No summary available.
ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ መኰንን ገ/ህይወት አመልካች፡- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተጠሪ፡- አብካለ እንደሻው ጠቅላላ ንግድ ኃ/የተወሰነ የግል ማህበር መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሁኑ የሰበር አመልካች ከሳሽነት የተጀመረው በሐዋሳ ከተማ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁኑ ተጠሪም 1ኛ ተከሳሽ ነበር። ክሱም ፤ተከሳሽ በተጨማሪ እሴት ታክስ ቀ.1079.39005 እና በግብር ከፋይ መለያ ቁጥር( TIN) 00512280 ለከሳሽ መሥሪያ ቤት ግብር ከፋይ ሲሆን፤ ግብይት ሲያካሂድ በተጨማሪ እሴት ታክስ ማከናውን የህግ ግድታው ሆኖ እያለ በ07/08/2003 ዓ/ም ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት በተደረገው ድንገተኛ ክትትል ድርጅቱ ያለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ግብይት ሲያከናውን በመገኘቱ በወ/ህ/ቁ/ 34(1) ፣አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 56(1) እና ይህንኑ አዋጅ ለማሻሻል በወጣውን አዋጅ ቁጥር 609/2001 አንቀጽ 22(1) እና 50(ለ)(1) የተደነገገውን በመተላለፉ ተከሷል የሚል ነው።
ተከሳሽ ድርጅትም ክስ የቀረበበትን ወንጀል አለመፈጸሙንና ጥፋተኛ አለመሆኑን ክዶ በመከራከሩ የግራ ቀኙ ማስረጃዎችን ፍርድ ቤቱ በመስማትና በመመዘን በሰጠው ፍርድ የከሳሽ ማስረጃዎች ያስረዱትን ፍሬ ነገሮች ተከሳሽ ድርጅት ባቀረባቸው የመከላከያ ማስረጃዎች በቂ በሆነ ሁኔታ አስተባብሐል በሚል በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ.149(2) መሰረት በነጻ አሰናብቶታል።
ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም የግራ ቀኙን ወገን ካከራከረ በኋላ የሥር ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ.
195(2)ለ)(2) መሰረት አጽንቷል።
የሰበር አቤቱታም የቀረበው በሥር ፍርድ ቤቶች ወሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ሲሆን አመልካች በዋናነት የጠቀሰው የቅሬታ ነጥብም ሲጠቃልል፡ተጠሪው ያለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ግብይት ያከናወነ መሆኑ በሚገባ ተረጋግጦበት እያለ የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔ ፍርድ ቤቶቹ ማስተላለፍ ሲገባቸው በወ/ህ/አንቀጽ 34(1) አንድ በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው ድርጅት በወንጀል የሚጠየቀው ከድርጅቱ ሀላፊዎች ወይም ሰራተኞች አንዱ ከድርጅቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የድርጅቱን ህጋዊ ግድታ በመጣስ ወይም የድርጅቱን ጥቅም በህገ ወጥ መንገድ ማራመድ ሲሆን ይህንኑ በአንቀፁ የተቀመጠውን ሁኔታ ባለማገናዘብ ከክሱ በነጻ እንዲሰናበት የወሰኑት ተገቢ አይደለም የሚል ነው።
ተጠሪው በበኩሉ በሰጠው መልስ፡- አንድ የንግድ ማህበር ወይም ድርጅት የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁ/285/1994 እና ማሻሻያውን አዋጅ ቁ.609/2001 ተላልፏል በሚል በወንጀል ጥፋኛ ላሰኝና ላቀጣ የሚችለው የተጣሉበትን መሰረታዊ የግብር ከፋይነት ግድታዎችን በመጣስ ሥርዓቱን በሚጻረር ህገ ወጥ የግብይት አሰራር ዘርግቶ ሲገኝ ወይም አሰራሩ ህገ ወጥ ግብይትን የሚያበረታታ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፣በዚህ ጉዳይም አንድ ዕለት ተፈጸመ በተባለና በተጨባጭም ባላተፈጸመ ስህተት ብቻ አዋጁን በሚጻረር መልኩ ህገ ወጥ የግብይት ሥርዓት ዘርግቷል ላያሰኝና በአዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 56(1) እንደተሻሻለው አንቀጽ 22(1) ላያስቀጣ የሚችል አንድም ሁኔታ ባለመኖሩ የስር ፍርድ ቤቶች ይህንኑ በመገንዘብ በነጻ ያሰናበቱ ስለሆነ ውሳኔው የህግ ስህተት ያልተፈጸመበት ነው በሚል ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም፡- ተጠሪው ከቀረበበት ክስ በነጻ እንዲሰናበት የተወሰነው በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
አመልካች ሁለት ምስክሮችን አቅርቦ ማሰማቱን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሚያመለክት ሲሆን እነዚህ ሁለቱም ምስክሮች ወንጀሉ ተፈጸመ በተባለው ወቅት በተጠሪ ድርጅት ጭማቂ (ጅውስ) የጠጡና ያለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ግብይቱ የተፈጸመ ስለመሆኑ ያስረዳሉ በሚል የቀረቡ ናቸው። ምስክሮቹም ለሥር ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያስረዱት ፍሬ ነገርድንገተኛ ፍተሻ ለማድረግ ሶስት ሆነው ወደ ተጠሪው ድርጅት ሄደው ሶስት ጭማቂ (ጅውስ) አዘው ጭማቂው ከመጣላቸው በኋላ ጠጥተው ብር 30 ለአስተናጋጁ ሰጥተው መልሱን ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ አስተናጋጁም ዝም በማለቱ መልስ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ የሚመለስ ገንዘብ አለመኖሩን በመግለጹ ከ3-5 ደቂቃ ያህል ቆይተው ወደ ገንዘብ ያዥ (ካሸር) አስተናጋጁን ይዘው ሄደው የተቆረጠ ደረሰኝ መኖሩንና አለመኖሩን በመጠየቅና የተቆረጠ ደረሰኝ አለመኖሩን ማረጋገጣቸውንና በተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ጥራዝ (ፓድ) የጭማቂው ሽያጭ አለመመዝገቡን ነው። ከዚህ በተጨማሪም ምስክሮቹ የድርጅቱ ሥራ አስያኪያጅ በቦታው የነበሩ ስለመሆናቸው ለሥር ፍርድ ቤት ማስረዳታቸውን ፍርድ ቤቱ በፍርዱ ላይ አስፍሯል።
የተጠሪ ምስክሮች ደግሞ ለስር ፍርድ ቤት ያስረዱት ፍሬ ነገሮች ፡-ተጠሪው ደርጅት ግብይት የሚያካሂደው በተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ መሆኑን፣ የድርጅቱ ሰራተኞችም በየዕለቱ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጁን ተከትለው እንዲሰሩ ተጠሪው ቅስቀሳ የሚያደርግ መሆኑን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከቀረቡት 2 የመከላከያ ማስረጃዎች 1ኛው የመከላከያ ማስረጃ ወንጀሉ ተፈጸመ በተባለው ዕለት በቦታው ባለመኖሩ ምክንያት የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ መቆረጡንና አለመቆረጡን እንደማያውቅ ማስረዳቱን፣ እንዲሁም 2ኛ የመከላከያ ምስክር ደግሞ በጊዜው የተሸጡ ጭማቂዎች ሶስት ብቻ እንደሆኑና በደረሰኝ ሁለት ጫማቂዎች፣ በደረሰኝ ደግሞ አንድ ጭማቂ የተሸጠ ስለመሆኑ ማስረዳቱን የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍርዱ አመልክቷል። ከፍተኛው ፍርድ ቤትም እነዚህን የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮች መነሻ በማድረግ 3ኛ ተከሳሽ የነበረውን የተከሳሽ ድርጅት(ሐሮኒ ኢንተርናሽናል ሆቴል)ሥራ አስኪያጅ ቁጥጥር ባለማድረጋቸው ምክንያት ያለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ግብይት ወይም ሽያጭ ተፈጽሟል በሚል የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል።
የወንጀል ህግ አንቀጽ 34 የህግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት የወንጀል ተካፋይ ላሆን የሚችልበትን አግባብ የሚደነግግ ሲሆን በዚሁ ደንጋጌ በንዑስ አንቀጽ (1) በሁለተኛው ፓራግራፍ አንድ ደርጅት ወንጀል እንዳደረገ ተቆጥሮ የሚቀጣው ከሀላፊዎቹ ወይም ከሰራተኞቹ አንዱ ከድርጅቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የድርጅቱን ጥቅም በህገ ወጥ መንገድ ለማራመድ በማሰብ ፣ወይም ሕጋዊ ግድታ በመጣስ፣ወይም ድርጅቱን በመሳሪያነት ያለአግባብ በመጠቀም በዋና ወንጀል አድራጊነት ፣በአነሳሽነት ወይም በአባሪነት ወንጀል ሲያደርግ መሆኑ ተመልክቷል። በዚህ በተያዘውም ጉዳይ የተጠሪ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ በወንጀል ተከሰው የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔ እስከተሰጠባቸው ድረስም በወንጀል ህግ አንቀጽ 34(1) በሁለተኛ ፓራግራፍ መሰረትም ተጠሪው ድርጅት የወንጀሉ ተካፋይ እንደሆነ የሚቆጠር በመሆኑም ተጠሪው ድርጅት በተከሰሰበት የወንጀል ህግ አንቀጽ 34(1) አዋጅ ቁጥር 285/1995 አንቀጽ 56(1) ስር ጥፋተኛ መሆን ያለበት ነው።
ይህ ሆኖ ሳለ የሥር ፍርድ ቤቶች ተጠሪው ድርጅት ለግብሩ አከፋፈል የሚያገልግሉ ደረሰኞች የህትመት ፈቃድ ከአመልካች መ/ቤት በማግኘትና በሥራ ላይ በማዋል የሚጠበቅበትን አሟልቶ በመገኘት ለመንግሥት ገቢ መሆን ያለበትን ገንዘብ በአግባቡ እንዲሰበሰብ ያመች ዘንድም ለድርጅቱ ሥራ አሰኪያጅ በመቅጠር ስለ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሽያጭ ደረሰኝም ለሰራተኞቹ ትምህርትና ጥንቃቄ እንዲያደረጉ ተገቢውን ጥረት ስለማድረጉ የአመልካች ምስክሮች ከሳረዱት በተሻለ ሁኔታ የተጠሪው ምስክሮች ክሱን አስተባብለዋል በሚል ከክሱ ተጠሪው ድርጅት በነጻ እንዲሰናበት የወሰኑት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 34(1) እና አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 56(1) የተደነገገውን እና ይህ ችሎት የወንጀል ጥፋት በአንድ ድርጅት ተፈጽሟል ላባል ስለሚችልበት ሁኔታ በተመሳሳይ ጉዳይ በሰ/መ/ቁ/48850 የሰጠውን አስገዳጅ ውሳኔ ያልተከተለ በመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ በወ/መ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ. 195(2)(ሀ) መሰረት በመሻር ተጠሪው ድርጅት በተከሰሰበት የወንጀል ህግ አንቀጽና እና በአዋጁ ድንጋጌ አንቀጽ 56(1) ሥር ጥፋተኛ ነው ብለናል።
የሰ/መ/ ህዳር 06 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሤ መኰንን ገ/ሕይወት አመልካች፡- የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዐ/ሕግ - አልቀረበም ተጠሪ፡- እብካለ እንዳሻው ጠ/ንግድ ኃ.የተ.የግል ማህበር - አልቀረበም መዝገቡ የተቀጠረው የቅጣት ውሣኔ ለመስጠት ተብሎ ሲሆን የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ከሕግ ጋር በማገናዘብ መርምረን ተከታዩን የቅጣት ውሣኔ ሰጥተናል።
ቅ ጣ ት ተጠሪ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 56/1/ን የተላለፈ ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን አጥፊ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለበት። ቅጣት የሚወሰነው ደግሞ በወ/ሕ/አንቀጽ 88/2/ ስር ያሉትን ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ ነው። ይህ ችሎትም እነዚህን ሁኔታዎች ተመልክቷል፣ አመዛዝኗልም።
ተጠሪ ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል ሲሆን ጥፋተኛ የተባለበት የወንጀል ድርጊት የሚያስቀጣው ከብር 10,000.00 (አስር ሺህ ብር) በማያንስ እና ከብር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺህ ብር) በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እና ከሁለት እስከ አምስት አመት በሚደርስ እስራት መሆኑን አዋጅ ቁጥር 285/1994 በአዋጅ ቁጥር 609/2001 እንደተሻሻለ ያሳያል። በተጠሪ አይነት ሰው ላይ ቅጣት የሚወሰንበትን አግባብ ደግሞ የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 90 መሰረት መሆኑን የወንጀል ህጉ የሚገልፅ ሲሆን የሕግ ሰውነት ባለው አካል ላይ የገንዘብ ቅጣት እና እስራት በሚጣልበት ጊዜ የእስራት ቅጣቱ ሁኔታ ወደ ገንዘብ በመቀየር መሆኑን የአንቀጹ ንዑስ ቁጥር ሶስት ድንጋጌ ይገልፃል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት እስከ አምስት አመት ቀላል እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ብር አስር ሺህ፣ እስከ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ለሚያስቀጣ እስከ ብር ሃያ ሺህ፣ እስከ አስር ዓመት ለሚያስቀጣ እስከ ብር ሃምሳ ሺህ፣ ከአስር ዓመት በላይ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል በአንቀጹ ንዑስ አንቀጽ እስከተመለከተው ከፍተኛ ወሰን ማለትም እስከ ብር አምስት መቶ ሺህ ድረስ የገንዘብ መቀጮው ላደርስ እንደሚችል ሕጉ ያሣያል። እንዲሁም የገንዘብ ቅጣትም በንዑስ ቁጥር አራት ድንጋጌ እንደተደነገገው እስከ አምስት እጥፍ እንደሚደርስ በግልጽ ተቀምጧል። በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 90/3/ ድንጋጌ መሰረት እስከ አምስት ዓመት ላደርስ የሚችል ጽኑ እስራት እስከ ብር 20,000.00 ድረስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚቀየር ተደንግጓል። በመሆኑም የተጠሪን የድርጊት አፈፃፀም ስንመለከተው ቀላል ተብሎ ላመደብ የሚገባ በመሆኑ በአመልካች ላይ ላጣል የሚገባው የገንዘብ መቀጮ ብር 10,000.00 /አስር ሺህ ብር/ ሁኖ የእስራት ቅጣቱን ደግሞ የሁለት አመት ጽኑ እስራት ሁኖ አግኝተናል። ይህ የሁለት አመት ጽኑ የእስራት ቅጣት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 90/3/ በተደነገገው ስልት መሰረት ወደ ገንዘብ ሲቀየር የሚመጣው ብር 8,000.00 በመሆኑ እና ይህ ከገንዘብ መቀጮ ከብር 10,000.00 ጋር ሲደመር የሚመጣው ውጤት ብር 18,000.00 /አስራ ስምንት ሺህ ብር/ ተጠሪን የሚያርም፣ ልሎችን የሚያስተምርና የሚያስጠንቀቅ ሁኖ አግኝተናል። በመሆኑም ተጠሪ ይህንኑ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ እንዲያደርግ፣ አመልካችም ተከታትሎ እንዲያስፈፅም ብለናል።
No topics extracted.