No summary available.
ጥር 02 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የአብጃታ ሻላ ሶዳ አሽ አክሲዮን ማህበር - ጠበቃ ተሾመ ቢራ ቀረቡ ተጠሪ፡- የአብጃታ ሻላ ሶዳ አሽ መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ስለ ተወካይ ጃራ ኡሻ ቀረቡ
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የጡረታ መብት ይጠበቅልን ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በቦርድ ሲሆን ከሳሽ የነበረው የአሁኑ ተጠሪ ነው። ተጠሪ ክሱን ያቀረበው ከ158 በላይ የሆኑትን ሰራተኞች በመወከል ሲሆን ሰራተኞቹ ከ1979 ዓ.ም ወይም በጊዜያዊነት የስራ መደብ ከተቀጠሩበት ጊዜ ጀምሮ በማህበሩ በአባልነት ተመዝግበው እንደሚገኙ፣ ማህበሩ በጡረታ አዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀፅ 11(4/ሰ) ስር የሰራተኛው የአገልግሎት ዘመን እና የሰራተኛው የጡረታ መዋጮ 4% እና ከማህበሩ በተጠቀሰው መሰረት ሲፈፅሙ ከሰራተኞቹ አብዛኛዎቹ ለረዥም ጊዜያት በጊዜያዊነት ቅጥር የስራ መደብ ላይ ላገለገሉበት ጊዜ ለጡረታ ሳይመዘገብ በቋሚነት ከተቀጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ብቻ በመመዝገብ ላይ ስለሆነ ይህ አፈፃፀም ትክክል ያልሆነ መሆኑ ተገልፆላቸው በማህበሩ ሰራተኞች መካከል ልዩነት ሳይፈጥር አካሄዱን በማስተካከል የጡረታ አዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀፅ 11(4/ሰ) ድንጋጌ በሚያዘው መሰረት የጡረታ ጊዜያአቸውን በጊዜያዊነት ከተቀጠሩበት ጊዜ ጀምሮ በመመዝገብ የጡረታ መዋጮ ከሰራተኛው ደመወዝ የሚቆረጥ 4% ፣ ከማህበሩ ተቆራጭ የሚደረገው መዋጮ 6% በመሰብሰብ ከባንክ ወለድ ጋር ለጡረታና ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በመላክ ገቢ እንዲሆንላቸው ዳኝነት ጠይቋል። የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር ክርክር አቅርቧል። አመልካች ቦርዱ ጉዳዩን ለማየት የዳኝነት ስልጣን የልለው መሆኑንና ማህበሩ ክስ የመሰረተላቸው ሰራተኞች ጊዜአዊ ሰራተኞች በመሆናቸው ለቋሚ ሰራተኞች የተጠበቀውን የጡረታ መብት ለመጠየቅ ክስ ለመመስረት መብት ወይም ጥቅም የልላቸው መሆኑን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ያነሳ ሲሆን በፍሬ ነገር ደረጃም ማህበሩ ክስ ያቀረበላቸው ሰራተኞች በኮንትራትና በቀን ስራ እንዲሁም በጊዜአዊነት የተቀጠሩ በመሆናቸው የአገልግሎት ዘመናቸው እና የስራ ልምዳቸው የተቆራረጠ በመሆኑ የስራ ልምድ ማስረጃ ለመስጠትም አስቸጋሪ መሆኑንና ሰራተኞቹ በኮንትራት ያገለገሉት ጊዜ ለጡረታ እንዲያዝላቸው የማድረግ ስልጣን የተከሳሽ ድርጅት ያለመሆኑን ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል። ቦርዱም የግራ ቀኙን የቃል ክርክር ከሰማ በኋላ ጉዳዩ በቦርዱ ስልጣን የሚወድቅ አይደለም በማለት መዝገቡን ዘግቶት የነበረው ሲሆን ማህበሩ በዚህ የቦርዱ ብይን ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ቦርዱ ጉዳዩን የማየት የስረ ነገር ስልጣን እንዳለው በመግለፅ ውሳኔ በመስጠቱ ጉዳዩ ለቦርዱ የተመለሰለት ሲሆን ቦርዱም ጉዳዩን ማየት በመቀጠል ጉዳዩን መርምሮና አጣርቶ ክሱ የሚመለከታቸው ሰራተኞች ሁሉ የጡረታ ጊዜያቸው ላቆጠር የሚገባው ስራቸውን ሳያቋርጡ መስራት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ አመልካች ድርጅት በእጁ ያለውን ማስረጃ መርምሮ እንዲያስብላቸውና ከሰራተኞቹ የሚሰበስበውን መዋጮ 4% እና የአመልካች መዋጮ 6% አንድ ላይ በማጣመር ለሚመለከተው አካል ማሳወቅና ገቢ ማድረግ እንዲችል፣ ጡረታው ላቆጠር ከሚገባው ጊዜና ቀን ጀምሮ እንዲቆጥርላቸውና እንዲፈጸምላቸው በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ አመልካች ባለመስማማት ይግባኙን ለኦሮሚያ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ይግባኙ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 337 መሰረት ተሰርዞበታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ጉዳዩ የጡረታ መብት ይጠበቅልኝ ሁኖ እያለ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የተከበሩት መብቶችን ለማየት ስልጣን ለተሰጠው ቦርድ ቀርቦ መወሰኑ ያላግባብ መሆኑና ተጠሪ ክስ የመሰረተላቸው ሰራተኞች የኮንትራት ሰራተኞች በመሆናቸው ለቋሚ ሰራተኞች የተጠበቀላቸው መብት እንዲጠበቅላቸው የተወሰነው ከሕግ ውጪ ነው በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው።
አቤቱታው ተመርምሮም ለሰበር ችሎቱ ያስቀርባል የተባለው ቦርዱ ጉዳዩን አይቶ የመወሰን ስልጣን የነበረው መሆን ያለመሆኑን፣ የተጠሪዎች ጥያቄ በይርጋ የሚታገድ አይደለም የመባሉን በአዋጅ ቁጥር 345/1995 አንቀፅ 11(1(ሀ)(ሰ)) መሰረት ተጠሪዎች ስራቸውን መስራት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ይቆጠርላቸው የመባሉን አግባብነት ለመመርመር ተብሎ ነው። ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበውም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያሰፈልገው ጉዳይ ቦርዱ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን አለው? ወይስ የለውም?
የሚለው ተገኝቷል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪዎች ዳኝነት የተጠየቁት የጡረታ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ነው። ቦርዱ ይህንኑ የተጠሪዎች ጥያቄ አይቶ ለመወሰን ስልጣን ያልነበረው መሆኑን ገልፆ ክሱን ዘግቶ የነበረ ሲሆን ጉዳዩን እንደገና አይቶ ላወስን የቻለው በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሰረት መሆኑን በውሳኔው ላይ ጠቅሷል። ይህ ችሎትም ይህንኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀድሞ የሰጠውን ውሳኔ አሁን እንደገና ማየት ተገቢ መሆን ያለመሆኑን የተመለከተው ጉዳዩ የስልጣን ጥያቄ በመሆኑና የስልጣን ጥያቄ ደግሞ በተከራካሪ ወገኖች ባይነሳም ክርክሩ ባለበት በማናቸውም ደረጃ በፍርድ ቤት በራሱ አነሳሽነት መነሳት የሚችል ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 9 እና 231 /1/ለ/ ድንጋጌዎች ስር ከተመለከቱት ድንጌዎች ይዘትና መንፈስ እንዲሁም ይህ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80/3/ሀ/ አዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10፣ 22 እና አዋጅ ቁጥር 454/1997 2/1/ ከተሰጠው ስልጣን አኳያ ነው በመሆኑም ችሎቱ ተመሳሳይ ለሆኑ ጉዳዮች በአገሪቱ ወጥ የሆነ የፍርድ አሰጣጥ ስርዓት እንዲኖር አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እንዲሰጥ በሕግ ስልጣን የተሰጠው በመሆኑና የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ደግሞ በሕጉ አግባብ ጉዳዩን የመዳኘት ያለመዳኘታቸውን በዳኝነት ሥልጣኑ መቆጣጠር ያለበት በመሆኑ የስልጣን ጥያቄውን አሁን ክርክሩ ባለበት ደረጃም ቢሆንም ማየቱን ስነ ሥርዓታዊ የማያደርገው ሕጋዊ ምክንያት አላገኘም።
ከዚህ አንጻር ቦርዱ ጉዳዩን ለመወሰን ስልጣን ያለው መሆን ያለመሆኑን ስንመለከት ለቋሚ ቦርድ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ተለይተው የተሰጡት የዳኝነት ስልጣን ጉዳዮች በአዋጁ አንቀጽ 142 እና 147 ድንጋጌዎች ስር የተዘረዘሩት ናቸው። በእነዚህ ድንጋጌዎች ከተዘረዘሩት ጉዳዮች መካከል ደግሞ የሰራተኛ የጡረታ መብት ይከበር ጥያቄ በቦርዱ ስልጣን ስር የሚወድቅ መሆኑን የሚገልጽ ድንጋጌ የለም። ክርክሩ በተነሳበት ጊዜ ስለጡረታ መብትን የሚገዛው አዋጅ ቁጥር 345/1995 ሲታይም ከአሰሪያቸው ጋር ያለው ግንኙነት በአዋጅ ቁጥር 377/1996 የሰራተኞች የጡረታ መብታቸውም የሚገዛበት አግባብ መኖሩን አያሳይም።
ተጠሪዎች ሥራ ሲጀምሩ አመልካች ድርጅት የመንግስት ሙሉ ይዞታ ነበር ቢባል እንኳን የተጠሪዎችን የጡረታ መብት ይከበርልን ጥያቄ በቦርድ የሚዳኝበት አግባብ ስለመኖሩ ለመንግስት ሰራተኞች የጡረታ መብት ይደነግጉ የነበሩት አዋጅ ቁጥር 209/1955 እና ማሻሻያዎቹ አያሳዩም አመልካች በመንግስትና በልላ አካል በአክሲዮንነት ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮም ቢሆንም እንደማንኛውም የግል ድርጅት የሚታይ በመሆኑ ለግል ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ መብት አግባብነት ያለው አዋጅ ቁጥር 715/2003 አንጻር ጉዳዩ የሚታይ በመሆኑ በዚህ አዋጅ በተዘረጋው ስርዓት መሰረት የሚታይ ነው። በዚህ አዋጅ አግባብ የግል ድርጅት ሰራተኞች የጡረታ መብት ጥያቄ ላይ ስልጣን ያለው አካል የግል ድርጅት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጂንሲ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 53/1/ ስር በግልጽ የተመለከተ ሲሆን ይህ አካል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 202/2003 ተቋቋሞ ስራውን የሚሰራ መሆኑ ይታወቃል። ስለዚህ ከሰኔ ዐ7 ቀን 2003 ዓ/ም ጀምሮ በአንድ የግል ድርጅት የሚሰራ ሰራተኛ በአዋጅ ቁጥር 715/2003 አግባብ ለጡረታ መብት ብቁ መሆን ያለመሆኑን በመመርመር ውሳኔ ላሰጥ የሚችለው የግል ድርጅቶች ማሕበራዊ ዋስትና ኤጄንሲ እንጂ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የተቋቋመው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ አይደለም። ተጠሪዎች አዋጅ ቁጥር 715/2003 ለጉዳዩ አግባብነት የለውም በማለት የሚከራከሩት ክሱ አዋጁ ከመጽናቱ በፊት ሲሆን አዋጁ ከመጽናቱ በፊት ስለግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ግልጽ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ አልነበረም። ቀድሞውኑ በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩ ድርጅቶች ወደ ግል ሲዞሩም የሰራተኞችን መብትና ጥቅም በተመለከተ የሚነሳበት አግባብ ላኖር አይገባም ከሚባል በስተቀር የጡረታ መብቱን በተመለከተ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የተቋቋመው ቦርድ ለመዳኘት ስልጣን የሚያሰጥ አይሆንም ። በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 147/2/ እና አንቀጽ 142/ሀ/ ድንጋጌ መሰረት ቦርዱ ስለደመወዝና ስለልሎች ጥቅሞች አወሳስን በሚል በአማርኛው ቅጅ የተቀመጠው የሰራተኞችን የጡረታ መብት ሁሉ ላያጠቃልል የሚችል ነው በማለት ተጠሪዎች የሚያቀርቡት ክርክር በድንጋጌው “wages and other benefits” በሚል ከተጠቀሰው የእንግላዘኛ ቅጂ እና ለጡረታ መብት ብቁ መሆን ያለመሆኑ ለመወሰን የሰራተኛውን የተለያዩ ማስረጃዎችን መያዝና ማጠናቀርን የጡረታ አበል መጠንና የአከፋፈሉን ሁኔታ እንዲሁም ልሎች ዝርዝር ጉዳዮችን የሚገዛ ዝርዝር ሕግ እንዲኖር የሚጠይቅ ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ሲታይ “ልሎች ጥቅሞች” የሚለው የድንጋጌው ሐረግ የጡረታ መብትን ሁሉ ይጨምራል ብሎ መተርጐም ከጡረታ መብት አጠቃላይ ዓላማና ለመብቱ ብቁ ለመሆን መማላት ከሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ጋር አብሮ የማይሄድ ነው።
በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 147/2/ እና አንቀጽ 142/1/ሀ/ ድንጋጌዎች ከአዋጅ ቁጥር 715/2003 አንቀጽ 53 እና ከደንብ ቁጥር 202 አንቀጽ 5/7/ ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 የተቋቋመው ቦርድ የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ለጡረታ መብት ብቁ መሆን ያለመሆናቸውን አይቶ ለመወሰን የሚያስችለው ስልጣን ያለው መሆኑን የማያሳይ ሆኖ ስለአገኘነው በዚህ ረገድ ተጠሪዎች የሚያቀርቡት ክርክር ተቀባይነት የልለው ነው።
ሲጠቃለልም ተጠሪዎች ላከበርልን ይገባል የሚሉት የጡረታ መብት ላወሰን የሚገባው በአዋጅ ቁጥር 377/1996 በተቋቋመው ቦርድ ባለመሆኑ ጉዳዩ ቦርድ መወሰኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሀተት ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል።
በምስራቅ ኦሮሚያ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ 730/01/2004 በቀን 18/12/2004 ዓ.ም ተሰጥቶ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ መስከረም 15 ቀን 2005 ዓ.ም. የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥሕ/ቁጥር 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
የተጠሪዎች የጡረታ መብት ይከበርልኝ ጥያቄ በቋሚ ቦርድ ታይቶ የሚወሰን አይደለም ብለናል።
በክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ይለናል።
No topics extracted.