No summary available.
ጥቅምት ዐ9 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- የመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ - ነ/ፈጅ ኦላኒ በክረ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ቦጋለ ዱንፋ - ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የጅማ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤትና የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የስራ ግንኙነትንና ተፈፃሚነት ያለውን ህግ የሚመለከት ነው።
ተጠሪ በአመልካች ድርጅት የጥበቃ ስራ መደብ ላይ ተመድቦ ሲሰራ ከየካቲት 22 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ከስራና ከደመወዝ ያገደኝ በመሆኑ ውዝፍ ደመወዝ ከፍሎ ወደስራዬ ይመልሰኝ በማለት ለወረዳው ፍ/ቤት ክስ አቅርቧል። አመልካች ሰራተኞቹ በሲቪል ሰርቪስ ህግ (አዋጅ ቁጥር 515/99) መሰረት የሚተዳደሩ በመሆኑ የወረዳው ፍ/ቤት ሥልጣን የለውም። ተጠሪ የኤጀንሲውን ሰራተኛ በመደብደቡ ከስራ የተሰናበተ ስለሆነ ስንብቱ ህጋዊ ነው በማለት ተከራክሯል። የወረዳው ፍ/ቤት ጉዳዩን የማየት ሥልጣን አለኝ፣ ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ያለው አዋጅ ቁጥር 377/96 ነው በማለት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ አመልካች ተጠሪን ያለአግባብ ከስራ ያሰናበተው በመሆኑ ወደ ስራው ይመለስ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት አመልካች ይግባኝ ለዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርቧል። የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ ቁጥር 337 መሰረት ይግባኙን ሰርዞታል።
አመልካች ግንቦት 22 ቀን 2004 ዓ.ም. በተፃፈ የሰበር አቤቱታ አመልካች አዋጅ ቁጥር 553/1999 በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣበት ነሐሴ 29 ቀን 1999 ዓ.ም. ጀምሮ የፍድራል መንግስት መስሪያ ቤት እንደሆነ ተደንግጓል። አመልካች ሰራተኞቹን የሚያስተዳድረው በሲቪል ሰርቪስ ህግ መሰረታዊ መርሆዎች መሰረት እንደሆነ ተመልክቷል። ይህም በመሆኑ ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 515/1999 መሰረት መብቱን ለፍድራል ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አስተዳደር ፍ/ቤት ማቅረብ ሲገባው ለጅማ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ማቅረቡና የበታች ፍ/ቤቶችም ጉዳዩን ተቀብለው መወሰናቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት አመልክቷል።
ተጠሪ በበኩሉ የአመልካች አቤቱታ የህግ መሰረት የለውም። ተጠሪ በዲሲፕላን ኮሚቴ የተሰጠብኝ ውሳኔ የለም የበታች ፍ/ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ሰኔ 28 ቀን 2004 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርቧል። አመልካች ሀምል 13 ቀን 2004 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ ሰጥቷል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍ/ቤቶች ጉዳዩን ለመዳኘት ሥልጣን የልላቸው መሆኑን አመልካች ያነሳውን መቃወሚያ በማለፍ ውሳኔ መስጠታቸው ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረና።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች በአዋጅ ቁጥር 553/1999 ራሱን የቻለ የፍድራል መንግስት መስሪያ ቤት ሆኖ የተቋቋመ መሆኑን በአዋጁ አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 1 በግልፅ ተደንግጓል። የአመልካች ዋና ዳይሬክተርም የፍድራል ሲቪል ሰርቪስ ህግን መሰረታዊ መርሆዎች በመከተል ቦርዱ በሚያፀድቀው መመሪያ መሰረት የኤጀንሲውን ሰራተኞች የሚቀጥርና የሚያስተዳድር መሆኑ በአዋጅ ቁጥር 553/1999 አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀፅ 2(ለ) በግልጽ ተደንግጓል። ይህም የአመልካች ሰራተኞችን መሰረታዊ መብትና ግድታ የዲሲፕላን እርምጃ አወሳሰድና የስራ ስንብት ህጋዊነት በተመለከተ ተፈፃሚ የሚሆነው የህግ ማዕቀፍ አዋጅ ቁጥር 377/1996 ሳይሆን አዋጅ ቁጥር 515/1999 መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።
የጅማ ዞን ወረዳ ፍ/ቤትና የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በአዋጅ ቁጥር 515/1999 የሚተዳደሩ የፍድራል የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች የሚያቀርቡትን አቤቱታ የመቀበልና ውሳኔ የመስጠት ስልጣን አልተሰጣቸውም። በመሆኑም የበታች ፍ/ቤቶች አመልካች ያቀረበውን መቃወሚያ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁጥር 9 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት በመቀበል ጉዳዩን አከራክሮ ለመወሰን የሚያስችለን የዳኝነት የስረ ነገር ስልጣን የለንም በማለት መዝጋት ሲገባቸው፣ አመልካች በራሱ ገቢ የሚተዳደር መስሪያ ቤት ስለሆነ ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ያለው አዋጅ ቁጥር 377/1996 ነው በማለት ውሳኔ መስጠታቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
የኦሮሚያ ክልል የጅማ ከተማ ወረዳ ፍ/ቤትና የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የሰጡት ውሳኔ ተሽሯል።
ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 515/1999 መሰረት የሚታይ በመሆኑ የጅማ ወረዳ ፍ/ቤትና የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ጉዳዩን የማየት የዳኝነት ስልጣን የላቸውም በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍ/ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
No topics extracted.