No summary available.
ህዳር 03 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሤ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- ኢትዮ ቴልኮም - ነ/ፈጅ በፍቃዱ መኮንን ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ ንጉሤ ረፈራ - አልቀረበም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ለዚህ የሰበር ክርክር መነሻ የሆነው ጉዳይ በአሁኑ የሰበር አመልካች ድርጅት ከሳሽነት የተጀመረው በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁን ተጠሪም ተከሳሽ ነበር። ክሱም፡- ተከሳሽ የከሳሽ ድርጅት ንብረት የሆነውንና ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ የተዘረጋውን ኦፕቲካል ፋይበር የሚባል ኬብል በ1/2 ሜትር ጥልቀት መሬት ውስጥ መቀበሩን እያወቀና እያየ በ10/06/2001 ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡30 ሲሆን ይዞታውን በዶማ በመቆፈር መስመሩ እንዲቋረጥ በማድረግ በብር 48,998.72 የሚገመት ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ተከሳሽም ጉዳት ማድረሱን በማመን መስመሩን ለመጠገን ሲባል ለጥገና፣ ለባለሙያዎችና ለጉልበት ሰራተኞች እንዲሁም ለትራንስፖርት የወጣውን ወጪ ለመክፈል በ08/07/2001 ዓ.ም.
በተጻፈ ደብዳቤ ከሳሽ ድርጅትን በመጠየቁ ከሳሽም ተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ጨምሮ ብር 48,998.72 እንደሚፈለግበት ቢያሳውቅም ገንዘቡን ለመክፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ገንዘቡን ከነወለዱ እንዲከፍል ይወሰንበት የሚል ነው።
ተከሳሽ በበኩሉ በሰጠው መልስ፡- የወላሶ ከተማ አስተዳደር በ1997 ዓ.ም. 1,888 ካሬ ሜትር የሆነ የከተማ ቦታ ከነፕላኑ ሲሰጠኝ በአዋጅ ቁጥር 464/1994 አንቀጽ 3(3) መሰረት በሰጠኝ መሬት ውስጥ የከሳሽ ንብረት የሆነው ኦፕቲካል ፋይበር ኬብል መኖሩን ሳላልነገረኝ ማወቅ የምችልበት ሁኔታ የለም፣ መስመሩ ከዋናው መንገድ ከ15 ሜትር በላይ መራቅ እንደልለበት እየታወቀ 150 ሜትር ርቀት ላይ የተቀበረ ሲሆን በቦታው የተቀበረ ስለመሆኑ ከሳሽ ድርጅት ያደረገው ምልክት የለም፣ጉዳቱን በማመን ደብዳቤ ጽፏል የተባለውም ቢሆን በአገር ንብረት ላይ ደርሷል የተባለውን ጉዳት በተመለከተ በቅንነት የተጻፈ እንጂ እያወቅኩና እያየሁኝ ጉዳቱን አድርሻለሁ በሚል የተጻፈ አይደለም። ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት የለብኝም እንጂ አለብህ የሚያሰኝ በቂ ምክንያት ቢኖር ከሳሽ ያቀረበው የጉዳት ግምት የተጋነነ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲል ተከራክሯል።
ጉዳዩ በመጀመሪያ ደረጃ የቀረበለት ከፍተኛው ፍርድ ቤትም የከተማ አስተዳደር መሬቱን ለተከሳሽ ሲሰጥ የኬብል መስመር ስለመኖሩ የነገረው መሆን አለመሆኑን ማረጋገጫ እንዲልክ ጠይቆ አስተዳደሩም የከሳሽ ድርጅት ካርታ ለከተማው አስተዳደር ያልተሰጠው በመሆኑ ለተከሳሽ መስመሩ ስለመኖሩ ያልተነገረው መሆኑን በመግለጹ ፍርድ ቤቱም ለተከሳሽ በተሰጠውም ፕላን የኬብል መስመር ስለመኖሩ ስላልተገለጸ ተከሳሽ የኬብል መስመሩ በቦታው ስለመኖሩ ያውቅ ነበር ወይም አይቷል ለማለት አይቻልም፣ ተከሳሽ ለከሳሽ በጻፈው ደብዳቤም ጉዳቱን አምኗል በሚል ከሳሽ ያቀረበው ክርክርም ቢሆን ከደብዳቤው ይዘት መገንዘብ የተቻለው መስመሩ ከመንገድ 150 ሜትር ርቆ ያለ በመሆኑ ማወቅ አለመቻሉንና ጉዳቱ የደረሰውም የልማት ሥራ እየተሰራ በመሆኑ ኬብሉ የተጠገነበትን ወጪ እንዲሁም ለባለሙያና ለጉልበት ሰራተኞች ትራንስፖርትን ጨምሮ የወጣውን ልክፈል የሚልና ከሳሽ ያቀረበው የወጪ ግምት የተጋነነ ነው የሚል በመሆኑ ጉዳቱን አምኗል ለማለት የሚቻል አይሆንም ሲል ክሱን ውድቅ በማድረግ በነጻ አሰናብቶታል።
ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በበኩሉ የግራ ቀኙን ወገኖች ካከራከራቸው በኋላ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ አጽንቷል።
አመልካች የሰበር አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው በሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል ሲሆን በዋናነት የጠቀሳቸው የቅሬታ ነጥቦችም፡- በአዋጅ ቁጥር 464/1997 አንቀጽ 3(3) የግንባታ ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት በመሬት ውስጥ ኬብል መዘርጋቱንና አለመዘርጋቱን የማረጋገጥ ኃላፊነት የወላሶ ከተማ አስተዳደርና የግንባታ ፈቃድ ጠያቂው አካል (የተጠሪው ግድታ) መሆኑ በግልጽ የተቀመጠውን ድንጋጌ በማለፍ እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 49/1989 አንቀጽ 23(1) መሰረት ኬብል ስለመዘርጋቱ የከተማው አስተዳደርም ሆነ ተጠሪው አመልካች ድርጅትን ጠይቀው ማረጋገጥ እንዳለባቸው የተጣለባቸው የህግ ግድታ ሆኖ እያለ መታለፉ ያለአግባብ ነው፣ ተጠሪው የልማት ሥራ ሲሰራ በቸልተኝነት ጉዳት ማድረሱን አምኖ ግምቱ ተቀንሶ ለመክፈል መከራከሩ ግልጽ ሆኖ ባለበት በቀረበው ክስ መሰረት አምኗል የሚያሰኝ አይደለም በሚል አመልካች ያቀረብኩትን ክስ ፍርድ ቤቶቹ ውድቅ ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም የሚሉ ናቸው።
ተጠሪው በበኩሉ በሰጠው መልስ ፡- ከከተማው አስተዳደር በተሰጠኝ ቦታ ኬብል የተዘረጋ ስለመሆኑ የተገለጸልኝ ነገር ባለመኖሩ ተጠሪው በመሬት ውስጥ ኬብሉ የተዘረጋ ስለመሆኑ የማወቅ ግድታ አለበት በሚል አመልካች ያቀረበው ክርክር ተቀባይነት የለውም፣ በሥር ፍርድ ቤቶች በተደረገው ክርክር ያመንኩት ጉዳት መድረሱን እንጂ ጉዳቱ የደረሰው በተጠሪው ጥፋት ነው በሚል አይደለም፣ሲል ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከዚህ በላይ የተገለጸው ሲሆን እኛም፡- ተጠሪው በአመልካች ድርጅት ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት አለበት? ወይስ የለበትም?
ተጠሪው ለጉዳቱ ኃላፊነት አለበት ቢባል የሚከፍለው የኪሳራው መጠን ምን ያህል መሆን አለበት? የሚሉትን ጭብጦች ይዘን ክርክሩን እንደሚከተለው መርምረናል።
አንደኛውን ጭብጥ በተመለከተ፡- ከክርክሩ መገንዘብ የተቻለው ተጠሪው የከተማው አስተዳደር በሰጠው የከተማ ቦታ ቁፋሮ ሲያካሂድ የአመልካች ንብረት የሆነው ኦፕቲካል ፋይበር ኬብል መቁረጡን ነው። ሆኖም የሥር ፍርድ ቤቶች በንብረቱ ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠሪው ኃላፊነት የለበትም በሚል የወሰኑት ለተጠሪው በተሰጠው ፕላን ላይ ኬብል ስለመኖሩ የተደረገ ምልክት የለም፣ የከተማው አስተዳደርም መስመሩ ስለመኖሩ ለተጠሪው የገለጸው ነገር ባለመኖሩ እያወቀ ወይም እያየ ጉዳት አድርሷል ለማለት አይቻልም በሚል ነው። እነዚህን ፍርድ ቤቶቹ የጠቀሱአቸውን ምክንያቶች የቴልኮሙኒኬሽንና የኤልትሪክ ሀይል አውታሮችን ደህንነት ለመጠበቅ ከወጣው አዋጅ ቁጥር 464/1997 እና አግባብነት ካላቸው የፍትሐብሕር ድንጋጌዎች አንጻር መመርመር የሚገባ ሆኖ አግኝተናል። አዋጅ ቁጥር 464/1997 በአንቀጽ 3(3) ሥር የፍድራልና የክልል ከተማ አስተዳደር አካላት የግንባታ ፈቃድ ከመስጠታቸው በፊት የቴልኮሙኒኬሽን ወይም የኤልትሪክ ሀይል አውታር ስለመኖሩ እና ፈቃድ ጠያቂው አካልም ግንባታ ከማካሄዱ በፊት በቴልኮሙኒኬሽን ወይም በኤልትሪክ ሀይል አውታር ላይ ጉዳት የማይደርስ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ተደንግጓል። ድንጋጌው በቴልኮሙኒኬሽንና በአልትሪክ ሀይል አውታሮች ላይ በግንባታ ወቅት ጉዳት እንዳይደርስ አስቀድሞ እንዲያረጋግጡ ግድታ የጣለው በፍድራልና በክልል አስተዳደር አካላት ብቻ ሳይሆን የግንባታ ፈቃድ ጠያቂ ላይ ጭምር ነው። ተጠሪውም በዚህ የህግ ድንጋጌ መሰረት በቴልኮሙኒኬሽን አውታር ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የተጣለበትን አስቀድሞ የማረጋገጥ ግድታ ሳይወጣ ቦታውን በቸልነኝነት በመቆፈሩ ምክንያት ጉዳቱ ላደርስ ችሐል። በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት በቴልኮሙኒኬሽንና በኤልትሪክ ሀይል አውታሮች ላይ እያወቀም ሆነ በቸልተኝነት ጉዳት ያደረሰ ሰው የሚቀጣ ስለመሆኑም ተደንግጓል ።
ወደ ፍትሐብሄር ህጉ ስንመለስ አንድ ሰው በራሱ በኩል ምንም የገባው ግድታ ሳይኖር በራሱ ጥፋት(አስቦ ወይም በቸልተኝነት) በልላ ሰው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ኃላፊ እንደሆነ በቁጥር 2027(1) ከተደነገገው መገንዘብ ይቻላል። እንዲሁም በህግ በትክክል ተገልጾ የተመለከተውን ልዩ ድንጋጌ፣ ልዩ ደንብና ሥርዓት የጣሰ ሰው ደግሞ ጥፋተኛ ላሆን እንደሚገባ በፍ/ህ/ቁ 2035(1) ተመልክቷል። በአዋጁም ሆነ በፍትሐብሕር ህጉ በዚህ መልኩ ተደንግጎ እያለ ተጠሪው ጉዳት ማድረሱን ባልካደበት ጉዳት የደረሰበት ኬብል በቦታው ስለመኖሩ ለተጠሪው የከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት አላስታወቀም፣ እንዲሁም አመልካች ድርጅት በቦታው ላይ ያደረገው ምልክት የለም የሚሉትን ምክንያቶች የስር ፍርድ ቤቶች በመጥቀስ በተጠሪው የተጣለበትን የህግ ግድታ ባለማገናዘብ ድርጊቱን የፈጸመው እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ስለመሆኑ ስላልተረጋጠ ለጉዳቱ ኃላፊነት የለበትም ሲሉ የወሰኑት በአዋጅ ቁጥር 464/1997 አንቀጽ 3(3) የተደነገገውን እና ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን የፍትሐብሄር ህግ ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ ተቀባይነት ያለው አይደለም።
ሁለተኛውን ጭብጥ በተመለከተ፡- ማንም ሰው ከራሱ ጥፋት የተነሳ በልላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ ላደረገው ጉዳት ኪሳራ የመክፈል ግድታ እንዳለበት በፍ/ህ/ቁ/2028 በአስገዳጅ ሁኔታ የተደነገገ ሲሆን ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ መሆኑ በህግ የታወቀ ሰው ደግሞ የሚከፍለው የጉዳት ካሳ መጠን ኃላፊነቱ ያመጣው ጉዳይ በተበዳዩ ላይ ከደረሰው ጉዳት ጋር እኩል ሆኖ በማመዛዘን ስለመሆኑ ከፍ/ህ/ቁ 2090(1) እና 2091 ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻል ነው።
በዚህ በተያዘው ጉዳይ ተጠሪው በአመልካች የኬብል መስመር ላይ ጉዳት ማድረሱን በማመን ልዩ ልዩ የጥገና ወጪዎችን ለመክፈል በጻፈው ደብዳቤ ከአመልካች በኩል የቀረበው የኪሳራ መጠን የተጋነነ መሆኑን ስለመግለጹ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የደብዳቤውን ይዘት በፍርድ ላይ ካሰፈረው መገንዘብ የተቻለ ከመሆኑም ልላ ተጠሪው ከሥር ጀምሮ ባደረገው ክርክርም የጉዳቱ መጠን ግምት የተጋነነ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክሯል። ተጠሪው በአመልካች በኩል የቀረበውን የኪሳራ መጠን ግምት እስከተቃወመ ድረስም ግምቱ የተጋነነ ነው የሚልበትን ምክንያት እና አመልካችም ለግምቱ ምክንያት ያደረጋቸውን ሁኔታዎች የግራ ቀኙን ማስረጃዎች በመስማትና በመመዘን መወሰን የሚገባ ነው።
በአጠቃላይ የስር ፍርድ ቤቶች ተጠሪው በአመልካች ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ባልካደበት ተጠሪውን ለጉዳቱ ኃላፊነት የለበትም በሚል በነጻ ያሰናበቱት በአዋጅ ቁጥር 464/1997 አንቀጽ 3(3) የግንባታ ፈቃድ ጠያቂ ግንባታ ከማከናወኑ በፊት የቴልኮሙኒኬሽን እና የኤልትሪክ አውታሮች ላይ ጉዳት የማይደርስ መሆኑን የማረጋገጥ ግድታ ያለበት ስለመሆኑ የተደነገገውን እንዲሁም ከውል ወጪ ኃላፊነት ላከተል ስለሚችልበት ሁኔታ በፍ/ህ/ቁ/2027(1)፣ 2028፣ እና 2035 የተደነገጉትን ሁኔታዎች ያላገናዘበ በመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በማግኘታችን ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/21371 በቀን 07/04/2003 ዓ/ም በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/112894 በቀን 28/03/2004 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የሰጠውን ውሳኔ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/348(1) መሰረት ሽረናል።
ተጠሪው በአመልካች ንብረት ላይ ላደረሰው ጉዳት ኃላፊነት አለበት ብለናል። ስለሆነም በደረሰው የጉዳት መጠን ላይ የግራ ቀኙን ወገኖች በማከራከርና የግራ ቀኙን ማስረጃዎች በመስማት፣ እንዲሁም ተገቢ ሆኖ ከተገኘም በገለልተኛ ባለሙያ በማጣራት በጉዳዩ ላይ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰጥበት ክርክሩን በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ/343(1) መሰረት መልሰናል።
የዚህን ፍርድ ቤት ወጪና ኪሳራ የግራ ቀኙ ወገኖች የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.