No summary available.
መጋቢት 25 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮልጅ ጠበቃ ንጋቱ ታደሰ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ለገሰ ደሣለኝ - ቀረቡ መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን፤መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የቀረበው በግራ ቀኙ መካከል የነበረው የሥራ ግንኙነት የተቋረጠው በሕጉ መሰረት ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን አከራካሪ ነጥብ በሥር ፍ/ቤቶች በነበረው ክርክር ከተረጋገጡት የፍሬ ነገር ጉዳዮች በመነሣት አግባብነት ያለውን የሕግ ትርጉም ለመስጠት ሲባል ነው።
የአሁን ተጠሪ ሕጉ ከደነገገው ውጭ አመልካች የሥራ ውልን አቋርጧል፤ስለሆነም ለሕገ ወጥ ስንብት በሕጉ የተፈቀደውን ልዩ ልዩ ክፍያዎች ይፈጽምልኝ በማለት የክፍያ ዓይነቶችን ዘርዝሮ ዳኝነት ሲጠይቅ፤ የአሁን አመልካች በበኩሉ ተጠሪ ከየካቲት 2ዐ እስከ 26 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም ድረስ ባሉት ተከታታይ ቀናት በሥራ ገበታው ባለመገኘቱ ምክንያት የሥራ ውሉ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27/1/ለ/ በሚያዘው መሰረት እንዲቋረጥ ተደርጓል። ስለሆነም ለሕጋዊ ስንብት ክፍያ እንድንፈጽም አንገደድም በማለት ተከራክሯል።
ሆኖም የአሁን አመልካች በሁለተኛው ወሰን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ለመምህራን የሚያስተምሩትን የትምህርት ዓይነቶች /ኮርሶችን/ ሲደለድል፤ ለአሁን ተጠሪ እንደ መምህርነቱ የሚያስተምረውን የትምህርት ዓይነት ለመመደብ የሚቻልበትን ምክንያት ሣይገልፅ የሚያስተምረውን ኮርስ እንዲያገኝ ስለማድረጉና የኮርስ ድልደላ ከመደረጉ በፊት የነበረውን የጥር ወር ደመወዝ እንዳይከፈለው ማገዱን፤ ለምን እንዳይከፈል እንደተደረገ ተጠሪ በጽሑፍ ከመግለጽ ጋር ይኸው ደመወዝ እንዲከፈለው የካቲት 13 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም ሲጠይቅ በጥያቄው መሰረት ያልተከፈለው ከመሆኑም በላይ ላለመክፈል የሚያስችል በቂ ምክንያት ስለመኖሩ አመልካች በአሰሪነቱ መልስ እንዳልሰጠው የተረጋገጡ እውነታዎች ናቸው።
አመልካችም እነዚህን ሁኔታዎች ይቀበልና ተጠሪው የሚያስተምረውን ኮርስ አለመደልደል መብቱ እስካልተጓደለበት ድረስ ከሥራ እንዳሰናበትነው ላያስቆጥር አይችልም በማለት ይከራከር እንጂ አመልካች ያደረገው ተግባር ተጠሪው የሚያስተምረውን የትምህርት ዓይነት አለመስጠቱ ብቻ ሣይሆን የትምህርት ዓይነቶች ለመምህራን ከመደልደላቸው በፊት ያለውን የጥር ወር ደመወዝ ለመክፈል እምቢተኛ የሆነበትን በቂ ምክንያት አቅርቦ አላስረዳም ሰለሆነም የአሁን አመልካች እንደውላቸው ሰራተኛው የሚሰራውን ሥራ የማቅረብ በሕግ ግድታ ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አመልካች ተጠሪው የሚያስተምረውን ትምህርት ደልድሎ አለመስጠቱ ብቻ ሳይሆን በተቀጣሪነቱ ላያገኝ የሚገባውንም የጥር ወር ደመወዝ እንዳይከፈለው አድርጓል(ነፍጐታል)።
ስለሆነም የተጠሪው መብት እስካልተጓደለ ድረስ የሚያስተምረውን የትምህርት ዓይነት አለመደልደል ሰራተኛውን ለማሰናበት ተፈልጐ እንደተደረገ ተግባር ላቆጠር አይገባም የሚለው ክርክሩ በሥር ፍ/ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠውን ያለበቂ ምክንያት ደመወዝ የማግኘት መብቱን ክልከላ ያላገናዘበ፤ በመሆኑ ክርክሩ ሕጋዊ መሰረት ያለው አይደለም።
በመሆኑም የአሁን አመልካች የተጠሪን የጥር ወር ደመወዝ እንዳይከፈል ለማድረግ የሚያበቃው ሕጋዊ ወይም በቂ ምክንያት ሳይኖረው የዚህኑ የጥር ወር ደመወዝ እንዳይከፈል የከለከለው መሆኑና በተከታዩም በየካቲት ወር ተጠሪው ሰራተኛ መሆኑን ተቀብሎ የሚሰራው ሥራ እንዳይሰጠው የከለከለበት ወር መሆኑ እየታወቀ እና እነዚህም ሁለት ተግባራት ድርብ ውጤት ተጠሪው የአመልካች ሰራተኛ መሆኑን ተገንዝቦ እንደማንኛውም ሰራተኛ የሥራ ቀንና የሥራ ሥዓት አክብሮ እንዲገኝ ከማድረግ ይልቅ ሰራተኛነቱን ያልተቀበለው መሆኑን የሚያመለከት ሆኖ እያለ እንደገና ተጠሪው በዚህ በየካቲት ወር በነበረው የሥራ ጊዜ ከየካቲት 2ዐ እስከ የካቲት 26 ቀን ባሉት ከአምስት ተከታታይ ቀናት በላይ ከሥራ ገበታው ስለቀረ ተሰናብቷል። ይህም ሕጋዊ ስንብት መሆኑን ያመለክታል የሚለው ክርክሩ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 27(1)(ለ) የተመለከተውን ድንጋጌ ይዘት መንፈስና ዓላማ መሰረት ያላደረገ፤ ድንጋጌውን ተፈፃሚ ለማድረግ የሚያበቁ ሁኔታዎችን ያላሟላ ክርክር በመሆኑ የሥር ፍ/ቤቶች የአሁን ተጠሪ ከአመልካች ድርጅት በሕጉ ከተደነገገው ውጭ እንዲሰናበት ተደርጓል፤
ስንብቱ ሕገ-ወጥ ነው በማለት ለዚህ ዓይነት ሕገ-ወጥ ስንብት ላከፈል የሚገባውን የክፍያ ዓይነትና መጠን ገልፀው የሰጡት ትርጉም ሕጋዊ እንጂ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አላገኘነውም።
ው ሣ ኔ
በዚህ ጉዳይ ላይ ይግባኝ ሰሚው የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/መ/ በቀን 18/11/2ዐዐ4 ዓ.ም የሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ፀንቷል።
የአሁን አመልካች በሰበር ደረጃ ያቀረበው ክርክር ሕጋዊ መሰረት ያለው አይደለም ብለናል።
የአሁን አመልካች ተጠሪን በሕጉ ከተደነገገው ውጭ ከሥራ አሰናብቶታል፤ ስንብቱ ሕገ-ወጥ ነው በማለትና ለዚህ ሕገ-ወጥ ስንብት የሁለት ወር ደመወዝ በማስጠንቀቂያ ምክንያት፤ የሥራ ስንብት 2,125.ዐዐ /ሁለት ሺህ አንድ መቶ ሃያ አምስት ብር/ የካሣ ክፍያ ብር 9ዐዐዐ.ዐዐ /ዘጠኝ ሺህ ብር/ ያልተከፈለው የጥር ወር ደመወዝ ብር 15ዐዐ.ዐዐ /አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር/ ከብር 4ዐዐ.ዐዐ /አራት መቶ ብር/ የወጭና ኪሣራ ገንዘብ ጋር ይከፈለው መባሉ አግባብ ነው ብለናል።
በዚህ የሰበር ደረጃ ግራ ቀኙ ሲከራከሩ በክርክሩ ምክንያት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ።
No topics extracted.