No summary available.
ሐምል 18 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶለሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካቾች፡- እነ ወ/ት ፍቨን የሺጌታ (12 ሰዎች) የቀረበ የለም ተጠሪ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠበቃ ሸዋዬ ታከለ ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
በዚህ መዝገብ አመልካቾች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት የስራ ውላችንን በማቋረጥ ከስራ ያሰናበተን አላግባብ በመሆኑ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ የተቋረጠ ማናቸውም ክፍያ ተከፍሎ ወደ ስራችን እንድንመለስ ይወሰንልን በማለት በአሁኑ ተጠሪ ላይ በፍ/መ/ደ/ፍ/ቤት አቅርበው በነበረው ክስ ሳቢያ ፍ/ቤቱ ክርክሩን ከሰማ በኃላ ከሳሾቹ ከተከሳሹ ጋር የነበራቸው ግንኙነት የሰልጣኝ እና የአሰልጣኝ ከመሆኑ ውጪ አግባብነት ባላቸው የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ አዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌዎች መሰረት የተቋቋመ የስራ ውል የነበራቸው መሆኑን ስላላስረዱ ተከሳሹ የስራ ውላችንን አላግባብ አቋርጦብናል በሚል ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ይወሰንላቸው ዘንድ ያቀረቡት ጥያቄ የሕግ መሰረት የለውም በማለት የሰጠው እና በፍ/ከ/ፍ/ቤት በትዕዛዝ የጸናው ብይን መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ነው።
ከሳሾቹ በ07/11/2003 ዓ.ም. አዘጋጅተው ያቀረቡት ክስ ይዘት ባጭሩ ተከሳሽ በተለያየ ቀን እና ዓ.ም.
ከከሳሾቹ ጋር በተናጠል ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር የሚቆይ የስልጠና እና የብድር ስምምነት እንደፈረመ፣ስልጠናው በአራት ክፍሎች የተከፈለ ሆኖ ከሳሾቹ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍሎች "ሰልጣኝ"፣በቀሪዎቹ ሁለት ክፍሎች ደግሞ "ሰራተኛ" የሚል ስያሜ ተሰጥቶአቸው እንደነበረ፣የመጨረሻዎቹን ሁለት ክፍሎች ስልጠና ሲወስዱ መካከለኛ የበረራ አስተናጋጅ ተብለው በወር ብር 1,242 ደመወዝ እየተከፈላቸው ይሰሩ እንደነበረ፣ከሳሾቹ መብትና ግድታ የተጠበቀላቸው ሰራተኞች ስለመሆናቸው በ23/04/2002 ዓ.ም.በተዘጋጀው ማንዋል ላይ በግልጽ እንደተቀመጠ፣በዚህ ሁኔታ ተከሳሽ እና ከሳሾች የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ያላቸው ሆኖ እያለ ተከሳሽ የቀጣሪነት የበላይነቱን ተጠቅሞ ሕገወጥ ውል በማስፈረም 3ኛ፣ከ5ኛ እስከ 8ኛ፣10ኛ፣11ኛ እና 12ኛ ከሳሾችን የሁለት ዓመት ከስድስት ወር የስልጠና ጊዜው ከመጠናቀቁ በፊት እንዳሰናበታቸው፣ቀሪዎቹን 1ኛ፣2ኛ፣4ኛ እና 9ኛ ከሳሾችን ደግሞ የስልጠናው ጊዜ ከተጠናቀቀ ከስድስት ወር በኃላ እንዳሰናበታቸው የሚገልጽ ሆኖ ተከሳሽ ያልተከፈሉ ክፍያዎችን ፈጽሞ ከሳሾችን ወደ ስራቸው እንዲመልስ ይወሰን ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው።ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ በ28/11/2003 ዓ.ም. በተጻፈ መልስ በመካከላቸው የነበረው ውል የስልጠናና የብድር ብቻ እንደሆነ፣ከሳሾቹ ሰራተኞች እንዳልሆኑ፣መካከለኛ የበረራ ሰራተኛ በሚል ስያሜ መጠራትና መስራትም በስምምነቱ መሰረት የስልጠናው አካል እንደሆነ፣ በወር ይከፈላቸው የነበረው ብር 1,242 ደመወዝ ሳይሆን የኪስ ገንዘብ እንደሆነ፣ደመወዝ ባለመሆኑም ግብር እንደማይከፈልበት እና የሰራተኛ ማህበር መዋጮ እንደማይቆረጥበት፣የስልጠናና የብድር ስምምነቱን ወደ ጎን በመተው ለጉዳዩ አግባብነት የልላቸውን ልሎች ሰነዶች በመጥቀስ የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት እንደልለው በመግለጽ ተከራክሮአል።ፍ/ቤቱም ክሱን ከሰማ እና የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ ከሳሾቹ ከተከሳሽ ጋር በሕጉ አግባብ የተቋቋመ በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ውል ያላቸው መሆኑን አላስረዱም በማለት ክሱን በብይን ውድቅ ያደረገው ሰራተኛ ማለት በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 4 በተመለከተው መሰረት ከአሰሪ ጋር በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነት ያለው ግለሰብ ማለት እንደሆነ፣በግራ ቀኙ መካከል የቅጥር ግንኙነት የሚኖረው የስልጠናው ጊዜ ተጠናቆና ተከሳሽ ሰልጣኞቹን ለመቅጠር የሚፈልግ ሆኖ የቅጥር ውል ሲደረግ ብቻ ስለመሆኑ በስልጠናና በብድር ውሉ በአንቀጽ 8 እና 9 ላይ እንደተመለከተ፣መካከለኛ የበረራ አስተናጋጅ የሚል ስያሜ የተሰጣቸውም ከሳሾቹ ከተከሳሽ ጋር ባደረጉት ተጨማሪ ስምምነት እንደሆነ፣ክፍያውም ደመወዝ ሳይሆን የኪስ ገንዘብ ስለመሆኑ በስምምነቱ በአንቀጽ 3 እና 4 እንደተመለከተ፣ የሁለት ዓመት ከስድስት ወር የስልጠና ጊዜ ከማብቃቱ በፊትም ሆነ ካበቃ በኃላ የተሰናበቱት ከሳሾች ከተከሳሽ ጋር ከስልጠናና ብድር ስምምነት ውጪ በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ውል የነበራቸው ስለመሆኑ እንዳላስረዱ፣ከሳሾቹ በተዋዋዮቹ መካከል ሕግ የሆነውን የስልጠናና የብድር ስምምነት ይዘት ወደጎን በመተው ለክርክሩ አግባብነት የልላቸውን የተከሳሽ ድርጅት ሰነዶች በማጣቀስ ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት እንደልለው በዝርዝር በመግለጽ ሲሆን ከሳሾቹ በብይኑ ቅር በመሰኘት ያቀረቡለትን ይግባኝ የፍ/ከ/ፍ/ቤት ዘግቶ አሰናብቶአል።ቀደም ሲል እንደተገለጸው አመልካቾቹ የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ይዘቱ ከላይ የተጠቀሰው የሁለቱ የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት ሲሆን አቤቱታ የቀረበበትን የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔ አግባብነት ተጠሪ ባለበት ለመመርመር ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ አጠቃላይ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም የስር ከሳሾች ከስር ተከሳሽ ጋር በሕጉ አግባብ ያቋቋሙት የስራ ውል መኖሩን አላስረዱም በማለት በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት ይቻላል ወይስ አይቻልም? የሚል ነጥብ መሰረት በማድረግ ጉዳዩን መርምረናል።
በዚህም መሰረት አመልካቾች በተናጠል ከተጠሪ ጋር ያቋቋሙት ውል እና ተጨማሪ ውል ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር የሚቆይ የስልጠና እና የብድር ስምምነት መሆኑ፣በስምምነቱ መሰረት አመልካቾች በአራት ክፍሎች የተከፈለውን የስልጠና መርሐ ግብር በስኬት ካጠናቀቁ በኃላ አመልካቾችን ሰራተኛ አድርጎ በመቅጠር ረገድ የመወሰን መብት የተሰጠው ለተጠሪ መሆኑ፣ተጠሪ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከአመልካቾች መካከል ከፊሎቹን ያሰናበተው የስልጠና መርሐ ግብሩን ከማጠናቀቃቸው በፊት መሆኑ፣ከፊሎቹ ደግሞ የስልጠና መርሐ ግብሩን በስኬት ያጠናቀቁ ቢሆንም ተጠሪው በስምምነቱ በተሰጠው መብት መሰረት ሰራተኛ አድርጎ ለመቅጠር ያልወሰነ መሆኑ በክርክሩ የተረጋገጡ ፍሬ ነገሮች ሲሆኑ የስር ፍ/ቤቶችም አግባብነት ባላቸው የአዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌዎች መሰረት አመልካቾች ከተጠሪ ጋር በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ውል ያቋቋሙ መሆኑን አላስረዱም በማለት ክሱን ውድቅ ያደረጉትም ከላይ የተጠቀሱ በክርክሩ የተረጋገጡ ፍሬ ነገሮችን መሰረት በማድረግ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያስረዳል።ሰራተኛ ማለት በአዋጁ በአንቀጽ 4 በተመለከተው መሰረት ከአሰሪ ጋር በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነት ያለው ግለሰብ መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 377/96 በአንቀጽ 2(3) የተመለከተ ሲሆን የስራ ውል የሚመሰረተውም ማንኛውም ሰው ደመወዝ እየተከፈለው በአሰሪው መሪነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ወይም የተወሰነ ስራ ለአሰሪው ለመስራት ሲስማማ መሆኑ በአዋጁ በአንቀጽ 4(1) ተደንግጎአል።አመልካቾች ከተጠሪ ጋር በተናጠል ያቋቋሟቸው ውሎች እና ተጨማሪ ውሎች ደግሞ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የስልጠና እና የብድር ውል እንጂ በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ውል አይደለም።ህግ ከወሰናቸውና ከከለከላቸው ነገሮች በቀር ተዋዋዮች ሁሉ የሚዋዋሉበትን ጉዳይ እንደመሰላቸው የመወሰን መብት እንዳላቸው በፍ.ሕ.ቁ. 1711 የተመለከተ በመሆኑ እና በሕጉ አግባብ የተቋቋሙ ውሎች ደግሞ ባቋቋሟቸው ሰዎች ላይ ሕግ መሆናቸው በፍ.ሕ.ቁ.1731(1) የተደነገገ በመሆኑ ተጠሪው የቀጣሪነት የበላይነቱን በመጠቀም ሕገ ወጥ ውል አስፈርሞናል በማለት አመልካቾች ያቀረቡት የክርክር ነጥብ ሕጋዊ መሰረት ያለው አይደለም።አመልካቾቹ ውሉ ሕገ ወጥ ነው የሚሉበት ምክንያት ቢኖር እንኳ ይህን የውሉን ሁኔታ መሰረት አድርገው ክስ እና ክርክር ማቅረብ ይችሉ የነበረው ውሉ ፍጻሜ ከማግኘቱ በፊት እንጂ ውሉ ፍጻሜ አግኝቶ ተጠሪ የማይቀጥራቸው መሆኑን ካረጋገጡ በኃላ አይደለም።በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች አመልካቾቹ ከተጠሪ ጋር በሕጉ አግባብ የተቋቋመ የስራ ውል ያላቸው መሆኑን አላስረዱም ሲሉ ክሱን ውድቅ በማድረግ የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት ስላልተቻለ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቶአል።
119009 በ24/09/2004 ዓ.ም. በትዕዛዝ የፀናው ብይን በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 348(1) መሰረት ፀንቶአል።
የሰበር ክርክሩን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቶአል።
No topics extracted.