No summary available.
ሚያዚያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ መንግስቱ ኦሾ /ቀረቡ/ ተጠሪዎች፡-
ጉዳዩ የጥብቅና አገልግሎት ክፍያን የሚመለከት ሆኖ በአሁን የሰበር አመልካች ከሳሽነት የተጀመረው በአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪዎች ደግሞ ተከሳሾች ነበሩ። ከሳሽ ባቀረቡት ክስ፡- ከተከሳሾች ጋር በ22/10/2002 ዓ/ም ባደረግነው የጥብቅና አገልግሎት ውል በውርስ ንብረት ላይ ክርክር እንዳካሂድና ከሚያገኙት ድርሻም ብር 30,000 በቁርጥ ለመከፈል የተስማሙ ሲሆን እኔም በውሉ መሰረት በተለያዩ መዛግብት ክርክር በማድረግ ያስወሰንኩ ቢሆንም በተለያየ ጊዜ ብር 9,000 ከፍለው ቀሪውን የሚፈለግባቸውን ብር 20,000 ያልከፈሉኝ ስለሆነ ይህንኑ ገንዘብ በውሉ ከተቀመጠው የገደብ መቀጫ ብር 6,000 ጋር እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ ብለዋል።
ተከሳሾችም ለክሱ በሰጡት መልስ፡- ከሳሽ የጥብቅና አገልግሎት እንዲሰጡ መስማማታችን የማይካድ ቢሆንም በ22/10/2002 ዓ/ም በጽሁፍ ያደረግነው ስምምነት የለም፣በማስረጃነት ባቀረቡት የውል ኮፒም ላይ የተፈረመው ፊርማ የእኛ አይደለም፣ከከሳሽ ጋር በቃል ስምምነት ያደረግን ሲሆን ስምምነቱም በፍርድ ቤት ቀጠሮ ባለበት ቀን ብቻ ቆመው እንዲከራከሩልን ሲሆን በስምምነታችን መሰረት የሚፈለግብንን ብር 4,000 የከፈልን በመሆኑ በሀሰት ያቀረበብን ክስ ውድቅ ላሆን የሚገባ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
ፍርድ ቤቱም ኮፒው የቀረበው የጽሁፍ ውሉ የተካደ በመሆኑ ዋናውን ውል ከሳሽ እንዲያቀርቡ አዞ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ከጠየቁ በኋላ ዋናው ውል ከመዝገቡ ውስጥ የጠፋብኝ በመሆኑ ማግኘት አልቻልኩም በማለታቸው በቀረበው የውል ኮፒ ላይ ስማቸው የተጠቀሰውን የከሳሽ ምስክሮች እና ተከሳሾች ያቀረቡአቸውን ምስክሮች በመስማት በሰጠው ውሳኔ የከሳሽ ምስክሮች በ22/10/2002 ዓ/ም ከሳሽና ተከሳሾች ባደረጉት ውል ተከሳሾቹ ለጥብቅና አገልግሎት ብር 30,000 ለመክፈል በከሳሽ ጽ/ቤት ውስጥ መስማማታቸውን ሲያስረዱ በተከሳሾች በኩል ከቀረቡት ምስክሮች ውስጥ 1ኛው ምስክር ከሳሽ እና ተከሳሾች እንደ ቤተሰብ የሚታዩ እና ከሳሽም ተከሳሾች በፍርድ ቤት ቀጠሮ ባላቸው ጊዜ ብቻ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ሲከራከሩ መቆየታቸውንና ተከሳሾችም በተለያዩ ጊዜያት ገንዘቡን ሲከፍሉ ማየታቸውን ከዚያም በፐርሰንት ክፈሉ ውልም ፈርሙ በማለታቸው የተነሳ ተከሳሾቹ ስላልተስማሙ ግንኙነታቸው መቋረጡን ማስረዳታቸውን 2ኛ ምስክር ደግሞ በፍርድ ቤት በቀጠሮ ቀን ለዋሉበት ተከሳሾቹ ለከሳሽ ገንዘብ ሲከፍሉ መቆየታቸውን እንጂ ስምምነቱ በጽሁፍ ወይም በቃል ስለመሆኑ እንደማያውቁ ማስረዳታቸውን በመግለጽ፤ ተከሳሾች ብር 30,000 ለመክፈል የተስማሙ መሆናቸውን በውሉ ኮፒ ላይ ስማቸው የተጠቀሰው ምስክሮች ያስረዱ ስለሆነና ተከሳሾችም ስምምነቱ ውሸት መሆኑን ገልጸው ከመከራከራቸው በስተቀር ገንዘቡን ስለመክፈላቸው በግልጽ ክደው ባለማከራከራቸውና ባቀረቡአቸው ምስክሮችም ባለማስተባበላቸው ቀሪውን ገንዘብ ብር 20,000 ላከፍሉ ይገባል ሲል ወስኗል።
የመቀጫ ገንዘብን በተመለከተ ግን ከሳሽ በአንድ በኩል ውሉ እንዲፈጸምላቸው እየጠየቁ በልላ በኩል የመቀጫ ገንዘብ እንዲከፈላቸው የጠየቁት ተገቢ ባለመሆኑ በፍ/ህ/ቁ/1890(2) መሰረት ላከፈላቸው አይገባም ብሐል።
ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ይግባኙን በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/337 መሰረት በመዝጋት ይግባኝ ባዮችን አሰናብቷቸዋል።
የስር ተከሳሾችም በፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ ላይ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በማቅረባቸው ችሎቱ የግራ ቀኙን ወገን በማከራከር በሰጠው ውሳኔ፡በጽሁፍ የተደረገ የውል ስምምነት የለም በሚል በአንደኛው ተከራካሪ ወገን በተካደ ጊዜ ውል አለ የሚለው ወገን ዋናውን ውል ወይም የግልባጩ ትክክለኛነት የተረጋገጠውን በማስረጃነት ማቅረብ የሚገባው ሲሆን በዚህ በተያዘው ጉዳይ ግን ተጠሪው ዋናውን ውል ማቅረብ የማይችሉ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ያቀረቡት የውሉ ግልባጭም (ኮፒ) ይህንኑ ለማረጋገጥ ሥልጣን በተሰጠው አካል ዘንድ ቀርቦ ያልተረጋገጠ ነው። በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤቶች የውል ስምምነት መኖር አለመኖሩን በውሉ ላይ ያሉትን ምስክሮች ላሰሙ የማይገባ ሆኖ ሳለ ሰምተው የወሰኑት የፍ/ህ/ቁ/1719፣1726 እና 1727 ፣2001፣2003፣2005 እና 2012 ድንጋጌዎችን የሚቃረን ነው በማለት የሥር ፍርድ ቤቶች አመልካቾች(የሥር ተከሳሾች) ገንዘቡን እንዲከፍሉ የሰጡትን ውሳኔ ሽሯል።
No topics extracted.
የሰበር አቤቱታም ለዚህ ችሎት የቀረበው በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ሲሆን በዋናነት የጠቀሱት የቅሬታ ነጥብ ሲጠቃለል፡- ተጠሪዎች የአባታቸውን እና የእናታቸውን የውርስ ሀብት በተመለከተ እንድከራከርላቸው በቀን 01/10/2002 ዓ/ም የተጻፈ ውክልና ሰጥተው በዚሁ ውክልና መሰረት በ6 መዛግብት ላይ በወረዳ ፍርድ ቤት ተከራክሬ አስወስኜ እያለሁና ተጠሪዎቹም ስከራከርላቸው ስለመቆየቴ አምነው በጽሁፍ ውል አልተዋዋልንም ሲሉ በመከራከራቸው የወረዳው ፍርድ ቤት በውሉ ላይ ያሉትን የአመልካች ምስክሮችና የተጠሪዎችን ምስክሮች በመስማትና በመመዘን የአመልካች ምስክሮች ያስረዱትን የተጠሪዎቹ ምስክሮች ማስተባበል አለመቻላቸውን በማረጋገጥ የሰጠውን ውሳኔና ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ያጸናውን ሰበር ሰሚው ችሎት ዋናው ሰነድ ከጠፋ ኮፒው በፍጹም ዋጋ እንደልለው አድርጎ የፍርድ ቤቶቹን ውሳኔ የሻረው የህግ መሰረት የለውም የሚል ነው።
ተጠሪዎች በበኩላቸው በሰጡት መልስ፡- አመልካች ተጠሪዎች ያልፈረምንበትን የሐሰት ውል አዘጋጅተው ዋናው ስለጠፋ በውሉ ላይ ባሉት ምስክሮች ይረጋገጥልኝ ሲሉ ያቀረቡትን ክርክር የወረዳው እና ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተቀበለው ቢወስኑም የጠፋ ሰነድ የሚመሳከርበት ልላ ሰነድ እስካልቀረበ ድረስ በሰው ማስረጃ ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ ምክንያት ሰበር ሰሚው ችሎት ክሱን ውድቅ ያደረገው ተገቢ በመሆኑ አቤቱታቸው ተቀባይነት ላያገኝ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።
ለተጠሪዎች መልስም፡- አመልካች የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ በመሻር ተጠሪዎች ክስ የቀረበባቸውን ገንዘብ ላከፍሉ አይገባም ሲል የወሰነው በአግባቡ ነው?
ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
የግራ ቀኙ ተከራካሪዎች በመካከላቸው የጥብቅና አገልግሎት ውል ስለመኖሩ የሚያምኑት ጉዳይ ሲሆን የሚያለያያቸው ነጥብ ግን ውሉ የተደረገበት ሁኔታና የገንዘቡ መጠን ነው። ይሕውም አመልካች ውሉ በጽሁፍ መደረጉንና የተዋዋሉበት የገንዘብ መጠንም ብር 30,000 መሆኑን ገልጸው የሚከራከሩ ሲሆን ተጠሪዎች ግን ውሉ የተደረገው በጽሁፍ ሳይሆን በቃል መሆኑን እና በስምምነቱ መሰረትም የሚፈለግባቸውን ብር 4,000 ስለመክፈላቸው በመጥቀስ ተከራክረዋል። በጽሁፍ እንዲደረጉ በግልጽ በህግ ካልተደነገጉ የውል ዓይነቶች በስተቀር ማንኛውም ውል በቃል፣በተለመዱ ጠቅላላ ምልክቶች ወይም ግድታ ለመግባት መፍቀድን በማያጠራጥር አሰራር በማስታወቅ ላደረግ ይችላል። እንዲሁም ውሉ በጽሁፍ እንዲደረግ ህጉ ባያስገድድም ተዋዋይ ወገኖች ውላቸውን በጽሁፍ እንዲሆን የማድረግ መብት አላቸው። በዚህ ጉዳዩ ግን ውሉ በጽሁፍ ተደርጓል የሚሉት አመልካች ሲሆኑ ለዚህም በማስረጃነት የውሉን ኮፒ ማቅረባቸውን ከክርክሩ መገንዘብ የሚቻል ነው። አመልካች የውሉን ኮፒ ያቀረቡት ዋናው ውል ጠፍቷል በሚል ሲሆን ይህ በማስረጃነት የቀረበው የውሉ ኮፒም አግባብ ባለው አካል ከዋናው ውል ጋር ስለትክክለኛነቱ በፍ/ህ/ቁ/2011(1) መሰረት የተረጋገጠ አይደለም። አመልካች ውሉ በጽሁፍ ተደርጎ ተፈራርመናል እስካሉ ድረስም ዋናውን ውል በተመለከተ ማስረዳት የሚጠበቅባቸው ውሉ የጠፋ ስለመሆኑ እንደሆነ በፍ/ህ/ቁ/2003 ከተደነገገው መገንዘብ የሚቻል ነው። በአንድ ውል የተጠቀሱ ምስክሮችም መሰማት ያለባቸው ተዋዋዮች ውሉን ተስማምተው የፈጸሙ መሆናቸውንና የውሉ ቃል ምን እንደሆነ ለማረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እንደሆነ በፍ/ህ/ቁ/1730(1) ተመልክቷል።በዚህ ጉዳይ ግን ዋናው ውል ስለመጥፋቱ አመልካች በማስረጃ ሳያስረዱ በውሉ ኮፒ ላይ ስማቸው የተጠቀሰውን ምስክሮች እንዲሰሙላቸው ያቀረቡትን ክርክር የወረዳው ፍርድ ቤት ተቀብሎ የምስክሮችን ቃል መስማቱ ህጋዊ መሰረት ያለው አይደለም።
አመልካች ዋናውን የጽሁፍ ውል በማስረጃነት ማቅረብ የማይችሉ ከሆነና ኮፒውም አግባብ ባለው አካል ስለትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ከሆነ በልሎች ማስረጃዎች ተጠሪዎች በውሉ ለጥብቅና አገልግሎት ለመክፈል የተስማሙ ስለመሆናቸው ክሱን ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል። ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ የማስረዳት ሸክማቸውን ማስረጃን የመስማትና የመመዘን ሥልጣን ላላቸው የሥር ፍርድ ቤቶች ማስረጃዎቻቸውን አቅርበው አለማስረዳታቸው ተረጋግጧል። በልላ በኩል ተጠሪዎች ባቀረቡአቸው ማስረጃዎች አመልካች በቀጠሮ ቀን ብቻ ፍርድ ቤት የሚገኙ ስለመሆናቸው እና ለተገኙባቸው የቀጠሮ ቀናትም ገንዘብ የከፈሉአቸው ስለመሆኑ በስር ፍርድ ቤቶች በተደረገው ክርክር በማስረጃ ካስረዱት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
አመልካች ክሱን አስረድተዋል ቢባል እንኳን ተጠሪዎቹ እንዲከፍሉአቸው የጠየቁት የአገልግሎት ክፍያ ተገቢና ሚዛናዊ መሆን ስላለመሆኑ ጉዳዩ የቀረበለት ፍርድ ቤት በመመርመር ከመጠን በላይ ተዋውለው ከተገኙም ለመቀነስ የሚችል ስለመሆኑ በፍ/ህ/ቁ 2635 ከተደነገገው መገንዘብ ይቻላል። ይሁን እንጂ በዚህ ችሎት እምነት አመልካች በክሳቸው ተጠሪዎቹ እንዲከፍሉዋቸው ከገለጹት ገንዘብ መጠን እና ተጠሪዎች በቃል ውሉ አመልካች በቀጠሮ ቀን ብቻ ፍርድ ቤት እየተገኙ እንዲከራከሩላቸው ተስማምተናል በሚል በማስረጃ ካረጋገጡት ፍሬ ነገር አንጻርም የተቀበሉት ገንዘብ በቂ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው።
በመሆኑም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ምንም እንኳን የጽሁፍ ማስረጃ በመኖሩ የሰው ምስክሮችን መስማት አይገባም ሲል በውሳኔ ላይ ያሰፈረው ትችት ከውል ጋር ተያይዞ የጽሁፍ ማስረጃ ቢኖር እንኳን ምስክሮች ላሰሙ ስለሚችሉበት አግባብ በፍ/ህ/ቁ/1730(1) የተመለከተውን መሰረት ያደረገ ባይሆንም፤ እንዲሁም በተከራካሪዎቹ መካከል የጸሁፍ ውል ባይኖርም የቃል ውል ስለመኖሩ ተጠሪዎቹ አምነው በተከራከሩበት ሁኔታ ሰበር ሰሚው ችሎት ውል የለም ሲል በውሳኔው ያሰፈረው የፍሬ ነገር ክርክሮችን የሚመረምሩ ፍርድ ቤቶች ካረጋገጡት ፍሬ ነገር ውጪ በመሆኑ ተቀባይነት ባይኖረውም በዉጤት ደረጃ በውሉ ኮፒ ስማቸው የተጠቀሰውን ምስክሮች በመስማት ከተጠሪዎች ምስክሮች ቃል ጋር በማመዛዘን በክሱ የተመለከተውን ገንዘብ ተጠሪዎች ላከፍሉ ይገባል ሲሉ የሥር ፍርድ ቤቶች የወሰኑት ውሳኔ በመሻር ገንዘቡን ላከፍሉ አይገባም በሚል በሰጠው ውሳኔ ላይ የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ባለማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የኦ/ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/147419 በቀን 05/02/2005 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በውጤት ደረጃ በመቀበል በፍ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት አጽንተናል።
አመልካች ዋናው ውል የጠፋ መሆኑን ባላስረዱበትና በማስረጃነት ያቀረቡት የውሉ ኮፒም ከዋናው ውል ጋር ተገናዝቦ ትክክለኛነቱ አግባብ ባለው አካል ባለመረጋገጡ በተከራካሪዎቹ መካከል በጽሁፍ የተደረገ የጥብቅና አገልግሎት ውል የለም ብለናል። ሆኖም በቃል በተደረገው ውል መሰረት ተጠሪዎች ተገቢውን የአገልግሎት ክፍያ ለአመልካች የከፈሉ ስለመሆናቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ቀደም ሲል ከከፈሉት ገንዘብ በተጨማሪ ላከፍሉ አይገደዱም ብለናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ።