No summary available.
ታህሳስ 14 ቀን 2006ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች- ወ/ሮ ተዋበች ኃይል ቀረቡ ተጠሪ- ወ/ሮ አያንቱ በዬቻ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በሽያጭ ምክንያት ተይዞ በቆየው ይዞታ ላይ ለተሰራ ቤት የወጣው ወጪ /ገንዘብ/ ይተካልኝ የሚል ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኗ አመልካች ባሁኗ ተጠሪ እና በአቶ በዬቻ ሆርዶፋ ላይ በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሚያዚያ 20 ቀን 2002 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት የክስ ማመልከቻ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም አቶ በዬቻ ሆርዶፋ ሕዳር 10 ቀን 1992 ዓ/ም በተጻፈ የብድር ውል ነሐሴ 30 ቀን 1992 ዓ/ም የሚመለሰውን ብር 10,000.00 (አስር ሺ ብር) ተበድረው መውሰዳቸውን፣ይህንኑ ገንዘብ በውሉ በተጠቀሰው ጊዜ ካልመለሱ ደግሞ በአለምገና ከተማ ቀበል 01 ክልል ውስጥ የሚገኘውንና በ147 ካ/ሜትር የቦታ ስፋት ላይ የሰፈረውን ባለአስራ ስድስት ሉክ/ዚንጎ/ ቆርቆሮ ፣በመያዣነት መስጠታቸውንና ስምም ለማዞር ግድታ ገብተው የነበሩ መሆኑን፣በዚህ የውል ስምምነት መሰረት ግድታቸውን እንዲወጡም በመ/ በሆነው ክስ አቅርበው አቶ በዬቻ ወርዶፋ የውል ግድታቸውን አምነው መልስ በሰጡበት ሁኔታ የአሁኗ ተጠሪ በብድር ገንዘቡ ምክንያት ለመያዣነት የተሰጠው ቤት የአቶ በዬቻ ወርዶፋ የግል ቤት ሳይሆን ከሟች እናታቸው ከወ/ሮ ጌጤ በዳኔ ጋር በጋብቻ የተፈራ የጋረ ንብረት በመሆኑ ስምምነቱ ሕጋዊ አይደለም በሚል ምክንያት ወደ ክርክሩ ገብተው ክርክሩ ከተካሄደ በኋላ በቤቱ ላይ የተደረገው ስምምነት ሕጋዊ አይደለም ተብሎ የመጨረሻ ፍርድ የተሰጠበት ቢሆንም ይህንኑ ውሳኔ የሰጠው ፍርድ ቤት አመልካች በብድር ስምምነቱ መነሻ ያወጡትን ወጪ የመጠየቅ መብታቸውን የጠበቀላቸው መሆኑን፣አመልካች ለአቶ በዬቻ ሆርዶፋ ከብድር ገንዘቡ በተጨማሪ ብር 20,800.00(ሃያ ሺ ስምንት መቶ ብር) በቦታው ላይ የሰሩትን ቤት ላለቁላቸው በአገር ሽማግል ፊት ተስማምተው የሰጡ ቢሆንም ይህ ስምምነትም በአሁኗ ተጠሪ ተቀዋሚነት በወራሽነታቸው ድርሻ ላይ ስምምነታቸውን ያልሰጡበት ነው ተብሎ በፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገ መሆኑን፣በቦታው ላይ የሰሩት ባለሰባ ስምንት ሉክ/ዚንጎ/ቆርቆሮ መኖሪያ ቤትም ግምቱ ብር 88,330.00(ሰማንያ ስምንት ሺ ሶስት መቶ ሰላሳ ብር)መሆኑን ጠቅሰው በድምሩ ብር109,130.00(አንድ መቶ ዘጠኝ ሺ አንድ መቶ ሰላሳ ብር) ከተለያዩ ወጪዎች ጋር እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው። የአሁኗ ተጠሪ ለክሱ በሰጡት መከላከያ መልስም አመልካች ውል የፈፀመችው ከአቶ በዬቻ ጋር መሆኑን፣ውሉም ፈርሶ ወደ ነበሩበት ይመለሱ ተብሎ የተወሰነ በመሆኑ ውጤቱን በተመለከተ ክስ ማቅረብ የሚችሉት ውሉን ከተዋዋሉት ሰው ጋር መሆኑን፣በቦታው ላይ የተሰራ ቤት ካለመኖሩም በላይ ቤት እንዲሰሩበት ስምምነት የልለ መሆኑን፣ከባለይዞታው ፈቃድ ውጪ ለተሰራ ቤት የሚጠየቁበት ሕጋዊ ምክንያት ያለመኖሩንና የግንባታ ወጪ መጠኑም በተገቢው ማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን ጠቅሰው ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል።አቶ በዬቻ ወርዶፋ በበኩላቸው ጉዳዩ ቀድሞ በፍርድ ማለቁንና በአፈጻጸም ሂደት ላይ እንደሚገኝ እንዲሁም በቦታው ላይ የተሰራ ቤት ያለመኖሩን ጠቅሰው ተከራክረዋል።የሥር ፍርድ ቤትም የቤቱን ግምትም በተገቢው ባለሙያ እንዲገመት ከአደረገ በኋላ የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመመርምር ተጠሪንና አቶ በዬቻን ለክሱ ኃላፊ ያደረጋቸው ሲሆን የኃላፊነት መጠኑን በተመለከተ ግን አቶ በዬቻ ከብድሩ በኋላ በሽማግልዎች ፊት የወሰዱትን ብር 20,800.00 እና የቤቱን ግምት ግማሽ ብር 41,507.87(አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ሰባት ብር ከሰማንያ ሰባት ሳንቲም) በድምሩ ብር 62,307.87(ስልሳ ሁለት ሺህ ሶስት መቶ ሰባት ብር ከሰማንያ ሰባት ሳንቲም) የአሁኗ ተጠሪ ደግሞ የቤቱን ግምት ግማሽ ብር 41,507.87(አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ሰባት ብር ከሰማንያ ሰባት ሳንቲም) እንዲከፍሉ ሲል ወስኗል። ወጪና ኪሳራን በተመለተከም ብር 600.00 በቁርጥ፣የዳኝነት ብር 3,487.95 ተጠሪና አቶ በዬቻ ወርዶፋ ለአመልካች እንዲተኩላቸው በማለት ወስኗል።በዚህ ውሳኔ የአሁኗ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው አመልካች ጋር እንዲከራከሩ ከተደረገ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪ አመልካች ከባዬቻ ሆርዶፋ ጋር ባደረጉት ውል የወጣውን ወጪ የሚተኩበት ሕጋዊ ምክንያት የለም ሲል ተጠሪን በተመለከተ የተሰጠውን የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሽሮ የክሱ ምክንያት የሆነውን ጠቅላላ ገንዘብ ብር 103,815.75(አንድ መቶ ሶስት ሺህ ስምንት መቶ አስራ አምስት ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም) አቶ በዬቻ ሆርዶፋ ለአመልካች ላተኩላቸው ይገባል በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ የአሁኗ አመልካች ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ የሕግ ስህተተ የለበትም ተብሎ ፀንቷል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ተጠሪ በቦታው ላይ በተሰራው አዲስ ቤት የግማሽ ባለመብት ሁነው እያለ የቤቱን ግምት ላከፍሉ አይገባም ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው የሚል ነው።የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪም ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
No topics extracted.
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔና አግባብነት ከአላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው ጭብጥ፡- ተጠሪ የአከራካሪውን ቤት ግምት ግማሽ ለአመልካች ለመክፈል ይገደዳሉ ወይስ አይገደዱም የሚለው ነጥብ ሁኖ ተገኝቷል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች በተጠሪና በአቶ በዬቻ ሆርዶፋ ላይ ክስ የመሰረቱት አቶ በዬቻ ሆርዶፋ ለገንዘብ ብድር በዋስትና ውል አሳልፈው በሰጧቸው ቦታ ላይ አዲስ ቤት ሰርተው ቤትና ይዞታውን በመያዝ በመጠቀም ላይ እያሉ ይሄው የመያዣ ውል ሕጋዊ አይደለም፣ላፀና አይገባም የሚል ክርክር በተጠሪ በኩል ቀርቦ ውሉ ላፈርስ እንደሚገባና ይፈርሣል ከተባለም ግራ ቀኙ ወደ ነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ ተብሎ በመ/ በስር ፍርድ ቤት ከተወሰነ በኋላ ለአሁኑ የሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነው ክስ መቅረቡን፣በዚህ ክስም አመልካች ዳኝነት የጠየቁት ለአዲስ ግንባታ ያወጡት ወጪ አቶ በዬቻ ሆርዶፋና ተጠሪ እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ መሆኑን ነው። ተጠሪም የመያዣ ውሉ የተደረገው ከአቶ በዬቻ ሆርዶፋ ጋር በመሆኑ ተጠሪን የሚያስጠይቅበት ህጋዊ ምክንያት ያለመኖሩንና ከባለይዞታው እውቅናና ፈቃድ ውጪ ለተሰራ ግንባታ ተጠያቂ የሚሆኑበት የህግ አግባብ ያለመኖሩን ጠቅሰው ውሉ በተጠሪ ላይ ተጠያቂነት የሚያስከትል አይደለም በማለት የሚከራከሩ መሆኑን ተገንዝበናል።
በአመልካችና በአቶ በዬቻ ሆርዶፋ መካከል የተደረገው የመያዣ ስምምነት በባልና ሚስት የጋራ ንብረት ላይ የተደረገ ነው ተብሎ ሕጋዊ የሆነ የቤት መያዣ ውል እንደልለ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተረጋገጠ ሲሆን ውሉ ፈራሽ ነው ተብሎ በፍርድ ቤት ሲወሰንም አመልካች አለኝ የሚሉትን መብት በክስ ማስጠበቅ የሚችሉ መሆኑ ተገልጾ መወሰኑን ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ ችለናል። አመልካች ለአሁኑ የሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነውን ጉዳይ ያቀረቡትም የቤት መያዣ ውል ሕጋዊ አይደለም፤ ፈራሽ ነው፣ ቤቱን ለተጠሪና ለአቶ በዬቻ ሆርዶፋ ላያስረክቡ ይገባል ተብሎ ውሣኔ ከተሰጠ በሁዋላ ሲሆን ተጠሪ በይዞታው ላይ በአመልካች ገንዘብ የተሰራ አዲስ ግንባታ መኖሩን በተመለከተ ያቀረቡት የማስተባበያ ክርክር በማስረጃ ያልተደገፈ ሁኖ በመገኘቱ በስር ፍርደ ቤት ውድቅ የሆነ ሲሆን የበላይ ፍርድ ቤቶችም በዚህ ረገድ የተለዬ ድምዳሜ ላይ አልደረሱም።አመልካች አዲስ ግንባታ መኖሩን ጠቅሰው ይህንኑ ለማስረዳት የቆጠሩት ማስረጃ በስር ፍ/ቤት ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን የቤቱ ግምትም በሚመለከተው አካል ተገምቶ ብር 83,015.75 ነው ተብሎ መረጋገጡን የስር ፍ/ቤት የውሣኔ ግልባጭ ያሣያል።
የበላይ ፍርድ ቤቶች ተጠሪን የተሰራውን ቤት የግንባታ ወጪ ግማሹን ተጠሪ ላጠየቁ አይችሉም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሱት ለመያዣ ውሉ ስምምነት ምክንያት የሆኑት ተጠሪ ሳይሆኑ አቶ በዬቻ ሆርዶፋ ናቸው በሚል ምክንያት ነው።
እንግዲህ ከላይ የተመለከቱት ነጥቦች በስር ፍ/ቤት የተረጋገጡ ሲሆን ከላይ እንደተገለጸው ምንም እንኳን የመያዣ ውሉ የጋራ ባለንብረቶችን ስምምነት ሳያገኝ የተደረገ ነው ተብሎ ፈራሽ ቢሆንም ውሉ በመፍርሱ ወይም በመሰረዙ ምክንያት ንብረት የመመለስ ግድታ ያለበት ሰው ንብረቱን ለውጦ ወይም በዚሁ ላይ ወጪ አውጥቶ ከሆነ ባወጣው ወጪ መጠን ላጠይቅ እንደሚገባ የፍ/ሕ/ቁ 1818 ያመለክታል። ስለሆነም አመልካች ይዞታውንና ቤቱን እንዲለቁ ሲደረግ ቤቱንና ቦታውን እንዲረከቡ ዳኝነት ያገኙት ሰዎች በቦታው ላይ የሰፈረውን ቤት ግምት ላከፍሉ የማይገባበት ምክንያት የለም።ምክንያቱም አመልካች በቦታው ላይ አዲስ ቤት ሲገነቡ ተቃውሞ የቀረበባቸው መሆኑ በፍሬ ነገር ያልተረጋገጠ ሲሆን ይዞታውን ለመያዝም የቻሉት ሕጋዊ ውል አለኝ በሚል እምነት መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል። ይህ ድንጋጌ የወጪውን መመለስ በተመለከተ ያላግባብ ስለመበልፀግ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት እንደሚኖራቸውም ያስገነዝባል። ከውል መፍረስ ጋር ተያይዞ ለሚነሳ የወጪ ክርክር ወጪውን አውጣሁ የሚለው ወገን በሕጉ ያለው መፍትሕ ምን እንደሆነ ሕጉ ያስቀመጠው ሁኔታ ይህ ከሆነ ተጠሪ በቤቱ ላይ መብት አለኝ የሚሉት በሟች እናታቸው በወ/ሮ ጌጤ በዳኔ ድርሻ በመሆኑ እና አዲስ የተሰራውንም ቤት እንዲረከቡ መብት የተጠበቀላቸው ስለሆነ በአመልካች ጥሬ ገንዘብ የተሰራውን ቤት ሲወስዱ ገንዘቡን የማይመልሱበት ሕጋዊ አግባብ የለም። ምክንያቱም ጉዳዩ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1818 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የሚታይ ነው እንጂ ተጠሪን በውሉ ስምምነት ያልሰጡ መሆኑን ብቻ መሰረት አድርጎ የሚታይ አይደለም። ያላግባብ የመበልጸግ ጥያቄ የውል ግንኙነትን መሰረት በማድረግ የዳኝነት መፍትሕ የሚሰጥበት አለመሆኑ ግልጽ ሁኖ እያለ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ከተጠሪ የውሉ ተካፋይ ያለመሆን ጋር በማያያዝ የሰጡት ዳኝነት የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1818 እና በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2162 እና ተከታይ ቁጥሮች ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ባለገናዘበ መልኩ ሁኖ ተገኝቷል።ሲጠቃለልም አመልካች በቤት መያዣ ውል ምክንያት በያዙት ይዞታ ላይ በራሳቸው ገንዘብ ለሰሩት ግንባታ ተጠሪ የቤቱን ግማሽ ድርሻ እንዲረከቡ ከተደረገ ቤቱ የተሰራበትን ወጪ ለአመልካች የማይተኩበት ህጋዊ ምክንያት ያለመኖሩን ከፍ/ሕ/ቁጥር 1818፣2162 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንረዳው በመሆኑ ተጠሪን በተመለከተ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል። በመሆኑም ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል።
ው ሣ ኔ
በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ የካቲት 06 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ መጋቢት 09 ቀን 2005 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ሐምል 22 ቀን 2003 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
ተጠሪ አመልካች የሰሩትን ቤት ዋጋ ግምት ግማሽ ብር 41,507.87 (አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ሰባት ብር ከሰማንያ ሰባት ሳንቲም) በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተጠቀሰው አግባብ ለክርክሩ ከወጡ ወጪዎች ጋር የመክፈል ግድታ አለባቸው ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።