No summary available.
መስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድረጅት ነ/ፈጅ ታደሰ በቀለ ቀረቡ ተጠሪዎች፡
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል
**
ጉዳዩ የጎደለ ገንዘብን ከማስከፈል ክርክር ጋር ተያይዞ የቀረበ ሲሆን ክርክሩም የተጀመረው በአ/ብ/ክ/መንግስት ቄለም ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በአሁኑ አመልካች ከሳሽነት ሲሆን ተጠሪዎች ደግሞ ተከሳሾች ነበሩ።
በአመልካች የቀረበው የክሱ ይዘትም በአመልካች ድርጅት ውስጥ 1ኛ ተጠሪ ፖስተኛ ሆኖ በሚሰራበት ጊዜ ግምቱ ብር 54,150 የሆነ ቨውቼር ካርድና ብር 6,338 የሆነ ቴምብር ቀረጥ በድምሩ ብር 61,088 የጎደለ ስለመሆኑ በሂሳብ ባለሙያ የተረጋገጠበት መሆኑን ጠቅሶ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ደግሞ 1ኛ ተጠሪ ሲቀጠሩ እያንዳንዳቸው ብር 30,000 ዋስ ስለሆኑ ሶስቱም ተጠሪዎች ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ከነ ወለዱ እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ የሚል ሲሆን 1ኛ ተጠሪም ቀርቦ በሰጠው መልስ የስራ ድርሻው ፖስተኛ ስለሆነ ጎደለ የተባለው ገንዘብ እሱን እንደማይመለከትና ተደርጓል የተባለው የኦዲት ስራም እሱ በልለበት መሆኑን ጠቅሶ ለክሱ ኃላፊ ላሆን እንደማይገባ በመከራከር መልሱን ሰጥቷል። 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች በበኩላቸው ዋስትና የገቡት 1ኛ ተጠሪ ለ6 ወራት ብቻ በጊዜያዊ ቅጥር በፖስተኛነት ለተቀጠረበት ስራ ነው እንጂ ከዚያ በኋላ በ1ኛ ተጠሪና አመልካች መካከል በአዲስ መልክ የቅጥር ውሉ ለታደሰው ስራ አለመሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው ፍ/ቤትም ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ 1ኛ ተጠሪ ለክሱ መነሻ የሆነውን ገንዘብ ማጉደሉ ተረጋግጦበታል በማለት ገንዘቡን ለዳኝነት ከተከፈለው ገንዘብና ወጪና ኪሳራ ብር 1500 ጋር ለአመልካች እንዲከፍል ሲወሰንበት 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎችን በተመለከተ ግን እነዚህ ተጠሪዎች ዋስትና የገቡበት የ1ኛ ተጠሪ ጊዜያዊ ቅጥር ውል ጊዜው አልቆ ውሉ በአዲስ መልክ በልላ ስራ መደብ ላይ በ1ኛ ተጠሪና አመልካች መካከል ሲደረግ የዋስትና ውሉ አብሮ ያልተደሰ በመሆኑ ኃላፊነት የለባቸውም በማለት በነፃ አሰናብቷቸዋል።
በአመልካች ጠያቂነት ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ይግባኙን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 337 መሰረት በመሰረዝ የስር ፍ/ቤቱን ውሳኔ ያፀና ሲሆን አሁን የቀረበው ሰበር አቤቱታም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ሆኖ መሰረታዊ ይዘቱም የዋስትና ውሉ በጊዜ ያልተገደበና እንዲሁም የ1ኛ ተጠሪ ጊዚያዊ የስራ ቅጥር ውል መታደስ በራሱ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች በመጀመሪያ ቅጥር ጊዜ የገቡትን የዋስትና ግድታ ቀሪ ላያደርገው እንደማይችል እየታወቀ የበታች ፍ/ቤቶች 2ኛና 3ኛ ተጠሪዎችን ከኃላፊነት ውጭ ማድረጋቸው መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ውሳኔው ተሽሮ በገቡት ዋስትና መጠን ከነወለዱ እንዲከፍሉ ይወሰንልን የሚል ነው።
አቤቱታውም ተመርምሮ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች የገቡት የዋስትና ውል በጊዜ አለመገደቡ እየታወቀ የስር ፍ/ቤት ዋሶቹ ለታደሰው 2ኛ ቅጥር ውል ዋስትና ግድታ ስላልሰጡ ለእዳው ተጠያቂነት የለባቸውም በማለት ከኃላፊነት በነጻ የማሰናበቱን አግባብነት ለመመርመር ሲባል መዝገቡ ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ ተደርጎ በአመልካችና 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች መካከል የጽሑፍ ክርክር የተደረገ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ግን ጥሪ ተደርጎለት ባለመቅረቡ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፏል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ተይዞ ከነበረው ጭብጥ አንፃር ብቻ በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
መዝገቡን እንደመረመርነው 2ኛና 3ኛ ተጠሪዎች የዋስትና ግድታ የገቡበት የ1ኛ ተጠሪ የመጀመሪያ ጊዜያዊው የስራ ቅጥር ውል ጊዜው አልቆ በልላ ሰራ ቅጥር ውል እንዲተካ ወይም በአዲስ መልክ ተሻሽሎና የስራ መደቡም ከፖስተኛነት ወደ ክለርክነት እንዲቀየር በተደረገበት ጊዜ የዋስትና ውሉም አብሮ አለመታደሱ ወይም ዋሶቹ ፈቃዳቸውን አለመስጠታቸው በስር ፍ/ቤት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ይህ ለዋስትና ውል መሰረት የሆነው የመጀመሪያ ውል ተለውጦ በልላ ውል በሚተካበት ጊዜ ዋስትና ግድታው ለተለወጠው ቅጥር ውልም ቀጣይነት ኖሮት እንዲቆይ በግልጽ ካልተሰማሙ በስተቀር ወደ ተለወጠው ውል ላተላለፍ እንደማይችል ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1827/1/ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
No topics extracted.
በዚህ ጉዳይም ተፈርሞ የነበረው የዋስትና ግድታ ወደ ተለወጠውና 2ኛ ቅጥር ውል እንዲተላለፍ በግልጽ የተሰማሙ መሆናቸውን አመልካች ያላስረዳ በመሆኑ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎቹ ተጠያቂነት የለባቸውም ተብለው በስር ፍ/ቤት ከኃላፊነት በነፃ መሰናበታቸው የሚነቀፍ ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
በዚህ ጉዳይ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ እና ትዕዛዝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ቁ 348/1/ መሰረት ፀንቷል።
በአመልካች የቀረበው የሰበር አቤቱታ ተቀባይነት የለውም ብለናል።
የሰበር ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል። መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መ/ቤት ይመለስ።