No summary available.
ጥቅምት 20 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- 1.አቶ ሀይላይ ተክሉ 2. አቶ ተክላይ ገ/ላባኖስ ጠበቃቸው አበበ መስፍን ቀረቡ ተጠሪ፡- የመቀል ከተማ ሰሜን ምድብ ዐ/ህግ አልቀረበም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
የአሁኑ የሰበር ተጠሪ የአሁን የሰበር አመልካቾችን ጨምሮ በ 8 ተከሳሾች ላይ ነሐሴ 11 ቀን 2002 ዓ/ም ያቀረበው ክስ፡- ተከሳሾች በትግራይ መንገዶች ባለሥልጣን የመኪና ግዥ የጨረታ የቴክኒክ ኮሚቴ ሆነው ሲሰሩ መሥሪያ ቤቱ ያወጣውን ባለ 11 ቴክኒካል መስፈርቶችን ወደ ጎን በመተው ከተጠየቀው መለኪያ በታች ያቀረበውን ሐግቤስ የተባለው ተወዳዳሪ ድርጅት ቅናሽ ዋጋ አቅርቧል በሚል ጨረታውን እንዲያሸንፍ አድርገው መስፈርት ያላሟላ መኪና እንዲገዛ በማድረጋቸው መኪናው የሚፈለገውን አገልግሎት ሳይሰጥ የተበላሸ በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊ ያልሆነ ወጪ እንዲያወጣ በማድረግ በወ/ህ/አ/ 420/2/ የተደነገገውን በመተላለፋቸው ተከሰዋል የሚል ነው።
ተከሳሾችም ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ፡- ከሳሽ ጠቅሶ ያቀረበብን የወንጀል ህግ አንቀጽ 420 /2/ በእስራት የሚያስቀጣ ሲሆን የእስራት ጊዜውም በወንጀል ህግ አንቀጽ 106(1) ሥር እንደተደነገገው ከአስር ቀን እስከ ሶስት ዓመት በመሆኑና የቀላል እስራት ይርጋ ዘመንም በወ/ህ/አንቀጽ 217(1)(ሰ) መሰረት አምስት ዓመት በመሆኑ ከሳሽ የወንጀሉ ድርጊት ተፈጽሟል በማለት በክሱ ከጠቀሰበት 29/04/1997 ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት እስከ 11/12/2002 ዓ/ም ድረስ አምስት ዓመት ከስምንት ወር ያለፈ በመሆኑ ክሱ በይርጋ የሚታገድ ነው ሲሉ ተከራከረዋል።
ከሳሽም የቀረበውን የይርጋ መቃወሚያ በተመለከተ በሰጠው መልስ፡- ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል እስከ ሶስት ዓመት የሚያስቀጣ ቢሆንም ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው የታወቀው በ29/04/1997 ዓ.ም. ሳይሆን በ14/04/2001 ዓ.ም. ነው። በክሱ የተጠቀሰው ቀን 29/4/1997 ዓ.ም. ተከሳሾች የሚሰሩበት መ/ቤት ጨረታ ያወጣበት ሲሆን ጉዳዩ የታወቀበት 14/04/2001 ዓ.ም. በመሆኑ ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ሲቆጠርም የይርጋ ጊዜው ያላለፈ ስለሆነ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ተቀባይነት የለውም ሲል ተከራክሯል።
የወረዳው ፍርድ ቤትም፡- ከሳሽ ተከሳሾች ወንጀሉን የፈጸሙት በ29/04/1997 ዓ/ም ሲሆን የወንጀሉ ድርጊት የታወቀው ደግሞ በ14/4/2001 ዓ/ም ነው ቢልም የክልሉ ኦዲተር ለክልሉ ፍትህ ቢሮ በ24/9/2001 ዓ.ም. የጻፈው ደብዳቤ በ14/4/2001 ዓ/ም መሆኑን አይገልጽም፣ በክሱ ወንጀሉ ተፈጽሟል የተባለው በ29/04/1997 ዓ/ም በመሆኑ ከሳሽ ክሱን መመስረት የሚገባው በ29/04/1997 ዓ/ም ነው፣ ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀልም እስከ ሶስት ዓመት ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን ከአንድ ዓመት በላይ የሚያስቀጣው ቀላል እስራትም የይርጋው ዘመን አምስት ዓመት በመሆኑ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ከ29/04/1997 ዓ/ም ጀምሮ ክሱ እስከቀረበበት ድረስም ያለው ጊዜ ሲቆጠር ከአምስት ዓመት በላይ ስለሆነ ክሱ በወ/ህ/አ/ 216 (ሰ) መሰረት በይርጋ የሚታገድ ነው ብሐል።
ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የመቀል ከተማ ማዕከላዊ ፍርድ ቤትም፡- ይግባኝ ባይ ያቀረበውን ይግባኝ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/195(1) መሰረት በመሰረዙ ይግባኝ ባይም በሥር ፍርድ ቤቶች ብይን ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል የሰበር አቤቱታውን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበ ሲሆን ችሎቱም የግራ ቀኙን ወገኖች ካከራከረ በኋላ በሰጠው ፍርድ፡በዚህ ጉዳይ ወንጀሉ ተፈጽሟል የተባለው በ29/04/1997 ዓ.ም. በመሆኑ ክሱ እስከቀረበበት እስከ 11/12/2002 ዓ/ም ያለው ጊዜ የሚቆጠር ነው። ሆኖም ተጠሪዎች ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ፖላስና ዐቃቤ ህግ ምርመራ ማጣራት የጀመሩት በ14/04 2001 ዓ.ም. መሆኑን የምርመራ መዝገቡ የሚሳይ ሲሆን የምርመራው መጀመር የይርጋውን መቆጠር የሚያቋርጥ ስለመሆኑ የወንጀል ህግ አንቀጽ 221 ስለሚደነግግ አመልካች ያቀረበው ክስ የክስ ማቅረቢያ ጊዜ ያላለፈበት በመሆኑ በይርጋ የሚታገድ አይደለም በሚል የስር ፍርድ ቤቶችን ብይን ሽሯል።
አመልካቾችም በክልሉ ሰበር ሰሚው ችሎት ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል ሲሉ የሰበር አቤቱታቸውን ለዚህ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት የጠቀሱአቸው የቅሬታ ነጥቦችም፡- ፖላስ በተጠርጣሪዎች ላይ ምርምራ ለማድረግ ከፍርድ ቤት የመያዣ ወይም የብርበራ ትዕዛዝ ሳያገኝ የምርምራ መቅደም በ14/04/2001 ዓ.ም. መክፈቱን በመግለጹ ብቻ የይርጋ መቆጠርን ያቋርጠዋል በሚል ሰበር ሰሚው ችሎት መወሰኑ በወ/ህ/አ/219 እና 221 የተደነገገውን የሚቃረን ነው፣ ፖላስ በአመልካቾች ላይ ምርመራ ጀምሯል ላባል የሚችለውም በጉዳዩ ላይ የተከሳሽነት ቃላችንን እንድንሰጥ ደብዳቤ ከተጻፈልን ከ27/05/2002 ዓ.ም. ጀምሮ ስለሚሆን ወንጀሉ ተፈጸመ ከተባለበት ከ29/04/1997 ዓ/ም ጀምሮ ደብዳቤው እስከተጻፈበት ድረስም ያለው ጊዜ ሲቆጠር አምስት ዓመት ያለፈው ስለሆነ ክሱ በይርጋ የሚታገድ ነው የሚሉ ናቸው ።
ተጠሪው በበኩሉ በጉዳዩ ላይ መልሱን እንዲያቀርብ ታዞ መጥሪያ የደረሰው ቢሆንም ቀርቦ መልስ ያልሰጠ በመሆኑ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፏል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም፡- በአመልካቾች ላይ የቀረበው ክስ በይርጋ የሚታገድ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
ተጠሪው አመልካቾች የተጣለባቸውን የስራ ኃላፊነት ባለመወጣት በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሰዋል በሚል በወንጀል ህግ አንቀጽ 420(2) ሥር ክስ ያቀረበባቸው ሲሆን በዚህ ድንጋጌ ጥፋተኞች ሆነው ቢገኙ ላወሰንባቸው የሚችለው ቀላል እስራቱና መቀጮው በህጉ እስከተወሰነው ከፍተኛው ቅጣት ላደርስ እንደሚችል ከድንጋጌው መገንዘብ የሚቻል ነው።
ቀላል እስራትም ከአስር ቀን እስከ ሶስት ዓመት የሚያስቀጣ መሆኑን የወንጀል ህግ አንቀጽ 106(1) የሚደነግግ ሲሆን በወንጀሉ ከባድነት የተነሳ በህጉ ልዩ ክፍል ተደንግጎ ሲገኝ ወይም በቀላል እስራት የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲኖሩ ወይም ወንጀለኛው በተደጋጋሚ ሲቀጣ ቀላል እስራቱ አስከ አምስት ዓመት ላደርስ እንደሚችል የድንጋጌው 2ኛው ፓራግራፍ ያመለክታል።
ከአንድ ዓመት በላይ ቀላል እስራት ለሚያስቀጣ ወንጀል የክስ ማቅረቢያ የይርጋ ዘመን አምስት ዓመት መሆኑ በወንጀል ህግ አንቀጽ 217(1)(ሰ) ስር የተደነገገ ሲሆን የይርጋ ዘመኑም መቆጠር የሚጀምረው ጥፋተኛው የወንጀሉን ድርጊት ከፈጸመበት ቀን አንስቶ ስለመሆኑ የወንጀል ህግ አንቀጽ 219(2) ይደነግጋል። ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ አመልካቾች ወንጀሉን ፈጽመዋል በሚል በክሱ የተጠቀሰው 29/04/1997 ዓ/ም ሲሆን ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ክሱ እስከቀረበባቸው እስከ 11/12/2002 ዓ/ም ያለው ጊዜ ሲቆጠርም የክስ ማቅረቢያው አምስት ዓመት ማለፉ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ወንጀሉ ተፈጽሟል የተባለው በ29/04/1997 ዓ/ም ቢሆንም ወንጀሉ መፈጸሙ የታወቀውና ፖላስ ምርመራ እንዲያጣራባቸው የተደረገው በ14/4/2001 ዓ/ም ስለመሆኑ በስር ፍርድ ቤቶች በተደረገው ክርክር የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነው። ፖላስ በአመልካቾች ላይ ከ14/04/2001 ዓ/ም ጀምሮ ምርመራ ማድረጉ እስከተረጋገጠ ድረስም በወንጀል ህግ አንቀጽ 221 እንደተደነገገው የይርጋ ዘመኑን መቆጠር የሚያቋርጠው ሆኖ ይርጋው እንደ አዲስ መቆጠር የሚጀምር ይሆናል።
በመሆኑም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካቾች ላይ ፖላስ ምርመራ ማጣራት የጀመረው በ14/4/2001 ዓ/ም በመሆኑ ክሱ በወ/ህ/አንቀጽ 221 መሰረት በይርጋ የሚታገድ አይደለም በሚል የሰጠው ፍርድ የህግ ስህተት ያልተፈጸመበት በመሆኑ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የትግራይ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠ/ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ በቀን 19/03/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠውን ፍርድ ወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/195(2)(ለ)(2) መሰረት አጽንተናል።
ተጠሪ በአመልካቾች ላይ ያቀረበው ክስ የክስ ማቅረቢያ ጊዜ ያላለፈበት በመሆኑ በይርጋ የሚታገድ አይደለም ብለናል።
No topics extracted.