No summary available.
የካቲት 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ሲሳይ ረታ ጠበቃ አቶ መዝገቡ ወልድ ቀርቧል ተጠሪ፡- የኢትዩጵያ እህል ንግድ ድርጅት ነ/ፈጅ አቶ ሙሉጌታ ቀርቧል **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የመጋዘን ኪራይ ውል ጋር ተያይዞ የቀረበ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው ያሁኑ ተጠሪ በአ/ብ/ክ/መንግስት ሰሜን ጎንደር መስተደድር ዞን ከ/ፍ/ቤት በአመልካች ላይ ባቀረበው ክስ መነሻነት ነው። የክሱ ይዘትም ባጭሩ የተጠሪ ንብረት የሆነውና በጎንደር ከተማ ቀበል ዐ1 ውስጥ የሚገኘው መጋዘን አመልካች ከመጋቢት 1 ቀን 1997ዓ.ም እስከ የካቲት 3ዐ ቀን 2ዐዐ1ዓ.ም ድረሰ የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ በወር ብር 51ዐ9.45 ኪራይ እየከፈለ ሲጠቀም የቆየ መሆኑን ጠቅሶ የኪራይ ውሉ ከሚያበቃበት መጋቢት 1 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ጀምሮ ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ አመልካች የመጋዘኑን ወራሃዊ ኪራይ ክፍያ ብር 13,800 እየከፈለ ውሉ በዚህ መልኩ ተሻሽሎ እንዲቀጥል ወይም በዚህ መልኩ ተስማምቶ ለመቀጠል ካልፈለጉ ደግሞ መጋዘኑን እንዲያስረክብ በተለያዩ ደብዳቤዎች ማስጠንቀቂያ ቢጻፍለትም እምቢተኛ በመሆንና ከእኛ ፈቃድ ውጪ የቀድሞውን የመጋዘኑን የኪራይ መጠን በባንክ ሂሣባችን እያስገባ በመጋዘኑ መጠቀም የቀጠለ በመሆኑ የመጋዝኑን ኪራይ ከቀን 1/7/2ዐዐ1ዓ.ም እስከ ነሐሴ 3ዐ ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ድረስ ያለውን የ18 ወራት ኪራይ ክፍያ በ13,800 ታስቦና ካለእኛ ፈቃድ የከፈለው ተቀንሶለት ባጠቃላይ ብር 156,429 እንዲከፍልና እንዲሁም ከመስከረም1 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም ጀምሮ መጋዝኑን እስኪያስረክብ ድረስ ያለውን ብር 13,800 ወርሃዊ ኪራይ ክፍያ ታስቦ ከወለድ ጋር እንዲከፈላቸው ዘንድ ዳኝነት ጠይቋል። አመልካችም ቀርቦ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና በፍሬ ጉዳዩ ላይም ወርሃዊ የመጋዘኑን ኪራይ ክፍያ በተመለከተ በብር 13,800 እንዲከፍል የሚያስገድደው የውልም ሆነ የህግ ግድታ አለመኖሩን በመከራከር መልስ ሰጥቷል። ጉዳዩን የተመለከተው ፍ/ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ከመረመረ በኋላ የቀድሞው የኪራይ ውል ጊዜ ከማለቁ በፊት ተጠሪ ከመጋቢት 1 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ጀምሮ የመጋዘኑ ወርሃዊ ኪራይ መጠን ብር 13,800 መሆኑን ጠቅሶ በተለያዩ ጽሑፎች ለአመልካች በመግለጽና በዚሁ መልኩ ውሉ ተሻሽሎ እንዲቀጥል አልያም በዚህ የማይስማማ ከሆነ ደግሞ መጋዘኑን እንዲያስረክብ በተገለፀለት መሰረት አመልካች ቀርቦ ካለመዋዋሉም ባሻገር የቀድሞ ኪራይ ውል ጊዜ ከተጠናቀቀም በኋላ መጋዘኑን ሣያስረክብ ይዞ መጠቀሙን መቀጠሉ በተጠሪ የቀረበለትን ድርድር ወይም አዲሱን ወርሃዊ የኪራይ መጠን በዝምታ የተቀበለ መሆኑን ስለሚያሳይ ከመጋቢት 1 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም እስከ የካቲት 15 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም ድረስ ያለው ወርሃዊ ክፍያ በብር 13,800 ታስቦና የተከፈለው ተቀንሶለት ብር 387,990.45 ለተጠሪ ከፍሎ መጋዝኖቹንም እንዲያስረክብ ሲል ወስኗል።
አመልካች በዚህ ውሣኔ ባለመስማማት ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ቅሬታውን ያቀረበ ቢሆንም ፍ/ቤቱ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 337 መሰረት ቅሬታውን ሰርዞታል።
አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታም ይህንኑ በመቃወም ሲሆን አመልካች ሰኔ 25 ቀን 2ዐዐ4ዓ.ም ጽፎ ያቀረበው የሰበር አቤቱታ ማመልከቻ ይዘትም ባጭሩ አመልካች የመጋዘኑን ኪራይ በተመለከተ በወር ብር 13,800 ለመክፈል በየትኛውም መልኩ የተስማማሁት ውል ሣይኖር እና እንዲሁም አዲሱን የኪራይ መጠን እንደማልቀበል በግልጽ ለተጠሪ ምላሸ በመስጠትና ይልቁንም በመጀመሪያ የኪራይ መጠን መቀጠል እንደምፈልግ ሐሳቤን በመግለጽ አሳውቄ እያለሁ አዲሱን ዋጋ በዝምታ ተቀብሎታል በማለት የተሰጠው ውሣኔ የፍ/ብ/ህ/ቁ 1684 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ በመሆኑ ውሣኔው ታርሞ በተዋዋልኩት ውል መሰረትና በቀድሞው የኪራይ መጠን እንዲከፍል ውሣኔ እንዲሰጥለት ዘንድ ጠይቋል። አቤቱታውም ተመርምሮ አመልካች አዲሱን የመጋዘን ኪራይ ዋጋ በዝምታ በመቀበል ተስማምቶበታል ተብሎ በአዲሱ የኪራይ ዋጋ ስልት መሰረት የኪራይ ገንዘቡን እንዲከፍል የመወሰኑን አግባብነት ከፍ/ብ/ህ/ቁ 295ዐ አኳያ ለመመርመር ሲባል መዝገቡ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ ተደርጎ ተጠሪም ቀርቦ የስር ፍ/ቤቶች ውሣኔ ላይ የተፈጠረ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት አለመኖሩን ጠቅሶ የቀረበውን የሰበር አቤቱታ ባለመቀበል የስር ፍ/ቤቶች ውሣኔ ፀድቆ ከበቂ ወጪና ኪሣራ ጋር እንዲወሰንለት ዘንድ በመጠየቅ መልሱን የሰጠ ሲሆን አመልካችም የበኩሉን የመልስ መልሰ ሰጥቶበታል።
No topics extracted.
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድጋጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መዝገቡ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
እንደመረመርነውም አመልካች የቀረበለትን አዲሱን የኪራይ ዋጋ በዝምታ በመቀበልና መጋዘኑንም የቀድሞ የኪራይ ውል ጊዜ ከተጠናቀቀም በኋላ ሣያስረክብ መጠቀሙን የቀጠለ በመሆኑ በአዲሱ ዋጋ እንደተስማማ ተቆጥሮ የኪራዩን ገንዘብ በዚህ ስልት ዋጋ አመልካች ላከፍል ይገዳደዳል በሚል ተጠሪ የሚከራከር ሲሆን አመልካች ደግሞ በተጠሪ የቀረበውን የኪራይ ዋጋ እንደማልቀበልና እንደማልስማማበት ሐሳቤን ገልጨ ስቃወም ስለነበረ በዝምታ እንደተቀበልኩ ተቆጥሮ የሚወሰድበት የሕግ አግባብ የለም በማለት ይከራከራል ። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ አመልካች በተጠሪ የቀረበለትን አዲሱን የመጋዝን ኪራይ ዋጋ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1684 ድንጋጌ ስር በተመለከተው መልኩ በዝምታ ተቀብሎ እንደተስማማበት ላቆጠር ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚለው መፍትሕ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል።
በተጠሪ የቀረበለትን የኪራይ ዋጋ ማሻሻያ መጠን አስመልክቶ አመልካች በመቃወም ምላሽ የሰጠ ስለመሆኑና ይህንኑ ምላሽ የሰጠበትን የጽሑፍ ሰነድም በማስረጃነት ቆጥሮ ለስር ፍ/ቤት በማቅረብ የተከራከረ ስለመሆኑ ከቀረቡት ውሳኔ ግልባጮች መገንዘብ ተችሐል። ተጠሪም የኪራይ ማሻሻያውን አመልካች በዝምታ ተቀብሎታል በሚል በደፈናው መከራከሩን እንጂ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1684 (2) ስር እንደተመለከተው ለምላሹ በቂ ጊዜ ተቆርጦለት በዚያው በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ አመልካች መልስ ሣይሰጥ በመቅረቱ የማሻሻያ ዋጋውን እንደተቀበለ ይቆጠራል በሚል የቀረበ ክርክር የለም። ምላሹ የተቆረጠ የጊዜ ገደብ ስለመኖሩ የተገለፀ ነገር ካለመኖሩም ባሻገር በዚህ ረገድ የቀረበ ክርክርም ባለመኖሩ በተጠሪ የቀረበውን የኪራይ መጠን ማሻሻያ ዋጋ ድርድር ወይም ሐሳብ አመልካች በደረሰ በወሩ ወይም ከዚህም በበለጠ ጊዜ ውስጠ አመልካች የተቃውሞ ሓሳቡን በመግለጽ ምላሹን ከሰጠ ድርድሩን በዝምታ ተቀብሎታል ተብሎ ላወሰድ የሚቻልበት የሕግ አግባብ አይኖርም በተጠሪ የቀረበለትን የኪራይ መጠን ዋጋ ማሻሻያ ሐሳብ ከላይ በተገለፀው መልኩ አመልካች በዝምታ እንደተቀበለ የሚቆጠርበት አግባብ የለም የሚል መደምደሚያ ላይ ከተደረሰ ደግሞ የኪራይ መጠኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2950(1) ስር እንደተገለፀው በሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ተወስኗል ለማለት አይቻልም።
በልላ መልኩ ደግሞ ምንም እንኳ የቀድሞው የኪራይ ውል ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ አዲሱ የኪራይ ልክ በሕጉ አግባብ በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ተወስኖ ያልታወቀ ቢሆንም አመልካቹ መጋዘኑን መጠቀም የቀጠለ በመሆኑ ላገኘው አገልግሎት ኪራይ ላከፍል ይገደዳል ። ምን ያህል የኪራይ ልክ ላወሰን ይገባል የሚለውን በተመለከተ አመልካች የቀድሞውን የኪራይ ውል መነሻ በማድረግ በወር ብር 5,109.45 መሆን አለበት ብሎ የሚከራከረውም ሆነ ተጠሪ በወር ብር 13,800 መሆን አለበት የሚለው ክርክር ከላይ በተገለፀው መልኩ የሁለቱንም ወገኖች ስምምነት መነሻ ያደረገ ባለመሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2950(2) ስር በተመለከተው መልኩ የኪራይ ልኩ በተዋዋይ ወገኖቹ ስምምነት ሣይወሰን የቀረ እንደሆነ የማዘጋጃ ቤት ባለስልጣናት በወሰኑት በታሪፍ መሰረት ወይም ይህ በልለ ጊዜም የአካባቢውን የወቅቱን ነፃ ገበያ ዋጋ መነሻ በማድረግ ላወሰን እንደሚገባ መገንዘብ ይቻላል።
ሲጠቃለል የሰሜን ጎንደር መስተዳድር ዞን ከ/ፍ/ቤት ከመጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን የመጋዘኑን ወርሃዊ የኪራይ መጠን እላይ በተገለፀው መልኩ በማዘጋጃ ቤቱ የተወሰነ ታሪፍ ካለ በዚያ መሰረት ይህ ከልለ ደግሞ የአካባቢውን ልማድ ወይም ወቅታዊ ነፃ ገበያ ዋጋ መነሻ በማድረግ መወሰን ሲገባ የአመልካች ፍቃድና ስምምነት የልለበትን ወርሃዊ ኪራይ ክፍያ ብር 13,800 በመቀበልና በዚህ አስልቶ መወሰኑና እንዲሁም የክልሉ ጠ/ፍ/ቤትም ይህን ስህተት ማረም ሲገባ ማፅናቱ በውሳኔዎቹ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል። በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
በዚህ ጉዳይ የሰሜን ጎንደር መስተዳድር ዞን ከ/ፍ/ቤትም ሆነ የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት የመጋዘኑን ወርሃዊ ኪራይ መጠን ብር 13,800 እንደሆነ በመወሰድና ከመጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን የኪራይ ገንዘብ በዚህ በማስላት ያልተከፈለውን ብር 387,990.45 አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል የተወሰነው የውሳኔ ክፍል ብቻ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የሰሜን ጎንደር መስተዳድር ዞን ከ/ፍ/ቤት የራሱ መ/ የሆነውን በማንቀሳቀስ ከመጋቢት 1 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ያለውን ወርሃዊ የኪራይ መጠን እላይ በፍርዱ ክፍል ውስጥ በተገለፀው መልኩ ግራ ቀኙን በድጋሚ አከራክሮ በመስማት አጣርቶ ከወሰነ በኋላ ያልተከፈለውን የኪራይ ገንዘብ በዚያ በማስላት ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥበት በፍ/ብ/ስ/ስ ህ/ቁ 343(1) መሰረት በመመለስ ተወስኗል።
በዚህ ችሎት በተደረገው ክርክር ምክንያት ግራ ቀኙ ያወጡትን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
በዚህ መዝገብ ላይ መስከረም 24 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተሰጥቶ የነበረው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል። ይፃፍ።