆነውን ውሳኔ ለሰጠው ፍርድ ቤት ክስ ማቅረባቸውን፣ ንብረቶቹን ከአንደኛ አመልካች ገዙ የተባሉት የአሁኑ ከተራ ቁጥር ሁለት እስከ አምስት ያሉት አመልካቾች ደግሞ የአሁኑ የብቻ ልጆች ሆነው የራሳቸው መተዳደሪያ የልላቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ለአቅመ አዳም እንኳን ያልደረሱ መሆኑን ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የፍድራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በውሳኔ ላይ መግለፁን፣ ንብረቶቹን የተጠሪ ባል የሆኑት የአሁኑ አመልካች ለልጆቻቸው ለመሸጥ ስልጣን ያገኙት ከተጠሪ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ/ም በተሰጠው ስልጣን ቢሆንም ንብረቶቹ የተሸጡት ከተጠሪ ጋር ያለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ በአፋጣኝ ስለመሆኑ ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ማረጋገጡን ነው። አንደኛ አመልካች በዚህ የክርክር ደረጃ አጥብቀው የሚከራከሩት ከተጠሪ ጋር አሜሪካን አገር ለመኖር በማሰብ ንብረቶቹ መሸጣቸውንም ተጠሪ ያውቁ እንደነበር ገልፀው ተከራክረው ከአመልካች ልጆች ውስጥ የራሳቸው ገቢና መተዳደሪያ ያላቸው ሁሉ እያሉ ይሕው ሳይጣራ ተገቢ ያልሆነ የክርክር አመራር በስር ፍ/ቤት ተከናውኖ ውሳኔ መሰጠቱ ሐቁ እንዳይወጣ ሆኗል፣ ተጠሪ ባሁኑ ጊዜ የሚኖሩት አሜሪካን አገር መሆኑም ከአመልካቹ ጋር የነበራቸውን የቀደመ ሐሳብ የሚያረጋግጥ ነው በሚል ሲሆን ልሎች አመልካቾች ደግሞ ሽያጩ በተጠሪ እውቅና የተደረገ ሆኖ እያለ ፈራሽ ነው ተብሎ መወሰኑ ያለግባብ ነው በሚል ነው። የፍድራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያለው ችሎት ሲሆን ንብረቶቹ አንደኛ አመልካችና የአሁኗ ተጠሪ በመካከላቸው ያለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ በአፋጣኝ ለአሁኑ አንደኛ አመልካች ልጆች ለሆኑትና የራሳቸው መተዳደሪያ ገቢ ለልላቸው ጭምር መሸጣቸው ከክርክሩ ሂደት መገንዘቡን በውሳኔ ላይ አስፍሯል። ይህ የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የፍሬ ነገር ድምዳሜ ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ከደረሰበት ድምዳሜ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሲሆን ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች ከተሰጠው የመሰረታዊ ሕግ ስህተት የማረም ስልጣን አንፃር ሲታይ የበታች ፍ/ቤቶች በፍሬ ነገር ደረጃ ድምዳሜ የያዙት ጉዳይ የሚለወጥበት አግባብ የለም። በመሆኑም አንደኛ አመልካች ንብረቶቹን ከተጠሪ ጋር ያለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ በአፋጣኝ መሸጣቸው በፍሬ ነገር ደረጃ ከተረጋገጠ ንብረቶቹን ሸጥኩ የሚሉበት ምክንያት አሜሪካን አገር ለመኖር ከተጠሪ ጋር ባደረጉት ስምምነት ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በማስረጃ እንዲነጥር ያለመደረጉ ለጉዳዩ አወሳሰን መሰረታዊ ጠቀሜታ የልለው ነው። በአንድ የፍትሃ ብሕር ክርክር ማስረጃ የሚሰማውና ፍሬ ነገሩ እንዲነጥር የሚደረገውም በማስረጃ የሚነጥረው ፍሬ ነገር ለዳኝነት አሰጣጡ እጅጉን አስፈላጊና የግድ ሆኖ ሲገኝ ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 136፣ 137፣ 138፣ 246፣ 247፣ 248፣ 256፣ እና ልሎች ስለማስረጃ አቀራረብና አመዛዘን ከሚደነግጉት ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በልላ አገላለፅ ማንኛውም የክርክር ነጥብ ሁልጊዜ በማስረጃ እንዲነጥር የሚደረግበት አግባብ የለም። ማስረጃ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ሆኖ ተከራከሪ ወገኖች በተለያዩባቸውና ዳኝነት በሚሹ ነጥቦች ላይ ከሚሰማ በስተቀር በማንኛውም ፍሬ ነገር ላይ እንዲሰማ የግድ የሚል የማስረጃ አቀራረብና አመዛዘን ደንብ የለም። ከሁሉም በላይ ማስረጃ እንዲሰማ የሚፈልግ ተከራካሪ ወገን ማስረጃው የሚሰማበት ነጥብ ለይቶ የማስረጃውን አይነትና የሚገኝበትን ቦታ ሁሉ በመጥቀስና በእጁ ላይ ያለውን ማስረጃውም አያይዞ ማቅረብ እንዳለበት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 223፣ 234፣ 137(3)፣ 145፣ 256 እና ልሎች ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያሳያል።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም 1ኛ አመልካች በስር ፍ/ቤት የመከላከያ ማስረጃ ጥር 25 ቀን 2003 ዓ/ም ዘርዝረው ሲያቀርቡ በመልስ ማመልከቻው ውስጥ የዘረዘራቸው ፍሬ ነገሮችን የሚያውቁና የሚያስረዱ ሶስት የሰው ምስክሮችን ዘርዝረዋል። ይሁን እንጂ ምስክሮቻቸው የተሰሙ ስለመሆኑ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ግልባጭ የማያሳይ ቢሆንም ከላይ እንደተገለጸው ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ንብረቶቹ የተሸጡበት ተጠሪ ከአመልካች ጋር ወደ ያለመግባባቱ ከገቡ በኋላ በተፋጠነ ሁኔታ መሆኑ ከረጋገጡ አንፃር ሲታይ የአመልካች ምስክሮች ያለመሰማት መሰረታዊ የመሰማት መብትን አጣብቧል ለማለት የሚያስችል ሆኖ አላኘነውም። ተጠሪ የውክልና ውሉን መሰረት አድርገው ክስ ያለመመስረታቸውም በክርክሩ ሂደት አመልካቾች በመከላከያነት ክርክር እስካቀረቡ ድረስ ፍ/ቤቱ ውክልናውን ተከትሎ የተፈፀመውን ተግባር ሕጋዊ መሆን ያለመሆኑን ከመመርመርና ተገቢውን ዳኝነት ከመስጠት የሚያገደው አይደለም። ይልቁንም ውክልናው መኖሩን የበታች ፍርድ ቤቶች አረጋግጠው ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎችን በመለየት ዳኝነት መስጠታቸውን የክርክሩ ሒደት የሚያሳይ በመሆኑ ተጠሪ ክስ ሲመሰርቱ ውክልናን ጠቅሰው ያለማቅረባቸው በክርክር አመራሩና ዳኝነት አሰጣጥ ውጤት ላይ መሰረታዊ የሕግ ግድፈት አስከትሐል ለማለት የሚያስችል አይደለም። ልላው አንደኛ አመልካች ንብረቶቹን ለብቻ ልጆቻቸው የሸጡ መሆኑን ሳይክዱ አንድ ተወካይ ላወጣ የሚገባውን ሕጋዊ ግድታ ተወጥተው ንብረቶቹን የሸጡ ስለመሆኑ ጠቋሚ ላሆኑ የሚችሉትን የንብረቶቹን የገበያ ዋጋ ለንጽጽር እንኳን ጠቅሰው እሰከዚህ ሰበር ደረጃ በአቀረቡት ክርክር ያለመጥቀሳቸው ሲታይም የአመልካቾች የማስረጃ ያለመሰማት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የማያስችል አስፈላጊ ፍሬ ነገር አልተሟላም ለማለት የማያስደፍር መሆኑን የሚያስገነዝብ ሁኖ ተገኝቷል።
አንደኛ አመልካች ንብረቶቹ ተሸጡ በተባለባቸው ጊዜያት የተጠሪ ባልና ተወካይ መሆናቸው ተረጋግጧል።
ተወካዩ ከወካዩ ጋር የሚያሰተሳስረው ግንኙነት ውስጥ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና ላኖረው እንደሚገባ በፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 2208(1) ስር ተደንግጓል ። ከዚህ በተጨማሪ ተወካዩ የተወካይነት ሥራውን የሚፈጽመው በተለይ የወካዩን ጥቅም ላሰጥ በሚችልበት መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 2209 (1) ድንጋጌ ያሳያል። ከዚህም በተጨማሪ ተወካዩ በውክልና ሥራው ላይ በሚገኝባቸው ጊዜዎች ሁሉ በውክልና በተሰጠው አደራ አንድ መልካም የቤተሰብ አባት ቤተሰቡን ለመጠበቅ እንደሚያደርገው ሁሉ በትጋትና በጥንቃቄ መጠበቅ ያለበት መሆኑን በፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 2211(1) ስር በግልጽ ተደንግጓል። አንደኛ አመልካች ከላይ በጠቀስናቸው አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌዎች የተጣለባቸውን ግድታና ኃላፊነት ያልተወጡ መሆናቸውን ከዚሀ በሚቃረን አኳኋንና የፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 2187(1) ባላገናዘበ መልኩ ለብቻ ልጆቻቸውና የራሳቸው የሆነ መተዳደሪያ ለልላቸው ከተራ ቁጥር ሁለት እስከ አምስት ለተጠቀሱት አመልካች ከተጠሪ ጋር ያለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ በአፋጣኝ አከራካሪ ንብረቶችን መሸጣቸው ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመወሰን ሥልጣን ባላቸው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚ በሆነው ፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተረጋግጧል።
ለአንደኛ አመልካች በውክልና ከተጠሪ የተሰጣቸውን አደራ በመጣስና ንብረቶቹን ከጋብቻ የጋራ ውጤት ከመሆን ለማሸሽ ክፉ ልቦና የፈፀሙት የንብረት ሽያጭ ስለመሆኑ ንብረቶቹ በአፋጣኝ መሸጣቸው የሚያስገነዝብ መሆኑን ይግባኝ ሰሚ ችሎት ከአረጋገጠ ደግሞ የአንደኛ አመልካች ተግባር በፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 2188(1) ድንጋጌ መሰረት የጥቅም ግጭት መኖሩን የሚያሳይ ነው። ሲጠቃለልም ከላይ በዝርዝር በተጠቀሱት ሕጋዊ ምክንያት የበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል።
በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ግንቦት 01 ቀን 2003 ዓ.ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/፣70632 ታህሳስ 24 ቀን 2004 ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
በአከራካሪ ንብረቶች የተደረጉ ውሎች እንዲፈርሱ፤ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ተብሎ በተሰጠው ውሳኔ ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
በዚህ ችሎት መጋቢት 21 ቀን 2004 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል ለሚመለከታቸው አካላት ይፃፍ ብለናል።
No topics extracted.