No summary available.
ሚያዝያ 22 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የማይክሮላንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮልጅ ኃ.የተ.የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ዳዲ ሁንድ ቀረቡ ተጠሪ፡- የፍድራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ነ/ፈጅ ትቤሶ በዛብህ ቀረቡ።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ከኪራይ ውል ጋር ተያይዞ የተነሳውን የንብረት ጉድለትና የተቋረጠ ጥቅም ክፍያን የሚመለከት ነው።
ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መነሻ ነው።የክሱ ይዘትም፡- ከአሁኑ አመልካች ጋር ሐምል 01 ቀን 1990 ዓ/ም በተፈረመ ውል በጉለል ክፍለ ከተማ ቀበል 10/11/12 የሚገኘውንና ቁጥሩ 672 የሆነውን የተጠሪን ህንጻ ለአሁኑ አመልካች ማከራየቱን፣የኪራዩ ዘመንም ተራዝሞ ከአስር አመት በላይ አመልካች ሕንጻውን ሲገለገልበት መቆየቱን፣የኪራይ ዘመኑ ሲያልቅ ሕንጻውን አድሶና ተረክቧቸው የጠፉ፣የተሰበሩና ያረጁ እቃዎችን በአዲስ ተክቶ ላያስረክብ ተከራይ የሆነው አመልካች ግድታ መግባቱን፣የኪራይ ዘመኑ ካለቀ በኋላ የርክክብ ሁኔታውን በተመለከተ ሰኔ 16 ቀን 2001 ዓ/ም በተፈረመ ሰነድ ሕንጻውን አድሶ የጠፉ፣የተሰበሩና የአረጁ እቃዎችን በአዲስ ተክቶ ላያስረክብ መተማመኛ መስጠቱን፣ሕንጻውን ለማሳደስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የጨረታ ማስታወቂያ ወጥቶ እድሳቱ በብር 151,725.25 እንዲከናወን አሸናፊ መመረጡን፣ለጠፉ፣ለተሰበሩና ላረጁ እቃዎች መተኪያ የብር 150,848.00 ፕርፎርማ መሰብሰቡን፣በዚህ መሰረት ሕንጻውን አሳድሶና እቃዎቹን ተክቶ እንዲያስረክብ የአሁኑ አመልካች ቢጠየቅም ፈቃደኛ ያለመሆኑን፣ተጠሪ ህንጻውን በወር በብር 20,000.00፣የህንጻውን አዳራሽ ደግሞ በወር ብር 4000.00 አከራይቶ ገቢ ላያገኝ ይችል እንደነበር፣አመልካች የውል ግድታውን ባለመፈጸሙ ተጠሪ ከመስከረም 01 ቀን 2001 ዓ/ም አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2002 ዓ/ም ድረስ ባሉት ሃያ ሁለት ወራት ብር 528,000.00 የኪራይ ገንዘብ ማጣቱን፣ለህንጻው ማሳደሻ ብር 302,573.25 እንደሚያስፈልግ እንዲሁም እንደውሉ ባለመፈፀሙ ደግሞ በውሉ አንቀፅ 6(12) መሰረት ብር 30,000.00 ለመክፈል ስምምነት ማድረጉን ዘርዝሮ በድምሩ ብር 860,573.25 እና ለክሱ የወጣውን ወጪና ኪሳራ እንዲከፍል ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው።
የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም አመልካች ህንጻውን አሳድሶ መስከረም 01 ቀን 2001 ዓ/ም ሙሉ በሙሉ መልቀቁን፣ተጠሪ ህንጻውን አመልካች እንዲረከብ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቶና ተደጋጋሚ መፃጻፍ አድርጎ ሰኔ 16 ቀን 2001 ዓ/ም ህንጻውን ተጠሪ መረከቡን፣ርክክቡ የዘገዬው በተጠሪ ጥፋት በመሆኑ ለዘገዬበት ጊዜ ተጠሪ የጠየቀው የኪራይ ገንዘብ ተቀባይነት ላኖረው እንደማይገባ፣በህንጻው ያለመታደስ ምክንያት እንድት አድርጎ የብር 528,000.00 ጉዳት እንደደረሰበት ተጠሪ ያለማስረዳቱን፣የቀረበው ስልትም የውል መሰረት እንደልለውና ርክክቡን ተጠሪ ለማከናውን ያልቻለው በመጠነኛ ጉድለት ምክንያት እንጂ ህንጻውን ለመጠቀም የማያስችሉ ጉድለቶች በመኖራቸው ምክንያት ያለመሆኑን፣ሕንጻውን ተጠሪ የተረከበው መልሶ ለማከራየት ሳይሆን ለራሱ ላጠቀምበት በመሆኑ የኪሳራው ጥያቄ ተቀባይነት እንደልለው፣ሕንፃው ለረዥም ዘመን ያገለገለ በመሆኑ በተፈጥሮ ማርጀቱንና የተጠሪ ጥያቄ ህንጻውን ማሳደስ ሳይሆን መቀየር በመሆኑ የራሱን የጨረታ ኮሚቴ አቋቁሞ ያቀረበው የእድሳት ገንዘብ ጥያቄ አግባብ ያለው እንዳልሆነ፣ህንጻውን ሲረከብ የነበረው የተፈጥሮ እርጅና ግምት ውስጥ ገብቶ ተጠሪ እዳሳት የማያስፈልገውን የሕንፃ ክፍል ለይቶ አመልካችም ለዚያ እድሳት ለምን ኃላፊ እንደሚሆን አስረድቶ ሕንፃውን ሲሰራ ወይም ህንጻ ሲሰራ ወደ ነበረበት ሁኔታ ሳይሆን በአመልካች ጥፋት እድሳት ላስፈለገው የህንጻ አካል ብቻ በገለልተኛ ወገን በሚገመተው መሰረት እንዲያሳድስ እንዲወሰንለት፣የሚተኩ እቃዎችን በተመለከተ የቀረበው ጥያቄ ግልፅ ባለመሆኑ ክሱ ተሻሽሎ እንዲቀርብ፣ሕንጻው በሰጠው አገልግሎት ምክንያት ያረጁትን እቃዎች ሁሉ እንዲተካ መጠየቁ አግባብነት የልለው መሆኑንና የቀረቡት ፕሪፎርማዎችን የተነጋነነ ዋጋ የያዙ መሆኑን እንዲሁም ዋጋውም ስምምነቱን መሰረት ያላደረገ መሆኑና የኃላፊነት መጠኑ ከብር 50,000.00 እንደማይበልጥ በውሉ መመልከቱን፣አመልካች የውል ግድታውን ባይፈፅም የሚኖርበት የኃላፊነት መጠን የብር 30,000.00 ብቻ ስለመሆኑ ውሉ እንደሚያስረዳ ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ አመልካችን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ ለህንፃው ማሳደሻ የተጠቀየውን ገንዘብ ብር 302,573.25፣ተጠሪ ያጣውን የኪራይ ገቢ ብር 488,000.00 ክስ ከተመሰረተበት ከሐምል 29 ቀን 2002 ዓ/ም ጀምሮ ገንዘቡ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ ከሚታሰብ ሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍል፣ወጪና ኪሳራ በቁርጥ ብር 2000.00(ሁለት ሺህ) እንዲከፍል ወስኖበታል።በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦ ግራ ቀኙ ህንጻው ቢከራይ ኑሮ ላያስገኝ ይችል በነበረው የኪራይ ገቢ መጠኑ ላይ ብቻ እንዲከራከሩ ከተደረገ በኋላ ችሎቱ በዚህ ረገድ ግራ ቀኙ ያቀረቡትን ክርክር በመመርመር አመልካች ለጉዳዩ ኃላፊ መባሉን በመቀበል የኃላፊነት መጠኑን በተመለከተ ግን ከብር 488,000.00 ወደ ብር 244,000.00(ሁለት መቶ አርባ አራት ሺህ ብር) ዝቅ አድርጎ አመልካች ይህንኑ ገንዘብ እንዲከፍል መጠኑን ለይቶና ለእድሳት ያስፈልጋል የተባለውን ገንዘብ ብር 302,573.25 ለተጠሪ እንዲከፍል በስር ፍርድ ቤት የተሰጠውን የውሳኔ ክፍል በማፅናት ዳኝነት ሰጥቷል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም በስር ፍርድ ቤት የቀረቡትን የመከራከርያ ነጥቦችን በማጠናከር የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን በተገቢው መንገድ ያልተመለከቱት መሆኑንና የሕግ መሰረት በልለው አኳኋን መወሰኑን የሚጠቅስና ውሳኔው እንዲሻር ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው።አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ ላታይ ይገባዋል በመባሉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም ጉዳዩ ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ በጭብጥነት የተያዘው ነጥብ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ሕንጻ ተጠሪ ለጳውሎስ ሚዲካል ኮልጅ እያከራየው የነበረ ስለመሆኑ በከፊልም ቢሆን አምኖ እያለ የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን በርትዕ አይቶ ለመወሰን የሕግ መሰረት የነበረው መሆን ያለመሆኑን የሚመለከት በመሆኑ ጉዳዩን ከዚሁ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር ብቻ ተመልክተናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ከተጠሪ ህንጻውን ተከራይቶ ሲጠቀምበት የቆየ መሆኑንና የኪራይ ዘመኑ ሲያልቅ ሕንጻውን አድሶና ተረክቧቸው የጠፉ፣የተሰበሩና ያረጁ እቃዎችን በአዲስ ተክቶ ላያስረክብ ተከራይ ግድታ መግባቱን፣የኪራይ ዘመኑ ካለቀ በኋላ የርክክብ ሁኔታውን በተመለከተ ሰኔ 16 ቀን 2001 ዓ/ም በተፈረመ ሰነድ ሕንጻውን አድሶ የጠፉ፣የተሰበሩና የአረጁ እቃዎችን በአዲስ ተክቶ ላያስረክብ መተማመኛ መስጠቱን፣ሕንጻውን ለማሳደስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የጨረታ ማስታወቂያ ወጥቶ እድሳቱ በብር 151,725.25 እንዲከናወን አሸናፊ መመረጡን፣ለጠፉ፣ለተሰበሩና ላረጁ እቃዎች መተኪያ የብር 150,848.00 ፕሪፎርማ መሰብሰቡን፣በዚህ መሰረት ሕንጻውን አሳድሶና እቃዎቹን ተክቶ እንዲያስረክብ የአሁኑ አመልካች ቢጠየቅም ፈቃደኛ ያለመሆኑን፣ ተጠሪ ሕንፃውን በወር ብር 20,000.00፣የህንጻውን አዳራሽ በወር ብር 4000.00 ተከራይቶ ገቢ ላያስገኝ ይችል እንደነበር ቢገልፅም የአደራሹ የኪራይ ገቢ ያለመቋረጡን፣አመልካች የውል ግድታውን ባለመፈጸሙ ተጠሪ ከመስከረም 01 ቀን 2001 ዓ/ም አንስቶ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2002 ዓ/ም ድረስ ባሉት ሃያ ሁለት ወራት ብር 528,000.00 የኪራይ ገንዘብ ማጣቱን ቢገልፅም የበታች ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ የቀረበውን የተጠሪ የዳኝነት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ያለመቀበላቸውን፣ለህንጻው ማሳደሻ ብር 302,573.25 እንደሚያስፈልግ በጨረታ ኮሚቴ መረጋገጡንና አመልካችም በሂደቱ ሲሳተፍ የነበረ መሆኑ በፍሬ ነገር ደረጃ መረጋገጡን ነው።ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው አመልካች በኪራይ ሲጠቀምበት የነበረው ሕንጻ በተገቢው ጊዜ ለተጠሪ ያላስረከበው በአመልካቹ ጥፋት ነው? ወይስ በተጠሪው ጥፋት ነው? የሚለው ጭብጥ በስር ፍርድ ቤቶች ታይቶና የግራ ቀኙ ክርክሮችና ማስረጃዎች ተመርምረው ርክክቡ ያልተፈጸመው በአመልካች ጥፋት መሆኑን ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ መሆኑን ነው።ይህ ችሎት ርክክቡ የዘገዬው በአመልካች ጥፋት ነው? ወይስ በተጠሪ ጥፋት ነው? የሚለውን በማስረጃ የሚነጥረውን የፍሬ ነገር ክርክር በመመርመር የበታች ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ የደረሱበትን ድምዳሜ ለመለወጥ የሚያስችለው ስልጣን የልለው መሆኑን ከኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ በመሆኑ አመልካች የርክክቡ ጊዜ በተጠሪ ጥፋት የዘገዬ ነው በማለት የሚያቀርበውን ክርክር የሚቀበልበት አግባብ አልተገኘም።ልላው አመልካች ህንጻውን አድሼአለሁ፣የእቃ ርክክብም ፈፅሜአለሁ እንዲሁም ጠፉ፣ተሰበሩ የተባሉት እቃዎች በህንጻው እርጅና የተከሰቱ ናቸው በማለት የሚያቀርበው ክርክር ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶቸ ውድቅ የተደረገ የማስረጃ ምዘና ጉዳይ እንጂ የመሰረታዊ ሕግ ስህተትን መመዘኛ የሚያሟላ የክርክር ነጥብ ባለመሆኑ ተቀባይነት ላሰጠው የሚገባው አይደለም።እንግዲህ አመልካች በኪራይ የተረከበውን ህንፃ ከኪራይ ዘመኑ ማለቅ በኃላ በተገቢው ጊዜ በማደስ፣የጠፉ፣የተሰበሩና የአረጁ እቃዎችን በመተካት ለባለንብረቱ ተጠሪ ለማስረከብ በውል ስምምነት ማድረጉ ከመረጋገጡም በላይ በውሉ በገባው ግድታ መሰረት ግድታውን ያለመወጣቱ ከተረጋገጠ ተጠሪ በሕግ አግባብ በተቋቋመ ውል መሰረት አመልካች ግድታውን እንዲወጣ መጠየቁና ፍርድ ቤቶቹም በጉዳዩ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎችን በመመርመር አመልካችን ግድታውን አልተወጣም በማለት መወሰናቸው በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1678(ለ)፣1731፣1790 እና 1757 ድንጋጌዎች አንፃር ተገቢ ነው ከሚባል በስተቀር የሚነቀፍበት የሕግ አግባብ የለም።
በሕግ አግባብ የተቋቋመ ውል እንደውሉ ያልተፈጸመለት ወገን እንደውሉ እንዲፈፅምለት ለመጠየቅ መብት ያለው ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1678(ለ)፣1718፣1771(1)፣1790 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።በዚህ አግባብ ጥያቄ የሚያቀርበው ተዋዋይ ወገን ልላኛው ተዋዋይ ግድታውን ባለመፈጸሙ ውሉን በግድታ እንዲፈጽም ወይም እንዲፈረስ ከማስደረግም በቀር ከነዚሁ ማሻሻያዎች ጋራ አጣምሮ አንዱ ወገን ለደረሰበት ጉዳት ኪሳራ መጠየቅ እንደሚችል የፍ/ሕ/ቁጥር 1790(1) ድንጋጌ በግልጽ የሚያሳይ ሲሆን ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት ያቀረበው ጥያቄም አመልካች በውሉ በገባው ግድታ ተገቢውን እንዲፈፅምና ባለመፈፀሙ ደግሞ የደረሰውን ኪሳራ እንዲተካ ይወሰን ዘንድ የሚያሳይ ነው።ከዚህ አንፃር ጉዳዩ ሲታይ የእድሳት ወጪም ሆነ ለክርክሩ ምክንያት የሆኑት እቃዎች ዋጋ በጨረታ ተወዳዳሪ ተጋብዞ የዋጋ መጠናቸው የተለዩ ስለመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ከላይ እንደተገለጸው በዚህ ረገድ በሰበር አቤቱታ ላይ የቀረበው ክርክር የሕግ ትርጉም የሚያስፈልገው ጭብጥ ያልተያዘበትና የፍሬ ነገረ ክርክር በመሆኑ የመጠኑ ተገቢነት በዚህ ችሎት የሚታይ አይደለም።የህግ ትርጉም ያስፈልገዋል ተብሎ ከጉዳት ጋር ተያይዞ የቀረበው ነጥብ አመልካች ህንጻውን በተገቢው ጊዜ አድሶ ባለማስረከቡ ለባከነው ጊዜ ሕንፃው ቢያከራይ ኑሮ ላገኝ ይችል የነበረ የኪራይ ገቢ መጠን ምን ይህል ላሆን ይገባል?፣በርትዕስ መወሰኑ ተገቢነት አለው ወይስ የለውም? የሚለው ነጥብ ነው።
በመሰረቱ በውል አፈፃጸም ሂደት የሚደርሰው የጉዳት ኪሳራ የሚሰላበት አግባብ በፍ/ሕ/ቁጥር 1790 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ስር ተመልክቷል።ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘት መረዳት የሚቻለውም የጉዳት ኪሳራ መጠን በጉዳዩ በሚቀርበው ማስረጃና አእምሮ ያለው ሰው ውሉ ባለመፈጸሙ ይደርሳል ብሎ በሚገምተው አስተያየት ልክ ላወሰን እንደሚችል፣የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1800 በተለይ ሲታይም ባለገንዘቡ ከጠየቀው ዝቅ ያለ ጉዳት ያገኘው መሆኑን ባለእዳው ያስረዳ እንደሆነ ኃላፊነቱ በዚሁ ልክ እንደሚሆንና የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1790(2) ድንጋጌም ኪሳራው ልኩ ከውል ውጪ ስለሚደርስ አላፊነት በሚለው ምዕራፍ በተጻፉት ድንጋጌዎች መሰረት እንደሚወሰን ደንግጓል።ከውል ውጪ የኪሳራ ልክ ከሚወሰንባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ርትዕ ስለመሆኑ የፍ/ሕ/ቁጥር 2102(1) ድንጋጌ ያሳያል።ይህ ድንጋጌ ኪሳራ የሚወሰነው ያለምንም መነሻ ሳይሆን የኪሳራውን ልክ በትክክል ለመወሰን ያልተቻለ የሆነ እንደሆነ ዳኞቹ የነገሮቹን ተራ ሁኔታዎችንና ተጎጂውም ያደረገውን ጥንቃቄ አመዛዝነው በመገመት የኪሳራውን ልክ በርትዕ እንደሚወስኑ ያሳያል። የሚከፈለው ካሳ መጠንና የጉዳቱ መፈፀም የሚያጠራጥር በሆነ ጊዜ ግን ማናቸውንም የጉዳት ካሳ እንዲከፈል ለማድረግ የማይቻል መሆኑን የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2102(2) ድንጋጌ በግልጽ አስቀምጧል።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች ሕንጻውን በውሉ በገባው ግድታ መሰረት በተገቢው ጊዜው አድሶ ባለማስረከቡ ተጠሪ በኪራይ ያገኝ የነበረው ገቢ መቋረጡ በማስረጃ ተረጋግጧል።መጠኑም በተመለከተም አመልካች በስር ፍርድ ቤት ባቀረበው ስልት መሰረት ሕንፃው በወር በብር 20,000.00 አደራሹ በብር 4000.00 ላከራይ ይችል እንደነበር ጠቅሶ ለሃያ ሁለት ወራት ብር 528,000.00 ገቢ ማጣቱን ገልጾ የተከራከረ ሲሆን የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች አዳራሹን ለአስር ወራት በብር 4000.00 ሺህ አከራይቶ ገቢ ማግኘቱ መረጋገጡን መሰረት በማድረግ ብር 40,000.00 የኪራይ ገቢን ተጠሪ ከጠየቀው የኪራይ ገቢ መጠን ብር 528,000.00 ተቀናሽ አድርጓዋል።በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተወሰነው የብር 488,000.00 የሕንፃው የወር ኪራይ ገቢ መጠን የፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በግማሽ ዝቅ ያደረገው ህንጻውን ተጠሪ ለጳውሎስ ሚዲካል ኮልጅ እያከራዬ ነው በማለት አመልካች ያቀረበውን ክርክር ተጠሪ በከፊል አምኖታል በሚል ነው።ይሁን እንጂ አመልካች ህንጻውን እንደለቀቀ ወዲያውኑ ተጠሪ ሕንፃውን ሳይታደስ ለኮልጁ አከራይቶ ጥቅም ሲያገኝበት የነበረ መሆኑን ያልተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ በዚህ ረገድ የቀረበው የአመልካች ክርክር ኮልጁ ዘግይቶም ቢሆንም ህንፃው ባልታደሰበት ሁኔታ መከራየቱ ሕንጻው ላከራይ ይችል የነበረ ስለመሆኑ የሚያሳይ ነው የሚል በመሆኑና ሕንፃው ኮልጁ ከተከራየው በኋላ ስለመታደሱ ማስተባበያ ክርክር በአመልካች በኩል ያልቀረበበት በመሆኑ በተጠሪ ላይ ጉዳት አልደረሰበትም ለማለት የሚያስችል አይደለም።ይልቁንም ተጠሪ ሕንጻው ለኮልጁ አከራይቶ ብር 60,000.00 በወር ገቢ ማግኘቱን አመልካች የሚያምነው ሐቅ መሆኑ ሲታይ ተጠሪ ሕንጻው ሳይታደስ ቆይቷል ለተባለበት ጊዜ በወር ብር 24,000.00 ገቢ ያስገኝ ነበር በማለት ክስ ማቅረቡ ጉዳዩን በርትዕ ለመወሰን መሰረት ለማድረግ የሚቻልበት አግባብ የልለ መሆኑን የሚያሳይ ነው።በልላ አገላለጽ ተጠሪ ህንጻው ባለመታደሱ ምክንያት ያጣውን የገቢ መጠን በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1799(1) ድንጋጌ አስረድቶ እያለና አመልካች በፍ/ብ/ህ/ቁጥር 1800 ድንጋጌ መሰረት በተጠሪ ላይ የደረሰው ጉዳት ዝቅ ያለ ነው በማለት ማስረጃ አቅርቦ ባላስረዳበት ሁኔታ ተጠሪ ህንፃው ሳይታደስም ማከራየት ይችል ነበር በማለት ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የሚያገኝበት አግባብ የለም።በተጠሪ ላይ የደረሰ ጉዳት በማስረጃ ተረጋግጦ እያለና አመልካች ህንጻውን ለማሳደስ በውሉ ግድታ ከመግባቱም በላይ ግድታውን ለመወጣት በጨረታ አወጣጡ ሂደት ሁሉ ሲሳተፍ ቆይቶ የጨረታውን ውጤት ከአወቀ በኋላ ግድታውን ለመወጣት ፈቃደኛ ስላለመሆኑ በማስረጃ በተረጋገጠበት ሁኔታ ሕንፃው ሳይታደስም ቢሆን መከራየት ይችል ነበር የሚል እንድምታ ባለው ምክንያት ይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የካሳውን መጠን በርትዕ መወሰኑ ግራ ቀኙ በጉዳት መጠኑ ላይ በሕጉ የተጣለባቸውን ግድታ ከመወጣት አንጻር ታይቶ የተወሰነ ነው ላባል ከሚችልና በውጤቱም አመልካችን የጠቀመ ነው ከሚባል በስተቀር ውሳኔው የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1790(2)፣1799፣1800፣1802 እና 2102 ድንጋጌዎችን የጣሰ ነው ለማለት የሚቻል ሁኖ አልተገኘም።ሲጠቃለልም በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የልለበት በመሆኑ ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ግንቦት 30 ቀን 2003 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ መጋቢት 27 ቀን 2004 ዓ/ም ተሻሽሎ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
አመልካች ለህንፃው ማሳደሻ የተጠቀየውን ገንዘብ ብር 302,573.25(ሶስት መቶ ሁለት ሺ አምስት መቶ ሰባ ሶስት ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም)፣ተጠሪ ያጣውን የኪራይ ገቢ ብር 244,000.00(ሁለት መቶ አርባ አራት ሺህ ብር) እንዲከፍል፣ወጪና ኪሳራ በቁርጥ ብር 2000.00(ሁለት ሺህ) እንዲከፍል በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.