No summary available.
ህዳር 03 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- የአዲስ አበባ ከተማ ፍትህ ቢሮ - ነ/ፈጅ መስፍን አበበ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ መኮንን ተክሉ - ቀረቡ **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ከአቃቤ ሕግ ሙያ ጋር ተያይዞ የተነሳውን የስራ መደብና ቦታ ዝውውርን መቃወምን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ ተጠሪ ባሁኑ አመልካች ላይ በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው። ተጠሪ በአመልካች ላይ የመሰረቱት ክስ ይዘት ሲታይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት በአቤቱታ ምርመራና ክስ አቀራረብ ንዑስ የስራ ሂደት በምርመራና ክስ ኤክስፐርትነት የስራ መደብ ታክስን ጨምሮ ብር 4,210.00 ደመወዝ እየተከፈላቸው ለሁለት አመታት ያገለገሉ መሆኑን፣ የአካል ጉዳተኛ መሆናቸውንና በ2002 ዓ.ም እና 2003 ዓ/ም በተደረገ የስራ አፈጻጸም ግምገማ የላቀ የስራ አፈጻጸም ውጤት ያላቸው መሆኑን ገልጸው አመልካች ያላግባብ ወደ ልደታ ክፍለ ከተማ ንቃተ ሕግ መፍጠር ንኡስ የስራ ሂደት ተጠሪ ተዛውረው በሕግ ኤክስፐርትነት እንዲሰሩ በማድረግ ከቀድሞው ደመወዝና ጥቅማጥቅም ብር 425.00 እንዲቀነስ በማድረጉ ከሕግ ውጪ የተደረገና የተከናወነ ተግባር ነው፣ መድሎም ተፈጽሟል ተብሎ እና አንባቢ ተመድቦላቸው ወደ ቀድሞው ስራ እንዲመለሱ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው። የአሁኑ አመልካች ለክሱ በሰጠው መከላከያ መልስም አመልካች ዝውውሩን ለመፈጸም ስልጣን እንደአለውና ጉዳዩም በፍድራል ፍርድ ቤቶች ላታይ የማይገባው እና በከተማው ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር እንደሚወድቅ ገልጾ ክሱ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እንዲዘጋ ዳኝነት የጠየቀ ሲሆን በፍሬ ነገር ረገድም ተጠሪ የተሻለ ውጤት ላያስመዝገቡ ይችላሉ ተብሎ በታመነው የስራ መደብ ላይ እንዲመደቡ መደረጉንና በደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ረገድም የስራ ቦታው የትራንስፖርት አበል የማያስፈልገው በመሆኑ ምክንያት ይኸው አበል ከመቀነሱ ውጪ የተቀነሰ ደመወዝ የልለ መሆኑን ጠቅሶ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል።
ተጠሪ በቃል ክርክር ወቅት ከአዋጅ ቁጥር 568/2000 አንጻር የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለማየት ስልጣን እንደአለው ገልጸው ተከራክረዋል። ጉዳዩ በዚህ መልክ የቀረበለት የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም የተጠሪ የዳኝነት ጥያቄ መሰረት ያደረገው አዋጅ ቁጥር 568/2000 መሆኑና በዚህ አዋጅ አንቀፅ 2(7) ስር ደግሞ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመዳኘት የሚችል መሆኑን በሚያስገነዝብ መልኩ መደንገጉን ጠቅሶ በዚህ ረገድ አመልካች ያቀረበውን ተቃውሞ ያለፈው ሲሆን ፍሬ ነገሩን መርምሮም የተጠሪ ዝውውር በአድሎአዊ ተግባር የተፈጸመ ሳላለመሆኑ አመልካች በአዋጁ አንቀጽ 7(2) ድንጋጌ መሰረት የማስረዳት ሸክሙን አልተወጣም ወደሚለው ድምዳሜ ደርሶ ዝውውሩን ሽሮ ተጠሪ ቀድሞ ይሰሩበት ወደ ነበረው ቦታና የምርመራና ክስ ኤክስፐርትነት የስራ መደብ እንዲመለሱ ሲል ወስኗል። ከዚህ በኋላም አመልካች ይግባኙን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ፀንቷል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም ጉዳዩ በፍርድ ቤቱ የታየው ከስልጣኑ ውጪና ባልተረጋጠ ፍሬ ነገር ነው በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች ጉዳዩ መታየት ያለበት በአዋጅ ቁጥር 568/2000 መሰረት በሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤት ነው በማለት ያቀረበው ተቃውሞ ታልፎ የበታች ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ከዓቃቤ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 24/1999 መሰረት አስተናግደው ዝውውሩ ሕገ ወጥ ነው በማለት የመወሰናቸውን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበውም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም የተጠሪ የዳኝነት ጥያቄ በፍርድ የሚያልቅ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ ተገኝቷል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ በአመልካች መስሪያ ቤት የሚሰሩት በአቃቤ ሕግነት ሙያ መሆኑን፣ ተጠሪ በአመልካች ላይ ክስ የመሰረቱት ተጠሪ ከሚሰሩበት፤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የፍትህ ጽ/ቤት የአቤቱታ ምርመራና ክስ አቀራረብ ንዑስ የስራ ሂደት በምርመራና ክስ ኤክስፐርት የስራ መደብ ወደ ልደታ ክፍለ ከተማ ፍትህ ጽ/ቤት ንቃተ ሕግ መፍጠር ንዑስ የስራ ሂደት አመልካች ያላግባብ አዛውሯል፣ ከቀድሞው ደመወዝና ጥቅማጥቅም ብር 425.00 እንዲቀንስ በማድረጉ ዝውውሩ ከሕግ ውጪ ነው፣ አካል ጉዳተኛ በመሆኔም መድሎ ተፈጽሟል በሚል ምክንያት መሆኑን ነው። አመልካች በበኩሉ ተጠሪ በአቃቤ ሕግነት ተሹመው የሚሰሩ መሆኑን ሳይክድ ዝውውሩ ስራና ሰራተኛን ለማገናኘት የተደረገ መሆኑን ጠቅሶ ጉዳዩ በፍድራል ፍርድ ቤቶች ላታይ እንደማይገባና በሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤት ወይም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የሚታይ መሆኑን ገልጾ መከራከሩን ከመዝገቡ ተመልክተናል። ከዚህ በቀላሉ መገንዘብ የሚቻለው ተጠሪ በአቃቤ ሕግነት ተሹመው የሚሰሩ የአመልካች ሰራተኛ መሆናቸውን ነው።
በመሰረቱ የበታች ፍርድ ቤቶች የተጠሪን ክስ ለመዳኘት የቻሉት የአዋጅ ቁጥር 568/2000 አንቀጽ 2(7) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በዋቢነት በመጥቀስ ነው። ይህ ድንጋጌ ፍርድ ቤት ማለት የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወይም የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወይም የፍድራል ወይም የክልል ሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤት እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል። አዋጁ በአንቀጽ 10(1) ስርም በአዋጁ ድንጋጌዎች ወይም ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የወጡ ደንቦች ወይም መመሪያዎች ባለመከበራቸው ምክንያት መብቱ የተነካበት ማንኛውም የአካል ጉዳተኛ ወይም አካል ጉዳተኛ አባል የሆነበት የአካል ጉዳተኞች ማህበር ወይም አካል ጉዳተኛው አባል የሆነበት የሰራተኛ ማህበር ወይም አዋጁን የሚያስፈጽም አግባብ ያለው አካል ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ እንደሚችል የተቀመጠ ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 3 ደግሞ አዋጁ በማንኛውም ስራ ፈላጊ አካል ጉዳተኛ ወይም አካል ጉዳተኛ ሰራተኛና በአሰሪ መካከል በሚኖር የስራ ስምሪት ግንኙነት ላይ ተፈፃሚነት እንደሚኖረው ተደግንጓል።
እንዲሁም አዋጁ የአካል ጉዳተኞችን የስራ መብት መጠበቁና አድሎም መከልከሉን እንደ ቅደም ተከተላቸው በአንቀፅ 4 እና 5 ስር በዝርዘር አስቀምጧል። እንግዲህ እነዚህ ድንጋጌዎች የሚያሳዩት በሹመት የሚያዙ የስራ መደቦችን ሁሉ በተመለከተ በአዋጁ ለመግዛት የታሰበ ያለመሆኑን ነው። ይህ ማለት ግን በአዋጁ የተቀመጡት የአካል ጉዳተኛ መብቶችን ተሿሚ የሆነውን አካል ጉዳተኛ የሚያስተዳድረው አካል ላያከብራቸው አይገባም ማለት አይደለም።
በመሆኑም ተሿሚ የሆነውን የአካል ጉዳተኛ ጉዳይ በአዋጁ አንቀጽ 2(7) መሰረት ፍርድ ቤት ላመለከተው ይገባል ከተባለ በተለይም በዳኝነት ስራ ወይም በአቃቤ ሕግነት ስራ የተሰማሩትን አካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በዚህ ረገድ በሕግ አግባብ የተቋቋሙት አካላት እንዳይመለከቱ የማድረግ ውጤትን የሚያስከትል ነው። ስለሆነም አዋጅ ቁጥር 568/2000 ስለ አካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት የወጣ አዋጅ ሁኖ በአዋጁ፣ አግባብ ባለው ደንብና መመሪያ የተከበሩ መብቶችን የሚነካ ተግባር ሲፈጸም በፍርድ የሚያልቅበት አግባብ ያለ መሆኑን የሚደነግግ ቢሆንም ተሿሚ የሆኑ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ግን ጉዳዩ በፍርድ ቤት ክስ የሚቀርብበት ሳይሆን በዚህ ረገድ በሕግ ተለይተው ለተቋቋሙት አካላት የሚቀርብና እነዚህ አካላትም አዋጁንና ልሎች አግባብነት ያላቸውን ሕጎች መሰረት አድርገው ጉዳዩን የሚያስተዳደሩበት ስለመሆኑ አግባብነት ያላቸውን ሕጎች ይዘት፣ መንፈስና ዓላማ በማገናዘብ የምንረዳው ጉዳይ ነው።
ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈፃሚነት ባለው የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዐቃቢያነ ሕግ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 24/1999 አንቀፅ 2(4) ዐቃቤ ሕግ ማለት በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሕር የፍትህ አስተዳደር እንዲያገለግል በደንቡ አንቀጽ 4 በተመለከቱት ደረጃዎች በአንዱ የተሾመ ሰራተኛ መሆኑን ትርጉም የተሰጠበት ጉዳይ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 6/2000 አንቀጽ 2(5(ሐ)) ድንጋጌ ሲታይም የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ዳኞችና አቃቢያነ ሕግን እንደማያካትት የተደነገገ ሲሆን የእነዚህ ባለሙያዎችን ጉዳይ በተመለከተ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ፍርድ ቤት የሚያስተናግድበት አግባብ አይኖርም። ከእነዚህ የሕግ ማዕቀፎች በግልጽ መረዳት የሚቻለው የአቃቢያነ ሕግ ስራ የሚገኘው በሹመት መሆኑን ሲሆን ጉዳዩን የሚገዛው የተለየ ሕግም በደንብ ቁጥር 24/1999 ወጥቶ ስራ ላይ ያለ መሆኑንና ይህ ደንብ በሕግ አግባብ ያልተለወጠ መሆኑን ነው። ደንቡ የዐቃቤነ ሕግ አስተዳደር ጉባኤ መቋቋሙን በአንቀፅ 44 በግልጽ ያስቀመጠ ሲሆን በአንቀጽ 46 ስር ደግሞ ስለጉባኤው ስልጣንና ተግባር ዘርዝሮ አስቀምጧል።
ከጉባኤው ስልጣንና ተግባራት መካከል አንዱ ደግሞ ደረጃቸው ከምክትል ረዳት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በታች የሆኑ አቃቤያነ ሕግን ቅጥር፣ ዝውውርና የደረጃ እድገት በሚመለከት ውሳኔ መስጠት ስለመሆኑ ደንቡ በአንቀጽ 46(3) ድንጋጌ ስር አስገዳጅነት ባለው መልኩ አስቀምጧል። ደንቡ የይግባኝ መብትን በተመለከተም በአንቀፅ 41 ስር አስቀምጧል። ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት ያለው ደንብ ይህን ያህል ግልጽ ከሆነ ደግሞ የከተማውን አቃቤያነ ሕግን በተመለከተ በመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ምክንያት የተለየ ሕግ ባልወጣበት ሁኔታና አዋጅ ቁጥር 568/2000 በሕግ ተዋረድ ከደንቡ በላይ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም አዋጁ ደንቡን ሙሉ በሙሉ የተካበት መንገድ ያለ ስለመሆኑ በግልጽ የሚያሳይ ድንጋጌ ሳይኖር በአዋጅ ቁጥር 568/2000 መሰረት የአካል ጉዳተኞች አቃቤያነ ሕግ የዝውውር ጉዳይ የአድሎ ተግባር የተፈፀመ ነው ተብሎ ስለተገለጸ ብቻ በፍርድ እንዲያልቅ የሚደረግበት አግባብ የለም።
ስለሆነም የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ በአቃቤያነ ሕግነት ተመድበው የሚሰሩ ሰራተኛ እና ስራው ሹመት ሁኖ የተለየ የሕግ ማዕቀፍ በሆነው በደንብ ቁጥር 24/1999 የሚገዛ መሆኑን ከአዋጅ ቁጥር 568/2000 ይዘትና መንፈስ አዛምደው ሳይመለከቱ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ቀጥታ ክስ የሚቀርብበትና እልባት የሚሰጥበት ነው በሚል ምክንያት ጉዳዩን መዳኘታቸው በሕጉ ባልተሰጣቸው ስልጣን ሁኖ ስለአገኘን ከኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37፣ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 4፣ 9 እና 231(1(ለ)) ድንጋጌዎች አኳያ ሲታይ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ሐምል 08 ቀን 2003 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ህዳር 22 ቀን 2004 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
ተጠሪ አካል ጉዳተኛ ቢሆኑም በደንብ ቁጥር 24/1999 መሰረት ተሹመው የሚሰሩ በመሆኑ አከራካሪው ጉዳያቸው በደንቡ መሰረት ስልጣን ባለው አካል ከሚታይ በስተቀር በፍርድ ላያልቅ የሚችል አይደለም ብለናል።
ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.