No summary available.
ጥር 01 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- መሪጌታ ፍቅረ ማርያም ካሴ ጠበቃ ማርታ በቀለ ቀረቡ ተጠሪ፡- የቤንች ማጂ ዞን ዐ/ሕግ አልቀረቡም መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የቀረበው የአሁን አመልካች በቀረበበት የወንጀል ህግ አንቀጽ 539/1/ ድንጋጌ ሥር ጥፋተኛ መባሉ አግባብ ነው ወይስ አይደለም? እንዲሁም የተጣለበት የቅጣት መጠን በቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት በአግባቡ ተሰልቷል ወይስ አልተሰላም የሚሉትን ነጥቦች ለማየት በሚል ነው።
በዚህ አከራካሪ ነጥብም ላይ ግራ ቀኙ በዚህ የሰበር ደረጃ በበኩላቸው ያላቸውን ክርክር በፅሑፍ አቅርበዋል።
እኛም በየደረጃው ባሉት ፍ/ቤቶች የተሰጠውን ውሣኔ የአሁን አመልካች ለዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ እና ተጠሪ ዐ/ሕግ ለሰበር አቤቱታው ከሰጠው መልስ ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን እንደሚከተለው ተመልክተናል።
የአሁን አመልካች በወንጀል ህግ አንቀጽ 539/1/ የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የሰው ህይወት ለማጥፋት አስቦና አቅዶ የፀቡ መነሻ ምን እንደሆነ ባልታወቀ ምክንያት ተነሳስቶ ሚዛን ከተማ ዕድገት ቀበል ውስጥ ልዩ ስሙ ሸኮ በር አካባቢ ወ/ሮ ጥንቅሽ መታፈሪያን ሰርቪስ ቤት ከዲማ የመጣ መሆኑንና የመጣውም በገብርኤል ቤተክርስቲያን በቅስና ላያገለግል ተቀጥሮ እንደሆነ ትክክለኛ ስሙን በመቀየር ቄስ ዘካርያስ ነኝ በማለት ህዳር ዐ7 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም ከተከራየ በኋላ ህዳር ዐ8 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም በግምት ከልላቱ 7፡ዐዐ ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ ቀን አብሮት ሲዘዋወር የነበረውን ሟች ሽፈራው ደሳለኝን ከተከራየው ቤት ውስጥ በመጫኛ ገመድ አንቆ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ አንገላቶ በጭካኔና ነውረኛ በሆነ መንገድ አንቆ ገድሐል በሚል በግፍ ሰው አገዳደል ወንጀል ክስ ተከሷል።
ተከሣሹ የአሁን አመልካች ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም በማለት ክዶ በመከራከሩ የዐ/ሕግ የሰው ማስረጃዎች ቀርበው ተሰምተዋል። ሟች ታንቆ የተገደለበትም መጫኛ በኢግዚቢትነት ቀርቧል። የአስከሬን ምርመራ ውጤቱንም የሚገልፅ ከሚዛን አማን ሆስፒታል የሰነድ ማስረጃ እና ሟች ሞቶ የተገኘበትን ሁኔታ የሚገልፅ ፎቶ ግራፍ በገላጭ ማስረጃነት ቀርቧል።
በዐ/ሕግ በኩል የቀረቡት ማስረጃዎች እንደ ክሱ አቀራረብ ተከሣሹ ልላት በግምት 7፡00 ሰዓት አካባቢ ሲሆን ለሟች ሞት ምክንያት የሆነውን ድርጊት የፈፀመው የአሁን አመልካች ነው ከሚል መደምደሚያ ላያደርስ የሚችለውን ድርጊቱ በተፈፀመበት ጊዜ ከሟች የተሰማውን ጩኸት ይህንን ጩኸት ሰምተው ሟች ሞቶ ወደ ተገኘበት ቤት ሄደው በሩን ቢደበድቡ ፤
ቢያንኳኩ ተከሣሹ መብራት አጥፍቶ ድምፅ እንዳልሰጠ ፤ በኋላ በሩን በቁልፍ ከኋላ በኩል እንደሚቆልፉበት ሲገልፁለት ሟች ታሞብኝ ነው ማለቱንና መብራት ያጠፋው ይጋጭብኛል በማለት እንደሆነ ሁሉ አስረድተዋል። አመልካች ይህንን ድርጊት ከመፈፀሙ በፊት ለአቀደው ተግባር ዝግጅት ይሆን ዘንድ ስሙን በመቀየር ፤ የመጣበትም ተግባር ለቅስና አገልግሎት መሆኑን የመጣበትም አድራሻ ከትክክለኛው አድራሻ የተለየ መሆኑን ሁሉ ገልፆ ሟች ሞቶ የተገኘበትን ቤት መከራየቱንና ሟች ሞቶ ከቤት ውስጥ ከመገኘቱ በፊት ይኸው አመልካች በቤት አለመገኘቱን በጊዜው ከሁለቱ በቀር ልላ ሰው አለመኖሩን ይልቁንም መጥፋቱን በኋላም በክትትል ከትክክለኛው አድራሻ መያዙን ሁሉ ገልፀው የመሰከሩ ሲሆን፤ የሟችን አሟሟት ሁኔታ ይገልፃል በተባለው የሟች አስከሬን ምርመራ ውጤት ላይ ደግሞ በሟች አንገት ላይ የመታነቅ ምልክት የነበረ እና ከቀኝ አይኑ የመመታትና የመበለዝ ምልክት የነበረ መሆኑ ተመልክቷል። ሟች በሞተበት ጊዜ የተገኘው መጫኛም በችሎት የቀረበው መሆኑ በሰው ማስረጃዎችም ተነግሯል።
የሥር ፍ/ቤትም ከዚህ በላይ በዐ/ሕግ በኩል ክሱን ለማስረዳት የቀረበውን ማስረጃ ከክሱ ጋር በማገናዘብ መርምሮ ተከሣሹ የአሁን አመልካች የወንጀሉን ድርጊት የፈፀመ ለመሆኑ ላያረጋግጥ የሚችል አጥጋቢ ማስረጃ መሆኑን ጠቅሶ ይከላከል ሲል በይኗል። ይህም በሥር ፍ/ቤት የተሰጠው ብይን ቀርቦ የተሰማ የታየ እና የተመረመረ ማስረጃ በዐ/ሕግ በኩል የቀረበን ክስ ለማስረዳት ባለው የማስረጃነት ክብደት በመመርመር ረገድ ባለው ፍሬ ነገርን በማስረጃ የማረጋገጥና የተረጋገጠውን ጉዳይ በማስረጃነት በመመዘኑ ሥልጣን በመገልገል የሰጠው ዳኝነት በመሆኑ የአሁን አመልካች በማስረጃ አልተረጋገጠብኝም የሚለው ክርክሩ የማስረጃ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 141 እንደተደነገገው ከላይ የሰፈረው የዐ/ሕግ ማስረጃ የቀረበውን የወንጀል ጉዳይ ለማስረዳት በወንጀል ጉዳይ መቅረብ ከሚገባው የማስረጃ የማስረዳት ሁኔታ /standard of proof/ አንፃር ይታይ ቢባልም በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 141 የተመለከተውን ድንጋጌ በመፈፀም ረገድ የሥር ፍ/ቤት የህግ ስህተት መፈፀሙን የሚያመለክት ሆኖ አልተገኘም።
የአሁን አመልካችም እከላከላለሁ በማለት የሰው ማስረጃዎችን አቅርቦ ቢያሰማም እነዚህ የሰው ማስረጃዎች ከፊሎቹ ስለጉዳዩ ምንም የሚያውቁት ጉዳይ አለመኖሩን ቀሪዎቹ ደግሞ በዐ/ሕግ ማስረጃ የተረጋገጠበትን ጉዳይ ለማስተባበል የማይችል መሆኑን የሥር ፍ/ቤት ማስረጃውን መዝኖ ውድቅ ያደረገው በመሆኑ ከላይ እንደተመለከተው ይህ ማስረጃውን የመመዘን የዳኝነት ሥራ እንጂ የህግ ጥያቄን የሚያስነሳ ሆኖ አልተገኘም።
በልላ በኩል በወ/መ/ሕ/ቁ 539/1/ ሥር የተመለከቱ ንዑሳን የህግ ክፍሎች እያሉ በየትኛው ንዑስ ክፍል የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፍ ድርጊቱን የፈፀምኩ ለመሆኑ በግልፅ ተጠቅሶ ባለመከላከል የተነሣ ክሱን በመከላከል ረገድ መብቴን አጣቧል በማለት ይከራከር እንጂ በቀረበበት የወንጀል ክስ ዝርዝር ላይ የተገለፁት ፍሬ ጉዳዮች በሙሉ የአመልካች አድራጐት ሰውን ለመግደል አስቦ አመቺ ጊዜና ቦታ መርጦ ሟችን የገደለው መሆኑና አገዳደሉም ቢሆን ጭካኔንና ነውረኛነትን የተላበሰ መሆኑ ሁሉ የተገለፁ በመሆኑ አድራጐቱ በወ/ሕ/ቁ 539/1/ሀ/ የተመለከተውን በመተላለፍ በሚል እንደሆነ እጅግ ግልፅ የሆነ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 111 እና 112 የተመለከቱትን ድንጋጌዎች አፈፃፀም ያልጣሰ በመሆኑ በዚህ በኩል ያቀረበውም የክርክር ነጥብ የህግ መሰረት ያለው አይደለም። በዚህ ሁሉ ምክንያት የአሁን አመልካች በወ/ሕ/ቁ 539/1/ሀ/ የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፎ ሟችን በመግደሉ በግፍ ሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ ነው በሚል የተሰጠው የጥፋተኛነት ውሣኔ በአግባቡ ከመሆኑ በቀር መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አላገኘነውም።
በልላ በኩል በዚህ አጥፊ ላይ ተገቢውን ቅጣት ለመጣል የሥር ፍ/ቤት የግራ ቀኙን የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ተቀብሎ በመረመረበት ጊዜ በአሁን አመልካች በኩል አንድ የቅጣት ማቅለያ መቅረቡን አረጋግጦ ተቀብሐል። ሆኖም የዚህ አንድ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ሶስት እርከን ላያስቀንስ የሚችል ስለመሆኑ በፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በወጣው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002 አንቀጽ 16/7/ ስር በግልፅ ተመልክቶ እያለ ሁለት እርከን ብቻ መቀነሱ ይህንኑ የቅጣት መመሪያ ያልተከተለ ከመሆኑም በላይ ተጠሪ ዐ/ሕግም ይህንኑ ተገንዝቦ በዚህ ረገድ ቅጣቱ ተስተካክሎ ቢወሰን ተቃውሞ እንደልለው ገልፆ መልሱን በፅሑፍ ሰጥቷል። ስለሆነም በቅጣት አጣጣል ረገድ የሥር ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል። ስለሆነም ከላይ በፍርድ ሐተታው ላይ የተገለፁትን ሁሉ በማየት የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት በቤንች ማጂ ዞን የቤንች አካባቢ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ ጥር 16 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ ፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ መጋቢት 18 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም የተሰጠው ውሣኔ እና የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መ/ ሰኔ 12 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም የተሰጠው ትዕዛዝ ሁሉ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 195/2/ለ/2/ መሰረት ተሻሽሐል።
በአመልካች ላይ በሥር በየደረጃው ባሉት ፍ/ቤት የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሣኔ ፀንቷል።
የአሁን አመልካች ጥፋተኛ በተባለበት የወንጀል ህግ አንቀጽ 539/1/ሀ/ ሥር የተቀመጠውን የቅጣት ዓይነት መነሻ በማድረግ ፤ እና ዝቅተኛውን የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት በመያዝ በቅጣቱ መመሪያ አንቀጽ 13/8/ ላይ የተመለከተውን እርከን 38 የወደቀ መሆኑን የሥር ፍ/ቤት መወሰኑን ተቀብለን ከዚሁ እርከን ላይ በፍርድ ሐተታው ላይ እንደተገለፀው ሶስት እርከን በአንድ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ሲቀነስ 35 እርከን ላይ የሚወድቅ በመሆኑ በዚሁ እርከን ላይ የተቀመጠውን የቅጣት አንጓ በማየት አመልካች ከህዳር 19 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም ጀምሮ በሚታሰብ በአስራ ዘጠኝ ዓመት (በ19 ዓመት) ፅኑ እስራት ይቀጣ በማለት አሻሽለን ወስነናል።
በዚህ ተሻሽሎ በተወሰነው የቅጣት ውሣኔ መሰረት ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ለሚዛን ማረምና ማነፅ ተቋም ትዕዛዝ ይድረሰው ብለናል።
መዝገቡ ተዘግቷል። ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.