No summary available.
ጥር 17 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል አላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ ሙስጠፋ አህመድ አመልካቾች፡-
በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የወንጀል ክርክር ሲሆን የተጀመረውም በቤ/ጉ/ክልል በመተከል ዞን በቡላን ወረዳ ፍ/ቤት ነው። የወረዳው ዐ/ሕግ በቁጥር 1569/2/89 በ28/11/03 በተፃፈ ማመልከቻ በአሁኖቹ አመልካቾች ላይ ያቀረበው ክስ በኢ.ፍ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/እና 433 ስር የተደነገገውን ተላልፈው በ28/11/03 ከቀኑ 5. ሰዓት ላይ ከሚመለከተው ባለስልጣን ሳያስፈቅዱና ፈቃድ ሳይኖራቸው ከቡላን ወረዳ ደቢና ባሩዳ ቀበል 15 የቀንድ ከብቶችን ገዝተውና በመኪና ጭነው ወደ ታግኒ ከተማ ሲጓዙ ኬላ ላይ በመያዛቸው ያለፈቃድ ከብት የማዘዋወር ወንጀል አድርገዋል የሚል ሲሆን ፍ/ቤቱም የዐ/ሕግን የሰው ማስረጃ እና የተከሳሾቹን የጽሑፍ መከላከያ ከመረመረ በኋላ በተከሳሾቹ ላይ በተከሰሱበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ውሳኔ እና በነፍስ ወከፍ የብር 1,200 መቀጮ ከወሰነ በኋላ በኤግዚቢትነት የተያዙት 15 ከብቶች ተሸጠው የጠባቂዎች አበል ከተቀነሰ በኋላ የሽያጩ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ትእዛዝ ሰጥቷል።
አመልካቾቹ በቀጣይ እርከን ለሚገኙ የክልሉ ፍ/ቤቶች ያቀረቡት ይግባኝ እና አቤቱታ ተቀባይነት ሳያገኝ የቀረ ሲሆን በ18/ዐ4/ዐ4 ለዚህ ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ ይዘትም በኤግዝቢትነት የተያዙት የቀንድ ከብቶች በወንጀል የተገኙ ናቸው ባልተባለበት እና አመልካቾቹ ጥፋተኛ የተባሉበት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 433 ድንጋጌ የንብረት መውረስን ባልደነገገበት ሁኔታ ከብቶቹ ተወርሰው ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑ በወረዳው ፍ/ቤት የተሰጠውና በበላይ ፍ/ቤቶች የፀናው ትእዛዝ ከወንጀል ድርጊቶች ጋር ተያይዞ ንብረት ስለሚወረስበት ሁኔታ በወንጀል ሕጉ የተመለከተውን መርህ የሚጥስ እና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ላሻር ይገባዋል የሚል ነው። ተጠሪ በበኩሉ በ26/06/04 በተፃፈ ማመልከቻ በሰጠው መልስ የውርስ ትእዛዙ ዋና ቅጣት ሳይሆን ተጨማሪ ቅጣት መሆኑ የዚህ ዓይነቱ የውርስ ትእዛዝ በወ/ሕ. አ. 761/ሀ/ 791 እንዲሁም በፍድራል የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/200 በአንቀጽ 6ዐ ድንጋጌዎች መሰረት ተቀባይነት ያለውና የወንጀል ሕጉን መርህ መሰረት ያደረገ መሆኑን በዝርዝር በመግለጽ የሰበር አቤቱታው ውድቅ ተደርጐ የውርስ ትእዛዙ የተሰጠው በአግባቡ ነው ተብሎ እንዲፀና ተከራክሮአል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል፡ በዚህም መሰረት አመልካቾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ የተሰጠባቸውን የጥፋተኛነት እና የቅጣት ውሳኔ አግባብነት ተቀብለው መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል በማለት አቤቱታ ያቀረቡት በውርስ ትእዛዙ ላይ ብቻ ሲሆን ለሰበር ክርክሩ በጭብጥነት የተያዘውም ይኸው ነጥብ ነው። በመሰረቱ በወንጀል ጉዳይ ንብረት ወይም ሀብት ላወረስ ወይም ለመንግስት ገቢ ላደረግ የሚችልባቸው ሁኔዎች በወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል ተደንግገው የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ ድንጋጌዎች መካከልም በሕግ በግልጽ በተደነገገ ጊዜ ፍ/ቤቱ የወንጀለኛው ንብረት በሙሉ ወይም በከፊል እንዲወረስ ላወስን የሚችል ስለመሆኑ /አንቀጽ 98/ ፣አንድ ሰው ለወንጀል ስራ እንዲነሳሳ ወይም ወንጀሉን ለመስራት እንዲረዳው ወይም ወንጀሉን ለፈፀመበት ዋጋ እንዲሆነው የተሰጠው ወይም ላሰጠው የታቀደው ማናቸውም ጥቅም ሁሉ ለመንግስት ገቢ ስለሚሆንበት አግባብ /አንቀጽ 1ዐዐ/ እና ወንጀልን ለመፈፀም ያገለገሉ ወይም ላያገለግሉ የሚችሉ ወይም የወንጀል ተግባር ፍሬ የሆኑ ማናቸውም ነገሮች ስለሚወረሱበት አግባብ /አንቀጽ 14ዐ/ በመሰረታዊነት የሚጠቀሱ ናቸው። ፍ/ቤቶች የጥፋተኝነት ና የቅጣት ውሳኔን ተከትሎ ንብረት ወይም ሀብት እንዲወረስ ወይም ለመንግስት ገቢ እንዲሆን መወሰን የሚችሉትና የሚገባቸው እነዚህን ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ ነው።
በተያዘው ጉዳይ አመልካቾች ጥፋተኞች የተባሉበት የወ.ሕ.አ. 433 ድንጋጌ የንብረት ውርስን አልደነገገም። በዚህ ድንጋጌ ስር የሚሰጥ የጥፋተኛነት ውሳኔ የንብረት መወረስን ወይም ለመንግስት ገቢ መደረግን የሚያስከትል መሆኑን የሚገልጽ ልላ ድንጋጌ የለም። በአመልካቾቹ ላይ ክሱን ያቀረበው የቡለን ወረዳ ዐ/ሕግ የጥፋተኛነት ውሳኔን ተከትሎ ባቀረበው የቅጣት አስተያየት ከብቶቹ በውርስ ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑ ያቀረበው ጥያቄ አለመኖሩን የመዝገቡ ግልባጭ ያስረዳል። የወረዳው ፍ/ቤትም ሆነ ቀጥሎ ያሉት የክልሉ ፍ/ቤቶች ለንብረት ውርሱ ውሳኔ መሰረት ያደረጉትን ድንጋጌ በውሳኔአቸው አልገለጹም። ከብቶቹ ተሸጠው ገንዘቡ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን የተሰጠው ትእዛዝ ወይም ውሳኔ ከላይ ከተጠቀሱ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 98፣ 1ዐዐ እና 14ዐ ድንጋጌዎች በአንዳቸውም ቢሆን የሚሸፈን ሆኖ አልተገኘም።
ተጠሪ በመልሱ የጠቀሳቸው በደንብ መተላለፍ ክፍል የሚገኙት የወ.ሕ. አ. 761(ሀ) እና 791 ድንጋጌዎች ለጉዳዩ አግባብነት እንደልላቸው ከይዞታቸው መገንዘብ የሚቻል ከመሆኑም በላይ የፍድራል የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2000 አንቀጽ 6ዐ ድንጋጌ አመልካቾቹ ያልተከሰሱበትና ጥፋተኛ ያልተባሉበት በመሆኑ ለንብረት ውርስ ውሳኔው መሰረት ላሆን የሚችሉበት አግባብ አልተገኘም ። በመሰረቱ የወንጀል ሕግ ስለልዩ ልዩ ወንጀሎችና በወንጀል አድራጊዎች ላይ ስለሚፈፀሙት ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎች በዝርዝር እንደሚደነግግ እና ፍ/ቤቶች በሕግ ከተደነገጉት በቀር ልሎች ቅጣቶችንና የጥንቃቄ እርምጃዎችን መወሰን እንደማይችሉ በወ.ሕ.አ. 2 (1) እና (2) ተመልክተዋል። ንብረት ወይም ሀብት እንዲወረስ ወይም ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ማድረግን ጨምሮ ፍ/ቤቶች በወንጀል ረገድ የሚሰጡት ማናቸውም ውሳኔ በወ/ሕ/አ. 2 የተደነገገውን የሕጋዊነት መርህ መሰረት ያደረገ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።
በዚህም ሁኔታ በኤግዚቢትነት የተያዙት ከብቶች ተሸጠው የጠባቂዎች አበል ከተቀነሰ በኋላ የሽያጩ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ እንዲሆነ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ትእዛዝ /ውሳኔ/ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላተገኘ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
በኤግዚቢትነት የተያዙት ከብቶች ተሸጠው ገንዘቡ ለመንግስት ገቢ ይሁን በማለት የቡላን ወረዳ ፍ/ቤት በወ.መ.ቁ. 01035 በ04/12/03 የሰጠው ትእዛዝ እንዲሁም የመተከል ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ በ11/12/03 የቤ/ጉ/ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 03253 በ04/03/04 እና የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ በ04/04/04 ከሰጡት ትእዛዝ ውስጥ የንብረት ውርሱን የሚመለከተው ክፍል በወ.መ.ሕ.ሥ.ሥ.ቁ. 195/2/ለ/2/ መሰረት ተሽረዋል።
በኤግዚቢትነት የተመዝገቡት 15 የቀንድ ከብቶች ከተሸጡበት ገንዘብ ውስጥ የጠባቂዎች አበል ተቀንሶ ለመንግስት ገቢ የተደረገው መጠን ለአመልካቾቹ ተመላሽ እንዲደረግ ወስነናል። የውሳኔው ቅጂ ይላክ።
በበዓል ምክንያት ውሳኔው በአዳሪ በ17/05/05 ተነገረ
ክርክሩ ውሳኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል። ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.