No summary available.
ጥቅምት 18 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- የኢትዮጵያ ኤርፖርት ድርጅት ነ/ፈጅ እፀገነት ከድር ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ በሪሁን በላይ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ውሣኔ ይሰጥልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የሥራ ውል መቋረጥን የሚመለከት ነው በሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሣሽ አመልካች ተከሣሽ በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ያቀረበው ክስ ነው። ከሣሽ /ተጠሪ/ 23-10-2002 ዓ.ም ጀምሮ በጥበቃ የሥራ መደብ ተቀጥሬ ስሰራ ተከሣሽ /አመልካች/ 27-04-2004 ዓ.ም በተፃፈ የሥራ ስንብት ደብዳቤ ከ30-05- 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከሥራ ያሰናበታቸው በመሆኑ ወደ ምድብ ሥራዬ እንዲመልሰኝ ይወሰንልኝ ወይም የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍል ፍርድ ይሰጥልኝ በማለት አመልክቷል። አመልካች በተከሣሽነት ቀርቦ ከሣሸ የተመደበበት የሥራ መደብ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሆኖ እያለ ተከሣሽ /ተጠሪ/ 10-02- 2004 ተረኛ ሆኖ ተመድቦ ሲሰራ ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ወደውስጥ ዘልቆ እንዲገባ በማድረግ ሰውየው አውሮፕላን የሚቆምበትና የተከለከለ ቦታ ላይ ቆሞ በፖላሶች ተይዟል። እንዲሁም ከሣሽ በተመሣሣይ ሁኔታ 27-03-2004 ዓ.ም አራት ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ወደ ውስጥ ዘልቀው እንዲገቡ በማድረጉ እና በድርጅቱ ላይ የከፋ ችግር በመፍጠሩ ማስጠንቀቂያ በጽሑፍ ተሰጥቶት የሥራ ውል በሕጋዊ መንገድ የተቋረጠ በመሆኑ የከሣሽ ክስ የሕግ መሰረት የለውም በማለት ተከራክሯል።
የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ተከሣሽ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ የተጠሪን የሥራ ውል ያቋረጠ መሆኑንና ተጠሪ በጥበቃ ሥራ ላይ እያለ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ወደ ድርጅቱ እንዲገቡ በማድረግ ጥፋት የፈፀሙ መሆኑን ገልጿል። ነገር ግን በተጠሪ ጥፋት ምክንያት በድርጅቱ ላይ የተፈጠረ ችግር የልለ በመሆኑ የሥራ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው በማለት አመልካች የተለያዩ ክፍያዎችና የማስጠንቀቂያ ክፍያ ከፍሎ ተጠሪን ከሥራ ያሰናብተው በማለት ውሣኔ ሰጥቷል። በዚህ ውሣኔ ቅር በመሸኘት አመልካች ይግባኝ በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች ለተጠሪ ማስጠንቀቂያ የሰጠ በመሆኑ የማስጠንቀቂያ ክፍያ መክፈል የለበትም በማለት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በዚህ ነጥብ ላይ ብቻ በማሻሻል ውሣኔ ሰጥቷል።
አመልካች በ22-09-2005 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ ማንነታቸው የማይታወቅና ያልተፈቀደላቸውን ሰዎች ወደ ድርጅቱ ውስጥ በማስገባት ድርጅቱን ለከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት የዳረገ መሆኑና አመልካች የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ከሥራ ያሰናበተው መሆኑ ተረጋግጦ እያለ የሥራ ውል የተቋረጠው ከሕግ ውጭ ነው በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት አመልክቷል። ተጠሪ 3-11-2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም የሚለውን ነጥብ በመዘርዘር ተከራክሯል። አመልካች 11-11-2005 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከሥር የክርክር አመጣጥና በሰበር የቀረበው የጽሑፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች ተጠሪን ከሥራ ያሰናበተው ከሕግ ውጭ ነው በማለት የሰጡት ውሣኔ በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው ተጠሪ በተሰማራበት የጥበቃ ሥራ ላይ እያለ ጥቅምት 10 ቀን 2004 ዓ.ም ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ሣይፈተሽ ወደ ኦውሮፕላኖች ማረፊያ ድርጅቱ እንዲገባ ያደረገና ሰውየውም አውሮፕላኖች መቆሚያ ቦታ ላይ በፖላሶች መያዙ በበታች ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል። ተጠሪም ይህንን ጥፋት የፈፀመ መሆኑን በማመን በጽሑፍ ይቅርታ የጠየቀ መሆኑና በጋራዥና ትራንስፖርት በር ላይ ተመድቦ እንዲሰራ አመልካች 16-02-2004 ዓ.ም ውሣኔ የሰጠ መሆኑን ግራ ቀኙ በሥርና በሰበር ደረጃ ካደረጉት ክርክር ተረድተናል።
አመልካች ተጠሪን 10-2-2002 ዓ.ም በማስጠንቀቂያ ያለፈው ቢሆንም ተጠሪ ሕዳር 27 ቀን 2004 ዓ.ም በጥበቃ ሥራ ላይ እያለ የጥበቃ ቀጠናውን ክፍት ትቶ በመሄዱ አራት ሰዎች ወደ ውስጥ ገብተው ክላኒኩ አከባቢ ሲደርሱ በፖላስ የተያዙ መሆኑ በበታች ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል። ተጠሪ 27/03/2004 ዓ.ም. ይህንን ጥፋት ከፈፀመ በኃላ የጥበቃ አስተባባሪው በትራንስፖርትና ጠቅላላ አገልግሎት ቡድን ሪፖርት ያቀረበ መሆኑና የትራንስፖርት አገልግሎት ቡድን ሁኔታውን ከመረመረ በኃላ የተጠሪ የሥራ ውል ታህሣስ 30 ቀን 2004 ዓ.ም የሚያበቃ መሆኑን ገልፆ የተጠሪ የስራ ውል ለአንድ ወር ብቻ እንዲራዘምና ይህም የቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጫ ጊዜ ሆኖ ተቆጥሮ የሥራ ውላቸው እንዲቋረጥ ታህሣስ 23 ቀን 2004 ዓ.ም ውሣኔ የሰጠ መሆኑን ተረድተናል።
ተጠሪ የሚሰራበት ድርጅት የጥበቃ ሥራ በከፍተኛ ጥንቃቄ መከናወን የሚገባውና ለድርጅቱም ሆነ ለተገልጋዮና ደንበኞች ደህንነት አጠባበቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ተረጋግጧል። ተጠሪ ይህንን የሥራ ተግባሩን በአግባቡና በጥንቃቄ ባለመፈፀሙ የድርጅቱን ደህንነት ለከፍተኛ ችግር ያጋለጠና ማንነታቸው ያልታወቀና ያልተፈተሹ ሰዎች ወደ ድርጅቱ ዘልቀው ገብተው በፖላስ የተያዙ ስለመሆኑ ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል። ተጠሪ የፈፀመው ጥፋት በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1/ሸ/ የሚሸፈንና የተጠሪን የሥራ ውል ያለ ማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያስችል በቂ ምክንያት ሆኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ የጥበቃ ተግባሩን በአግባቡ ባለማከናወኑና ሰዎቹ ሣይፈተሹ ወደ ድርጅቱ ዘልቀው በመግባታቸው በአመልካች ላይ የደረሰበት የፀጥታና ደህንነት ችግር /ጉዳት/ የለም በማለት ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ሲሉ በማለት የሰጡት ውሣኔ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 17/1/ሸ እና /ቀ/ እንዲሁም አንቀጽ 14/2/ሀ/ ድንጋጌ መሰረታዊ ይዘት መንፈስ አላማ ያላገናዘበ ሆኖ አግኝተነዋል።
ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካች የተጠሪን የሥራ ውል በአንድ ወር በማራዘምና ማስጠንቀቂያ በመስጠት ከተጠሪ ጋር ያደረገውን የሥራ ውል ማቋረጡ አመልካች የተጠሪን መብት ለመጠበቅ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረጉን የሚያሣይ እንጂ ሕገ ወጥ ተግባር ሆኖ አላገኘነውም። በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች የተጠሪን የሥራ ውል ያቋረጠው ከሕግ ውጭ ነው በማለት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ ተሽሯል።
አመልካች ተጠሪን ያሰናበተው በሕግ አግባብ በመሆኑ አመልካች የካሣ ክፍያ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም በማለት ወሰነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሣቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.