No summary available.
መስከረም 22 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ - የቀረበ የለም።
ተጠሪዎች፡- መምህር ባዬ ዋናያ የዳ - ቀረቡ።
መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ መምህራን በዲስፕላን ግድፈት ከስራ እንዲባረሩ የሚሰጥ ውሣኔ ለአስተዳደር ፍርድ ቤት በይግባኝ የሚቀርብበትን አግባብ የሚመለከት ነው።
ጉዳዩ የተጀመረው በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የአስተዳደር ፍ/ቤት ሲሆን በዚህ ፍርድ ቤት ይግባኙን ያቀረቡት የአሁኑ ተጠሪ ናቸው። የተጠሪ የይግባኝ አቤቱታ ይዘትም ባጭሩ ሲታይ ከዩኒቨርሲቲው ያላግባብ ከስራ እንደተባረሩ ገልፀው ወደ ስራ እንዲመለሱና ውዝፍ ደመወዝ እንዲከፍላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሣይ ነው። የአሁኑ አመልካች ከሰጠው መልስም በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሣኔ በየኒቨርሲቲው ቦርድ ሳይሰጥ ለአስተዳደር ፍርድ ቤት መቅረቡ ያላግባብ መሆኑና ይግባኙ መቅረብ የሚገባው ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ እንጂ ለአስተዳደር ፍርድ ቤት መሆኑን ገልፆ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የመዳኘት ስልጣን የለውም ሲል ተከራክሯል። ይግባኙ የቀረበለት የአስተዳደር ፍርድ ቤትም ጉዳዩን የማየት ስልጣን ያለው መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 515/1999 አንቀጽ 2(8) ስር መደንገጉን ገልፆ በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካች ተቃውሞ ሳይቀበለው ያለፈ ሲሆን በፍሬ ነገር ደረጃም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ ተጠሪ መምህር ከስራ የተሰናበቱት ያለግባብ ነው በሚል ምክንያት ተሰጠ የተባለውን ውሣኔ መሻሩን ገልፆ ተጠሪ ወደ ስራ እንዲመለሱና ያልተከፈላቸው ውዝፍ ደመወዝ በሕጉ አግባብ እንዲከፈላቸው ሲል ወስኗል። በዚህ ውሣኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቢያቀርብም ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዞበታል። የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሣኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የዩኒቨርሲቲውን መምህራን የዲሲፕላን ግድፈትን በተመለከተ ጉዳዩ የሚገዛው በደንብ ቁጥር 1/2002 ሁኖ በስንብት ውሣኔ ቅሬታ ያለው የአካዳሚክ ሰራተኛ ቅሬታውን ማቅረብ ያለበት ለየኒቨርሲቲው ቦርድ ሁኖ እያለና በቦርዱ የሚሰጠው ውሣኔም የመጨረሻ ሁኖ እያለ የፍድራሉ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር አስተዳደር ፍርድ ቤት ጉዳዩን ማየቱ ያላግባብ ነው በማለት መከራከሩን የሚያሣይ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ አመልካች የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለውም በማለት ያቀረበው ተቃውሞ የመታለፉን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በጽሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሣኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 650/2001 በተዘረጋው ስርዓት መሰረት የመጨረሻ ፍርድ አግኝተዋል ወይስ አላገኙም?
የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላመረመር የሚገባው ሁኖ ተገኝቷል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 650/2001 መሰረት ወደ አስተዳደር ፍ/ቤት የይግባኝ ቅሬታ ማቅረብ ያለብኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ከሰጠው ውሣኔ ይግባኝ ለማቅረብ በአዋጅ ቁጥር 515/1999 በተዘረጋው ስርዓት ተፈቅዶልኛል በማለት ሲሆን የአስተዳደር ፍርድ ቤትም ተጠሪ ለአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ይግባኝ የማቅረብ መብት አላቸው ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው በአዋጅ ቁጥር 515/1999 አንቀጽ 2(8) ስር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት የመንግስት መስሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ ተብሎ የሚመደብ በመሆኑና በዚህ ባለስልጣን በሚሰጠው ውሣኔ ለአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ይገባኝ ማቅረብ ይቻላል በሚል ምክንያት መሆኑን ነው። አመልካች የሚከራከረው የዩኒቨርሲቲው አካዳሚ ሰራተኞች የዲስፕላን አፈፃፀም ደንብ ቁጥር 1/2002 አንቀጽ 33(4) ይግባኙ የሚቀርበው ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ መሆኑንና ይህ አካል የሚሰጠው ውሣኔም የመጨረሻ ስለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 44(ኅ) ድንጋጌ ያሣያል በማለት መሆኑን ተረድተናል።
እኛም ይህንኑ የአመልካች መከራከሪያ ነጥብ በአዋጅ ቁጥር 65/2001 አንቀጽ 22(3)፣ 44(ኀ) መሰረት ለዩኒቨርሲቲ ቦርድ ከተሰጡት ኃላፊነቶችና ተግባራት አንፃር ተመልክተናል። በአዋጁ አንቀጽ 32 ሥር የአካዳሚክ ስራተኞች ግድታዎች የተዘረዘሩ ሲሆን የተጠቃሹ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር ሶስት ድንጋጌ ደግሞ ተቋማቱ በዚህ አንቀጽና አግባብነት ባላቸው የአዋጁ ልሎች ድንጋጌዎች ላይ የተመሰረተና የአካዳሚክ ሰራተኞችን ያሣተፈ የአካዳሚክ ሰራተኞች የዲስፕላን ደንብ አውጥተው ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርባቸው መሆኑን በአስገዳጅ ሁኔታ ተደንግጓል። በዚህ የአዋጁ አግባብም አመልካች ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ሰራተኞች የዲሲፕላን ደንብ ቁጥር 1/2002 አውጥቶ ተግባራዊ ያደረገ ስለመሆኑ አከራካሪ የሆነ ጉዳይ አይደለም።
በዚህ ደንብ የአካዳሚክ ሰራተኞች የዲሲፕላን ጥፋቶችና ቅጣቶች፣ የዲሲፕላን ክስ አመሰራረት፣ የምርመራ አፈፃፀምና ውሣኔ አሰጣጥ፣ የቅሬታ አቀራረብ ስርዓት፣ የይግባኝ ምክንያቶችና የጊዜ ገደብን የሚመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎች ተካተዋል። ደንቡ የአካዳሚክ ሰራተኛ የዲሲፕላን ግድፈት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ውሣኔ የሚሰጡበትን አግባብ በአንቀጽ 32 ያስቀመጠ ሲሆን ይህ አካል ከስራ የመባረርን ውሣኔ አስመልክቶ በሚሰጠው ውሣኔ ቅሬታ አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ሰራተኛ ጉዳዩ እንዲታይለት ይግባኙን በአስር ቀናት ውስጥ ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ ላያቀርብ እንደሚችል ተቀምጧል። በአዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 44(ኀ) መሰረትም የዩኒቨርሲቲው ቦርድ የሚሰጠው ውሣኔ የመጨረሻ መሆኑ ተመልክቷል። እንግዲህ ከላይ የተመለከተው ስርዓት አመልካች ዩኒቨርቲው በአዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 32(3) መሰረት የአካዳሚክ ሰራተኞችን የዲስፕላን ግድፈት ለመግዛት የዘረጋው ሰርዓት ነው። አዋጅ ቁጥር 650/2001 ከአዋጅ ቁጥር 515/1999 በኋላ የወጣ በመሆኑና የሚገዛው ጉዳይም ተለይቶ የተሰጠው በመሆኑ በአዋጅ በተካተቱት ጉዳዮች ከማንኛውም አቻ ሕግ የበላይ ገዥነት የሚኖረው ስለመሆኑ ተቀባይነት ያለቸው የሕግ አተረጓጉም ደንቦች የሚያሣዩን ሐቅ ነው። ስለሆነም በአመልካች ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ሰራተኞች የዲሲፕላን ጉዳይ ከአዋጅ ቁጥር 515/1999 ቀዳሚ ተፈፃሚነት ያለው አዋጅ ቁጥር 650/2001 በመሆኑ በዚህ አዋጅ የተዘረጋው ስርዓት ላከበር ይገባል።
በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ ይግባኙን ለቦርዱ ሣያቀርቡ ለአስተዳደር ፍርድ ቤት ያቀረቡት መሆኑን የክርክሩ ሂደት በግልጽ የሚያሣይ ከመሆኑም በላይ በሰበር የክርክር ደረጃ መልሣቸውን ለማሻሻል ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅትም ይህንኑ ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። ተጠሪ በዚህ ምክንያት የሰበር መልሣቸውን ለማሻሻል ያቀረቡት ጥያቄም ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 91 አንፃር ሲታይ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ አስፈላጊ ሆኖ ባለመገኘቱ አልፈነዋል። በመሆኑም ጉዳዩ ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ ቀርቦ ያልታየ መሆኑን ተረድተናል። ጉዳዩ ለዚህ ችሎት የቀረበው ውሣኔውን በሰ/መ/ ከተሰጠው የሕግ ትርጉም ጋር አዞምዶ ለመወሰን ሲባል ሲሆን በዚህ የሰበር መዝገብ የተሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ክርክር የተነሣበት ጊዜ፣ የተከራካሪ ወገኖች የሚገዙበት ሕግ አሁን ከተያዘው ጉዳይ ጋር የማይገናኝና በመሰረታዊ ነጥቦች ጉዳዮቹ የተለያዩ መሆናቸው ግልጽ ከመሆኑም በላይ አሁን በተያዘው ጉዳይ የአስተዳደር ፍርድ ቤት ለጉዳዩ ግንኙነት የልለውን የሰበር መዝገብ ከመጥቀሱ ውጪ ጉዳዩ የመጨረሻ የአስተዳደር ውሣኔ ያገኘ መሆን ያለመሆኑን፣ ፍርድ ቤቶች በዚህ አግባብ በተሰጠው ውሣኔ ላይ ስልጣን ያላቸው መሆን ያለመሆኑን ከአዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 44(ኀ) ድንጋጌ አኳያ ታይቶ መፍትሕ ያልተሰጠበት ጉዳይ በመሆኑ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ባሁኑ የክርክር ደረጃ በዚህ ረገድ ምላሽ የሚሰጠበት ጉዳይ ሁኖ አላገኘነውም። ባሁኑ የክርክር ደረጃ መታየት ያለበት አቢይ ነጥብ ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 650/2001 መሰረት በተዘረጋው ስርዓት ይግባኛቸውን አሟጠው ጨርሰዋል ወይስ አልጨረሱም? የሚል በመሆኑ ይህን ጭብጥ ይዘን ጉዳዩን ስንመለከተው ተጠሪ የይግባኝ ስርዓታቸውን ለሚመለከተው አካል አቀርበው ያልጨረሱ መሆኑን ተገንዝበናል። አመልካች በአስተዳደራዊ አካላት መታየት ያለበትን የይግባኝ ስርዓት ያልጨረሰ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ሰራተኞች የዲሲፕላን ጉዳይ ደግሞ በፍርድ ቤት የሚታይበት አግባብ አይኖርም።
በአጠቃላይ የተጠሪ ይግባኝ ወደ አስተዳደር ፍርድ ቤት የሄደው ስርዓቱን ጠብቆ ይግባኙን ሣይጨርስ በመሆኑ በፍድራል ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስተዳደር ፍርድ ቤት የተሰጠው ውሣኔና ይህንኑ ውሣኔ ያፀናው የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ትእዛዝ አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 32(3) እና አመልካች ዩኒቨርሲቲው ያወጣውን ደንብ ቁጥር 1/2002 አንቀጽ 34(4) ድንጋጌዎችን የጣሰና መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተነዋል። በዚህም መሰረት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የአስተዳደር ፍ/ቤት በይ/መ/ቁ. 01247/2004 ታህሣስ 05 ቀን 2004 ዓ.ም የተሰጠው ብይን እንዲሁም ይኸው አካል ታህሣስ 19 ቀን 2004 ዓ/ም የሰጠው ውሣኔ እና በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኘ ሰሚ ችሎት በመ/ መጋቢት 12 ቀን 2004 ዓ/ም የፀናው ብይንና ውሣኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 32(3) መሰረት ዩኒቨርሲቲው ባወጣው የአካዳሚክ ሰራተኞች የዲሲፕላን ደንብ ቁጥር 1/2002 አንቀጽ 33(4) መሰረት ይግባኙን ማቅረብ ያለባቸው ለአስተዳደር ፍርድ ቤት ሣይሆን ለዩኒቨርሲቲው ቦርድ ነው ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ በተመለከተ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.