No summary available.
መስከረም 23 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ጠበቃ ይልማ አቻሜ ቀረቡ ተጠሪ፡- የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበራት ኤጀንሲ ነ/ፈጅ መዓዛ ገ/ልዑል ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ በተጠሪ የታገደ ገንዘብ ይለቀቅልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ በይግባኝ ደረጃ የታየው በተጠሪ ቦርድ ነው። በዚህ ቦርድ ይግባኝ ባይ የነበረው የአሁኑ አመልካች ሲሆን የይግባኝ አቤቱታው ዋና ሐሳብም አመልካች የአዋጅ ቁጥር 621/2001 ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ በፊትና ደንብ ቁጥር 168/2001 በስራ ላይ ከመዋሉ በፊት ድርጅቱ በልዩ ልዩ ሁኔታ በህጋዊ መንገዶች ከውጭ ምንጭ ያገኘውን ገንዘብ ኤጂንሲው በቁጥር01/chsa- 2980/N1146 ታህሳስ 22 ቀን 2002 ዓ.ም. በፃፈው ደብደቤ በድርጅቱ የባንክ ሂሳቦች ላይ የጣለውን እገዳ በቦርዱ እንዲነሳ እና በደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀጽ 10(2) ድንጋጌን በተጻረረ መንገድ የተከናወነ እገዳ ከምዝገባችን ቀድሞ የተጣለብን መሆኑና ድርጅታችን ያልሰራበት ገንዘብ እንኳን ቢኖር ከለጋሾች ጋር በገባነው ስምምነት መሰረት ላመለስላቸው ሲገባ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ድርጅቱ ለረዥም ጊዜ በወለድ ያጠራቀመው ገንዘብ በጅምላ በመታገዱ ቦርዱ ይህንኑ አውቆ እገዳውን እንዲያነሳልኝ የሚል ነው። የአሁኑ ተጠሪ በበኩሉ አመልካች በአዋጁ መሰረት የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ መመዝገቡንና የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ደግሞ ከ10 ከመቶ በላይ ከውጭ ገቢ ምንጭ መጠቀም እንደማይችል አዋጁ የሚከለክል መሆኑንና በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከውጭ የሰበሰበው በርካታ ገንዘብ የነበረው ከመሆኑም በላይ አዋጁ ከጸናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 በኋላ በርካታ ገንዘብ ከውጭ የገቢ ምንጮች የሰበሰበ መሆኑን፣አዋጁ ከጸናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 ዓ.ም. በኋላ በቀድሞ ሕጎች የተገኙ መብትና ግድታዎች ተፈጻሚ የሚሆኑት አዋጁን የማይቃረኑ ብቻ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 111(1) መደንገጉንና ድርጅቱ ኢትዮጵያዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ የተመዘገበ በመሆኑ ገንዘቡን ለተሰማራበት ዓላማ መጠቀም የማይችል መሆኑን፣በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከአገር ውስጥ ምንጭ 90% የሚያመነጭ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ሆኖ መመዝገቡንና ከመመዝገቡ በፊት ከውጭ ምንጭ የሰበሰበው ስምንት ሚላዮን ብር የነበረው ቢሆንም በአዋጁ መሰረት ገንዘቡን መጠቀም ስለማይችል በኤጂንሲው መታገዱን፣በአዋጁ መሰረት ገንዘቡን ለልላ ድርጅት ማስተላለፍ ቢቻልም ኤጂንሲው የወሰደው አቋም ግን በየአመቱ 90% ከአገር ውስጥ አመንጭቶ ለኤጂንሲው ሲያቀርብ ቀሪው 10% ደግሞ ከታገደው ገንዘብ ውስጥ እየተለቀቀለት መንቀሳቀስ እንዲችል የሚያደርግ መሆኑን ዘርዝሮ ይግባኙ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል።
ቦርዱም የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የአመልካችን ክርክር ውድቅ በማድረግ የተጠሪ እርምጃ ሕጋዊ ነው በማለት ወስኗል። የአሁኑ አመልካች በአዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀፅ 104 በተዘረጋው የይግባኝ ስርዓት መሰረት ይግባኙን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የቦርዱ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ፀንቷል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ተጠሪ አከራካሪውን ገንዘብ ለማገድ ሕጉ ስልጣን የማይሰጠው መሆኑና እግዳውም የተደረገው አመልካች ድርጅት ሕጉ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በልዩ ልዩ ሁኔታና ሕጋዊ መንገዶች ከውጭ ምንጭ የተገኘ ገንዘብ የሚታገድበት ሕጋዊ አግባብ የለም ብሎ መከራከሩን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ከአዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀፅ 111(1)፣አዋጁን ለማስፈፀም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከወጣው ደንብ ቁጥር 168/2002 አንቀፅ 10(2) እና የፍትህ ሚኒስትር መጋቢት 16 ቀን 2001 ለተለያዩ የፍድራልና የክልል አካላት በአዋጁ መሰረት የምዝገባና የድጋሚ ምዝገባ ሥርዓት እስከሚጀምር ድረስ ነባር የበጎ አድጎት ድርጅቶችና ማህበራት ቀድም ሲል ሲሰሩ በነበረበት ሁኔታ ስራቸውን መቀጠል እንደሚችሉ በመግለጽ ከፃፈው ደብዳቤ አንፃር ለመመርመር ሲባል ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ለሰበር ችሎቱ ሲቀርብ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች ለቦርዱ አቤቱታውን ላያቀርብ የቻለው አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከመፅናቱ በፊትም ሆነ የምስክር ወረቀት እስከተሰጠበት እስከ ታህሳስ 06 ቀን 2002 ዓ/ም ድረስ ከውጭ የተሰበሰበውን ገንዘብ ያላግባብ ኤጂንሲው አግዶብኛል፣ይህንን ለማድረግ አዋጁም ሆነ ደንቡ አይፈቅዱለትም፤ስልጣን አይሰጡትም በሚል ምክንያት መሆኑን ነው።በዚህ የሰበር ሰሚ ችሎት ባቀረበው የሰበር ቅሬታም ተጠሪ በሕጉ ስልጣን ያልተሰጠው ከመሆኑም በላይ የአዋጁንና የደንቡን ዝርዝር ድንጋጌዎች እንዲሁም ከፍትህ ሚኒስቴር መጋቢት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. የተፃፈውን ደብዳቤ ይዘት ባላገናዘበ መልኩ እገዳውን ማከናወኑን ዝርዝሮ መከራከሩን ተመልክተናል።
በመሰረቱ አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከውጪ የሚሰበሰበው ገንዘብን መሰረት በማድረግ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንና ማህበራት ትርጉም፣ አይነታቸውንና ዓላማቸውን ለይቶ ገደብ ያደረገ ስለመሆኑ የሚያመላክቱ ድንጋጌዎችን ይዞ ይገኛል። ይህንኑ መለኪያ መሰረት አድርጎም አዋጁ ሶስት አይነት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በአገሪቱ የህግ ማዕቀፍ የሚታወቁ መሆኑን የሚያሳዩ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል። የአዋጁ አንቀፅ 2 ንዑስ ቁጥር (2)፣ ንዑስ ቁጥር (3) እና ንዑስ ቁጥር (4) ድንጋጌዎች እንደየ ቅደም ተከተላቸው ሲታዩም የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት፣የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት እና የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሕጉ የሚታወቁ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የማህበራት አይነቶች መሆናቸውን በመጥቀስ ትርጓሜአቸውን አስቀምጠው እናገኛለን። የእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ሲታይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የማህበራት አይነት የሚወሰነው በመሰረታዊነት የገቢ ምንጭን በመመርኮዝ ስለመሆኑ ያስረዳል። በመሆኑም በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ኢትዮጵያዊ ነው ተብሎ ላመደብ የሚገባው በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት መመስረቱ ብቻ ሳይሆን ከውጪ ምንጮች የሚገኘው የገቢ መጠን ከጠቅላላ ገቢው አስር ከመቶ (10%) የማይበልጥ ሲሆን ስለመሆኑ መገንዘብ ይቻላል።
ድርጅቱ ወይም ማህበሩ ከጠቅላላ ገቢው ከአስር ከመቶ በላይ የሆነውን ገቢ ከውጭ ምንጮች ስለማግኘቱ ከተረጋገጠ የኢትዮጵያ ነዋሪ ተብሎ እንደማይመደብ በአዋጁ አንቀፅ 2(2) እና 2(3) የተቀመጡት የትርጓሜ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያሳያል። ሕጉ በዚህ ረገድ ያስቀመጠው የትርጉም መሰረት ድርጅቱ ወይም ማህበሩ የሚሰማራበትን ዓላማ ለመለየትም መለኪያ ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 14 ድንጋጌ ከላይ ከተጠቀሱት የአዋጁ ድንጋጌዎች ጋር ተጣምሮ ሲነበብ የሚያስገነዝበን ጉዳይ ነው።
የአዋጁ አንቀፅ 14(2) የበጎ አድራጎት ማህበራትና ድርጅቶችን ዓላማዎች የዘረዘረ ሲሆን በአንቀፁ ንኡስ አንቀጽ 5 ድንጋጌ ስር ለኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ተለይተው የተሰጡትን ዓላማዎችን አስቀምጧል። በዚህ ንኡስ ድንጋጌ መሰረት ለኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ብቻ ተለይተው የተሰጡት አላማዎች የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊነትን ማበረታታት፣ የብሕሮች፣ ብሕረሰቦችና ሕዝቦች፣ የጾታ እና የሐይማኖት እኩልነት መረጋገጥን ማበረታታት፣ የሕጻናትና የአካል ጉዳተኞች መብቶች መከበርን ማበረታታት፣ የግጭት አፈታትን ወይም እርቅን ማስፋፋት እና የፍትህና የሕግ ማስፈጸም አገልግሎቶችን ቀልጣፋነት ማጠናከር ስለመሆናቸው በግልጽ ተለይቶ ተደንግጓል። አዋጁ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አይነትና ዓላማቸውን ለይቶ ከማስቀመጡም በላይ አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ደንቦችን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ላያወጣ እንደሚችል፣ ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው ሕጎች፣ የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች እንዲሁም አዋጁ የሚፀናበትን ጊዜ እንደየቅደም ተከተላቸው በአንቀፅ 109፣110፣111 እና በአንቀፅ 112 ስር አስቀምጧል። በዚኅ አግባብም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 168/2001 አውጥቶ ከጥቅምት 30 ቀን 2002 ዓ/ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን አዋጅ ቁጥር 621/2001 ደግሞ ከየካቲት 06 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ የጸና ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 112 በግልጽ ያሳያል። የአዋጁ ቁጥር 621/2001 አንቀጽ 111 ንዑስ ቁጥር (1) ድንጋጌ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ቀድሞ በነበረው ሕግ የተገኘ መብትና ግድታ አዋጁን እስካልተቃረነ ድረስ ብቻ እንደሚቀጥል ሲደነግግ የንዑስ ቁጥር(2) ድንጋጌ ደግሞ ቀደም ሲል የተመዘገቡ ማንኛውም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጁ ከጸናበት ቀን ጀምሮ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደገና መመዝገብ አለባቸው በማለት አስገዳጅነት ባለው መልኩ ደንግጓል።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም አመልካች ድርጅት የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት ሁኖ ታህሳስ 06 ቀን 2002 ዓ.ም. መመዝገቡንና አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከፀናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 በኋላ በርካታ ገንዘብ ከውጭ የገቢ ምንጮች የሰበሰበ መሆኑን ፍሬ ነገርን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው፤አቤቱታውን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የተጠሪ መስሪያ ቤት ቦርድና ጉዳዩን በይግባኝ እንዲመለከት በአዋጁ አንቀፅ 104(3) መሰረት ስልጣን የተሰጠው የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያረጋገጧቸው ነጥቦች ናቸው። አመልካችም በርካታ ገንዘብ ከውጭ ምንጮች አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከጸና በሁዋላ መሰብሰቡን ሳይክድ አንዱ የክርክር ነጥብ አድርጎ የሚያቀርበው ጉዳይ አመልካች ድርጅት አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከመውጣቱ በፊትም ሆነ ከወጣ በኋላ በውጭ በጎ አድራጎት ድርጅትነት ወይም ማህበርነት ተመዝግቦ አያውቅም፣ዜግነቱም ኢትዮጵያዊ ነው በሚል ነው።
ይሁን እንጂ አመልካች አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከመውጣቱ በፊት በማህበርነት ተመዝግቦ ሲሰራ የነበረ ሲሆን አዋጅ ቁጥር 621/2001 ከወጣ በኋላ በአዋጁ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ዳግም የተመዘገበ በመሆኑ አዋጁ ከጸና በኋላ በአዋጁ ለኢትዮጵያ ማህበር በተፈቀዱት ዓላማዎች መስራት ያለበት በአዋጁ መሰረት በመሆኑ ቀድሞ የውጭ በጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ሁኖ ያለማወቁ የአዋጁ ቁጥር 621/2001 አፈጻጸም ላይ የሚያመጣው ለውጥ ስለልለ በዚህ ረገድ የቀረበው ክርክር ተቀባይነት የልለው ሁኖ አግኝተናል።
እንዲሁም አዋጁ በአንቀጽ 108 ስር አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወደ ልላ በጎ አድራጎት ድርጅት አይነት ላቀይር ከፈለገ የሚችል ስለመሆኑ የሚሳይ ሲሆን አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀፅ 18(3) ድንጋጌ ስር ደግሞ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከውጪ ምንጭ ያገኘውን ገንዘብ ይዞ በሕጉ አግባብ ኢትዮጵያዊ ለመባል የማይችል ስለመሆኑ የተመለከተ በመሆኑ አመልካች በአዋጁ መሰረት እንደገና መመዝገቡ ከውጭ በጎ አድራጎት ድርጅትነት ወደ ኢትዮጵያዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደተቀየረ አያስቆጥረውም በማለት የሚያቀርበው ክርክር በአዋጁ የበጎ አድራጎት ድርጅት ኢትዮጵያዊ ለመባል መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችና ለኢትዮጵያዊ በጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር በሕጉ የተፈቀዱለትን ዓላማዎች አይነት ሳይለይ የቀረበ ክርክር በመሆኑ ተቀባይነት ያለው አይደደለም።
ልላው አመልካች አጥብቆ የሚከራከረው ነጥብ ደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀጽ 18 ተፈጻሚነት የሚኖረው በአዋጁ መሰረት ድርጅቱ ወይም ማህበሩ ፈቃድ አግኝቶ ከተመዘገበ በኋላ ነው በሚል ነው። ይሁን እንጅ አመልካች አዋጁ ቁጥር 621/2001 ከመውጣቱ በፊት በሕጉ አግባብ ተመዝግቦ ሲሰራ የነበረ ሲሆን አዋጁ ከወጣ በኋላ ዳግሞ ተመዝግቦ በአዋጁ ለኢትዮጵያዊ ድርጅት ወይም ማህበር የተፈቀዱትን ዓላማዎችን ይዞ እንደሚንቀሳቀስ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ አዋጁ ከፀናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ ከውጭ ምንጭ ከ10% በጀት በላይ መሰብሰብ የሚችልበት አግባብ የልለ መሆኑን የአዋጁን አንቀጽ 2(2)(3)፣14(5) እና የደንብ ቁጥር 18(3) ድንጋጌዎችን አንድ ላይ በምናነብበት ጊዜ የምንረዳው ጉዳይ ነው። ስለሆነም በዚህ ረገድ የቀረበው የአመልካች ክርክርም የሕግ መሰረት ያለው ሁኖ ስላላገኘን የምንቀበለው ሁኖ አልተገኘም።
አመልካች ገንዘቡ በችሮታ ጊዜ የተሰበሰበ በመሆኑ አዋጁንና ደንቡን ይቃረናል ላባል አይችልም በማለትም ክርክር አቅርቧል።ለዚሁ ክርክሩ መሰረት የሚያደርጋቸው የሕግ ድንጋጌዎቹም የአዋጁ አንቀፅ 111(1) እና የደንቡን አንቀጽ 10(2) ድንጋጌን ነው። የአዋጁ አንቀጽ 111 ርዕሱ "የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎች" በሚል የተቀመጠ ሲሆን ከላይ እንደተጠቀሰው ንዑስ አንቀፅ አንድ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ቀድሞ በነበረው ሕግ የተገኘ መብትና ግድታ አዋጁን እስካልተቃረነ ድረስ እንደሚቀጥል ሲያስቀምጥ፣ንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ ደግሞ ቀደም ሲል የተመዘገቡ ማንኛውም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጁ ከጸናበት ከየካቲት 06 ቀን 2001 ዓ/ም ጀምሮ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደገና መመዝገብ ያለባቸው ስለመሆኑ በአስገዳጅ መልኩ ደንግጓል። የደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀጽ 10(2) ደግሞ የድጋሚ ምዝገባ ውጤት ተግባራዊ የሚሆነው ምዝገባው በተጠናቀቀበት ጊዜ ሳይሆን አዋጁ ከጸናበት ጊዜ ከአንድ አመት በኋላ ይሆናል ሲል አስቀምጧል። እንግዲህ እነዚህ ድንጋጌዎች አንድ ላይ ሲታዩ ቅራኔ ያላቸው ናቸው ለማለት የሚቻል ሳይሆን እርስ በእርሳቸው የተጣጣሙ ናቸው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ በመሸጋገሪያ ጊዜው ውስጥ አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ከውጭ ምንጭ በሕጉ ከተመለተከው የገንዘብ መጠን በላይ እንዲሰበሰብ የሚፈቀድበት አግባብ የለም። ምክንያቱም የመሻጋገሪያ ድንጋጌ አይነተኛ አላማ ቀደም ሲል በነበሩ ሕጎች የተገኙ መብቶች እና ግድታዎች አዲስ ሕግ ሲወጣ አከራካሪ እንዳይሆኑ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ግልጽ ምላሽ ለመስጠት ነው ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች አንድ ላይ ሲታዩም ቀደም ሲል ለተገኙት መብቶችና ግድታዎች ተፈፃሚነት ያጣው ሕግ ተፈጻሚ እንዲሆን ማድረግ ሳይሆን በአዲሱ ሕግ እንዲሸፈኑ መደረጉን የሚያስገነዝቡን ናቸው። እንዲሁም ቀደም ሲል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ምዝገባ የሕግ ማዕቀፍ የልለውና ከአዋጅ ቁጥር 621/2001 ዓላማ ጋር አንድ ላይ የማይሄድና የማይጣጣም በመሆኑና እንደአይነታቸውና ባሕርያቸው በተለያዩ ድንጋጌዎች ስለሚገዙ አዋጁ በወጣ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደገና መመዝገብ አስፈላጊ መሆኑ መደንገጉ አዋጁ ከፀናበት ጊዜ ጀምሮ በአዋጁ የተከለከሉ ዓላማዎችን በቀድሞው ሕግ መሰረት ማከናወን መቀጠል የማይቻል ስለመሆኑ የሚያስረዳ ነው። አመልካች መጋቢት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. የፍትሕ ሚኒስቴር ፃፈ የሚለውን ደብዳቤ ይዘት ጠቅሶ ያቀረበውን ክርክር ስንመለከተውም የደብዳቤው ይዘት አዋጅ ቁጥር 621/2001 መፅደቁን አስታውሶ መንግስት በአዋጁ መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን የሚመዘግብና የሚከታተል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጂንሲ ለማቋቋም በሂደት ላይ ያለ ስለመሆኑ ጠቅሶ ኤጂንሲው ተቋቁሞ በአዋጁ መሰረት የምዝገባና የድጋሚ ምዝገባ ሥርዓት እስከሚጀምሩ ድረስ ነባር የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ከዚህ በፊት ይሰሩ በነበሩበት ሁኔታ እየሰሩ መቀጠል እንደሚችሉ ለሚመለከታቸው የአስፈጻሚ አካላት ስርኩላሩ መተላለፉን የሚያሳይ ነው። ይህ ሰርኩላር ይዘቱ የሚስገነዝበው የአዋጁን አፈጻጸም ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ኤጀንሲው እስከሚቋቋም ድረስ የሚመለከታቸው አካላት ላያከናውኑ የሚገባቸውን ተግባራት የሚያሳይና አዋጁን ለማስፈፀም ይቋቋማል የተባለው ኤጀንሲ ከተቋቋመ በኋላ ግን ሁሉም ነገር በአዋጁ መሰረት መሰራት ያለበት መሆኑን የሚያስረዳ በመሆኑ አመልካች በአዋጁ አንቀጽ 2(2) እና 111(2)፣በደንቡ አንቀጽ 10(2) ድንጋጌዎች መሰረት በችሮታው ጊዜ የራሱን አደረጃጀት በማስተካከል ያልተጠናቀቁ ስራዎችን ለማጠናቀቅ እንዲችል ሕጉ በሰጠው ችሮታ ጊዜ መንቀሳቀስ የሚገባበት እንጂ ገቢውን ከአዋጁ ይዘትና መንፈስ ውጪ እንዲሰበስብ እድል የሚሰጠውና የአዋጁን አላማ ውጤት አልባ በሚያደርግ መልኩ ተፈጻሚ የሚሆን አይሆንም።
አመልካች የአንድ ድርጅት ወይም ማህበርን ገቢ በማየት ዓላማ ላወሰን አይችልም፣ዓላማው የሚወሰነው በመተዳደሪያ ደንቡ ነው በማለት ያቀረበውን ክርክር ስንመለከተውም የድርጅቱ ወይም የማህበሩ ዓላማ በመተዳደሪያ ደንቡ መጠቀስ ያለመጠቀሱ በአዋጅ ቁጥር 621/2001 አንቀጽ 2(2)(3)(4)) እና 14(5) ድንጋጌዎች መሰረት ዋነኛው ነጥብ ድርጅቱ ወይም ማህበሩ ከውጪ የሚያሰባስበው የገንዘብ መጠን ከገቢው 10% በላይ ከሆነ በሕጉ ተለይተው ለኢትዮጵያዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበራት በተሰጡ ዓላማዎች ላይ መሰማራት አይችልም ተብሎ የተደነገገ በመሆኑ አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረበው ክርክር የሕግ መሰረት ያለው አይደለም።
ተጠሪ በሕግ ተቋቁሞ አዋጅ ቁጥር 621/2001 እንዲሁም አዋጁን ለማስፈጸም በሕጉ አግባብ ስልጣን የተሰጠው አካል ያወጣቸውን ደንቦች ለማስፈጸም የሚችል ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 6 ስር ከተዘረዘሩት ስልጣንና ተግባራት ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ሲሆን ዓላማዎቹን ለማሳካት አስፈላጊ የሆኑ ልሎች ተግባሮችን መፈጸም እንደሚችል በተጠቃሹ አንቀፅ ፊደል "ቸ" ስር ከተቀመጠው ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ ማየት የምንችለው ጉዳይ ነው። በአዋጁ አንቀፅ 90 መሰረት ለኤጀንሲው የተሰጠውን ስልጣን ስንመለከተው በተጠቃሹ የአዋጁ ድንጋጌ የንብረት ጥበቃ ወይም እገዳ ተግባር የሚፈፀመው ተገቢ ያልሆነ የስራ አመራር በበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም በማህበር መፈጸሙ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ የድንጋጌው ይዘት ያሳያል።
በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ የአመልካችን ገንዘብ ያገደው በአዋጁ አንቀፅ 90 መሰረት ተገቢ ያልሆነ የስራ አመራር በአመልካች ተፈጽሟል በሚል አይደለም። ይልቁንም በሕጉ ተለይቶ የተሰጠው ዓላማ አመልካች ኢትዮጵያዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚያደርገው ሁኖ እያለ አዋጁ ከጸናበት ጊዜ በፊትም ሆነ በኋላ ከውጪ ምንጭ በርካታ ገንዘብ ሰብስቧል፣አመልካች ዓላማው ኢትዮጵያዊ ድርጅት ሁኖ እስከተመዘገበ ድረስ ይህንኑ ከውጪ የተገኘውን ገንዘብ ለዓላማው ማስፈፀሚያነት ላያውለው አይችልም በሚል ነው። እንዲህ አይነት ተግባር ተፈጽሞ ሲገኝ መፍትሕው ምን እንደሆነ አዋጁን ለማስፈፅም የወጣው ደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀጽ 18 ምላሽ ይሰጣል። ይህ የደንቡ ድንጋጌ በኢትዮጵያ ውስጥ በአዋጁ መሰረት ፈቃድ አግኝቶ የተመዘገበ የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር በበላይ አካሉ ውሳኔ ወደ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅትነት ወይም ማህበርነት ላቀየርና የምስከር ወረቀት ላያገኝ እንደሚችል በንዑስ ቁጥር አንድ በግልፅ ያስቀመጠ ሲሆን ማንኛውም የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ወደ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅትነት ወይም ማህበርነት ሲለወጥ በባለቤትነቱ ስር ያለን ከውጭ ምንጭ የተገኘን ሀብት ለተለወጠው የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር ላያስተላልፍ እንደማይችል፣በንዑስ ቁጥር አንድ ድንጋጌ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅትነት ወይም ማህበርነት ለመለወጥ ያመለከተ የውጭ የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር የነበረው ከውጭ ምንጭ የተገኘን ሀብት በድርጅቱ የበላይ አካል ወይም በኤጀንሲው ውሳኔ ተመሳሳይ ዓላማ ላለው የውጪ የበጎ አድራጎ ድርጅት ወይም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር መተላለፍ እንዳለበት የአንቀፁ ንዑስ ቁጥር ሁለትና ሶስት እንደ የቅደም ተከተላቸው ሓይለ ቃልን በያዘ አቀራረፅ ያስቀመጡት ጉዳይ ነው።
በመሆኑም አመልካችን አይነት የበጎ አድራጎት ድርጅት ህጉ ከመፅናቱ በፊትም ሆነ በኋላ ከሕግ ውጪ ከውጭ ምንጭ የሰበሰበውን ገንዘብ ተጠሪ በሕጉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተመሳሳይ ዓላማ ላለው ድርጅት ወይም ማህበር ማስተላለፍ እንዳለበት የደንቡ አንቀጽ 18(3) በግልጽ ያሳያል። እንግዲህ በአመልካች የተፈፀመው ተግባር ላይ ተጠሪ በሕጉ ላያደርገው ይገባ የነበረው ገንዘቡን ከማገድ የበለጠ ውጤት ያለውን፤ ገንዘቡን ለልላ ተመሳሳይ ድርጅት ወይም ማህበር ማስተላለፉን የሚያሳይ ነው። እንዲህ ከሆነ በህጉ ከተቀመጠው ያነሰ እርምጃ ተጠሪ መውሰዱ አመልካችን የጠቀመ ነው ከሚባል በስተቀር ለተጠሪ በሕግ ከተሰጠው ስልጣን አድማስ ውጪ ነው ላባል የሚችል አይደለም። የተጠሪ እርምጃ ሕገ ወጥ ላሆን የሚችለው በሕጉ ተለይቶ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር ውጪ ተፈጽሞ ሲገኝ እንጂ በውጤቱ በሕጉ የተሰጠው ስልጣንና ተግባር ከሚያስከትለው ያነሰና ፍትሓዊ ነው የሚለውን አስተዳደራዊ እርምጃ በመፈፀሙ ተግባሩ ከስልጣኑና ከተግባሩ አድማስ ውጪ ነው ለማለት የሚያስደፍርበት ሕጋዊ ምክንያትና አግባብ የለም። በሕግ ያልተከለከለን ተግባር መፈፀም ተቀባይነት የማያገኝበት አግባብም የለም። በመሆኑም አመልካች የተጠሪን ስልጣንና የተወሰደውን እርምጃ መሰረት አድርጎ ያቀረበው ክርክርም ከአዋጁ አንቀጽ 90 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ እንዲሁም በደንቡ አንቀጽ 18(3) ስር ከተመለተከቱት እርምጃዎች ውጤት አኳያ ሲታይ ተቀባይነት ያለው ሁኖ አላገኘነውም።
ሲጠቃለልም የአመልካች ተግባር ከአዋጅ ቁጥር ቁጥር 621/2001 አንቀፅ 2(2፣3፣እና 4)፣6፣ 14(5)፣90፣111 እና 112፣እንዲሁም ከደንብ ቁጥር 168/2001 አንቀፅ 10(2)፣18(3) እና 36 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ አንፃር ሲታይ ገንዘቡ በተጠሪ እንዳይታገድ የሚያደርግበት ሕጋዊ ምክንያት ስለልለ ተጠሪ ገንዘቡን ማገዱም ሆነ አመልካች ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጭ 90% ያህሉን መሰብሰቡ እየተረጋገጠ ከታገደው ገንዘብ ውስጥ 10% እንዲለቀቅለት መደረጉ ሕጋዊ ከሚባልና በውጤቱም ፍትሃዊ ነው ተብሎ ከሚደመደም በስተቀር መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በተጠሪ ቦርድ ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥቅምት 13 ቀን 2004 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል።
የተጠሪ እርምጃ ሕገ ወጥ ነው ላባል የሚችልበት አግባብ የለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
ውሣኔው በ9/02/05 ዓ.ም. ተነበበ።
No topics extracted.