No summary available.
ግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ወ/ሮ እቴነሽ ካሳ - ጠበቃ አስቴር ዓለማሁ - ቀረቡ ተጠሪ፡- ሀጂ ጀማል ይማም - ጠበቃ ተሰማ ዘርፋ - ቀርበዋል **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ውልን መሰረት አድርጎ የቀረበውን ክርክር የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኗ አመልካች ላይ በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።የተጠሪ ክስ ይዘትም፡- ከአመልካች ጋር ጥር 30 ቀን 2000 ዓ/ም በተጻፈ የሽያጭ ውል በአዲስ አበባ ከተማ ቦል ክፍለ ከተማ ቀበል 10 ክልል ውስጥ የሚገኘውንና ቁጥሩ 3798 የሆነው ቤት በብር 200,000.00(ሁለት መቶ ሺህ) ከአመልካች በመግዛት በእለቱ ብር 55,000.00 አመልካች ከተጠሪ ተቀብለው ቤቱን ማስረከባቸውን፣ ቀሪውን ብር 145,000.00 (አንድ መቶ አርባ አምስት ሺ ብር) በገዥ ስም ካርታ አስርተው ለአመልካች ካስረከቡ ከአንድ ዓመት በኋላ ላከፍሉ መስማማታቸውና በስምምነቱ መሰረት አመልካች ካርታውን አሰርተው ለማስረከብ ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን ዘርዝረው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤትና ካርታውን እንዲያስረክቡና ውሉን ለማፍረስ በመሞከራቸውም ብር 30,000.00(ሰላሳ ሺህ) እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኗ አመልካች ለክሱ በሰጡት መልስም ከተጠሪ ጋር ያደረጉት ውል በባዶ ቦታ እንጂ በመኖሪያ ቤት ያልተደረገ ሕገወጥ መሆኑና በእለቱም ብር 5000.00 (አምስት ሺ) እንጂ ብር 55,000.00 (ሃምሳ አምስት ሺ) ያለመቀበላቸውን ጠቅሰው ብር 5000.00 ከፍለው ልላው የዳኝነት ጥያቄ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል።የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከሰማ በኋላ በግራ ቀኙ መካከል የተደረገው ስምምነት በመኖሪያ ቤት ሳይሆን በባዶ ቦታ የተደረገ ስለመሆኑ በማስረጃ መረጋገጡንና ስምምነቱም የኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 40(3) ድንጋጌን የሚጻረር መሆኑን በምክንያትነት ይዞ የተጠሪን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎ ወስኗል።በዚህ ውሳኔ ተጠሪ ባለመስማማት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ ጉዳዩን በመመርመር የስር ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ የሰው ምስክሮችን መስማቱ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2005 ድንጋጌን የሚጥስ መሆኑን በመጥቀስ በሰነዱ ላይ የተሸጠው መኖሪያ ቤት እንጂ ባዶ ቦታ ያለመሆኑ ተረጋገጧል በሚል ምክንያት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔን በመሻር የአሁኗ አመልካች በውሉ በገቡት ግድታ መሰረት ላፈጽሙ ይገባል ሲል ወስኗል። ከዚህም በኋላ የአሁኗ አመልካች ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው ይግባኝ ሰሚው ችሎትም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላና እስከቦታው ድረስ በመሄድ ጉዳዩን በማጣራት ጉዳዩን መርምሮ አመልካች የሸጡት መኖሪያ ቤት እንጂ ባዶ ቦታ መሆኑን ላያረጋግጡ አልቻሉም የሚል ምክንያት ይዞ የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አፅንቶታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ ከተጠሪ ጋር ያደረጉት ውል በባዶ ቦታ ስለመሆኑ የሰነዱ ይዘት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ተጠሪ ቁጥሩ 3798 የሆነውን ቤትና ቦታውን እንዲረከቡ የተሰጠው ውሳኔ አመልካች በሕጉ አግባብ ያገኙቱን 647 ካ.ሜትር ሁሉ አጠቃልሎ እንዲወሰድ የሚያደርግ እንዲሁም ሽያጩ በመኖሪያ ቤት አልተደረገም እንጂ ተደርጓል እንኳ ቢባል አመልካች መሐይም በመሆናቸውም በሕግ ፊት የማያስገድዳቸው ሁኖ እያለ በበታች ፍርድ ቤቶች መታለፉ ያላግባብ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው።አቤቱታቸው ተመርመሮም በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው በጽሑፍ በሰጡት መልስ አመልካች መሓይም ነኝ በማለት የሚያቀርቡት ክርክር በስር ፍርድ ቤት ያልተነሳና ስርዓቱን ጠብቆ ያልቀረበ መሆኑን እንዲሁም ጉዳዩ ይግባኙን በሰማው የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚገባ ተጣርቶ የተወሰነ መሆኑን ጠቅሰው በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ሲሉ ተከራክረዋል።አመልካች በበኩላቸው የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካለቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል ።እንደመረመረውም ጥር 30 ቀን 2000 ዓ/ም ተደረገ የተባለው ስምምነት አመልካችን በሕግ ፊት የማስገደድ ሃይል አለው? ወይስ የለውም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ ተገኝቷል።
No topics extracted.
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካችና ተጠሪ የሚከራከሩት ጥር 30 ቀን 2000 ዓ/ም ተፃፈ በተባለውና በ200 ካ.ሜትር ስፋት ቦታ ላይ የሰፈረው የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ውል አፈፃጸም መሰረት አድርገው መሆኑን፣ግራ ቀኙ ያደረጉት ውል በውልና ማስረጃ ያልተደረገ ከመሆኑም በላይ አመልካች መሓይም ሁነው ያደረጉት መሆኑና በሰነዱ ላይ ለአመልካች ተሰጠ የተባለው የቤት ስፋትና የገንዘብ መጠን በውሉ ላይ በተገለፀው አኳኋን ያለመሆኑን በምስክሮች ቃል የተረጋገጠው የተለያየ መሆኑን፤አመልካች በቦታው ላይ ቁጥር 3798 ተብሎ የተጠቀሰው ቤት የሰፈረው በ200 ካ.ሜትር ብቻ ሳይሆን በ647 ካ/ሜትር መሆኑን ጠቅሰው የሚከራከሩ ተጠሪ ግን በዚህ ረገድ ግልጽ መከራከሪያ ያላቀረቡ መሆኑን፣የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዳኞች እስከ አከራካሪው ቦታ ድረሰ ሂደው ተሸጠ የተባለው ባዶ ቦታ መሆኑን አመልካች ላያሳዩ ያልቻሉ መሆኑንና ይልቁንም መኖሪያ ቤት የሸጡ መሆኑን ማስተባበያ ላያቀርቡ አልቻሉም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሱ መሆኑን ነው።
ከፍ ሲል እንደተገለፀው ተጠሪ ክስ ያቀረቡት እንደውሉ እንዲፈጸምላቸው ሲሆን አመልካች ደግሞ ውሉ የቤት ሽያጭ ውል ያለመሆኑንና ሕጋዊ ያለመሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል።ተጠሪ አመልካች መሓይም ነኝ በማለት ስለ ውሉ ሕጋዊነት የሚያቀርቡት ክርክር በተመለከተ በስር ፍርድ ቤት ያልተነሳ ነው ከማለት ውጪ ልላ ማስተባበያ ክርክር ያላቀረቡበት ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ አመልካች በዚህ ረገድ መከራከሪያ ነጥብ አንስተው የተከራከሩ መሆኑን የክርክሩ ሂደት በግልጽ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የሽያጭ ሰነዱም በማስረጃነት የቀረበበትና የመኖሪየ ቤት ሽያጭ የለም በማለት የተከራከሩበት ጉዳይ ነው።በመሆኑም ተገቢውን ውሳኔ መስጠት ይቻል ዘንድ የሰነዱን ምንነት መለየት ጠቃሚ ይሆናል።ጥር 30 ቀን 2000 ዓ/ም የተፈረመው ሰነድ ርእሱ የ "መኖሪያ ቤት ሽያጭ ውል ስምምነት " የሚል ሲሆን የገዢና ሻጭ እንዲሁም የምስክሮች ፊርማ የያዘ መሆኑን ያመለክታል። ወደ ይዘቱም ሲገባ ሻጭ ተብለው የተጠቀሱት የአሁኗ አመልካች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦል ክፍለ ከተማ ቀበል 10 ክልል ወስጥ ቁጥሩ 3798 የሆነውን፣የቦታው ስፋት 200 ካ/ሜትር ሁኖ በካርታ ቁጥር ቦል/10/02/93- 4208/22572/01 የሆነውን በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኘወን የመኖሪያ ቤታቸውን ለአሁኑ ተጠሪ በብር 200,000.00 (ሁለት መቶ ሺህ) ሽጠው ብር 55,000.00 ልላ ደረሰኝ ሳያስፈልጋቸው በስምምነቱ እለት የተቀበሉና ቤቱን ያስረክቡ መሆኑን፣የመጨረሻውን ክፍያ ደግሞ ገዥ በሚፈልጉበት ቦታ ላይ በገዥ ስም ካርታ ሻጭ ከሚመለከተው ክፍል በስማቸው አሰርተው ካስረከቧቸው ከአንድ አመት በኋላ ብር 145,000.00(አንድ መቶ አርባ አምስት ሺ)አጠቃልለው ላከፍሐቸው መስማማታቸውን፣ የሸጡትን ቤት በቆርቆሮ አጥር አጥረው፣በር ገጥመው፣ውሃ፣መብራት፣ስልክ አስገብተው እንዲሁም ጊዜያዊ ሽንት ቤት ሰርተው ላያስረክቧቸው መስማማታቸውን የሚያሳይ ነው። ተጠሪም በውሉ በሰነዱ በተገለጸው አኳኃን ክፍያውን የፈፀሙና ለመፈጸም የተስማሙ ሁነው ቤቱን የተረከቡ መሆኑን በመግለፅ መስማማታቸው በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል። በሰነዱም ላይ ሁሉም ተዋዋዮችና ምስክሮች ፈርመውበታል።
ከላይ እንደተገለፀውም አመልካች ለክርክራቸው መሰረት ከአደረጓቸው ነጥቦች አንዱ መሓይምነት ሲሆን ክርክሩ ስለመነሳቱ ግንዛቤ ከተወሰደ ጉዳዩ በፍ/ሕ/ቁ.1728/3/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ የሚመለከት ሁኖ ተገኝቷል።
የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1728(3) ድንጋጌ አንድ ስምምነት በጽሁፍ እንዲሆን ሕግ ሲያስገድድ ውሉ በጽሁፍ መሆንና ግድታ ባለባቸው ሰዎች ሁሉና በሁለት ምስክሮች ተፈርሞ ላረጋገጥ እንደሚገባ፤ማየት የተሳናቸው ወይም የመሐይማን ፊርማ የነሱ ለመሆኑ ውል አዋዋይ ወይም የፍርድ ፀሐፊ ወይም አንድ ዳኛ በስራው ላይ ሆነው ካላረጋገጧቸው እንደማያስገድዷቸው ከፍ/ሕ/ቁ. 1727 እና 1728/3/ መረዳት ይቻላል።እንግዲህ ተዋዋዮች ንብረታቸውን አስመልክቶ ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት መብት ለማቋቋም፤ለመለወጥ፤ወይም ለማስቀረት በሚደረግ ስምምነት ሁለቱም ግድታ የሚገቡበትን ነገር አውቀውትና ተገንዝበውት ነፃ ፈቃዳቸውን ላሰጡ ስለሚገባ ማንበብና መፃፍ ለማይችሉ ወይም ማየት ለተሳናቸው ተዋዋዮች ህጉ ልዩ ጥበቃ ያደርግላቸዋል። በመሆኑም በጽሁፍ የሰፈረውን ውል ገለልተኛ በሆኑ 3ኛ ወገኖች ፊት ካልፈረሙ በውሉ ላገደዱ አይችሉም።አመልካችና ተጠሪ በ30/05/2000 ዓ/ም አደረጉ የተባለው ስምምነት ደግሞ በአዋዋይ ወይም በዳኛ ፊት እንዲደረግ ህጉ የሚያስገድደው ነው።በመሆኑም አመልካች መሃይምነታቸውን ምክንያት በማድረግ የሽያጭ ውል ስምምነቱ በዳኛ ወይም በአዋዋይ ፊት አልተደረገም በሚል ምክንያት እንደማያስገድዳቸው ያቀርቡት ክርክር በበታች ፍርድ ቤቶች መታለፉ የግራቀኙን የክርክር አቀራረብና የሰነዱን ይዘት ያላገናዘበ ሁኖ አግኝተናል።በመሆኑም የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰነዱ የመንደር ውል ሁኖ እያለ በሰነዱ የሰፈሩት ነጥቦች ሁሉ ደምዳሚ ናቸው በማለት ውሉ እንዲፈፀም መወሰኑም ሆነ የፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም አመልካች ውሉን አላስተባበሉም በማለት ውሉ እንዲፈጸም የሰጠው ውሳኔ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2005፣ 1723 እና 1728(3) ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ ተገኝቷል።የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ውጤቱ ሲታይ ግን መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት የሚያስችል ሁኖ አልተገኘም።ከላይ በተጠቀሱት ህጋዊ ምክንያቶች ተከታዩን ወስነናል።
በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ሰኔ 30 ቀን 2003 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ ሐምል 30 ቀን 2004 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የፍ/መ/ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ ህዳር 20 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው ችሎቱ አመልካችና ተጠሪ ጥር 30 ቀን 2000 ዓ/ም ያደረጉት ስምምነት ሕጋዊ አይደለም ብሎ የሰጠው የውሳኔ ክፍል በተለወጠ ምክንያት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 342 እና 348(1) መሰረት ፀንቷል።
ግራ ቀኙ ጥር 30 ቀን 2000 ዓ.ም የፈረሙት ስምምነት በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1728(3) መሰረት ያልተደረገ በመሆኑ አመልካችን በሕግ ፊት የማስገደድ ሓይል የለውም ብለናል።ይሁን እንጂ አመልካች ከተጠሪ ብር 5000.00(አምስት ሺ ብር) መቀበላቸውን ያልካዱ በመሆኑ ይህንኑ ገንዘብ ከጥር 30 ቀን 2000 ዓ/ም ጀምሮ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ(9%) ለተጠሪ ላመልሱ ይገባል ብለናል።እንዲሁም ተጠሪ ለአመልካች የከፈሉት ልላ ገንዘብ ካለ በሕጉ አግባብ ከመጠየቅ ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም ብለናል።
ግራ ቀኙ ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
ል/ተ