No summary available.
መስከረም 22 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- . አቶ አከለ ምህረቱ - ቀረቡ ተጠሪ፡- ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ - ነ/ፈጅ ተስፋዬ ምንዳገኝ ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ከጡረታ መብት አከባበር ጋር ተያይዞ የተነሳውን የመሰየም ውጤት የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ላይ ተጠሪ በሰጠው ውሳኔ የይግባኝ አቤቱታ በማቅረባቸው ምክንያት ነው። አመልካች ለዚህ አካል ባቀረቡት አቤቱታ ከሰላሳ አመታት በላይ በመንግስት መስሪያ ቤት ያገለገሉ ቢሆንም ተጠሪ መስሪያ ቤት ግንቦት 6 ቀን 2002 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ የሶስት አመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው በመሆኑ በጡረታ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 5/1967 አንቀጽ 34 መሰረት ከ1995 ዓ/ም በፊት የሰጡት አገልግሎት የማይያዝ ስለሆነ ለዘለቄታ ጡረታ መብት ብቁ እንዳልሆኑ ገልፆ የወሰነባቸው መሆኑን፣ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ወደ መደበኛ ስራቸው ተመልሰው እስከ ጥር ወር 2002 ዓ/ም ድረስ ሲያገለግሉ ቆይተው ከየካቲት 01 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ በጡረታ መገለላቸውን አሰሪው መስሪያ ቤታቸው መጋቢት 28 ቀን 2002 ዓ.ም. እና ሰኔ 02 ቀን 2002 ዓ.ም.
በፃፈው ደብዳቤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ መሰረት እድሜአቸው ከሃምሳ በላይ እና አገልግሎታቸው ከሃያ አምስት አመታት በላይ አገልግሎት የሰጡ የመንግስት ሰራተኞች የእድሜ ልክ የጡረታ አበል እንደሚከፈላቸው ተወስኖ የአመልካች መስሪያ ቤትም የጡረታ መብቱ እንዲከበርላቸው የጠየቀላቸው መሆኑን፣ አዋጅ ቁጥር 345/1995 በስራ ላይ ከዋለ በኋላ የጡረታ መብት ጥያቄ የቀረበ በመሆኑ መብታቸውን ጥያቄ ውስጥ ላያስገባ የሚችል ሕጋዊ ምክንያት እንደልለ በመግለጽ አሰሪው መስሪያ ቤት የጠበቀላቸው ቢሆንም ተጠሪ መስሪያ ቤት ተገቢውን ያልፈፀመ መሆኑን፣ በወንጀል ተከሰው በነበሩበት ጉዳይ የመሰየም ውሳኔ ከሐምል 10 ቀን 1999 ዓ/ም ጀምሮ የተሰጠላቸው መሆኑንና በአዋጅ ቁጥር 345/1995 በተሻረው አዋጅ ቁጥር 5/1967 መሰረት መብታቸው የሚገደብበት ምክንያት የልለ መሆኑን ዘርዝረው የዘላቂ የጡረታ መብት እንዲከበርላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል።
የአሁኑ ተጠሪም አመልካች ከመታሰራቸው በፊትም ሆነ በኋላ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥረው መስራታቸውን ሳይክድ የአመልካች የዘላቂ ጡረታ መብት ላከበርላቸው አይገባም በማለት የሚከራከረው ከመታሰራቸው በፊት ያገለገሉበት ጊዜ ላቆጠር አይገባም፣ መሰየም ውጤቱ ወደፊት ነው እንጂ ወደኋላ አይደለም በሚል ምክንያት ነው። ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ የመሰየም ውጤት ወደፊት እንጂ ወደኋላ ላሄድ እንደማይችል ገልፆ አመልካች ያላቸው መብት ከእስር ከተፈቱ በኋላ ያገለገሉበት የሰባት አመት ከዘጠኝ ወራት አገልግሎት የሚያስገኝላቸው መብት ዘላቂ የጡረታ መብት ሳይሆን እንደገና ከተቀጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ከስራ እስከተሰናበቱ ጊዜ ድረስ ከደመወዛቸው እየተቆረጠ ሲጠራቀም የነበረው 4% የጡረታ መዋጮ ነው ተብሎ በተጠሪ መወሰኑ በአግባቡ ነው በማለት ወስኗል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም የህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የመሰየም ውጤት ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይሰራም ተብሎ መወሰኑ ስለመሰየም የተደነገጉትን አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎችን ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ በመሆኑ ላታረም የሚገባው ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች እስራቱን ከጨረሱ በኋላ ወደቀድሞ መስሪያ ቤታቸው ተመልሰው ስራ ከመጀመራቸውና ከመሰየማቸው አንፃር ከእስራት በፊት ያበረከቱት አገልግሎት ላታሰብ አይገባም ተብሎ በኤጀንሲው የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ነው። በዚህም መሰረት ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት የቀረበ ሲሆን በነገረ ፈጁ አማካይኝት ባቀረበው የፅሁፍ ክርክር ችሎቱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የልለው መሆኑን፣ የመሰየም ውጤት ወደፊት እንጂ ወደኋላ ላሆን እንደማይችል፤ መሰየም ለጡረታ መብትም ላሰራ የማይችል መሆኑን ዘርዝሮ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ሲል ተከራክሯል። አመልካች በበኩላቸው የሰበር አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልሳቸውን ሰጥተዋል፡ የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን ከተያዘው ጭብጥ አንፃር በሚከተለው መልኩ መርምሮታል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካች በጡረታ መለያ ቁጥር ሰ/130745 የተመዘገቡና ከየካቲት 08 ቀን 1967 እስከ ህዳር 21 ቀን 1989 ዓ/ም ድረስ ለ22 አመታት ያህል በፍትህ ሚኒስቴር አገልግለው በወንጀል ተከሰው ከህዳር 22 ቀን 1989 እስከ የካቲት 08 ቀን 1994 ዓ/ም ድረስ በ5 አመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ተወስኖባቸው የእስር ጊዜአቸውን በመጨረስ የተፈቱ መሆኑን፣ ከእስር ከተፈቱ በኋላም ከግንቦት 01 ቀን 1994 ዓ.ም. እስከ ጥር 30 ቀን 2002 ዓ.ም. ድረስ ለሰባት አመታት ከዘጠኝ ወራት ያህል በመንግስት መስሪያ ቤት ሲያገለሉ ቆይተው ከየካቲት 01 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ መስሪያ ቤቱ ባካሄደው የአሰራር ለውጥ ማሻሻያ ጥናት መሰረት የተገለሉ መሆኑን፣ ከሐምል 10 ቀን 1999 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የተሰየሙ መሆኑን ነው። አመልካች የዘላቂ ጡረታ መብት ተጠቃሚነት ላከበርልኝ ይገባል በማለት የሚከራከሩት መሰየሙ ውጤቱ ከእስር በፊት የነበረውን የአገልግሎት ዘመን እንዲቆጠር ያደርገዋል፣ ይህ ጊዜ ከተያዘ የሃያ አምስት አመታት የአገልግሎት ዘመንና የሃምሳ አመት እድሜ ቅድመ ሁኔታ ይሟላልኛል በሚል ምክንያት ነው። እንግዲህ ከላይ በፍሬ ነገር ደረጃ ከተረጋገጡት ነጥቦች በመነሳት በሕጉ ረገድ መፍትሕ ማግኘት ያለበት ጉዳይ የመሰየም ውጤት ወደፊት ነው? ወይስ ወደኋላ? የሚለው መሆኑን ተገንዝበናል።
ይህንኑ ጭብጥ ከመመለሳችን በፊት የተጠሪ ነገረ ፈጅ ጉዳዩን ለዚህ ሰበር ችሎት አመልካች ላያቀርቡ አይችሉም ወይም ችሎቱ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን የለውም በማለት በሰ/መ/ የተሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በመጥቀስ ያቀረቡትን ተቃውሞ ተመልክተናል።
በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) ስር እንደተመለከተው ከአምስት ያላነሱ የዚህ ችሎት ዳኞች ተሰይመው የሚሰጡት የሕግ ትርጉም ተመሳሳይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማናቸውም እርከን የሚገኝን ፍርድ ቤትን የሚያስገድድ ነው። አንድ የሕግ ትርጉም ለተመሳሳይ ጉዳይ ገዥነት እንዲኖረው ለማድረግ ደግሞ በመሰረታዊ ነጥቦች ላይ ጉዳዮቹ መመሳሰል ያለባቸው ስለመሆኑ ከአስገዳጅ የሕግ ትርጉም ፅንሰ ሀሳብ የምንገነዘበው ነው። ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም በሰ.መ. የተሰጠው የህግ ትርጉም የማህበራዊ ዋስትና መብትንና ጥቅምን በሚመለከት የማህበራዊ ዋስትና ባለስልጣን በሰጠው ውሳኔ ይግባኝ የቀረበለት የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የመጨረሻ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ ውሳኔ ስለሰጠና ውሳኔውም ፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስላስተናገደው የቀረበ አቤቱታ ሲሆን የሰበር ሰሚ ችሎትም በህግ ተለይተው በአስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲቋጩ በተባሉ ጉዳዮች ላይ መደበኛ ፍርድ ቤት የመዳኘት የስረ ነገር ስልጣን የለውም፣ የማህበራዊ ዋስትና መብትንና ጥቅምን በሚመለከት የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ በመሆኑ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ለማየት የስረ ነገር ስልጣን የላቸውም በማለት ወስኗል። ውሳኔው ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱም ቢሆንም ላቀርብ የሚገባ አይደለም የሚል ይዘት የለውም። ለዚህ ውሳኔ መነሻ የሆነው በግለሰቦች የቀረበው ክርክር ደግሞ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ማህበራዊ ዋስትና ያላግባብ ከእኛ ሂሳብ አውጥቶ የወሰደውን ገንዘብ በሚመለከት የጡረታ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ለማህበራዊ ዋስትና ባለስልጣንም ሆነ ለይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ክስ አቅርበን በስማችን ውሳኔ ስለመስጠቱ የሚያስረዳ ማስረጃ አላቀረበም፣ የአገልግሎት ዘመናችን ተቀንሶብናል ወይም ያለአግባብ እድሜአችን ጡረታ ሳይደርስ በጡረታ እንድንገለል ተደርጓል በሚል ያቀረብነው ክስ ስለልለ በጡረታ ሕጉ መሰረት የሚታይ ጉዳይ የለም፣ አመልካች ያላግባብ ከሂሳባችን አውጥቶ የሰጠውን ገንዘብ ተቀብሎ ወደ ነበረበት ሂሳብ እንዲያስገባ በሚል የቀረበውን ክስ አይቶ የመወሰን ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት ነው የሚል ይዘት ያለው ነው። አሁን በተያዘው ጉዳይ ግን ቀጥታ ክስ በፍርድ ቤት የቀረበበት ወይም የይግባኝ አቤቱታ የቀረበበት ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም የማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚው ጉባኤ በሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ ላታረምልኝ ይገባል በሚል በቀጥታ ለዚህ ችሎት የቀረበ ነው። ጉዳዩ በተነሳበት ጊዜ ስራ ላይ በነበረው ሕግ አግባብ ማህበራዊ ዋስትና ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው ከተባለ በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 በተመለከተው አግባብ ለዚህ ሰበር ችሎት አቤቱታ ከማቀረብ የሚከለክል ሕጋዊ አግባብ የለም።
በሰ/መ/ የተሰጠው ትርጉም የሰበርን ስልጣንም የሚጨምር አይደለም።
በመሆኑም የተጠሪ ነገረ ፈጅ የሰ/መ/"ን" መሰረት በማድረግ ያቀረቡት ተቃውሞ በመዝገቡ ላይ ያሉትን መሰረታዊ የክርክር ነጥቦችንና ጉዳዩ መታየት የጀመረበትን አካሄድ አሁን ከተያዘው ጉዳይ ጋር በመሰረታዊነት የሚለይ መሆኑና ሰበር ችሎቱ በሕገ መንግስቱ በማናቸውም የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተትን የማረም ስልጣን ያለው መሆኑን ያላገናዘበ በመሆኑ ተቀባይነት የልለው ሆኖ ስለአገኘን ተቃውሞውን አልተቀበልነውም።
ወደዋናው ጭብጥ ስንመለስም በመሰረቱ የጡረታ አዋጅ ቁጥር 209/1955 በአዋጅ ቁጥር 5/1967 እንደተሻሻለው አንቀጽ 34 አንድ የመንግስት ሰራተኛ ወይም ጡረተኛ በወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ መሆኑ በሕግ በተቋቋመ ፍ/ቤት ሲረጋገጥና ቢያንስ የሶስት አመት የፅኑ እስራት ቅጣት ሲወሰንበት የጡረታ መብቱን እንደሚያጣ ወይም በመከፈል ላይ ያለው የጡረታ አበል እንደሚቋረጥ ደንግጓል። አመልካች ይህ ድንጋጌ በአዋጅ ቁጥር 345/1995 የተሻረ በመሆኑ የአዋጅ ቁጥር 345/1995 በስራ ላይ በነበረበት ጊዜ ለቀረበ ጥያቄ ተፈፃሚነት የለውም በማለት የሚከራከሩ መሆኑንም ተገንዝበናል። ይሁን እንጂ በአዋጅ ቁጥር 209/1955፣ በአዋጅ ቁጥር 5/1967 እንደተሻሻለ የተገኙት መብቶችና ግድታዎች ቀሪ ያልሆኑ ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀጽ 52/1/ ስር የተደነገገ በመሆኑ እና ይህ ሰበር ሰሚ ችሎትም በዚህ ረገድ በመ/ በቀረቡት ጉዳዮች ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠበት በመሆኑ በዚህ በኩል የቀረበው የአመልካች ክርክር ተቀባይነት ያለው ሆኖ አላገኘነውም።
የመሰየም ውጤትን በተመለከተ የቀረበውን ክርክርና በይግባኝ ሰሚ ጉባኤው የተሰጠውን ውሳኔ ሕጋዊነት ስንመለከትም መሰየም አንድ ተቀጪ በዋናው ቅጣት ወይም በዋናው ቅጣትና ተጨማሪው ቅጣት ምክንያት አጥቶት የነበረውን ንፁህ ሰው ሆኖ የመገመት መብቱን እንደገና መልሶ የሚያገኝበትንና ተወስኖበት የነበረው ዋናው ቅጣትም ሆነ ተጨማሪ ቅጣት ተመዝግቦበት ከነበረው ከግል የፍርድ ሰልዳው ላይ ተሰርዞ ለሶስተኛ ወገኖች ይኸው ሁኔታ የሚገለፅበትንና የሚታወቅበትን አግባብ የሚመለከት የሕግ አካሄድ ስለመሆኑ የኢ.ፍ.ዲ.ሪ.ህ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 232 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ከአስቀመጡት መንፈስና ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 235(1) ድንጋጌ በተለይ ሲታይም ተቀጥቶ የነበረው ሰው ከተሰየመበት ጊዜ ጀምሮ ተወስኖበት የነበረው የመብት፣ የማዕረግ፣ ወይም የችሎታ ማጣት ለወደፊቱ ቀሪ ሆኖለት ሕዝባዊ መብቱንና ቤተሰብ የማስተዳደርና የሙያ ስራ መስራት መብቱን እንደገና ለመያዝ ችሎታ ይኖረዋል በማለት አስገዳጅነት ባለው መልኩ አስቀምጦ እናገኛለን። ከዚህ ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለው ደግሞ ማንም ተቀጪ በመሰየሙ ላያገኝ የሚችለው መብት ከመሰየሙ አስቀድሞ በቅጣት ቀሪ ሆኖበት የነበረውን መብት ሳይሆን ከተሰየመበት ጊዜ ጀምሮ ወደፊት ላጠበቅበት የሚገባውን መብት ብቻ ስለመሆኑ ነው። በተያዘው ጉዳይም አመልካች ከመሰየማቸው በፊት በመንግስት መስሪያ ቤት ያገለገሉበት አገልግሎት ጊዜ በመሰየማቸው ምክንያት ዋጋ እንዲኖረው ላደረግ ይገባል በማለት የሚያቀርቡት ክርክር ከላይ ስለመሰየምና ውጤቱ በሕጉ በግልፅ የተመለከተውን መስፈርት መሰረት ያላደረገ ሆኖ አግኝተናል። በመሆኑም የይግባኝ ሰሚው ጉባኤ መሰየም ውጤቱ ወደፊት እንጂ ከመሰየም አስቀድሞ በቅጣት ቀሪ ሆኖ የነበረውን መብት መልሶ ማግኘት አይደለም በማለት አመልካች ከየካቲት 08 ቀን 1967 እስከ ህዳር 21 ቀን 1989 ዓ/ም ድረስ ያገለገሉት የአገልግሎት ዘመን ላያዝላቸው አይገባም በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
በጉዳዩ ላይ በይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
መሰየም ውጤት የሚኖረው ተቀጪው ከተሰየመበት ጊዜ ጀምሮ ወደፊት እንጂ ከመሰየሙ አስቀድሞ በቅጣቱ አጥቶት የነበረውን መብት አይደለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.