No summary available.
ህዳር 6 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ መኰንን ገ/ሕይወት አመልካች፡- ተስፋዬ ጡምሮ ተጠሪ፡- የፍድራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን - ዐቃቤ ህግ ዋልተንጉስ ፍቅሬ ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና የፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ያቀረበው የወንጀል ክስ ነው።
ተጠሪ አመልካች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ ቁጥር 419 ንዑስ አንቀጽ 1(ለ) የተመለከተውን በመተላለፍ፣ ከ1992 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ/ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ ሰርቷል። ተከሳሽ የመንግስት ሰራተኛ በነበረበት ጊዜ በወር ብር 420 (አራት መቶ ሃያ ብር) እና ብር 530 (አምስት መቶ ሰላሳ ብር) እየተከፈለው የቆየ ቢሆንም፣ በመንግስት ስራ ላይ በነበረበት ጊዜ ሲያገኝ ከነበረው ገቢ ጋር የማይመጣጠን ብር 1,167,637.60 (አንድ ሚላዮን አንድ መቶ ስልሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ሰላሳ ሰባት ብር ከስልሳ ሳንቲም) በዳሸን ባንክ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በወጋገን ባንክና በንብ ባንክ ሲያንቀሳቅስ በመቆየቱና የሰልዳ ቁጥሩ አ.አ. 2-78716 የቤት አውቶሞቢል መኪና በስሙ በመገኘቱ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዞ የመገኘት ወንጀል ፈፅሟል በማለት ጥር 14 ቀን 2002 ዓ.ም ያቀረበው የወንጀል ክስ ነው። አመልካች የክሱ ግልባጭ ከደረሰውና ከተነበበለት በኋላ የወንጀሉን ድርጊት አልፈጸምኩም ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ተከራክሯል።
ተጠሪ በአመልካች ላይ ያቀረበውን የወንጀል ክስ ለማስረዳት አመልካች ሲያንቀሳቅስ ስለነበረው ሒሳብ የሚያሳዩ ከተለያዩ ባንኮች የተሰጠውን የሂሳብ ማመዛዘኛ የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል። አመልካች በተጠሪ የቀረበበትን የሰነድ ማስረጃ መከላከያ ማስረጃ በማቅረብ እንዲያስተባብል የስር ፍ/ቤት ብይን ሰጥቷል። አመልካች ሾጌ የሲሚንቶ ውጤቶች የሁለገብ የህብረት ስራ ማህበር የሚባል በህግ የተመዘገበና ዕውቅና ያለው ድርጅት የሚሰጣቸው የሲሚንቶ ውጤቶች ዋጋ በመቀበል በስሙ ሒሳብ የሚያንቀሳቅስ መሆኑን የሚያሳዩ የሰነድ ማስረጃዎች ናቸው በማለት የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።
የከፍተኛው ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አመልካች በስሙ በተለያዩ ባንኮች ሲያንቀሳቅስ የነበረው በወንጀል ክሱ የተጠቀሰውን ገንዘብና መኪና ምንጩ ህጋዊ መሆኑን ለማስረዳት ያቀረባቸው ማስረጃዎች አጠራጣሪ ናቸው በማለት አመልካች በ1997 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 419 ንዑስ አንቀጽ 2(ለ) የተመለከተውን በመተላለፍ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ ይዞ የተገኘ ጥፋተኛ ነው ብሎ፣ አመልካች በሁለት ዓመት ከሶስት ወር ፅኑ እስራትና በብር 66,660 መቀጮ እንዲቀጣ። መኪናውና በባንክ የተገኘው ብር 27,330 (ሃያ ሰባት ሺህ ሶስት መቶ ሰላሳ ብር) እንዲወረሱ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት አቅርቦ፣ ይግባኝ ሰሚው ችሎት የስር ፍ/ቤት የሰጠውን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ አጽንቶታል።
አመልካች ጥቅምት 2 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ እኔ የመንግስት ሰራተኛ የነበርኩት ከ1992 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ/ም መሆኑ ተጠሪ ባቀረበው የወንጀል ክስ ማመልከቻ በግልፅ ተጠቅሷል። አዲሱ የወንጀል ህግ በስራ ላይ እንዲውል ህግ አውጭው የደነገገው ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ይህም የወንጀል ህጉ አንቀጽ 419 ወደ ኋላ ተመልሶ እንዲሰራ በማድረግ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 5 የተደነገገውን መርህ የሚጥስ እና መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ፍርድ የተሰጠብኝ መሆኑን ያሳያል። የታርጋ ቁጥር ኮድ 2- 78716 የሆነችው መኪና የተገዛቸው በ2002 ዓ.ም መሆኑና ምንጩም የታወቀ መሆኑን አስረድቼ እያለ ለመንግስት ውርስ እንድትሆን መወሰኑ የህግ ስህተት አለበት። ስለዚህ የስር ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ተሽሮ በነፃ እንድሰናበት በማለት አመልክቷል።
ተጠሪ በበኩሉ አመልካች የወንጀል ህጉ ወደኋላ ተመልሶ ላሰራ አይገባም በማለት ያቀረበውን መከራከሪያ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 130 መሰረት በመጀመሪያ ክስ መቃወሚያ አድርጎ አላቀረበም። ስለዚህ በሰበር ደረጃ ይህንን መከራከሪያ አድርጎ እንዲያቀርብ የሚፈቅድለት ህግ የልለ በመሆኑ ክርክሩ ውድቅ እንዲደረግልን። አመልካች የወንጀል ድርጊቱን 1992 እስከ 1996 ዓ/ም ባለው ጊዜ ብቻ እንደተፈፀመ አድርጎ ያቀረበው ክርክር የወንጀሉን ባህሪ ያላገናዘበ ነው። አመልካች የወንጀል ምርመራ እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስና እስከተከሰሰበት ድረስ የወንጀል ድርጊቱ ተፈፅሞ ተጠናቅቋል ለማለት ስለማይችል የአመልካቹ የሰበር አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግልኝ በማለት ጥር 5 ቀን 2004 ዓ.ም የተፃፈ መልስ ሰጥቷል።
አመልካች ጥር 23 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ የመልስ መልስ አመልካች የመንግስት ሰራተኛ የነበረው እስከ 1996 ዓ.ም መሆኑን ተጠሪ ለስር ፍ/ቤት ባቀረበው የወንጀል ክስ በግልጽ አስፍሯል። አመልካች የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸው ከ1996 ዓ.ም በኋላ ከቆመ፣ በዚህ መዝገብ አከራካሪ የሆነው ጉዳይ የወንጀል ምርመራ እስከተጣራበትና ክስ እስከቀረበበት ድረስ ወንጀሉ የሚቀጥልበት ሁኔታ የለም የሚል ክርክር አቅርበዋል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም (1) ተጠሪ አመልካች በ1997 ዓ.ም ሥራ ላይ የዋለው የወንጀል ህግ በእኔ ላይ ተፈፃሚነት የልለው በመሆኑ፣ በዚህ ህግ መሰረት ልከሰስና ልቀጣ አይገባኝም በማለት በወንጀለኛ መቅጫ ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 130 መሰረት በመጀመሪያ ክስ መቃወሚያነት ያላቀረበው በመሆኑ አሁን ይህንን ነጥብ የሰበር መከራከሪያ ላያደርገው አይገባም በማለት ያቀረበው ክርክር ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? (2) የስር ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት አመልካች በ1997 ዓ.ም የወጣውንና ግንቦት 1 ቀን 1997 የፀናውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 419 በመተላለፍ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዞ ተገኝቷል በማለት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? የሚሉትን ጭብጦች በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130 ንኡስ አንቀጽ 2 የተዘረዘሩት መቃወሚያዎች ተከሳሽ ወዲያውኑ ማቅረብ እንዳለበት የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130 ንዑስ አንቀጽ 3 ይደነግጋል። ሆኖም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130 ንዑስ አንቀጽ 2 የተዘረዘሩት የወንጀል ክስ መቃወሚያዎች አመላካች (indicative provision) እንጅ ሁሉንም በመቃወሚያነት ላቀርቡ የሚችሉ ጉዳዮችን በሙሉ የሚዘረዝር (exhaustive provision) ድንጋጌ አይደለም። አመልካች የሰበር መከራከሪያ ያደረገው ነጥብ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130(2) የተመለከተ አይደለም ሆኖም ተጠሪ አመልካች የመንግስት ሰራተኛ የነበረው የኢ.ፍ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ ከመጽናቱ ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ/ም በፊት 1992 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም እንደሆነ ተጠሪ ባቀረበው የወንጀል ክስ በግልፅ አስፍሮታል።
የወንጀል ህግ ወደኋላ ተመልሶ የማይሰራ መሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 22 እና በኢ.ፍ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረታዊ መርህ ሆኖ ተደንግጓል። ስለሆነም ዳኞች ወንጀሉ የተፈፀመበት ጊዜ የኢ.ፍ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ ፀንቶ በስራ ላይ ከመዋሉ በፊት መሆኑን ከተረዱ በማናቸውም ጊዜ አንስተው ውሳኔ ለመስጠት የማይከለክሉና በህገ መንግስቱ አንቀጽ 13(1) የተጣለባቸውን ሰብአዊ መብት የማስከበር ግድታቸውን የሚወጡበት አንደኛው መንገድ በመሆኑና የወንጀል ክስ የቀረበበት ድርጊት በወንጀለኝነት የሚደነግግ ግልጽ የወንጀል ህግ ድንጋጌ በልለበት ሁኔታ የኢ.ፍ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ ወደኋላ ተመልሶ እንዲሰራ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን የወንጀል ክስ ዳኞች በመመርመር የህገ መንግስቱንና የወንጀል ህጉን መሰረታዊ መርህ የማስከበር ግድታ አለባቸው። ስለዚህ ተጠሪ ያቀረበው የወንጀል ክስ የህገ መንግስቱን አንቀጽ 22 እና በወንጀል ህጉ አንቀጽ 5 የተደነገገውን መሰረታዊ መርህ የሚያሟላ መሆን አለመሆኑን በመመርመር የመወሰን ስልጣን በማናቸውም ደረጃ በሚገኝ ፍ/ቤት የተሰየሙ ዳኞች ያላቸው በመሆኑ በዚህ በኩል አመልካች ያቀረበውን ክርክር አልተቀበልነውም።
ይህንንም የወንጀል ህጉ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 2" የወንጀል ህጉ ድርጊቱ በዚህ ህግ መሰረት ወንጀል ሆኖ በተሻረው የወንጀል ህግ ግን እንደወንጀል ካልተቆጠረና የተፈፀመው ይህ ህግ ከመጽናቱ በፊት ከሆነ ላያስቀጣ አይችልም" በማለት ደንግጎታል።
ተጠሪ ለስር ፍ/ቤት ባቀረበው ክስ አመልካች የመንግስት ሰራተኛ የነበረው ከ1992 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም መሆኑን በግልጽ አስፍሯል። የወንጀል ህጉ በፀናበትና ስራ ላይ በዋለበት ግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም አመልካች የመንግስት ሰራተኛ እንዳልነበረ የተጠሪ የክስ ማመልከቻ ያረጋግጣል። ተጠሪ ክስ ያቀረበው አመልካች የወንጀል ህጉ ከመጽናቱ ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም በፊት የመንግስት ሰራተኛ የነበረ መሆኑንና አመልካች ምርመራ በተጣራበት 2001 ዓ.ም በስሙ የተለያዩ ባንኮች ሒሳብ ከፍቶ ሲያንቀሳቅስ የነበረውን ገንዘብና በስሙ የገዛትን መኪና ከ1992 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም ሲያገኝ ከነበረው ደመወዝ ጋር በማመዛዘን ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ይዟል በማለት ነው። ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈፀመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈፀሙ ወይም አለመፈጸሙ ወንጀል መሆኑ ካልተደነገገ በስተቀር ላቀጣ እንደማይችልና ወንጀሉ በተፈፀመበት ጊዜ ተፈፃሚ ከነበረው የቅጣት ጣሪያ በላይ ላቀጣ እንደማይችል በህገ መንግስቱ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 1 ተደንግጓል።
እንደዚሁም አገራችን ባፀደቀችው ዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 1 "No one shall| be held guilty of any criminal offence on account of any act or omission which did not constitute a criminal offence under national or international law, at the time which the criminal offence was committed" በሚል መንገድ ተደንግጓል።
አመልካች የመንግስት ሰራተኛ የነበረው የኢፍዲሪ ወንጀል ህግ ከመጽናቱ በፊት ነው። ስለዚህ አመልካች የመንግስት ሰራተኛ በነበረበት ጊዜ ተፈፃሚነት የነበራቸው የወንጀል የህግ ማዕቀፎች በ1949 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግና በ1974 ዓ.ም የወጣው የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት የተሻሻለው ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ አዋጅ ቁጥር 214/1974 ናቸው። በኢፍዲሪ የወንጀል ህግ የወንጀል ድርጊት ሆኖ የተደነገገውና ይዘቱ የተዘረዘረው የወንጀል ህግ አንቀጽ 419 ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ አመልካች የመንግስት ሰራተኛ በነበረበት ጊዜ ተፈፃሚነት ባላቸው የወንጀል ህግ ማዕቀፎች የወንጀል ድርጊት ሆኖ የተደነገገ ድርጊት አይደለም።
ስለሆነም ተጠሪ የኢፍድሪ የወንጀል ህግ ከመፅናቱ ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም በፊት የመንግስት ሰራተኛ በነበረውና የወንጀል ህጉ ከመፅናቱ በፊት የመንግስት ስራውን ለቅቆ በንግድ ስራ መሰማራቱ በክርክር ሂደት በተገለፀው አመልካች ላይ የኢፍዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 419 በመጥቀስ ያቀረበው ክስ የህገ መንግስቱን አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 1 የዓለም አቀፉን የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 1 እና የኢፍዲሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 2 የተደነገገውን መሰረታዊ የወንጀል ህግ መርህ የሚጥስና የአመልካችን መብት የሚያጣብብ ነው። የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ከላይ የተገለፀውን የህገ መንግስቱንና የወንጀል ህጉን መሰረታዊ መርህ በማስፈፀም የተጠሪን የወንጀል ክስ ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው አመልካች ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዞ በመገኘት የሙስና ወንጀል፣ የፈፀመ ጥፋተኛ ነው በማለት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው።
ስለሆነም የስር ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡትን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 195 ንዑስ አንቀጽ 2(ለ) 1 መሰረት በመሻር አመልካች በነፃ እንዲሰናበት ወስነናል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 195 ንዑስ አንቀጽ 2(ለ) 1 መሰረት ተሽሯል።
አመልካች በነፃ እንዲሰናበት የተወሰነ በመሆኑ በልላ ጉዳይ ካልታሰረ በስተቀር በዚህ ጉዳይ ከእስር እንዲለቀው ለክፍሉ ማረሚያ ቤት የመፈቻ ትዕዛዝ ይፃፍ።
አመልካች ከተከሰሰበት ወንጀል በነፃ የተሰናበተ በመሆኑ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የወሰኑት የገንዘብ መቀጮና በአመልካች ስም በባንክ የሚገኝ ገንዘብና ቁጥር 2-78716 አ.አ የሆነችው መኪና እንዲወረስ የሰጡት ውሳኔ ተሽሯል።
No topics extracted.