No summary available.
መስከረም 23 ቀን 2006 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አመልካች፡- ወ/ሮ የውብዳር ንጋቱ ተጠሪ፡- ገነት ሆቴል ነ/ፈጅ ፀጋዬ ጌታነህ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የቀረበውን የግል የስራ ክርክር የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኗ አመልካች ባሁኑ ተጠሪ ላይ በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው።የአመልካች የክስ ይዘትም በተከሳሽ ድርጅት ከ1975 ዓ/ም እስከ ጥር 21 ቀን 2004 ዓ/ም ድረስ ተቀጥረው እየሰሩ መቆየታቸው፣በደረሰባቸው የእግር በሽታ ምክንያት ከጥር 21 ቀን 2004 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን 2004 ዓ/ም ድረስ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምና ተከታትለው እያለና ስለሁኔታው ለስራ ባልደረቦቻቸው አቶ በላይ ተገኝ ነግረው እሳቸውም ለአቶ ታደሰ ሶልቤ ለተባሉት ኃላፊ ነግረው እያለ ድርጅቱ ይህንኑ ወደ ጎን በመተው የአመልካችን የስራ ውል ያቋረጠ መሆኑን ዘርዝረው የተጠሪ እርምጃ ሕገ-ወጥ ነው ተብሎ ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሐቸው ወደ ስራ እንዲመልሳቸው ወይም ሕጋዊ ክፍያዎች ተከፍሐቸው እንዲሰናበቱ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።የአሁኑ ተጠሪ ለክሱ በሰጠው መልስም አመልካች በተደጋጋሚ የስራ ሰዓት ባለማክበራቸው በማስጠንቀቂያ ታልፈው በመጨረሻም ከጥር 21 ቀን 2004 ዓ/ም ጀምሮ ከስራ ስለቀሩ የተሰናበቱ መሆኑን፣ስለመታመማቸው ተጠሪ የማያውቅ መሆኑን በመግለጽ ስንብቱ ሕጋዊ ነው፣ከተጠየቁት የክፍያ አይነቶች መካከልም ያልተከፈላቸው ደመወዝ፣የአመት ፍቃድ ክፍያና የሰርቪስ ቻርጅ ተገቢነት ያላቸው መሆኑና ልሎች የክፍያ አይነቶች ግን የማይገባቸው መሆኑን ጠቅሶ ተከራክሯል።የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ስለመታመማቸው ለተጠሪ ያላማሳወቃቸው መረጋገጡን፣አሳውቀዋል ቢባል እንኳን ሕመማቸው ተጠሪ ዘንድ ቀርበው በማግስቱ ለአሰሪያቸው ማሳወቅ/ፍቃድ ማግኘት የማይከለክላቸው ስለነበረና ይህንንም በአግባቡ ስላላሳወቁ አመልካች ከጥር 21 ቀን 2004 ዓ/ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናትና ከዚያ በላይ የቀሩት ያለበቂ ምክንያት ነው የሚል ምክንያት በመያዝና የአዋጅ ቀጥር 377/1996 አንቀጽ 27(1(ለ)) ድንጋጌን በዋቢነት በመጥቀስ የስራ ስንብት እርምጃው ሕጋዊ ነው በማለት ወስኗል።በዚህ ውሳኔ የአሁኗ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ጸንቷል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም አመልካች በሕመም ምክንያት የቀሩ መሆኑን የሚያሳይ የህክምና ማስረጃ ከመቅረቡም በላይ ስለሁኔታው ለተጠሪ አሳውቀው እያለ ይኼው ታልፎ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ተብሎ መወሰኑ ያላግባብ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው።አቤቱታቸው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በጽሑፍ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።እንደመረመረውም አመልካች በሕመም ምክንያት ህክምና ላይ የቆዩና ይህንንም በስራ ባልደረባቸው በኩል ለተጠሪ አሳውቀው መሆኑ ተረጋግጦ እያለ ስለሁኔታው በአካል ቀርበው ለተጠሪ ለማሳወቅ ህመሙ ክልከላ የማያደርግ ነው ተብሎ ከአምስት ተከታታይና ከዚያ በላይ የስራ ቀናት ከስራ ስለቀሩ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ተብሎ መወሰኑ በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላመረመር የሚገባው ሁኖ ተገኝቷል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ከጥር 21 ቀን 2004 ዓ/ም እስከ ጥር 30 ቀን 2004 ዓ/ም ድረስ በህመም ላይ ሁነው ህክምና ሲከታተሉ የነበሩ መሆኑን በሐኪም ማስረጃ የተረጋጠ ፍሬ ነገር ሲሆን አከራካሪው ፍሬ ነገር ስለህመሙ ለተጠሪ ማሳወቅ ያለማሳወቃቸው ሁኖ ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን የተሰጠው የስር ፍርድ ቤት በዚህ ረገድ ከአሰፈራቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ ለውሳኔው አብይ ምክንያት ያደረገው የህመሙ አይነት አመልካችን በአካል ቀርበው ለተጠሪ ስለህመሙ ከማሳወቅና ፈቃድ በሕጉ አግባብ ከመጠየቅ አይከለክላቸውም የሚል መሆኑን ነው።
በመሰረቱ አንድ ሰራተኛ በሕመም ምክንያት ከስራ ከቀረ ስለሁኔታው ለአሰሪው ማሳወቅና ፈቃድም ማግኘት ያለበት መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 85(4) ድንጋጌ ስር ከተመለከተው ድንጋጌ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።ድንጋጌው የህመም ፈቃድ ማግኘት በሕጉ የተጠበቀ መብት መሆኑና መብቱን ለማግኘት በቅድሚያ መሟላት ስለአለባቸው ሁኔታዎች በግልጽ የሚያስቀምጥ ቢሆንም ስለሁኔታው ለአሰሪው ያለማሳወቅ የሚያስከትለውን ውጤት ግን በግልጽ አያስቀምጥም።ይሁን እንጂ ሕመም ከስራ ለመቅረት እንደበቂ ምክንያት ላወሰድ የሚገባው መሆኑን ሕግ አውጪው ታሳቢ አድርጎ የሕመም ፈቃድ ማግኘትን መብት የደነገገ መሆኑ ግንዛቤ ከተወሰደ በሕጉ አግባብ የሕመም ፈቃድ ያልወሰደ ስለመሆኑ የተረጋገጠ ሰራተኛ ከስራ የቀረው በበቂ ምክንያት ነው ተብሎ የሚገመትበት አግባብ ስለማይኖር ያለበቂ ምክንያት ከስራ ስለመቅረትና ውጤቱን የሚደነግገው የአዋጁ አንቀጽ ለጉዳዩ ተፈፃሚ የማይሆንበት ሕጋዊ ምክንያት የለም።አዋጁ በአሰሪና በሰራተኛ መካከል ያለውን ግንኙነት በተለይ ለመግዛት ተብሎ ታስቦ የወጣ በመሆኑ በአዋጁ ውስጥ ያሉትን ድንጋጌዎችን አስተሳስሮ ተገቢውንና የአዋጁን ዓላማና መንፈስ የሚያሳካ ትርጉም ለአንድ ድንጋጌ መስጠት በሕግ አተረጓጎም ደንቦችም የተፈቀደ ጉዳይ ነው።
ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው አመልካች ስለመታመማቸው የሚያረጋግጥ የህክምና ማስረጃ ከሚመለከተው የህክምና ተቋም የወሰዱ መሆኑና ይህንኑም በስራ ባልደረባቸው በኩል ለተጠሪ ማሳወቃቸው በፍሬ ነገር ደረጃ ተቀባይነት ከአገኘ አመልካችን ያመማቸው ሕመም በአካል ቀርበው ለተጠሪ ለማሳወቅ ወይም ፍቃድ ለማግኘት የሚከለክላቸው አይደለም ተብሎ ከስራ ስለመቅረታቸው ያቀረቡት ምክንያት በቂ አይደለም ላባል የሚችል አይደለም።አንድ አሰሪ የህመም ፈቃድ ለሰራተኛው መስጠት እንዲችል ስለሁኔታው እንዲያውቅ የሚደረገው መሰረታዊ አላማም ሰራተኛው ከስራ በመቅረቱ ምክንያት የሚፈጠረውን ክፍተት በተገቢው መንገድ እንዲሞላ ለማድረግ ምርትና ምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳይፈጠርበት ነው ተብሎ የሚታመን መሆኑን አዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 85 ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ በመግቢያው ከተመለከተው የአዋጁ መሰረታዊ አላማ ጋር አንድ ላይ በማንበብ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።ስለሆነም ተጠሪ አመልካቿ በሕመም ላይ የነበሩ መሆኑን ከአወቀ በስራው ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር ተገቢውን ለማድረግ በሚያስችለው ሁኔታ ውስጥ የነበረ መሆኑን ተገንዘበናል።ይህ ሁኖ እያለ አመልካችን ያለበቂ ምክንያት ከስራ ቀርተዋል በማለት የስራ ስንብት እርምጃ መውሰዱ የሕጉን መንፈስና ይዘት ያገናዘበ ባለመሆኑ ሕገ ወጥ ነው።ስለሆነም የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ከዚህ አንጻር መመልከት ሲገባቸው አመልካች በአካል ቀርበው ለተጠሪ ማሳወቅ ነበረባቸው በሚል ምክንያት ላይ ትኩረት በማድረግ ስንብቱ ሕጋዊ ነው ሲሉ የደረሱበት ድምዳሜ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል።
ቀጥሎ የተመለከትነው ውጤቱን ነው።አንድ ሰራተኛ በአሰሪው ከስራው የተሰናበተው ህገ ወጥ በሆነ እርምጃ መሆኑ ከተረጋገጠ ውጤቱ ሰራተኛው ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራው እንዲመለስ ማድረግ ወይም በዚህ ምትክ ሕጋዊ ክፍያዎች ተከፍለውት እንዲሰናበት ማድረግ ስለመሆኑ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 39 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ያሳያሉ።እነዚህ በሕጉ የተመለከቱት ውጤቶች የሚወሰኑበት ምክንያትም የአዋጁን መሰረታዊ ዓላማ ያገናዘበ መሆን ያለበት ስለመሆኑ ከድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።በልላ አገላለፅ የእርምጃው ውጤት የሰራተኛውን የስራ ዋስትና እና የኢንዲስትሪውን ሰላም ለመጠበቅ በሚያስችል መንገድ ላወሰን እንደሚገባው የድንጋጌዎቹ መንፈስና ይዘት ያሳያል።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካችን ውዝፍ ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረግ ተገቢነት ያለው ሁኖ አልተገኘም።ምክንያቱም ለዚህ ክርክር መነሻ የሆነው ምክንያት ከመከሰቱ በፊትም አመልካች ከስራ በተደጋጋሚ ይቀራሉ በሚል ተጠሪ በማስጠንቀቂያ ያለፋቸው መሆኑን የክርክሩ ሂደት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ አመልካች ከተጠሪ 1ኛ ምስክር ከነበሩትና የቅርብ አለቃቸው ከሆኑት ሰው ጋርም በጥሩ ግንኙነት ውስጥ ያለመሆናቸውን፣ይልቁንም በመካከላቸው በተፈጠረው ፀብ የወንጀል ክስ አቤቱታ አቅርበው በሚመለከተው አካል ዘንድ በመታየት ላይ እንደሚገኝ ለዚህ ችሎት ባቀረቡት ክርክር የገለፁ በመሆኑ አመልካች ወደ ስራው ቢመለሱ ከተጠሪ ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት ይኖራቸዋል፣በስራ ቦታው ላይ የኢንዲስትሪ ሰላም ይሰፍናል ብሎ ለመገመት የሚያስቸግር መሆኑን የሚያሳዩ ምክንያቶች መሆኑን ክርክሩ የሚያሳይ ነውና።ስለሆነም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 43(3) መሰረት አመልካች ወደ ስራ ከሚመለሱ ይልቅ በምትኩ ሕጋዊ ክፍያዎች ተከፍሐቸው እንዲሰናበቱ ማድረግ ተገቢ ሁኖ ተገኝቷል።
ሲጠቃለልም ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች የተጠሪ እርምጃ ሕገ ወጥ ሲሆን ውጤቱን በተመለከተ ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 43(3) መሰረት መወሰን ያለበት ሁኖ ስለአገኘን ስንብቱን አስመልክቶ የተሰጠው የበታች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ነሐሴ 22 ቀን 2004 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥር 28 ቀን 2005 ዓ/ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረተ ተሻሽሐል።
የተጠሪ እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ብለናል።
አመልካች ወደ ስራ ከሚመለሱ ይልቅ በምትኩ ሕጋዊ ክፍያዎች፤በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 39 መሰረት የስራ ስንብት ክፍያ፣የሚገባው በአንቀጽ 42/4/ ካሳ፤በአንቀጽ 35/1/ሀ/ መሰረት የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ተከፍሐቸው ይሰናበቱ ብለናል።በስር ፍርድ ቤቶች የተወሰኑት የጥር ወር 2004 ዓ/ም የ21 ቀን ደመወዝ፣የታህሳስ ወር እና የጥር ወር 21 ቀናት 2004 ዓ/ም የሰርቪስ ቻርጅ ክፍያና የ43 ቀናት የአመት ፍቃድ በገንዘብ ተለውጦ የሚከፈለው ክፍያ እንደፀኑ ናቸው።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.