No summary available.
ግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ተሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ዮቴክ ኮንስትራክሽን ኃ.የተ.የግል ማህበር - ነ/ፈጅ ፋሲል አስራት ቀረቡ ተጠሪ፡- 1/ አቶ ገብሬ በላይነህ 2/ አቶ ግርማ ስንታየሁ 3/ አቶ አበጀ ካሴ አልተጠሩም 4/ አቶ መጣለም ገነት 5/ ወ/ሮ ገበያነሽ መኮንን **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አግባብ የቀን ሰራተኛ ሆነው የተቀጠሩ ሰራተኞች የሳምንት እረፍት ቀናት የዓመት እረፍት ቀናት እና የህዝብ በዓላት ቀናት ክፍያ ላያገኙ የሚችሉበት ሕጋዊ አግባብ መኖር ያለመኖሩን የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው በባህርዳር ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁን ተጠሪዎች ከሳሾች፣ አመልካች ደግሞ ተከሳሽ ነበር። የተጠሪዎች የክስ ይዘትም፡- በአመልካች ድርጅት በተለያየ ጊዜ በግንበኝነትና በአናፂነት ስራ ተቀጥረው በመስራት ላይ መሆናቸውንና ያገለገሉበትን ጊዜ ጠቅሰው በስራ ላይ በቆዩባቸው ጊዜያት ያልተጠቀሙበት የዓመት ፈቃድ የነበራቸው ከመሆኑም በተጨማሪ የሳምንት እረፍት የህዝብ በዓላት የሰሩበት ታስቦ ያልተከፈላቸው መሆኑን፣ ካልንደሩ የማይዘጋቸው ቀናትም ያላአግባብ ተዘግተው ስራ ሳይሰሩ የቀሩ መሆኑን ጠቅሰው ለእያንዳንዳቸው ገንዘቡ እንዲከፈላቸው ይወሰን ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና የፍሬ ነገር ክርክር አቅርቧል።
አመልካች በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ገልፆ የተከራከረው ጉዳዩ የወል የስራ ክርክር በመሆኑ በፍርድ ቤት ላታይ የሚገባው አይደለም፣ ይህ ከታለፈም ክሱ በይርጋ የታገደ ነው የሚሉትን ነጥቦችን በማንሳት ነው። በፍሬ ነገር ረገድም ተጠሪዎች በቀን የሚከፈላቸው ክፍያ በክሳቸው ላይ ያቀረቧቸው የክፍያ ጥያቄዎችን ክፍያ ከግምት ውስጥ አስገብቶና አጠቃልሎ የያዘ በመሆኑ የተለየ ክፍያ ላኖር የሚችል ስለመሆኑ የሚሰራበት መሆኑንና በቅጥር ውሉ ላይ የተለየ እንደማይደረግ እና ክፍያ የሚፈፀምላቸው በካርዳቸው ላይ ስራ የተሰራባቸው ቀናት ተቆጥረው ስራ ለተሰራበት ቀን ብቻ እንደሚከፈል የተስማሙ ስለሆነ ጥያቄው አግባብነት የለውም በማለት ተከራክረዋል። ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የወረዳው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ በአመልካች በኩል የቀረቡትን መከራከሪያ ነጥቦችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎ አመልካች ለተጠሪዎች የሳምንት እረፍት፣ የሕዝብ በዓላት እና የዓመት እረፍት ክፍያ በገንዘብ ተለውጦ እንዲከፍል ሲል ወስኗል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪዎች በቀን በሰሩት ስራ መጠን ታስቦ ክፍያ የሚፈጸምላቸው በመሆኑ የጠየቁትን የክፍያ አይነቶች ላያገኙ አይችሉም በማለት የወረዳው ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ የሰጠውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ሽሮታል። ከዚህም በኋላ የአሁኑ ተጠሪዎች የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ ክርክሩ የግል የስራ ክርክር በመሆኑ በመደበኛ ፍርድ ቤት መታየቱ ተገቢ መሆኑን፣ ተጠሪዎች በቀን በሰሩት ታስቦ በወር የደመወዝ ክፍያ የሚከፈላቸው መሆኑ የተረጋገጠ መሆኑን በምክንያትነት ይዞና የሕጉ ጥያቄ ከኢ.ፍ.ዲ.ሪ ህገ መንግስትም ሆነ ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንፃር ሲታይ ለክሱ መሰረት የሆኑትን የመብት ጥያቄዎች ተጠሪዎች ለመጠየቅ የማይችሉበት ሕጋዊ ምክንያት የልለ መሆኑን ጠቅሶ ተጠሪዎች የሳምንት እረፍት ጊዜ፣ የሕዝብ በዓላትና በካልንደሩ ላልተዘጉት ቀናት ክፍያ እንደሚገባቸው፣ የዓመት የረፍት ጊዜአት ግን የስራ ውሉ ባልተቋረጠበት ሁኔታ በገንዘብ ተቀይሮ ይከፈልን በማለት ተጠሪዎች መጠየቅ የማይችሉ መሆናቸውን ዘርዝሮ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የወረዳው ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማሻሻል ወስኗል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የተጠሪዎች ጥያቄ ከራሳቸው አልፎ ልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ተቀጥረው የሚሰሩትን በርካታ ሰራተኞችን ተመሳሳይ ጥያቄ እንዲያነሱ የሚያደርግ ሆኖ እያለ ክርክሩ የግል የስራ ክርክር መባሉ ያላግባብ ነው፣ ተጠሪዎች በስራ ላይ በቆዩባቸው ከሶስት አመታት የሚበልጥ ጊዜ ለሰሩባቸው ቀናት ብቻ እየታሰበ ሲከፈላቸው የነበረ መሆኑን፣ በቀን ታስቦ የሚከፈለው ገንዘብ የእሁድና የበዓላት ቀናትን የሚያጠቃልል መሆኑን ስራ ሲጀምሩ በተደረገው የስራ ውል ተስማምተው ክፍያው በዚሁ መልክ ሲፈፀም እና እየተሰራበት ያለ ሆኖ እያለ ለተጠሪዎች የተጠየቁት ክፍያዎች እንዲከፈሉ መወሰኑ ያለግባብ ነው በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ የተጠቀሰው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምሮታል። ጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ችሎት ሲቀርብ የተያዘው ጭብጥ፡- በተጠሪዎች የተጠየቁት የበአላት፣ የሳምንት እረፍትና የዓመት እረፍት ክፍያዎች አመልካች በስራ ላይ ተጠሪዎች ላሳለፉት ቀናት ብቻ እንጂ እነዚህን ክፍያ ላፈጸም አይገባም፣ ተጠሪዎች ከሶስት አመት በላይ በሰሩበት ጊዜም እነዚህን ጥቅማጥቅሞች ጠይቀው አያውቁም በማለት ያቀረበው ክርክር ውድቅ መደረጉ ተገቢ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ሲባል ነው። ይህ ችሎትም ጉዳዩን ከዚህ ጭብጥ አንፃር ብቻ መርምሯል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ድርጅት በኮንስትራክሽን ስራ የተሰማራና ተጠሪዎችን ቀጥሮ ሲያሰራ የነበረው በግንበኝነትና በአናፂነት ስራ መሆኑን፣ አመልካች ለተጠሪዎች ለቀን ስራ የሚያስበው የደመወዝ መጠን የተለያየ ሆኖ አከፋፈሉ ግን በወር ተጠቃልሎ በፔሮል የሚከፈል መሆኑን ነው።
በመሰረቱ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አግባብ ሲታይ በአጠቃላይ የቅጥር ውል አይነቶች ለተወሰነ ሥራ ወይም ለተወሰነ ጊዜ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ላደረግ የሚችሉ ናቸው። ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ሕጉ የቅጥር ውል አይነቱ ቋሚም ይሁን ጊዜያዊ ለሰራተኛው በሕጉ የተፈቀዱ ጥቅሞችና ከለላዎች የቅጥሩ አይነት መሰረት ተደርጎ ልዩነት ማድረግ የማይቻል መሆኑን ነው። በመሆኑም ጊዚያዊ ሰራተኞችም ሆነ ቋሚ ሰራተኞች በሕጉ የተጠበቁላቸውን ጥቅማጥቅሞችንና ከለላዎችን እንደሚያገኙ የህጉ ይዘትና መንፈስ ያሳያል። ከሁሉም በላይ የኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 42(2) ድንጋጌ ሲታይ ሰራተኞች በአግባቡ የተወሰነ የስራ ሰዓት እረፍት፣ የመዝናኛ ጊዜ፣ በየጊዜው ከክፍያ ጋር የሚሰጡ የእረፍት ቀኖች፣ ደመወዝ የሚከፈልባቸው የሕዝብ በዓላት እንዲሁም ጤናማና አደጋ የማያደርስ የስራ አካባቢ የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ሲሆን ይኼው የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግስት ድንጋጌ እነዚህን ጥቅሞችና ከለላዎችን የሚያገኙትን ሰራተኞች ብሎ በጥቅሉ ከማስቀመጥ ባለፈ የቅጥር አይነቱን ለይቶ አላሰፈረም። በመሆኑም ጊዜያዊ ሰራተኞችም ቢሆኑ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡትን ጥቅሞችና ከለላዎች ተጠቃሚ የማይሆኑበት አግባብ የለም።
አመልካች ተጠሪዎችን የቀጠረው በኮንስትራክሽን ስራ መሆኑ ከተረጋገጠ የቅጥሩ አይነት ለተወሰነ ስራና ጊዜ የተቀጠሩ መሆናቸው ግልፅ ነው። እንዲህ ከሆነ ከላይ እንደተጠቀሰው ተጠሪዎች በሕጉ የተጠበቁላቸውን ጥቅሞች ከለላዎች ተጠቃሚ የማይሆኑበት ምክንያት የለም። ከዚህ አንፃር ሲታይ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ተጠሪዎች የመብቶቹ ተጠቃሚ የማይሆኑበት ሕጋዊ ምክንያት የለም በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል ሕጋዊ ሆኖ አግኝተናል። ልላው አመልካች ከጊዜ ጋር በማያያዝ የሚያሳየው ክርክር ሲታይ ተጠሪዎች በአመልካች ድርጅት ከሶስት አመታት በላይ ሲሰሩ የጥቅማ ጥቅሞችን ጥያቄ አንስተው ያለማወቃቸው የሚገልፅ ሲሆን እንዲህ መሆኑ ተጠሪዎች ጥያቄውን ከእነጭራሹ እንዳይጠይቁ የማድረግ ሕጋዊ ውጤት የለውም። ምክንያቱም በሕጉ ተለይቶ የተቀመጠው የይርጋ ጊዜ ጥቅማ ጥቅሞችን ከማግኘት የሚያግዳቸው ከሚሆን በስተቀር የአመልካችን እርምጃ ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ ላያደርግ የሚችልበት ሕጋዊ አግባብ የልለ መሆኑን ከአዋጁ አንቀጽ 162 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በመሆኑም አመልካች ተጠሪዎች ለሶስት አመታት ያህል ጥያቄውን አላቀረቡም የሚለው ክርክር ተጠሪዎች ጥያቄውን ለማንሳት አይችሉም ለማለት የማያስችል ሲሆን የስር ፍርድ ቤቶች በይርጋ የማይታገዱትን ክፍያዎች ለይተው የወሰኑ በመሆኑ በዚህ ረገድም የሕግ ስህተት አለ ለማለት የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።
የዓመት እረፍትን በተመለከተም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ለተጠሪዎች እንደሚገባቸው፣ ግን የዓመት እረፍቱን መጠቀም ሲገባቸው በስራ ላይ እያሉ በገንዘብ ተቀይሮ እንዲከፈላቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 77(5) ድንጋጌ አንፃር ተገቢነት የልለው መሆኑን ገልፆ መወሰኑ ሕጋዊ እንጂ የሚነቀፍ አይደለም። ተጠሪዎች ስራ ለመስራት ዝግጁ ሆነው አመልካች ለተጠሪዎች ስራ የመስጠት ግድታውን ያለመወጣቱ የተረጋገጠ ሲሆን አመልካቹ ለተጠሪዎች ለእነዚህ ቀናት ደመወዝ የመክፈል ሕጋዊ ኃላፊነት የሚያስከትልበት ስለመሆኑ ከአዋጁ አንቀጽ 12(1(ሀ))፣ 12(2)፣ 53 እና 54 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በመሆኑም በዚህ ረገድ የተሰጠው ውሳኔም የሚነቀፍ ሆኖ አልተገኘም።
ሲጠቃለልም ተጠሪዎች ለተወሰነ ስራ የተቀጠሩና ደመወዝ በቀን ሂሳብ ታስቦ በወር የሚከፈላቸው ቢሆንም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 ለማንኛውም ሰራተኛ የተጠበቁትን ጥቅማጥቅሞችንና ከለላዎች የማግኘት መብታቸውን የሚነፈጉበት ሕጋዊ መሰረት የልለ በመሆኑ በይርጋ ያልታገዱትን ጥቅማ ጥቅሞችን ብቻ በመለየት ተጠሪዎች እንዲያገኙ ተብሎ በተሰጠው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለ ለማለት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
በአማራ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ጥር 06 ቀን 2005 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
ተጠሪዎች በቀን ሂሳብ ታስቦ በወር ደመወዝ የሚከፈላቸው ለተወሰነ ስራ የተቀጠሩ ሰራተኞች ቢሆንም የሳምንት እረፍት፣ የሕዝብ በዓላት እረፍት ደመወዝ ክፍያ የማግኘት፣ የዓመት እረፍት የማግኘትና ያለካልንደር የተዘጉ ቀናት ክፍያ ደመወዝ የማግኘት መብት አላቸው ተብሎ መወሰኑ ተገቢ ነው ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
የካቲት 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው እግድ ተነስቷል። ለሚመለከታቸው አካላት ይፃፍ።
No topics extracted.