No summary available.
ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች:- አቶ ዳንኤል ዘሚካኤል - ጠበቆች ፕሮፍሰር ጥላሁን ተሾመ እና አቶ ፊላጶስ አይናለም ቀረቡ።
ተጠሪ:- አቶ ቢሃሪ ባቡላል ሞዲ - ጠበቃ አቶ አምሃ በድሉ ቀረቡ መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን፤ መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የቀረበው የግራ ቀኙን የገንዘብ ጉዳይ ክርክር ሰምቶ በመወሰን ረገድ የሥር ፍ/ቤቶች ከተከተሉት የጉዳዩ አካሄድ አንፃር ተመልክቶ የሰጡት ዳኝነት አግባብነትን ለማየት በሚል ነው።
የጉዳዩ መነሻ የአሁን አመልካች በተጠሪ ላይ በፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበው ክስ ሲሆን ይዘቱም ተከሳሽ ለንግድ እንቅስቃሴው ባጋጠማቸው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ለንግድ ሥራቸው የሚውል ገንዘብ እንዲያበድሯቸው ከሳሽን በጠየቋቸው መሰረት ከሳሽ የተከሳሽን ችግር በመመልከት ከ1998 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 10 ቀን 1999 ዓ/ም ድረስ በተለያዩ ጊዜያት ከሳሽ ለተከሳሽ ላበደሯቸው ገንዘብ ተከሳሽ ታህሳስ 10 ቀን 1999 ዓ/ም የተፈረመ የገንዘብ ብድር መተማመኛ ውል መሰረት ብር 7,079,604.86 (ሰባት ሚላዮን ሰባ ዘጠኝ ሺህ ስድስት መቶ አራት ብር ከሰማንያ ስድስት ሳንቲም) ይፈለግባቸዋል። ከታህሳስ 10 ቀን 1999 ዓ/ም በኋላም በተከሳሽ ፈቃድ መሰረት በተለያዩ ጊዜያት ለተከሳሽ የንግድ ሥራ ያወጡላቸውን ወጭዎች ብር 946,270.06 (ዘጠኝ መቶ አርባ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ብር ከስድስት ሳንቲም) በብድር የወሰዱ ለመሆኑም ተከሳሽ በኢሜይል ደብዳቤዎች በፅሁፍ አረጋግጠዋል። በአጠቃላይ ብር 8,025,874.92 (ስምንት ሚላዮን ሃያ አምስት ሺህ ስምንት መቶ ሰባ አራት ብር ከ92/100 ሳንቲም) በዕዳ እንደሚፈለግባቸውና ይህንኑ ገንዘብ እንዲከፍሉ ሲጠየቁ የ6 ወራት የመክፈያ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ከዚህ ጊዜ በኋላ ገንዘቡን እንዲከፍሉ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም እከፍላለሁ በማለት የተስፋ ቃል ከመስጠት በቀር ላከፍሉ አልቻሉም። ስለሆነም የ6 ወሩ የዕዳ መክፈያ ከተጠናቀቀበት ከግንቦት 03 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ ከሚታሰብ ህጋዊ የወለድ ተመን ጋር በአንድ ጊዜ እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
ተከሳሽም በሰጠው የመከላከያ መልስ ከከሳሽ ጋር የቆየ መልካም የጓደኝነትና የንግድ ግንኙነት አልነበረኝም ተከሳሽ የገንዘብ እጥረት ያጋጠማቸው መሆኑን ለከሳሽ ገልፀው አያውቁም፣ ከከሳሽ ጋር ያለኝ የአሰሪና ሰራተኛ እንዲሁም የወካይና ተወካይ ግንኙነት ያለን በመሆኑ ገንዘብ ላያበድሩኝ የሚችሉበት ምክንያታዊ መነሻ የላቸውም፤ ታህሳስ 10 ቀን 1999 ዓ/ም በእኔ ተፈረመ የተባለውን ሰነድ አላውቀውም። ይህ ሰነድ ተፈረመ ከተባለበት ከ1999 ዓ/ም በፊትም ሆነ በኋላ ተከሳሽ በኢትዮጵያ ውስጥ አልኖሩም፤ ለአድዋ ዱቄት ፋብሪካ ሲባል ገባ የተባለውን ዕዳ ተከሳሽ በግለሰብ ደረጃ መተማመኛ ወይንም ማንኛውም ውል ላያደርጉ ስለማይችሉ በሰነዱ ልገደድ አልችልም።
ታህሳስ 10 ቀን 1999 ዓ/ም ተፃፈ በተባለው ሰነድ እንደተመለከተው ከሳሽ ለወደፊት ወጭ ያወጡ ከሆነ ተከሳሽ መተማመኛ ይሰጡ ዘንድ ብር 946,270.06 ወጭ ያደረጉ ስለመሆኑ የሚያመለክት ማስረጃም ያልቀረበ ስለሆነ የተጨማሪውም የገንዘብ ጥያቄው ተቀባይነት የለውም። ከብር 500.00 በላይ የሆነን የብድር ዕዳ ለማረጋገጥ በሚያስችል አኳኋን የቀረበ የሰነድ ማስረጃም አልቀረበም። የኢሜይል ሰነዶችንም በተመለከተ በተከሳሽ ያልተፃፈ ተከሳሽ የማያውቃቸው በሐሰት ተቀናብረው የተዘገጁ ናቸው ታህሣሥ 1ዐ ቀን 1999 ዓ.ም ተከሣሽ በከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀት በሽታ ምክንያት በሆስፒታል ተኝተው የነበረ በመሆኑ ሰነዱን ላፈርሙት አይችሉም።
በአጠቃላይ በከሣሽ በኩል የቀረበው ክስና ማስረጃ የህግ መሰረት የለውም የሚል ክርክር አቅርበዋል።
ይህ የግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር ከተጠናቀቀ በኋላ ፍ/ቤቱ የቃል ክርክር ካደረገና በተከሣሽ የተካደውን ታህሣሥ 1ዐ ቀን 1999 ዓ.ም ተፈረመ የተባለው ሰነድ ላይ የተቀመጠው ፊርማ በተከሣሽ የተፈረመ መሆኑን እና አለመሆኑን ለማረጋገጥ በፎረንሲክ ሳይንሳዊ ምርመራ ሁለት ጊዜ እንዲመረመር ካደረገና ውጤቱን ከተቀበለ በኋላ ግራ ቀኙን ያከራከራቸውን ነጥቦች ለይቶና ከግራ ቀኙ ማስረጃዎች ጋር አገናዝቦ መርምሮ በመ/ቁ. 87441 ጥር 25 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት፡ከሣሽ ለቀረበው ክስ በማስረጃነት ያቀረበው ታህሣሥ 1ዐ ቀን 1999 ዓ.ም የተፃፈው ሰነድ በተከሣሽ ያልተፈረመ ለመሆኑ ሁለት ጊዜ በተደረገው የፎረንስክ ምርመራ ውጤት የተረጋገጠ በመሆኑ ይህ ሰነድ ተከሣሽ ለከሣሽ ብር 7,079,604.86 የተበደረ ለመሆኑ አያረጋግጥም ።
በማስረጃነት የቀረበውም በኢሜል እና በፋክስ የመልእክት ልውውጥ የተደረገ በመሆኑ የብድሩ ስምምነት መኖሩን ያስረዳል በማለት የቀረቡት ሰነዶች ሲሆኑ በተከሣሽ የተደረጉ ሳይሆን ሰለሞን ቢሀሪ ሞዲ በተባለ ግለሰብ የተደረገ ስለመሆኑ ሰነዱ ያስረዳል ሰለሞን ቢሀሪ የተከሣሽ ልጅ ነው የሚባል ቢሆን እንኳ ስለተከሣሽ ሆኖ ገንዘብ ለመበደር የሚያስችል የውክልና ሥልጣን ተከሣሽ እስካልሰጠ ድረስ ማስረጃው ለጉዳዩ አግባብነት የለውም። እንዲሁም የኢሜል የመልእክት ልውውጥ ሁልጊዜም በባለአድራሻው የሚደረግ ነው ብሎ ለመደምደም የሚቻል አይደለም በዚህ ሁሉ ምክንያት ማስረጃው ለጉዳዩ አግባብነት ያለው አይደለም።
በተጨማሪነት ስለቀረበው የብር 946,270.06 የንግድ ሥራ ወጭ በሚመለከት ከሣሽ ይህንኑ ወጭ አወጣው የሚለው በውክልና ሰራው በሚለው ሥራ እንደመሆኑ መጠን ይህንኑ የገንዘብ ወጭ እያደረገ የተከሣሽን ሥራ ለመሥራት የማያስችለው ግልጽ የሆነ የውክልና ሥልጣን አልተሰጠውም ከብር 500.00 በላይ ተሰጠ ለሚል የገንዘብ ብድርም በሰው ማስረጃ ማስረዳት የሚቻል አይደለም በመሆኑም ከሣሹ ለተከሣሹ የንግድ ሥራ ውል በብድር መልክ ለተከሣሽ ይህንኑ የንግድ ሥራ ወጭ ያደረገ ስለመሆኑ አልተረጋገጠም በሚሉት ምክንያት ራሱ ከሣሽ ለብር 8,025,874.92 /ስምንት ሚላዮን ሃያ አምስት ሺህ ስምንት መቶ ሰባ አራት ብር ከ ዘጠና ሁለት ሣንቲም/ የብድር ገንዝበ ክስ በማስረጃ አስደግፎ አላረገገጠም ተከሣሹ ከክሱ ነፃ ነው በማለት ወስኗል።
በዚህ ውሳኔ ላይ የቀረበውን የይግባኝ ጉዳይ የተመለከተው የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ ይህንኑ ውሳኔ በማጽናት የመጨረሻ ዳኝነት ሰጥቶበታል።
ለዚህ የሰበር ጉዳይ መነሻ የሆነውም የአሁን አመልካች የሥር ፍ/ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡት ዳኝነት መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው የሚልበትን ክርክር የመከራከሪያ ነጥቦች በመጥቀስ በቀረበው የሰበር አቤቱታ ምክንያት ሲሆን ተጠሪውም ይኸው በበታች ፍ/ቤቶች የተሰጠው ዳኝነት በሕግ አግባብ መሰረት ስለሆነ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት አይደለም በማለት አመልካች በቀረበው የክርክር ነጥቦች አንፃር የጽሑፍ ክርክሩን አቅርቧል። አመልካችም የመልስ መልሱን በጽሑፍ አቅርቦ የግራ ቀኙ ክርክር ተጠይቋል።
እንግዲህ የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ ባጭር ባጭሩ የተመለከተው ሲሆን እኛም በስር ፍ/ቤቶች የተሰጡት ውሣኔዎች መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመባቸው ናቸው አይደሉም? የሚለውን ጉዳይ ለማስረዳት ግራ ቀኙ በሰበር ደረጃ ያቀረቡትን የመከራከሪያ ነጥቦች ለእነዚሁ በበታች ፍ/ቤቶች ከተሰጡት ውሣኔዎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምረናል።
የአሁን አመልካች ላቀረበው ክስ በማስረጃነት ያቀረበውን ታህሳስ 1ዐ ቀን 1999 ዓ.ም የተደረገውን የገንዘብ መተማመኛ ሰነድ ተከሣሹ በሰጠው መልስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 234/1/ሰ/ እንደተመለከተው በግልጽና በዝርዝር ክዶ የተከራከረ ለመሆኑ በፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ከተሰጠው የፍርድ ሐተታ በግልጽ ተመልክቶ እያለ በዚሁ ሰነድ ላይ የተቀመጠውን ፊርማ ተከሣሹ በግልጽ አልካደውም በሚል የአመልካች በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ደረጃ ያቀረበው ክርክር የተከሣሽን የመልስ ይዘት ያገናዘበ አይደለም።
በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2ዐዐ1 እና 2ዐዐ5 በተደነገገው መሰረት የአሁን አመልካች በተጠሪ ላይ በስር ፍ/ቤት ያቀረበውን ክስ ለማሰረዳት ካቀረባቸው ማስረጃዎች መካከል ታህሳስ 1ዐ ቀን 1999 ዓ.ም በተከሣሽ ፊርማ ተረጋግጦ ተሰጥቷል የተባለው የሰነድ ማስረጃ አንዱ ነው። የአሁን ተጠሪም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2ዐዐ7 መሰረት ይህንኑ የሰነድ ማስረጃ እንደማያውቀው ፊርማውም የእርሱ አለመሆኑን ክዶ ተከራክሯል። ይህ ሰነድም ውል ለማዋዋል ስልጣን ባለው አካል ፊት የተደረገ አይደለም። ይህንኑ ዓይነት ሰነድ አስመልክቶ በማስረጃነት የቀረበበት ወገን ጽሐፈቱን ክዶ የተከራከረ ከሆነ ሰነዱ ወይም ፊርማው በካደው ወገን የተደረገ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ለመለየት የጽሕፈት ምርመራ እንዲደረግ ፍ/ቤቱ ማዘዝ እንደሚችል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2ዐዐ8 ተደንግጓል። በዚህም መሰረት የጽሕፈት ምርመራው ስራ እንዲከናወን ፍ/ቤቱ በክርክር ሂደት ለፍደራል ፖላስ ፎረንሲክ ምርመራ ክፍል ትዕዛዝ ሰጥቶ በመጀመሪያው የምርመራ ውጤት በሰነድ የተቀመጠው ፊርማ በተከሣሽ የተደረገ አለመሆኑን አረጋግጧል። ይህ የምርመራ ውጤት ከታወቀ በኋላ የአሁን አመልካች የሰነድ ምርመራ ስራው በውጭ ሀገር እንዲደረግለት አመልክቶ ፍ/ቤቱ እንደ አመልካች ጥያቄ የሰነድ ምርመራው በውጭ ሀገር እንዲደረግ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ እንደገና በልላ ጊዜ ይህ በውጭ ሀገር በኩል ሰነድ ተመርምሮ እንዲቀርብ በሚል ተሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሶ ለማመሳከሪያነት የሚያገለግሉ ሰነዶች የሚመጡበትን ስፍራ እና እንድት መምጣት እንዳለባቸው አመልካች ባመለከተው መሰረት በተጨማሪነት ከሚመጡት የፊርማ ምርመራ ማመሳከሪያ ሰነዶች ጋር ተገናዝቦ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ በፎረንሲክ የምርመራ ክፍል ተመርምሮ ውጤቱ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በትዕዛዙም መሰረት የምርመራ ስራው ተጠናቆ ለሁለተኛ ጊዜ ፊርማው በተከሣሽ የተፈረመ አለመሆኑን የሚገልጽ ውጤት ቀርቧል።
ከዚህ ከሰነድ ምርመራ ስራ ሂደት ጋር በተያያዘ አመልካች ያቀረበው የመከራከሪያ ነጥብ አንዱ ፍ/ቤቱ ሰነዱ በውጭ ሀገር እንዲመረመር ካዘዘ በኋላ ዳኛ ሰለተለያየ ብቻ እንደ ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ያው ችሎት አስቀድሞ የሰጠውን ትዕዛዝ መሻሩ ከፍ ያለ የስነ ስርአት ጉድለት የፈፀመበት ነው በዚህ ጉልህ ስህተት ምክንያት ፍትህ ተጓድሎብኛል የሚለው ነው። ይሁን እንጂ አመልካች ይህ ክርክር ያስነሳውን ሰነድ በኢት/ያ የሚገኘው የፎረንሲክ ክፍል መርምሮ ትክክለኛ ውጤቱን ለመግለጽ ብቃት፣ ችሎታ እንደልለው አልገለፀም። ይልቁንም ይህንኑ ዓይነት ሰነድ አስመልክቶ የምርመራ ሥራ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የፍድራል ፖላስ ፎረንሲክ ክፍል ከዚህ በፊትም ሆነ አሁን እንደ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ የሰነድ ምርምራ ሥራ በሳይንሳዊ መንገድ እያከናወነ በሚሰጠው ማረጋገጫ መሰረት በአገሪቱ በሚከናወነው የወንጀልም ሆነ የፍ/ብሕር የፍትህ አስተዳደር የፍርድ ስራ ሂደት ሙያዊ ግድታውን የሚወጣ ክፍል ነው።
በዚህም ማረጋገጫ መሰረት ፍ/ቤቶች በቀረበላቸው ጉዳይ እንደ ህጉ ፍትህ ያገናዘበ ዳኝነት ሲሰጡ ቆይተዋል ይህ ሆኖ እያለ አመልካች የመጀመሪያ የሰነድ ምርመራ ውጤት በፎረንሲክ ምርመራ ክፍል ተደርጎ ለአመልካች ተቃራኒ የሆነ ውጤት መቅረቡን ካረጋገጡ በኋላ ይኸው መርማሪ ክፍል የዚህኑ ሰነድ ምርመራ ስራ በአጥጋቢ ሁኔታ ለማከናወን ለምን እንደማይቻል ከብቃት ከችሎታ ወይም ከገለልተኛነት የመነጨ አሳማኝ ምክንያትና ክርክር ባልተጠቀሰበት ሁኔታ በደፈናው አመልካች እንዳቀረበው ጥያቄ ፍ/ቤቱ ሰነድ በውጭ ሀገር ተመርምሮ ይቅረብ ማለቱን ችሎቱ በልላ ጊዜ ተገንዝቦ ቀደም ሲል በክርክር ሂደት የሰጠው ትዕዛዝ ሥነ-ሥርዓታዊ ጉድለት የፈፀመበት መሆኑን በተገነዘበ ጊዜ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 207 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ለማረም ስልጣኑ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው አከራክሪ ነጥብ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ አመልካች የክርክር ነጥብ ፍ/ቤቱ ስነ-ሥርዓታዊ ጉድለት ፈፅመዋል፤ ስህተት አድርጓል እንኳ ቢባል ይህንኑ ስህተት በሰበር ማረም የሚቻለው ስህተቱ መሰረታዊ ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ስለመሆኑ በህገ- መንግስቱ አንቀፅ 80(3)(ሀ) እና በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 10 እና 22 ተደንግጓል።
“መሰረታዊ” የሚለውም ህጋዊ ትርጉሙ ይኸው ስህተት ሳይታረም በመቅረቱ ምክንያት ውጤቱ ላለወጥ ያልቻለ ወይም በተከራካሪው ወገን ፍትህ የማግኘት መብት ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን የሚያመለካት ነው። ከዚህ አንፃር ይህንኑ ጉዳይ እንደተመለከትነው ከላይ እንደተገለፀው አመልካቹ ድሮውንም ቢሆን በውጭ ሀገር ሰነዱ ይመርምርልኝ በማለት ያቀረቡት የጥያቄ አግባብነት በምክንያት በማስረጃ ሳይደገፍ የቀረበ በመሆኑ ይህም ጥያቄ የቀረበው የመጀመሪያው የምርምራ ውጤት ከታወቀ በኋላ ከመሆኑ ይህም ሆኖ እራሱ አመልካች ባመለከተው መሰረት የማመሳከሪያ ሰነዶች እንደገና ይምጡ ከተባለበት ስፍራ እና ሲመጡም በተከሳሹ እጅ ሳይሆን ሰነዱን ለማረጋገጥ ሥልጣን ባለው ገለልተኛ መንግስታዊ አካል አማካኝነት እንዲመጡ እና በድጋሚ የሰነድ ምርምራ እንዲደረግ ከታዘዙ በኋላ በቀረበ የማረጋገጫ ውጤት እንዲቀርብ የተደረገበት የጉዳይ አካሄድ እንደመሆኑ መጠን ይህ በስር ፍ/ቤት ተፈጸመ የተባለው ስነ ስርዓታዊ ጉድለት መሰረታዊ ስህተት ሆኖ አላገኘነውም።
የሥር ፍ/ቤትም በዚሁ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት ብቻ ተመስርቶ ለጉዳዩ ፍርድ እንዲሰጥ ተቆጥሮ ሰበር ሰሚው ችሎት የፎረንሲክ የሰነድ ምርምራ ውጤት ስለማስረጃነቱ ያለውን የማስረዳት ብቃት ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት አባሪ ማስረጃ ነው ወይስ አይደለም? በሚል ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ከዚህ በፊት የሰጠውን ትርጉም በማጣቀስ የቀረበው ክርክር ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለው አይደለም የሥር ፍ/ቤቶች የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ስለጉዳዩ በሙግት የክርክር ደረጃ ጊዜ የአሁን አመልካች ላቀረበው ክስ በማስረጃነት ዘርዝሮ ያቀረባቸውን የሰነድ የሰው ማስረጃዎች ሁሉ አንድ በአንድ በማየት ማስረጃዎቹ ለጉዳዩ ያላቸውን አግባብነት እና የማሳመን የማስረዳት ብቃት እየመረመረ እና እየለካ ማስረጃዎችን መዝኖ ፍርድ የሰጠበት ጉዳይ ስለመሆኑ የፍርድ ይዘት አስረጂ ነው።
በከሳሽ የተቆጠሩት ምስክሮች እንደ ክሱ ጭብጥ ያስረዳሉ የተባለበትን ነጥብ አስመልክቶ ተከሳሹ ሰነዱን በኢት/ያ ሀገር ላፈርም የማይቻልበትን ምክንያት በመጥቀስ ላቀረበው ክርክር አመልካች ሰነዱ የተደረገው ኢት/ያ ውስጥ ሳይሆን ጅቡቲ ሀገር ነው የሚል ክርክር አላቀረበም ይልቁንም ፍ/ቤቱ እንደ ክሱ ጭብጥ ምስክሮች በማስረዳት ረገድ የሚሰጡትን ቃል ታማኝነት ከተከሳሹ ክርክር ጋር አጣቅሶ ለመለካት እንዲያስችለው ተከሳሹ ወደ ኢትዮጵያ ሀገር መቼ መቼ እንደገባ ሁሉ ለሚመለከተው በኢምግሬሽን ጽ/ቤት ማረጋገጫ አስቀርቦ ተመልክቷል። ጅቡቲ ሀገር ነው የተደረገው እንዳይባልም ምስክሮች ወደ ጅቡቲ ሀገር ወጥተው አያወቁም ለሚለው የክርክር ነጥብም ማስተባበያ እንዳላቀርበ በስር ፍ/ቤቶች ፍርድ የተረጋገጠ የፍሬ ጉዳይ ነጥብ ነው። እንግዲህ የአሁን አመልካች በእያንዳንዱ የክርክር ደረጃ የተደረሰበትን ዳኝነታዊ ውጤት እየተከተለ በማፈራረቅ ከሚያቀርበው ክርክር አንፃር የሰው ማስረጃዎች ስለጉዳዩ ቃላቸውን ሳይሰጡ በመታለፋቸው የመደመጥ መብታችን ታልፎብናል የሚለው ክርክሩ ህጋዊ መሰረት ያለው አይደለም።
ስለጉዳዩ ያስረዳል በሚል የአሁን አመልካች ያቀረበውን የኢሜል እና ፋክስ መልዕክት ልውውጥ በማን የተደረገ ነው ይዘቱስ ለጉዳዩ ያለው አግባብነት ምንድን ነው። ክርክር ከቀረበበት የገንዘብ መጠን አንፃር በማስረጃነቱ ያለውን ተቀባይነት ሁሉ በመዳሰስ የማስረጃውን አግባብነት ተቀባይ እና የማስረጃነቱን ዋጋ አይቶና መዝኖ የሰጠውም ዳኝነት የማስረጃ አቀባበል ስርዓትን መሰረት ያደረገ ከመሆኑ በቀር ጉድለት ያለበት አይደለም።
ከዚህም በቀር በተጨማሪ ማስረጃነት ቀርቦ እንዲታይልን ጠይቀን ጉዳዩን በተጨማሪ ማስረጃነት የማስረዳት ዕድሉን ተነፍገናል በማለት ያቀረቡትን ክርክር ይቅረብ ከተባለው የማስረጃ ስርአት አንፃር ሲታይም ሁለቱን ወገኖች ያለያያቸውን ነጥብ ለይቶ ለመወሰን የማስረጃነት አግባብነትና ብቃት የልለው መሆኑን ፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በፍርዱ ምክንያት ሰጥቶ ያለፈው በመሆኑም በይግባኝ ሰሚነቱ ስልጣን ስር የወደቀውን በተከራካሪ ወገን የሚቀርብ ማስረጃ ለጭብጡ አመሰራረት ሆነው የተያዙትን ፍሬነገሮች በማስረዳት በኩል ማስረጃው በትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ ያለውን ዋጋ ሁሉ በማየት የሰጠው ዳኝነት በመሆኑ የተጨማሪን ማስረጃን አቀባበል ስርዓት የጣሰ ሆኖ አላገኘነውም።
ከሁሉም በላይ ክርክር እንዳስነሳው ታህሳስ 10 ቀን 1999 ዓ.ም በተከሣሽ ተደረገ እንደተባለው የፅሑፍ ማስረጃ ላይ ተከሣሹ ይህንኑ መተማመኛ ሰነድ የፈረመው ከሳሹ በተለያዩ ጊዜ ተከሣሹ ላጋጠመው የገንዘብ እጥረት ማቃለያ ሲባል “7,079,604.86 ያበደሩኝ መሆኑን ከሰነዶች ያረጋገጥኩ በመሆኑ ወደፊትም ለንግድ ስራዬ ለሚያመጡልኝ ገንዘብ አባሪ ሰነዶች ኮፒ ተደግፎ ሲመጡልኝ የሚል ይዘት እንዳለው በግልፅ የተመለከተ በመሆኑ ከሳሹ የዚያን ማስረጃ መኖርና አለመኖር በስር ፍ/ቤት ሆነ በይግባኝ ሰሚው በትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ መስፈርት እነዚህን ደጋፊ ሰነዶች በሙሉ ወይም በከፊል በማቅረብ እንዲታይለት በማድረግ ከማስረጃው አግባትነትም ሆኖ የማስረጃ ብቃት አንፃር ጉዳዩ ታይቶ እንዲወሰን ማድረግ እየቻለ ይህ ዓይነት ሰነድ በየትኛውም ደረጃ ባለው ፍ/ቤት አለማቅረብና ለማቅረብ የአለመጠቀሱ ሁኔታ የስር ፍ/ቤት ዳኝነት አግባብነት የሚያመለክት እንጂ ከጉዳዩ አካሄድ አኳያ የመከራከር መብቱ የተገደበ መሆኑን አያሳይም።
በዚህ ሁሉ ምክንያት የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ዳኝነት መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ባለማግኘታችን የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል።
No topics extracted.