No summary available.
መጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ/ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ ሙስጠፋ አሕመድ አመልካች፡- ሆራይዘን አዲስ ጎማ (አ.ማ) ጠበቃ ሒሩት መለሰ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ መኮንን ዓለሙ ቀረቡ መዝገቡን ተመርምሮ የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የሥራ ሥንብት ህጋዊነት የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ ማመልከቻ ነው። ተጠሪ አመልካች በተለያዩ የሥራ መደቦች ሲያሰራኝ ቆይቶ ከሕግ ውጭ ከሥራ ያሰናበተኝ ስለሆነ ውዝፍ ደመወዝ ከፍሎ ወደ ሰራ እንዲመልሰኝ ወይም በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሰረት የተለያዩ ክፍያዎችን እንዲከፍል ይወሰንልኝ የሚል ይዘት ያለው ክስ አቅርቧል። አመልካች በተከሣሽነት ቀርቦ ከሣሽ /ተጠሪ/ በድርጅቱ ላይ ጉዳት አድርሷል፤ጆንያ ተቆጣጥሮና ተከትሎ እንዲያስረክብ ትእዛዝ ተሰጥቶት ለልሎች የቀን ሰራተኞች ኃላፊነቱን በመተው 390 /ሶስት መቶ ዘጠና/ ጆንያ ነው ተብሎ የተጫነው፣ መውጫ በር ላይ ሲቆጠር 580 /አምስት መቶ ሰማኒያ/ ሆኖ ተገኝቷል። ይህም ተከሣሽ 190 /አንድ መቶ ዘጠና ጆንያ/ ከድርጅቱ ላያሰወስድ የነበረ በመሆኑ ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ለማሰናበት የሚያስችል ጥፋት ነው በማለት ተከራክሯል። ተጠሪ በወቅቱ 190 ጆንያ በትርፍ ተጭኖ በር ላይ በጥበቃ ሰራተኞች የተያዘ መሆኑን ሣይክድ ጥፋቱ የተፈፀመው አሰሪው /አመልካች/ ልምድና ክህሎት በልለኝ የሥራ መደብ ላይ ስለመደበኝና በአንድ ጊዜ ተደራራቢ ሥራ እንድሰራ ትእዛዝ ስለሰጠኝ ነው በማለት ተከራክሯል።
የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ ተጠሪ በተመደበበት የሥራ መደብ በቂ የሆነ ልምድና ክህሎት ስለልለውና አመልካች ተደራራቢ ሥራ እንዲሰራ ትእዛዝ ስለሰጠው 190 ጆንያ በትርፍነት ተጭኖ ላወጣ ሲል በግቢው ጥበቃ ሰራተኞች ተይዟል። ይህንን ጥፋት የፈፀመው በልምድ ማነስና በሥራ ጉጉት ስለሆነ ጥፋቱ ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውሉን ለማቋረጥ የሚያስችል አይደለም፤ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው፤ አመልካች የስድስት ወር ደመወዙን ከፍሎ ተጠሪን ወደ ሥራው ይመልሰው በማለት ውሣኔ ሰጥቷል። አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ካለ በኃላ አመልካች በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት የተለያዩ ክፍያዎችን በመክፈል ተጠሪን ያሰናብተው በማለት ወስኗል።
የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህንን ውሣኔ በመቃወም ነው። ተጠሪ በኃላፊነት የተረከበውን ጆንያ በትእዛዙ መሰረት ቀንሶ እንዲጭን የማድረግና የድርጅቱ ትርፍ ጆንያ ያልተጫነ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት። ተጠሪ ይህንን ኃላፊነቱን በአግባቡ ስላለመወጣቱ 390 /ሶስት መቶ ዘጠና/ ጆንያ እንደተጫነ በመፈረም የሰጠው ማረጋገጫ እውነተኛ መሆኑና 580 /አምስት መቶ ሰማኒያ/ ጆንያ ተጭኖ የተገኘ መሆኑ ስለተረጋገጠ በአዋጅ 377/96 አንቀጽ 27/1/ሸ መሰረት ያለማስጠንቀቂያ መሰናበቱ ሕጋዊ ሆኖ እያለ ሕገ ወጥ ነው መባሉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት ጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የሰበር አቤቱታ አቅርቧል።
ተጠሪ በበኩሉ የካቲት 6 ቀን 2005 ዓ.ም በተፃፈ መልስ በወቅቱ ስህተት የተከሰተው አመልካች በሁለትና ከዚያ በላይ ሰው መስራት ያለበትን ሥራ በእኔ በማሰራቱ ከፍተኛ የሥራ መደራረብ ስለነበረብኝ ነው። እኔ ንብረቱን ለግል ጥቅሜ አላዋልኩም። ስለዚህ ከሃያ አመት በላይ ስሰራ በመልካም ባህሪ የሰራሁ በመሆኑ ጥፋቱ የሥራ ውሉን ለማቋረጥ የሚያስችል አይደለም ተብሎ የተሰጠው ውሣኔ ተገቢ ነው የሚል መከራከሪያ አቅርቧል።
አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን ተጠሪ በሕጋዊ መንገድ መጫን ከሚገባው ጆንያ ውጭ አንድ መቶ ዘጠና ጆንያ በትርፍነት ተጭኖ እንዲወጣ ሲያደርግ በጥበቃ ሰራተኞች የተያዘ ቢሆንም ጥፋቱ የሥራ ውሉን ለማቋረጥ የሚያስችል አይደለም በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው ተጠሪ 390 /ሶስት መቶ ዘጠና ጆንያ/ ብቻ እንዲያስጭንና ወጭ እንዲያደርግ ትእዛዝ ተሰጥቶት የነበረ መሆኑንና ተጠሪ 390 ጆንያ ነው በማለት ያስጫነው ማረጋገጫ የሰጠበት ጭነት በጥበቃ ሰራተኞች ሲፈተሽና ሲቆጠር 580 ጆንያ ሆኖ መገኘቱ በዚህ ምክንያትም አመልካች 190 /አንድ መቶ ዘጠና ጆንያ/ ወጭ ላደረግበት የነበረ መሆኑን ግራ ቀኙ አልተካካዱም ተጠሪ 190 ጆንያ በትርፍ ተጭኖ መገኘቱን ሣይክድ የልምድ ማነስ ስለነበረብኝ የሥራ መብዛትና መደራረብ ስላለብኝ ነው ስህተቱ የተሰራው የሚል መከራከሪያ አቅርቧል።
ተጠሪ ተደራራቢ የሥራ ትእዛዝ ከደረሱት ሥራዎችን በቅደም ተከተልና በአግባቡ የመፈፀምና በጊዜ አጥረትም ምክንያት ሣይሰራው የቀረውን ሥራ ኃላፊነት ሪፖርት ከሚያደርግ በስተቀር የድርጅቱ ንብረት በማስመዝበር ለሰራው ጥፋት የሥራ ብዛትና መደራረብ የይቅርታ ምክንያትና መከራከሪያ አድርጐ ለማቅረብ አይችልም። እንደዚሁም ሰራተኞች 390 ጆንያ ቆጥረው ለገዥው እንዲያስረክብ እና እንዳይጭኑ ማድረግና ይህንን ሥራ በኃላፊነት መቆጣጠር መከታተል፣ የተለየ የሥራ ልምድ ክህሎትና ችሎታ የሚጠይቅ ሥራ አይደለም።
በመሆኑም አመልካች ጥፋት የፈፀምኩት በሥራ ብዛት፣መደራረብና በልምድ ማነስ ነው በማለት ያቀረበው መከራከሪያ የሕግ መሰረት ያለው ሆኖ አላገኘነውም።
ሆነ ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት በአሰሪው ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰን ሰራተኛ ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ ለማሰናበት እንደሚችል በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ /1/ ሸ/ በግልጽ ተደንግጓል። እንዲሁም ተጠሪ በኃላፊነት የተረከበውን የአሰሪውን ንብረት /እቃ/ በጥንቃቄ የመጠበቅ ግድታውን በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 13/3/ መሰረት ያልተወጣ መሆኑን የግራ ቀኙ ክርክርና ከበታች ፍርድ ቤቶች ውሣኔ ለመረዳት ይቻላል።
የተጠሪ አድራጎት በአዋጅ አንቀጽ 27/1/ሸ የሚሸፈንና አመልካች ከተጠሪ ጋር ያለውን የሥራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የሚያስችለው መሆኑ ተረጋግጦ እያለ አመልካች የተጠሪን የሥራ ውል ያቋረጠው ከሕግ ውጭ ነው በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሣኔ ተሽሯል።
አመልካች ተጠሪን በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/1/ሸ መሰረት ከሥራ ያሰናበተው በመሆኑ አመልካች ለተጠሪ የሥራ ስንብት ክፍያ የካሣ ክፍያ፣ የማስጠንቀቂያ ክፍያ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሣቸው ይቻሉ። መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.