No summary available.
ጥቅምት 09 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- አቶ አበራ ኪዳኔ - አልቀረቡም ተጠሪ፡- የጋሞ ጎፋ ዞን አርባ ምንጭ ማህበራዊ ዋስትና ቅ/ጽ/ቤት - ነ/ፈጅ አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
አመልካች ለመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ባቀረቡት አቤቱታ የትውልድ ዘመናቸው 1943 መሆኑን በመጥቀስ በ30/07/2003 ዓ.ም. ዕድሜያቸው 60 ዓመት ስለሚሞላ ከ01/08/2003 ጀምሮ የዘለቄታ የጡረታ ባለመብት መሆናቸው ታዉቆ የጡረታ አበል እንዲወሰንላቸው የጠየቁ ሲሆን ኤጀንሲውም አመልካች በጋሞ ጎፋ ዞን ሥራና ከተማ ልማት በ1986 ዓ/ም ሲቀጠሩ የትውልድ ዘመናቸው 1943 ዓ.ም. ነው በሚል በሕይወት ታሪክ ፎርም የሞሉ ቢሆንም በገንዘብ ሚኒስቴር ተቀጥረው ሲሰሩ የትውልድ ዘመናቸው በ27/7/1933 በሚል የሞሉ ስለሆነ በጡረታ መገለል የነበረባቸውም በ01/08/1988 ዓ.ም. ነው። በገንዘብ ሚኒስቴር ተቀጥረው ከ01/03/1958-30/01/1969 በሚሰሩበት ወቅትም ገንዘብ በማጉደላቸው በወንጀል ተከሰው በ3 ዓመት ጽኑ እስራትና በብር 500 የተቀጡ ስለሆነ በተሻሻለው የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 5/1967 አንቀጽ 34 የመጀመሪያው አገልግሎታቸው ውድቅ የሚደረግ በመሆኑ የሚቆጠረውም ከ20/10/1986-30/07/1988 ዓ.ም. ያለው ነው።
ይህም ጊዜ 1 ዓመት ከ9 ወር ከ11 ቀን ስለሚሆን ላከፈላቸው የሚገባው የዘለቄታ የጡረታ አበል ሳይሆን የዳረጎት ክፍያ ነው በሚል የወሰነ ሲሆን፣ ከ01/9/1988-30/07/2003 ዓ.ም.
ድረስ ከዕድሜ ጣሪያ በላይ ለፈጸሙት አገልግሎትም የከፈሉት የጡረታ መዋጮ ተመላሽ ላደረግላቸው ይገባል ብሐል።
አመልካችም በኤጀንሲው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ቅሬታቸውን ለማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ያቀረቡ ቢሆንም ጉባዔው ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የኤጀንሲውን ውሳኔ በማጽናቱ አመልካች የሰበር አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት የጠቀሱአቸው የቅሬታ ነጥቦችም ፡- በወንጀል የተሰጠብኝ የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔ በመሰየም ተሰርዞ እያለ የአገልግሎት ዘመኔ ውድቅ መደረጉ፣ እንዲሁም የትውልድ ዘመኔ 1933 ዓ/ም ሳይሆን 1943 ዓ/ም ስለመሆኑ በፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ ተረጋግጦ እያለ ተቀባይነት የሚኖረው የትውልድ ዘመን 1933 ዓ/ም ነው ተብሎ መወሰኑ ተገቢነት የለውም የሚሉ ናቸው።
ተጠሪው መሥሪያ ቤት በበኩሉ በሰጠው መልስ፡- አንድ የመንግስት ሰራተኛ በጡረታ ከመንግስት ሥራ የሚሰናበተው ሰራተኛው በሚያቀርበው የልደት ዘመን ማስረጃ ሳይሆን በመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሲቀጠር በሞላው የህይወት ታሪክና የልደት ዘመን መሰረት ነው፣ መሰየም የታጣውን መብት እንደገና የሚያስገኝ አይደለም በማለት የኤጀንሲውና የይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ውሳኔ የህግ ስህተት የለበትም በሚል ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም፡- አመልካች ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ በህጉ መሰረት ደረጃውን ጠብቆ የቀረበ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን እንደሚከተለው መርምረናል።
በዚህ ጉዳይ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ጉባኤ ውሳኔ የሰጠው ሐምል 18 ቀን 2003 ዓ.ም.
ሲሆን ውሳኔው በተሰጠበትም ወቅት ተፈጻሚ የነበረው ስለመንግስት ሰራተኞች ጡረታ ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 714/2003 ነው። በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 56 (1) መሰረት በኤጀንሲው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ባለመብት ቅሬታውን በአዋጁ አንቀጽ 57 ለተቋቋመው የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ይግባኝ የማቅረብ መብት አለው። በንዑስ አንቀጽ 4 ደግሞ ይግባኝ ሰሚው ጉባዔ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ እንደሚሆን የተደነገገ ሲሆን ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት መሆኑን የሚያምን ተከራካሪ ደግሞ ውሳኔው በተሰጠ በ30 ቀናት ውስጥ ይግባኙን ለፍ/ጠ/ፍርድ ቤት የማቅረብ መብት ያለው መሆኑ በዚሁ ንዑስ አንቀጽ ተጠቅሷል። ከድንጋጌው የመጨረሻ ክፍል መገንዘብ የተቻለውም የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ውሳኔ በፍሬ ነገር ደረጃ የመጨረሻ መሆኑንና መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት መሆኑ ሲታመን ግን በይግባኝ ለፍ/ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መቅረብ የሚገባ መሆኑን ነው። ይህ ሆኖ ሳለ አመልካች ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚው ችሎት ማቅረብ ሲገባቸው በሰበር ለዚህ ችሎት ማቅረባቸው ህጉን የተከተለ ባለመሆኑ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
አመልካች ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ በህጉ የተቀመጠውን የአቀራረብ ደረጃ ጠብቆ የቀረበ ባለመሆኑ ውድቅ አድርገናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.