No summary available.
መጋቢት 27 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- አቶ ዳዊት ሸዋቀና - አልቀረቡም ተጠሪ፡- ስኳር ኮርፖሬሽን - ነ/ፈጅ አቶ ጌታቸው አክላሉ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሁኑ የሰበር አመልካች ከሳሽነት የተጀመረው በፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪው ደግሞ ተከሳሽ ነበር። ክሱም፡- በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ የኦዲት ክፍል ሀላፊ ሆኜ እየሰራሁ የሥራ አፈጻጸምህ ዝቅተኛ ነው፣እንዲሁም በሥራ ላይ ቸልተኝነት አሳይተሃል በሚል ያለማስጠንቀቂያ ሐምል 11 ቀን 2003 ዓ/ም የሥራ ውልን ያቋረጠብኝ በመሆኑ ወደ ሥራ እንዲመልሰኝ ካልሆነም ካሳ፣የስንብት ክፍያ፣የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፣ክፍያ በዘገየበት እና የዓመት ዕረፍት ወደ ገንዘብ ተለውጦ እንዲከፍል ይወሰንልኝ የሚል ነው።
ተከሳሽም ለክሱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና በአማራጭ በፍሬ ጉዳዩ ላይ መልስ ሰጥቷል። በፍሬ ጉዳዩ ላይ የሰጠው መልስም፡- ከሳሽ ከሥራ የተሰናበቱበት ምክንያት በተሰጣቸው የስንብት ደብዳቤ ላይ የተገለጸ ሲሆን ወደ ሥራ ለመመለስ ያቀረቡት ጥያቄም ተቀባይነት የሚኖረው አይደለም፣እንዲሁም እንዲከፈላቸው ከጠየቁአቸው ክፍያዎችም ውስጥ የዓመት ዕረፍት ወደ ገንዘብ ተለውጦ የተከፈላቸው ሲሆን ልሎች ክፍያዎች ግን ላከፈሉአቸው አይገባም ሲል ተከራክሯል።
የመ/ደረጃ ፍርድ ቤትም ተከሳሽ ያቀረበውን መቃወሚያ ቀደም ሲል በብይን ውድቅ ማድረጉን በመግለጽ በሰጠው ፍርድ፡- ተከሳሽ ለከሳሽ በጻፈው የስንብት ደብዳቤ የሥራ አፈጻጸማቸው ሲገመገም ዝቅተኛ ስለመሆኑ የተመዘኑበትን ማስረጃ ካለማቅረቡም ልላ በሥራቸው ቸልተኝነት አሳይተዋል ቢልም በምን ምክንያት ቸልተኝነት እንዳሳዩ አልዘረዘረም በማለት የሥራ ውሉ በህገ ወጥ መንገድ ተቋርጧል ሲል ወስኗል። ከሳሽ በአማራጭ ያቀረቡትን የዳኝነት ጥያቄ በተመለከተም የስራ መሪ ያለበቂ ምክንያት ከሥራ አሰሪው ቢያሰናብት ወደ ሥራ የመመለስ መብት እንዳለው በፍትሃብሕር ህጉ፣በህብረት ስምምነቱም ሆነ በሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ ስላልተገለጸ ተቀባይነት የለውም ሲል ወድቅ ያደረገ ሲሆን፤እንዲከፈላቸው የጠየቁትን ክፍያዎች በተመለከተም፡የስንብት ክፍያ እንዲከፈላቸው ሲወስን፤ የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ በሚመለከት ከሳሽ የሚሰሩበት ሥራ የእምነት ሥራ እና ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ ማስጠንቀቂያ አለመሥጠት በፍ/ህ/ቁ/2577(2) መሰረት ኪሳራ የሚያስከትል አይሆንም ሲል ያልተቀበለው ሲሆን ካሳ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ጥያቄ የህግ መሰረት ያለው አይደለም በሚል ውድቅ ሲያደርግ የዓመት ዕረፍት ወደ ገንዘብ ተለውጦ የተከፈላቸው መሆኑንም በቃል ክርክር ወቅት ከሳሽ ስላመኑ በድጋሚ ላከፈላቸው አይገባም ብሐል። እንዲሁም ክፍያ በዘገየበት የጠየቁትን ክፍያ በተመለከተም የሚከፈላቸው ክፍያ አይኖርም ሲል ሳይቀበለው ቀርቷል።
ከሳሽም በመ/ደ/ፍርድ ቤት ፍርድ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍ/ከ/ፍርድ ቤት ያቀረቡ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የይግባኙን መዝገብ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 337 በመዝጋት በማሰናበቱ የሰበር አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት አቅርበዋል። አመልካች በሰበር አቤቱታቸውም በዋናነት ያቀረቡት የቅሬታ ነጥብ፡- የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያና ካሳን ፍርድ ቤቶቹ በአዋጅ ቁጥር 377/1996፣በህብረት ስምምነቱና በሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ አግባብነት ባላቸው ድንጋጌዎች መሰረት መወሰን ሲገባቸው ሳይወስኑ ያለፉት አግባብ አይደለም የሚል ነው።
ተጠሪው በበኩሉ በሰጠው መልስ፡- ኮርፖሬሽኑ በደንብ ቁጥር 192/2003 የተቋቋመ ሆኖ እያለ አመልካች የተሻሩትን የሥራ መሪዎች ደንብና የህብረት ስምምነት መሰረት በማድረግ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፈሉአቸው ያቀረቡትን ክርክር ተቀባይነት የለውም ሲል ተከራክሯል።
አመልካችም ተጠሪው ላቀረቡት መልስ የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- አመልካች ከሥራ የተሰናበቱት በህገ ወጥ መንገድ ነው በሚል የሥር ፍርድ ቤቶች ከወሰኑ በኋላ ካሳና የማስጠንቂያ ጊዜ ክፍያ ላከፈላቸው አይገባም ያሉት በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? በሚል መዝገቡ ለሰበር ያስቀርባል ሲባል በተያዘው ጭብጥ መሰረት ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
ወደተያዘው ጭብጥ ከመመለሳችን በፊት ተጠሪው ድርጅት በአዲስ መልክ በደንብ ቁጥር 192/2003 የተቋቋመ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሥር ፍርድ ቤቶች ፍርድ ለመስጠት መሰረት ያደረጉት የሥራ መሪዎች ደንብና የህብረት ስምምነት ስለተሻሩ አግባብነት የላቸውም ሲል ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት ያለው መሆን አላለመሆኑ ላመረመር የሚገባ ሆኖ አግኝተናል። ደንብ ቁጥር 192/2003 ተፈጻሚ የሆነው ከጥቅምት 19 ቀን 2003 ዓ/ም ጀምሮ ስለመሆኑ በደንቡ አንቀጽ 12 የተደነገገ ሲሆን አመልካችም ክሱን ያቀረቡት ጥር 27 ቀን 2004 ዓ/ም በመሆኑ ክሱ የቀረበው ደንቡ ጸንቶ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ነው። በዚህ ደንብ ቀደም ሲል በየራሳቸው የማቋቋሚያ ደንብ ተቋቁመው የነበሩት አራት የስኳር ፋብሪካዎች የስኳር ኮርፖሬሽን በሚል መቋቋማቸውን ከደንቡ መገንዘብ የሚቻል ነው። ይሁን እንጂ ተጠሪው ቀደም ሲል በደንብ ቁጥር 122/1998 እንደተሻሻለው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በሚል ሲጠራ የነበረ ሲሆን የራሱ የሆነ የህብረት ስምምነት እና የሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ ያለው ነው።ተጠሪው የህብረት ስምምነቱና የሥራ መሪዎች የመተዳሪያ ደንቡ ተሽረዋል በሚል ክርክር ስለማቅረቡ የመ/ደ/ፍርድ ቤት ፍርድ የማያመላክት ሲሆን ክርክር አቅርበዋል ቢባል እንኳን ፍርድ ቤቱ ባለመቀበል በተሻሩ የሥራ መሪዎች ደንብና የህብረት ስምምነቱ መሰረት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሰጥቶ ከሆነ ጉዳዩን ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በማቅረብ ፍርዱን ማስለወጥ ሲገባው ይግባኝ አቅርቦ አላስለወጠም። በዚህ በሰበር ደረጃ ባደረገውም ክርክር የህብረት ስምምነቱ እና የሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ መሻራቸውን ከመግለጹ በስተቀር በየትኛው የህብረት ስምምነትና የሥራ መሪዎች ደንብ እንደተተኩ አልጠቀሰም። ስለሆነም የህብረት ስምምነቱና የሥራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ የተሻሩ ናቸው ሲል ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
ወደ ጭብጡ ስንመለስ፡- ተጠሪው የሥራ ውሉን ለመቋረጥ የጠቀሳቸው ምክንያቶች የአመልካች የሥራ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ነው፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ቸልተኝነት አሳይተዋል በሚል እንደሆነ ለሥር ፍርድ ቤቶች በማስረጃነት ከቀረበው የሥንብት ደብዳቤ የተረጋገጠ ሲሆን ተጠሪውም አመልካች በሥራ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ ስለመሆኑ የተመዘኑበትን ማስረጃ ባለማቀረቡ እንዲሁም በሥራ ላይ ቸልተኝነት አሳይተዋል ላለውም ምክንያቱን በመዘርዘር ማስረዳት ባለመቻሉ ሥንብቱ ህገ ወጥ ነው ወደሚለው ድምዳሜ የሥር ፍርድ ቤቶች ደርሰዋል።
በመሆኑም የሥራ ውሉ በህገ ወጥ መንገድ መቋረጡ የተረጋገጠ ፍሬ ነገር እስከሆነ ድረስ ተጠሪ ከሳና የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ላከፍል የሚገባ መሆን አለመሆኑን አግባብነት ካላቸው ህጎች ጋር አገናዝቦ መመልከት ይገባል። ከክርክሩ መገንዘብ እንደተቻለው አመልካች ሥራ መሪ ናቸው። አሰሪው የሥራ ውሉን ቀሪ በማድረግ ወይም አላድስም በማለት ይህን ውሳኔ በግልጽ የሚያረጋግጥ በቂ ምክንያት የልለው እንደሆነ ሰራተኛው ተገቢ የሆነ ኪሳራ የማግኘት መብት ያለው ስለመሆኑ በፍ/ህ/ቁ/2573 ከተደነገገው መገንዘብ የሚቻል ነው። በዚህ መልኩ በህጉ የሥራ ውሉ በቂ ባልሆነ ምክንያት የተቋረጠ ከሆነ አሰሪው ኪሳራ የመክፈል ግድታ ያለበት ስለመሆኑ በግልጽ ተደንግጎ እያለ የስር ፍርድ ቤቶች አመልካች የተሰናበቱት ያለበቂ ምክንያት መሆኑን በፍሬ ነገር ደረጃ ካረጋገጡ በኋላ ኪሳራውን ሳይወስኑ ማለፋቸው ህጉን የተከተለ አይደለም። ኪሳራ መክፈል ተገቢ መሆኑ ከታመነ ደግሞ ስለሚከፈልበት ሁኔታም አግባብነት ያላቸውን ህጎች መመልከት የሚገባ ነው። አመልካች በክሳቸው የ6 ወር ደመወዝ ካሳ እንዲከፈላቸው ዳኝነት የጠየቁት አዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት በማድረግ ነው። አንድ የሥራ መሪ የሥራ ውሉ ያለ በቂ ምክንያት ሲቋረጥ ላከፈል የሚገባው የኪሳራ ልክ ሰራተኛው ባለፈው ሶስት ወር ከተቀበለው ደመወዝ ላበልጥ እንደማይችል በፍ/ህ/ቁ. 2574 (2) የተደነገገ ሲሆን ይህንኑ የህግ አነጋገር ይዘን በታህሳስ ወር 2002 ዓ/ም ወደወጣው የተጠሪ የሥራ መሪዎች የመተዳደሪያ ደንብ ስንመለስ ፡በአንቀጽ 51(1) በዚህ ደንብ ውስጥ የተደነገጉት እንደተጠበቁ ሆነው በልሎች ህጎች ፣ደንቦች ወይም በልላ አኳኋን ተለይቶ የተወሰነው የተሻለና የበለጠ ጥቅም የሚያስገኝ ሆኖ በዚህ ደንብ ውስጥ ባልተጠቀሱም ሆነ በተጠቀሱ ጉዳዮች፣በህብረት ስምምነት የተደነገጉት፣በአሰራር ደንብ የተወሰኑትና የሚታወቁት ስለሥራ ሁኔታ፣ የሙያ ደህንነትና ጤንነት፣ የሥራ አካባቢ፣ጥቅሞች፣ግልጋሎቶች፣ሥልጠና፣የሥራ ዉጤት መለኪያ ዘድ እንዲሁም ይህን ደንብ የማይቃረኑ አግባብ ያላቸው ልሎች የሥራ ውል ግንኙነቶች የሚመለከቱ ዝርዝር ደንጋጌዎች የሥራ መሪው የሥራ ውል አካል ሆነው ይቆጠራሉ በሚል ተደንግጎ እናገኛለን። በዚሁ ደንጋጌ መሰረትም በፍ/ህ/ጉ ከተመለከተው የኪሳራ መጠን ይልቅ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 43(4)(ሀ) የተመለከተው የካሳ መጠን የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ በመሆኑ ለአመልካችም ተጠሪው ካሳ ላከፍላቸው የሚገባው በዚሁ የአዋጁ አንቀጽ መሰረት ላሆን ይገባል።
ልላው አመልካች የጠየቁት የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ነው። ተጠሪው የአመልካችን የሥራ ውል ሲያቋርጥ ቅድመ ማስጠንቀቂያ አለመስጠቱ የተረጋገጠ ጉዳይ ሲሆን የሥር ፍርድ ቤቶችም የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ለአመልካች አይገባቸውም በሚል የወሰኑት አመልካች የሚሰሩት የሥራ ባህሪ በመግለጽ ሲሆን ለዚህም መሰረት ያደረጉት የፍ/ህ/ቁ. 2577(2) ድንጋጌን ነው። በዚህ ድንጋጌ በንዑስ ቁጥር (1) የሥራው ውሉ ልዩ የሆኑ ችሎታዎችን የሚጠይቁ፣የእምነት ሥራዎች እንደሆኑ አሰሪው ውሉን ቀሪ የሚያደርግበትን ወይም የማያድስበትን ምክንያት ለማስታወቅ የማይገደድ መሆኑ የተደነገገ ሲሆን ኪሳራ ለመክፈል የሚገደደው ግን ውሉ እንዲቀር የተደረገው በማይገባ ጊዜና አንደኛውን ወገን ለመጉዳት ወይም ላደርስበት የሚችለውን ጉዳት ባለማሰብ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው። ከዚህ ውጪ ግን የውሉ ያለ ማስጠንቀቂያ ቀሪ መሆን አሰሪው ለሰራተኛው ኪሳራ እንዲከፍል የሚያስገድድ አይሆንም። በዚህ ጉዳይ ግን ውሉ ቀሪ የተደረገው በማይገባ ጊዜ ወስጥ ስለመሆኑ፣ወይም ተጠሪው አመልካችን ለመጉዳት ወይም ላደርስበት የሚችለውን ጉዳት ባለማሰብ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ውሉን ቀሪ ስለማድረጉ የተረጋገጠ ፍሬ ነገር የለም። አመልካች በተጠሪው ደርጅት የኦዲት ክፍል ሀላፊ የነበሩ እንደመሆናቸው መጠን የሥራ ውሉ ልዩ ችሎታን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ሥራውም በእምነት የሚሰራ በመሆኑ አስቀድሞ የሥራ ውል የሚቋረጥ ስለመሆኑ ማስታወቅ የአሰሪውን ጥቅም ላጎዳ የሚችልበት አጋጣሚ ላፈጥር ስለሚችል ማስጠንቀቂያ አለመሥጠቱ በፍ/ህ/ቁ.2577(2) እንደተመለከተው ኪሳራ እንዲከፍል የሚያስገድደው አይሆንም።
በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤቶች ተጠሪው ለአመልካች ከሚሰሩት የሥራ ባህሪ የተነሳ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ የሥራ ውሉን በማቋረጡ ምክንያት የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ለመክፈል አይገደድም ያሉት የሚነቀፍበት ምክንያት የለውም።
ሲጠቃልል፡- የሥር ፍርድ ቤቶች ለአመልካች የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ ላከፈላቸው አይገባም ያሉት ከዚህ በላይ በተገለጹት ምክንያቶች የተነሳ ተገቢ በመሆኑ የማስጠንቀቂያ ክፍያ ላከፈላቸው አይገባም በሚል ፍርድ ቤቶቹ የወሰኑት ተገቢ ቢሆንም የሥራ ውሉ በህገ ወጥ መንገድ የተቋረጠ ስለመሆኑ ተረጋግጦ ባለበት ሁኔታ ግን ካሳ እንዲከፈላቸው ሳይወስኑ ያለፉት መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍ/የመ/ደ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/03537 በቀን 15/10/2004 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ፍርድ እና የፍ/ከ/ፍርድ ቤት በመ/ቁ/126268 በቀን 17/12/2004ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት አሻሽለናል።
የስር ፍርድ ቤቶች የሥራ ውሉ በተጠሪው ህገ ወጥ ድርጊት ተቋርጦ እያለ ለአመልካች የካሳ ክፍያ እንዲከፈላቸው ሳይወስኑ ያለፉት ተገቢነት የለውም ብለናል። በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 43(4)(ሀ) መሰረት የአመልካች የቀን አማካይ ደመወዝ በ180 ተባዝቶ በሚመጣው ስልት መሰረት እንዲከፈላቸው ወስነናል።
የሥር ፍርድ ቤቶች ከካሳ ክፍያ በስተቀር የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያም ሆነ ልሎች ክፍያዎችን በተመለከተ የሰጡትን የውሳኔ ክፍል በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት አጽንተናል።
የካሳ ክፍያን በተመለከተ በዚህ ውሳኔ መሰረት እንዲያስፈጽም የአፈጻጸም ክሱን ለያዘው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይጻፍ ብለናል።
የግራ ቀኙ ወገኖች የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የየራሳውን ይቻሉ።
No topics extracted.