No summary available.
የሰ/መ/ ህዳር 05 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመስል አመልካቾች፡
በዚህ መዝገብ ለተያዘው ክርክር መነሻ የሆነው የአሁኖቹ 1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች እንዲሁም በክርክሩ ሂደት በሞት የተለየችው የምስራች ኃ/ኪሮስ የሟች አባታችን የአቶ ኃ/ኪሮስ አባይ ውርስ ይጣራልን ሲሉ በሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አንዳቸው በልላኛው ላይ ያቀረቡት ክስ መሆኑን የአሁኑ 2ኛ አመልካች ክሱን ያቀረበው በአሁኑ 1ኛ አመልካች እና በምስራች ኃ/ኪሮስ ላይ መሆኑን የምስራች ኃ/ኪሮስ ክስ ያቀረበችው ደግሞ በአሁኑ 1ኛ አመልካች ላይ መሆኑን ፍ/ቤቱም ለሁለቱ ክሶች የተከፈቱትን ሁለት መዝገቦች በማጣመር ውርሱ እንዲጣራ ያደረገ ቢሆንም የምስራች ኃ/ኪሮስ ባቀረበችው ይግባኝ መነሻ የአሁኑ 2ኛ አመልካች የውርስ ይጣራልኝ ክስ በይርጋ ይታገዳል ተብሎ በይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት በመወሰኑ የአሁኑ 2ኛ አመልካች ከክርክሩ ውጪ መሆኑን በምስራች ኃ/ኪሮስ ከሳሽነት እና በአሁኑ 1ኛ አመልካች ተከሳሽነት በመ.ቁ. 17994 የተጣራው ውርስ በአፈፃፀም ደረጃ ደርሶ የምስራች ኃ/ኪሮስ በሟች ባለቤት በወ/ሮ ዘላለም ስሜ ስም ተመዝግቦ የሚታወቅ ድርጅት (የውርስ ሀብት) በሀራጅ ለማሸጥ የጨረታ ማስታወቂያ ወጥቶ ጉዳዩ በቀጠሮ እያለ የምስራች ኃ/ኪሮስ በ12/11/02 በሞት በመለየቷ ምክንያት የጨረታው ሂደት ተቋርጦ መዝገቡ መዘጋቱን ከዚህ በኋላ በተከሳሽነቱ ሲከራከር የነበረው የአሁኑ 1ኛ አመልካች እና ቀደም ሲል ከክርክሩ ውጪ ተደርጎ የነበረው የአሁኑ 2ኛ አመልካች የሟች የምስራች ኃ/ኪሮስ ተተኪ ወራሾች መሆናቸውን በ05/12/02 በፍ/ቤት ያረጋገጡበትን ማስረጃ በመያዝ በ10/12/02 ቀርበውና ጉዳዩን አንቀሳቅሰው የውርስ ሀብቱ በሀራጅ እንዲሸጥ ተሰጥቶ የነበረው ትዕዛዝ ቀሪ ተደርጐ ድርጅቱን በስምምነት ሸጠው ለመቅረብ እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ፍ/ቤቱ በመቀበሉ ድርጅቱን በስምምነት አጐታቸው ነው ለተባለው ለአሁኑ 3ኛ አመልካች መሸጣቸውን ገልፀው የሽያጭ ውሉን ይዘው በ12/12/02 በመቅረባቸው ፍ/ቤቱ የሽያጩን ውሉን አጽደቆ በውሉ መሰረት እንዲፈጸም በዚሁ ዕለት ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡን ዘግቶ ያሰናበታቸው መሆኑን ከዚህ በኋላ የስር በመቃወም አመልካች (የአሁኑ ተጠሪ) የአቶ ኃ/ኪሮስ አባይ ወራሽ ስለመሆኑ ማስረጃ በማያያዝ የስር በመ/ተጠሪዎች (የአሁኖቹ አመልካቾች) ወራሽ መሆኔን እያወቁ እና የሟች የምስራች ኃ/ኪሮስ ውርስም በሕጉ አግባብ ሳይጣራ በ10/12/02 እና በ12/12/02 የሰጡት ትዕዛዝ መብቴን የሚነካ በመሆኑ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ 358-360 መሰረት እንዲነሳ ይወሰንልኝ ሲል መቃወሚያ ማቅረቡን ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ 1ኛ እና 2ኛ የመ/ተጠሪዎች ተተኪ ወራሽ ነን ብለው መዝገብ ከማንቀሳቀስ ውጪ የየምስራች ኃ/ኪሮስ ውርስ በሕጉ መሰረት እንዲጣራ እንዳደረጉ በ10/12/02 እና በ12/12/02 የተሰጡት ትዕዛዞች በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 3 መሰረት እንደፍርድ እንደሚቆጠሩ እና ወደ 3ኛ የመ/ተጠሪ የስም ዝውውሩ አለመፈፀሙን ከከተማው አስተዳደር እንዳረጋገጠ በዝርዝር በመግለፅ በመ. በ21/03/04 በሰጠው ውሳኔ በ10/12/02 እና በ12/12/02 ሰጥቷቸው የነበሩትን ትዕዛዞች በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 360 መሰረት መሰረዙን ከፍተኛው ፍ/ቤት በመ.
በ04/04/04 በሰጠው ትዕዛዝ የቀረበለትን ይግባኝ ሳይቀበለው መቅረቱን የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎትም አመልካቾች የሚኖሩት በደቡብ ክልል ተጠሪ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በመሆኑ ምክንያት በተለያዩ ክልሎች በሚኖሩ ተከራካሪ ወገኖች መካከል የተነሳ ክርክርን የማየት ስልጣን የፍ/ፍ/ቤቶች መሆኑን በመግለፅ በመ.ቁ. 56046 27/04/04 ጉዳዩን ማሰናበቱን የክርክሩ ሂደት ያስረዳል።
አመልካቾች በ1/05/04 አዘጋጅተው ያቀረቡት አቤቱታ ይዘት ባጭሩ ተከራካሪ ወገን የሚባሉት ከሳሽ እና ተከሳሽ እንጂ በመቃወም አመልካች ጭምር ስላልሆነ የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የአሁኑ ተጠሪን በተከራካሪ ወገንነት መፈረጁ ስህተት ነው በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ 358 መሰረት መቃወሚያ ላቀርብ የሚችለው በስረነገር ውሳኔ ላይ እንጂ በ10/12/02 እና በ12/12/02 በተሰጡት ዓይነት የአፈፃፀም ትዕዛዞች ላይ አይደለም 1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች የሽያጩን ገንዘብ የተቀበሉ የሰነድ እና የንብረት ርክክብ የተደረገ እና ውሉ እና ትዕዛዙ ከማህደሩ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በ12/12/02 የተሰጠው ትዕዛዝ ተፈፅሟል እነዚህ ሁኔታዎችም የስር ፍ/ቤቶች ውሳኔዎችና ትዕዛዞች መሰረታዊ የሕግ ስህተት እንዳለባቸው የሚያረጋግጡ በመሆኑ እንዲሻሩ ይወሰንልን የሚል ሲሆን ተጠሪው በበኩሉ በ7/9/04 በተፃፈ ማመልከቻ በፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ. 358 መሰረት መቃወሚያ ለማቅረብ የቻልኩት የአባቴ ኃ/ኪሮስ አባይ እና የእህቴ የምስራች ኃ/ኪሮስ ውርስ እንዲጣራልኝ በከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ መስርቼ 1ኛ እና 2ኛ አመልካቾች የፍ.ሥ.ሥሕ.ቁ 7 ድንጋጌን ጠቅሰው መቃወሚያ በማቅረባቸው እና ክስ ያቀረብኩበት መ. በመቃወሚያው መሰረት በመዘጋቱ ነው፣ ትዕዛዞቹ እንደፍርድ የሚቆጠሩ ናቸው ተብሎ የተሰጠው ትርጉም ስህተት የለውም የስም ዝውውር አልተፈፀመም በመ. በ20/12/02 ዕግድ አሰጥቻለሁ ወራሽ መሆኔን እያወቁ እና ውርስ ሳይጣራ አመልካቾቹ ውሉን አቅርበው ያስፀደቁት ከቅን ልቦና ውጪ ነው 3ኛ አመልካች የ1ኛ እና የ2ኛ አመልካቾች የእናት ወገን አጐት ነው በ10/12/02 በተደረገው ውል በአንቀጽ 2.2. መሰረት ስም እስኪዛወር ድረስ ብር 50,000 በገዥው እጅ እንደሚቆይ ስለተገለፀ ክፍያ ተፈጽሟል የተባለው ሀሰት ነው በዚህም ሁኔታ የስር ፍ/ቤት ውሳኔዎች ስህተት የልለባቸው በመሆኑ እንዲፀኑ ይወሰንልኝ በማለት መልስ ሰጥቶ እና አመልካቾችም በ29/09/04 የተፃፈ የመ/መልስ አቅርበው የጽሁፍ ክርክሩ በዚሁ ተጠናቋል።
ይህ ችሎትም ጉዳዩን መርምሯል። በክርክሩ ምላሽ ማግኘት የሚገባው ጭብጥ የደቡብ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለኝም በማለት አቤቱታውን ያሰናበተው በአግባቡ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህም መሰረት በሀገራችን ፍ/ቤቶች በተለያየ ደረጃ እና እርከን ተዋቅረው የሚገኙ ሲሆን ይህ አወቃቀር የክልል እና የፍድራል ፍ/ቤቶችንም የሚያጠቃልል ነው። በተለያየ ደረጃ እና እርከን ተዋቅረው ከሚገኙት መካከል እያንዳንዱ ፍ/ቤት የሚያስተናግዳቸው የጉዳይ ዓይነቶች የሚወሰነው ለየፍ/ቤቱ በሕግ ተለይቶ በተሰጠ የስረ ነገር እና የግዛት ስልጣን ነው። የግዛት ስልጣን በዋነኛነት መሰረት የሚያደርገው ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ጉዳይ የተፈጠረበትን ቦታ ለተከራካሪ ወገኖች የሚኖረውን አመቺነት እና መሰል ሁኔታዎችን ሲሆን የስረ ነገር ስልጣን መሰረት የሚያደርገው ግን ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ይዘት፣ የተከራካሪ ወገኖችን መብትና ጥቅም ክብደት እና መጠን የጉዳዩን የውስብስበነት ደረጃ እና መሰል ነጥቦችን በመሆኑ በጉዳዮች አመራር ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው እና በጥንቃቄ መጤን የሚገባው ነው። የፍ.ስ.ስ.ሕ.ቁ 9 እና 10 ድንጋጌዎች ተገናዝበው ሲታዩም ሕጉ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ከግዛት ስልጣን ይልቅ ለስረ ነገር ስልጣን መሆኑን መገንዘብ የሚያስችሉ ናቸው። የፍ/ቤቶች ስልጣን ልላው ገጽታ ፍርድን የማስፈፀም ስልጣን ነው። ፍርድን የማስፈጸም ጉዳይ በስረ ነገር ክርክሩ ተረጋግጠው የፍርድ ኃይል ያገኙት የተከራካሪ ወገኖች መብት እና ግድታ በስነ ስርዓት ሕጉ የተደነገገውን የአፈፃፀም ስርዓት ተከትለው እንዲፈፀሙ ከማድረግ ውጪ አዲስ መብት እና ግድታ የሚቋቋምበት ባለመሆኑ ብዙ ሲያከራክር አይታይም። በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 371 ላይ እንደተመለከተው የማስፈፀም ስልጣን የስረ ነገር ስልጣንን የሚከተል ነው። ተገቢ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙም ስረ ነገሩን የወሰነው ፍ/ቤት አፈፃፀሙን በውክልና ወደ ልላ ፍ/ቤት ላመራው እንደሚችል በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 372 የተመለከተ ሲሆን በላይኛው እርከን የሚገኙ ፍ/ቤቶች የአፈፃፀም ጉዳዮችን በውክልና በታችኛው እርከን ለሚገኙ ፍ/ቤቶች ጭምር የሚያስተላልፉባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። ይህ ሁኔታም ፍርድን የማስፈፀም ስልጣን ከስረ ነገር ስልጣን በእጅጉ የተለየ እና የስረ ነገር ስልጣን ለልለው ፍ/ቤት ጭምር በውክልና ላሰጥ የሚችል መሆኑን መገንዘብ በሚያስችል ነው።
ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ የደቡብ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለኝም ያለው ጉዳዩ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ግለሰቦች የሚከራከሩበት መሆኑን በመጥቀስ ነው። እንደተባለው ነዋሪነታቸው በተለያዩ ክልሎች በሆኑ ተከራካሪ ወገኖች መካከል የሚነሳ ክርክርን የማየት ስልጣን የፍድራል ፍ/ቤቶች መሆኑ በአዋጁ 25/1988 አንቀጽ 5(2) ስር ተመልክቷል። አዋጁ በዚህ ሁኔታ የደነገገው የስረ ነገር ስልጣንን ነው። ለሰበር ችሎት የቀረበው አቤቱታ ግን የተነሳው ከስረ ነገር ፍርድ ሳይሆን ከፍርድ አፈፃፀም ትዕዛዞች መሆኑን መዝገቡ ያስረዳል። ሰበር ችሎቱ የጠቀሰው የአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 5(2) ድንጋጌ ፍርድ የማስፈፀም ስልጣንን የሚገዛ አይደለም። ለአፈፃፀም የቀረበውን የስረ ነገር ፍርድ የሰጠው የሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ሲሆን ፍርዱን የማስፈፀም ስልጣን የሚኖረውም ይኸው ፍ/ቤት ነው። በአፈፃፀም ደረጃ ወደ ጉዳይ የገባው ተከራካሪ ወገን የልላ ክልል ነዋሪ መሆኑ በፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ 371 የተደነገገውን ፍርድን የማስፈፀም ስልጣን የሚነካ አይደለም።
በዚህም ሁኔታ ሰበር ችሎቱ አቤቱታውን ተቀብሎ ማስተናገድ ሲገባው ስልጣን የለኝም በማለት ያሰናበተው በአግባቡ ሆኖ አልተገኘም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የልላ ክልል ነዋሪ የሆነ ተከራካሪ ወገን በአፈፃፀም ደረጃ ወደ ክርክሩ መግባቱ ጉዳዩን ወደ ፍድራል ጉዳይነት ይለውጠዋል የሚባል ቢሆን ኖሮ ሰበር ችሎቱ አቤቱታውን አስተናግዶ የሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ነዋሪነታቸው በተለያዩ ክልሎች በሆኑ ተከራካሪ ወገኖች መካከል የተነሳ ክርክርን የማየት ስልጣን ነበረው ወይስ አልነበረውም ? በሚለው ጭብጥ ዙሪያ ተገቢውን ውሳኔ መስጠት የሚገባው ሆኖ እያለ ጉዳዩ በፍ/ፍ/ቤቶች ስልጣን ስር የሚወድቅ በመሆኑ የሰበር አቤቱታውን የማየት ስልጣን የለኝም በማለት አቤቱታውን ማሰናበቱ አቋሙ እና ትዕዛዙ የማይጣጣሙ መሆኑን መገንዘብ የሚያስችል ነው። ከላይ በዝርዝር በተገለፀው ሁኔታ የደቡብ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በሁለት የተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ግለሰቦች ተከራካሪ የሆኑባቸውን ጉዳዮች የማየት ስልጣን በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 5(2) መሰረት የፍ/ፍ/ቤት በመሆኑ የሰበር አቤቱታውን የማየት ስልጣን የለኝም በማለት የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ. በ27/04/04 የሰጠው ትዕዛዝ በፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ጉዳዩ በዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቅ መሆኑን ተገንዝቦ ጉዳዩን በማንቀሳቀስ የአሁኖቹ አመልካቾች አቅርበውለት የነበረውን የሰበር አቤቱታ መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ በፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ 341(1) መሰረት ወደ ክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት እንዲመለስ ውሳኔ ተሰጥቷል።
በዚህ ችሎት የተደረገው ክርክር ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
የውሳኔው ግልባጭ ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ይላክ።
እልባት ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል። ወደ መዝገብ ቤት ይምለስ።
No topics extracted.