No summary available.
ጥር 2 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ አዳነ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አሕመድ አመልካች፡- ሳይግን ቴክስታይል ቢዩልዲንግ ኮንስትራክሽን ትሬድ ኢንዳትሪ ኢንክ ኢትዮጲያ ብራንች ነ/ፈጅ መቅደስ ሽፈራው ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ተስፋዬ ጥላሁን ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ከአሰሪና ሰራተኛ ክርክር ጋር ተያይዞ የቀረበ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩም የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ በፍደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ክስ መነሻነት ነው። የክሱ ፍሬ ነገርም ባጭሩ ከሣሽ በተከሣሽ ደርጅት ውስጥ ከ22/06/02 ዓ.ም ጀምሮ በመሐንዲስነት እና በፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነት የስራ መደብ ተቀጥረው በማገልገል ላይ እያሉ ተከሣሹ ያለአግባብ የሥራ ውላቸውን ያቋረጠባቸው መሆኑን ጠቅሰው ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት ልዩ ልዩ ክፍያዎች እንዲፈፀምላቸው እንዲሁም የሥራ ምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው በሚል ዳኝነት የጠየቁ መሆናቸውን የሚያሣይ ነው። የሥር ተከሣሽም ቀርበው ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስ፡- ከሣሽ ተከሣሽን በመወከል ስራዎችን የሚያቅዱ ለሰራተኞች ስራ የሚሰጡ እና የሥራ ጥራታቸውን የሚቆጣጠሩ መሆኑን፣ ስራዎችን የሚያስተባብሩ እና የስራ አፈፃፀማቸው አጥጋቢ ባልሆኑ ሰራተኞች ላይ እርምጃ የሚወስዱ መሆኑን ጠቅሶ ከሳሽ የሥራ መሪ እንጂ ሰራተኛ ባለመሆናቸው የሥራ ክርክር ችሎቱ ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን ስልጣን የለውም በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና በፍሬ ነገሩ ረገድም የበኩሉን መከራከሪያ በማቅረብ መልስ መስጠቱን የሥር ፍ/ቤቱ ውሣኔ ግልባጭ ያስረዳል።
ጉዳዩን የተመለከተው የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሥራ ክርክር ችሎት በበኩሉ የግራ ቀኙ የጽሑፍ እና የቃል ክርክር ከሰማ እና ለከሣሽ የተሰጠው የሥራ መዘርዘር በትእዛዝ አስቀርቦ መመልከቱን ከገለጸ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ የከሣሽን የሥራ ተግባር የፕሮጀከቱን ስራ በኃላፊነት መምራት፣ማደራጀት፣ መቆጣጠር እና ማስተባበር መሆኑን በማስረጃ መረጋገጡን ከገለፀ በኃላ የዚህ አይነቱን ተግባራት የሚፈጽም ግለሰብ ደግሞ በአዋጁ ቁ.
377/96 አንቀጽ 3 እና በማሻሻያ አዋጁ ቁ.494/98 አንቀጽ 2/ሐ/ ድንጋጌዎች እንዲሁም የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በሰበር መ.ቁ.42901 በሰጠው የሕግ ትርጉም መሰረት የሥራ መሪ እንጂ ሰራተኛ ላባል ስለማይችል ጉዳዩ በአሰሪና ሰራተኛ ሕጉ መሰረት ስለማይስተናገድ የሥራ ክርክር ችሎቱ ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን የሥረ ነገር ስልጣን የለውም በማለት ክሱን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 244/2/ /ሀ/ መሰረት በብይን ውድቅ አድርጓል።
በአሁኑ ተጠሪ አመልካችነት ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በበኩሉ ግራ ቀኙን አስቀርቦ ከሰማ በኃላ ጉዳዩን በመመርመር ተጠሪ የተመደበበት የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ የስራ መደብ ሥራ መዘርዘር ሁኔታ ከአዋጅ ቁ. 494/98 አንቀጽ 2/ሐ/ ድንጋጌ ይዘት አኳያ ተገናዝቦ ሲታይ ተጠሪ የሥራ አመራር ፖላሲዎችን የማውጣትና የማስፈጸም ጭምር ኃላፊነት አልተሰጠውም፣ ከነዚህ በተጨማሪም ወይም እነዚሁኑ ሣይጨምር ሰራተኞችን የመቅጠር የማዛወር የማገድ የማሰናበት የመመደብ ወይም የስነ ስርዓት እርምጃ የመውሰድ ስልጣን ሣይሰጠው የሥር ፍ/ቤት ተጠሪ የፕሮጀክቱን ስራ በኃላፊነት ይመራሉ፣ ያደራጃሉ፣ ይቆጣጠራሉ በማለት ጉዳዩን ከሰበር መ.ቁ. 42901 ገዥ ውሣኔ ጋር በማያያዝ ተጠሪ የሥራ መሪ ናቸው የሚል ድምዳሜ ይዞ የሰጠው ብይን የሕግ ድጋፍ የለውም በማለት ብይኑን ሽሮ የሥር ፍ/ቤት በፍሬ ነገሩ ክርክር ላይ ተገቢውን ውሣኔ እንዲሰጥ ክርክሩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 341 መሰረት መልሶለታል።
አሁን የቀረበው የሰበር አቤቱታ ይሄንኑ በፍደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተጠሪ የሥራ መሪ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሶ በተሰጠው ፍርድ ላይ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታልና ስህተቱ በዚህ ሰበር ችሎት ታይቶ ይታረመልን የሚል ነው። አቤቱታውም በሰበር አጣሪ ችሎቱ ተመርምሮ ተጠሪ የሥራ መሪ ነው በሚል የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሰጠውን ብይን በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የመሻሩ አግባብነት ለተጠሪ ከተሰጠው ስራ ኃላፊነት እና ተግባር አኳያ ለመመርመር ሲባል አቤቱታው ለሰበር ሰሚ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪም የተደረገለትን ጥሪ መነሻ በማድረግ ቀርቦ ግራ ቀኙ በጽሑፍ ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥና ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም በበኩላችን የግራ ቀኙ የሰበር ጽሑፍ ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ተጠሪ የሥራ መሪ ነው? ወይስ ሰራተኛ? የሚለው ነጥብ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት እልባት ላሰጥበት የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል።
በመሰረቱ የሥራ መሪ ማለት በሕግ ወይም እንደየድርጅቱ የስራ ፀባይ በአሰሪው በተሰጠ የውክልና ስልጣን መሰረት የሥራ አመራር ፖላስዎችን የማውጣት የማስፈፀም ከነዚሁ በተጨማሪ ወይም እነዚሁኑ ሣይጨምር ሰራተኛን የመቅጠር፣ የማዛወር፣ የማገድ፣ የማስናበት የመመደብ ወይም የስነ-ስርዓት እርምጃ የመውሰድ ተግባሮችን የሚያከናውንና የሚወሰን ግለሰብ ስለመሆኑ በአሰሪና ሰሪተኛ አዋጁ ቁ. 377/96 3/2/ /ሐ/ አና በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/98 አንቀፅ 2(1) (ሐ) ስር ተመልክቷል። ከዚህ ድንጋጌ ይዘትም መገንዘብ የሚቻለው አንድ ተቀጣሪ ግለሰብ የስራ መሪ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ነጥብ ለይቶ ለመወሰን በቅድሚያ ተቀጣሪው ግለሰብ በቀጣሪው ተቋም እንዲያከናውን የተሰጠው ተግባራት እና የሥራ ኃላፊነቶች እያንዳንዳቸው ምን ምን እንደሆኑ በጥንቃቄ ተመልክቶ በቂ ግንዛቤ መያዝ የግድ መሆኑን ነው። ከዚያ በኃላ በግለሰቡ የሚከናወኑትን የስራ ተግባራት ወይም የሥራ ኃላፊነትቶቹን ከፍ ሲል ከተጠቀሰው የሕጉ ድንጋጌ ይዘት አኳያ አንድ በአንድ በጥንቃቄ አገናዝቦ መመልከቱ እና በመመርመር ተገቢ ወደ ሆነው ድምዳሜ ላይ መድረስን ይጠይቃል።
ከዚህ አኳያ ወደ ተያዘው ጉዳይ ተመልስን ስንመለከተው ተጠሪ በድርጅቱ የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነት የሥራ መደብ ላይ ተመድቦ የዚህን ስራ መደብ ተግባራትን ሲያከናውን የነበረ ስለመሆኑ እና በዚሁ መነሻነትም የድርጅቱ ማኔጅመንት አባልም በመሆኑ ጭምር አጠቃላይ የሆነውን የድርጅቱ ስራ አመራር ውስጥም በመሣተፍ የበኩሉን ድርሻሲያከናውን የነበረ ስለመሆኑ ተጠሪ ራሱ ባቀረበው ክስ አቤቱታ ማመልከቻ፣ በሥር ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ አቤቱታ ማመልከቻ እና በሥር ፍ/ቤት በተደረገው ቃል ክርክር የታመነ ጉዳይ ስለመሆኑ የሥር ፍ/ቤት ውሣኔ ግልባጭ ይዘት ያስረዳል። ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው ተጠሪ በፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነቱ ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና የሥራ ተግባራት እና ኃላፊነቶች በተጨማሪ በድርጅቱ የማኔጅመንት አባልነቱም በድርጅቱ የሥራ አመራር ኃለፊነት ውስጥ ተሣትፎ የነበረው መሆኑን መረዳት ይቻላል።
በፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅነቱ የስራ መደብ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ብዛት የመወሰን፣ በሥሩ ያሉትን ሰራተኞች የመምራት የመቆጣጠር የሥራ አፈፃፀማቸወን የመገምገም፣ ብቃታቸውን የማሣደግ፣ የፕሮጀክቱን ስራ አመራር የማቀድ፣ የመፈፀም፣ የማስተባበር እና የመሣሰሉትን ዋና ዋና የስራ ተግባራት እና ኃላፊነቶችን ሲያከናውን የነበረ ስለመሆኑ ተጠሪ ተመድቦ ይስራበት የነበረውን የሥራ መደብ ስራ መዘርዝር መረጋገጡን እንዲሁ ከሥር ፍ/ቤቱ ውሣኔ ግልባጭ መገንዘብ ይቻላል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ተጠሪ የአመልካች ድርጅት የሥራ መሪነት የሥራ ድርሻ ወይም ሚና ነበረው ከሚያሰኝ በቀር ሰራተኛ ነው ለማለት የሚቻል ሆኖ አላገኘንም በመሆኑም የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተጠሪ የሥራ መሪ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ የሰጠው ፍርድ ተጠሪ በድርጅቱ ማኔጅመንት አባልነቱም ሆነ በፕሮጀክት ስራ አስኪያጅነቱ ሲያከናውናቸው የነበረው የሥራ ተግባራት ኃላፊነቶች እና የሥራ አመራር የሥራ ድርሻነቱን በአግባቡ ያላገናዘበ በመሆኑ ከአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 አንቀጽ 3/2/ሐ/ እና የማሻሻያ አዋጁ ቁ.494/98 አንቀጽ 2/1/ሐ/ አኳያ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል በመሆኑም ተከታዩን ውሣኔ ሰጥተናል።
ውሣኔ
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በኮ/መ/ቁ. 135628 በ2/11/2005 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሥራ ክርክር ችሎት በኮ/መ/ቁ. 81696 በ15/8/2005 ዓ.ም የሰጠው ብይን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሰረት ፀንቷል።
ተጠሪ የሥራ መሪ ናቸው እንጂ ሰራተኛ አይደሉም ብለናል ስለዚህ ጉዳዩ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት የሚስተናገድ አይደለም።
የሰበር ክርክር ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል።
መዝገቡ ተዘግቷል፣ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
ቤ/ዮ
No topics extracted.