No summary available.
ጥር 13 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ስላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡-
ጉዳዩ ለመኪና ግዥ የተከፈለ ነው የተባለን ገንዘብ ከማስመለስ ጋር የተያያዘ ነው። ክርክሩ በተጀመረበት ፍ/ከ/ፍ/ቤት ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ ሲሆኑ አመልካቾቹ ደግሞ ተከሳሾች ነበሩ። የክሱ ይዘት ባጭሩ ተከሳሾቹ አብረው በንግድ ስራ የተሰማሩ መሆናቸውን 2ኛ ተከሳሽ አ/አበባ በነበሩበት በ26/07/03 ለከሳሽ መኪና እንደሚሸጡላቸው ከከሳሽ ጋር ተነጋግረው የመኪናው ዋጋ በ1ኛ ተከሳሽ በኩል እንዲልክላቸው በገለጹት መሰረት ከሳሽ በ28/07/03 ብር 750,000.00 በወጋገን ባንክ ተ/ሀይማኖት ቅርንጫፍ በኩል የላኩላቸው መሆኑን ተከሳሾቹ መኪናውን ሳይልኩ እንደቀሩና ገንዘቡንም እንዲመልሱ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ እንደቀሩ የሚገልጽ ሆኖ ለክሱ ኃላፊ የሚሆነው ተከሳሽ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 36/5/ መሰረት ተለይቶ ብር 750,000.00 ከወለድና ክሱ ካስከተለው ወጪ ጋር እንዲከፍል ውሳኔ እንዲሰጥ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው። ተከሳሾቹ በበኩላቸው መኪና ለመሸጥ 2ኛ ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር እንዳልተነጋገሩ ከከሳሽ ጋር የቆየ የንግድ ግንኙነት የነበራቸው በመሆኑ 2ኛ ተከሳሽ አ/አበባ ውስጥ የተነጋገሩት ከከሳሽ ስለሚፈለግ የእዳ መጠንና እዳው ስለሚከፈልበት ሁኔታ እንደሆነ ከሳሽ የሞባይል ቀፎዎችን ከተከሳሾች በካሽ እና በዱቤ ይገዙ ስለነበረ የብር 850,000.00 ዕዳ ይፈለግባቸው እንደነበር ከዚህ ውስጥ በ05/05/03 ብር100,000.00 በ2ኛ ተከሳሽ ስም በንብ ባንክ ወደ ጅጅጋ እንደላኩ በክሱ የተጠቀሰው ገንዘብም ከከሳሽ የሚፈለግ ቀሪ ዕዳ እንደሆነ ከሳሽ ክስ ላያቀርቡ የቻሉት የሞባይል ቀፎ ዋጋ በመውረዱ ገንዘብ እንዲመለስላቸው ጠይቀው ተከሳሾች ባለመስማማታቸው እንደሆነ እና በከሳሽ በምስክርነት የተቆጠሩት ግለሰቦች ከከሳሽ ጋር አብረው የሞባይል ቀፎዎችን ከተከሳሾች ላገዙ የነበሩ እንደሆነ በመግለጽ ተከራክረዋል።
ፍ/ቤቱም የግራ ቀኙን ምስክሮች ከሰማ እና የጽሑፍ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ከሳሹ ብር 750,000.00 የላኩት ለመኪና ግዥ ነው ወይስ ከተከሳሾቹ ጋር በነበራቸው የሞባይል ቀፎ ሽያጭ ንግድ ግንኙነት ነው? የሚል ጭብጥ መስርቶ ከሳሽ እና 2ኛ ተከሳሽ ስለመኪና ሽያጭ ጉዳይ መስማማታቸውን ያስረዳሉ ተብለው የተሰየሙት የከሳሽ ምስክሮች ከሳሽ እና 2ኛ ተከሳሽ ተገናኝተው ተነጋግረዋል ስለተባለበት ሰዓት እና የተለየበት እንዲሁም ስለተሽከርካሪው ዓይነት እና ዋጋ የሰጡት ምስክርነት ልዩነቶች የሚታይበት መሆኑን እነዚህ ልዩነቶችም ከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ተነጋግረናል ባሉበት ጊዜና ቦታ ምስክሮቹ ያልነበሩና በጥናት እንደቀረቡ የሚያመለክት መሆኑን ከሳሽ መኪና ለመግዛት ተሰማሙበት ውል እንኳ የልላቸው መሆኑን እና ምንም ውል ሳይኖር መኪና ለመግዛት ብር 750¸000.00 እንዲሁ ይሰጣሉ ብሎ ለማመን የሚከብድ መሆኑን በዝርዝር ገልጾ ከሳሽ ገንዘቡን የላኩት የነበረባቸውን ዕዳ ለመክፈል እንጂ ለመኪና ግዥ ነው ማለት አልተቻለም ሲል ክሱ ውድቅ በማድረግ ውሳኔ ሰጥቷል።
ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው የፍ/ጠ/ፍ/ቤት በበኩሉ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ከሳሽ የመኪና ግዥ ውል በጽሑፍ ባያቀርቡም የሀዋላ ሰነዱን በማስረጃነት እንዳቀረቡ ተከሳሾቹ ገንዘቡን መቀበላቸውን አምነው ምክንያቱን የካዱ በመሆኑ ከከሳሽ የሚፈልጉት እዳ ስለመኖሩ በጽሑፍ እስካላስረዱ ድረስ ገንዘቡን የማይመልሱበት ምክንያት እንደማይኖር እና ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ ቀረበበትን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ምስክሮችን በመስማት እልባት ለመስጠት መሞከሩ ተገቢነት ያለው የማስረጃ አቀራረብ ስርዓት እንዳልሆነ በዝርዝር ገልጾ የስር ፍ/ቤት ውሳኔን በመሻር ተከሳሾቹ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ከነወለዱ በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉ ውሳኔ ሰጥቷል። አመልካቾች ሰበር አቤቱታ ያቀረቡት የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ መሰረታዊ ህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ ላታረም ወይም ላሻር ይገባል በማለት ሲሆን ጉዳዩ ለሰበር ክርክር ያስቀርባል በመባል ግራ ቀኙ የስር ክርክራቸውን መሰረት በማድረግና በማጠናከር በሰበር ደረጃ የጽሑፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።
ጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ባጭሩ ከላይ ተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ ቀረበበት የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት መሆን አለመሆኑን በስር ፍ/ቤቶች በግራ ቀኙ ማስረጃ ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አንፃር መርምረናል።
በዚህም መሰረት ተጠሪ ለፍ/ከ/ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ መሰረታዊ ይዘት ከ2ኛ አመልካች ጋር የመኪና ሽጭ ውል ማድረጋቸውንና የሽያጩን ዋጋ 2ኛ አመልካች በጠየቁት መሰረት በ1ኛ አመልካች ስም በባንክ መላካቸውን የሚገልጽ ነው። በመሰረቱ አንድ ግድታ እንዲፈጸምለት የሚጠይቅ ሰው የግድታውን መኖር የማስረዳት ሸክም እንዳለበት በፍ/ሕ/ቁ 2001/1/ ተመልክቷል። በተያዘው ጉዳይ ተከሳሾ በከሳሽ የተላከውን ገንዘብ መቀበላቸውን አምነው ለገንዘቡ መላክ ምክንያት የሆነው ግን ከሳሽ እንደገለጹት የመኪና ሽያጭ ውል አለመሆኑን ክደው ተከራክረዋል። ይህ ከሆነ ደግሞ ከላይ በተጠቀሰው ድንጋጌ መሰረት የመኪና ሽያጭ ውል ተደርጎ የነበረ መሆኑን እና ገንዘቡም የተላከው በዚሁ ውል ምክንያት መሆኑን ማስረዳት የሚጠበቀው ከከሳሽ ወገን ነው። የውሉን መኖር ለማስረዳት ከሰሽ የሰሟቸው ምስክሮች በጥናት የቀረቡ ናቸው በሚል ከፍተኛ ፍ/ቤት ምስክርነታቸውን ውድቅ ያደረገ ሲሆን ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በበኩሉ ይህንን የከፍተኛ ፍርድ ቤት አቋም ወይም ትችት በዝምታ በማለፍ ከሳሽ የሚና ግዥ ውል በጽሑፍ ባያቀርቡም የሀዋላ ሰነድ አቅርበዋል ሲል በውሳኔው ላይ አስፍሮአል። በመሰረቱ የሀዋላ ሰነዱ በተከሳሾቹ ያልተካደውን የገንዘቡን መላክ እና በተከሳሾች እጅ መግባት የሚገልጽ ከመሆኑ ወጪ ስለተላከበት ምክንያት የሚጠቁመው ነገር አለመኖሩ በክርክሩ ተረጋግጧል። በመሆኑም ከሳሽ የሀዋላ ሰነዱን በማዘጋጀት በማቅረብ ማስረዳት ሸከማቸውን የተወጡት የገንዘቡን መላክ ምክንያት መሆኑን በተመለከተ ጭምር እንደሆነ አድርጎ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የያዘውና ለውሳኔው መሰረት ያደረገው አቋም ከላይ የተጠቀሰው ፍ/ሕ/ቁ 2001/1/ ድንጋጌ አተረጓጎም ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ተገኝቷል።
በልላ በኩል የመኪና ሽያጭ ውል መኖሩን ለማስረዳት መቅረብ የሚገባውን የማስረጃ አይነት በተመለከተ ግዙፍነት ያላቸው የተንቀሳቃሽ ንብረቶች ባለሀብትነት ንብረቱን በመግዛት ወይም በልላ አኳኋን ያገኘው ወይም በኑዛዜ የተሰጠው ሰው ንብረቱን በእጅ ባደረገ ጊዜ የተላለፈለት እንደሚሆን በፍ/ሕ/ቁ 1186/1/ የተደነገገ ሲሆን ልዩ የሆኑ አንዳንድ የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን የሚመለከቱት የህጎች ድንጋጌዎች የተጠበቀ መሆናቸውም በፍ/ህ/ቁ 1186/2/ ተመልክቷል።
መኪና ደግሞ ከልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚመደል በመሆኑ ባለሀብትነት የማስተላለፉ ጉዳይ በተለይ ሕጎች የሚመራ ነው። በዚህ ረገድ አንድ ተሽከርካሪ ባለሀብትነት እንዲተላለፍለት የሚጠይቅ ሰው አግባብነት ካላቸው ልሎች ሰነዶች በተጨማሪ ተሽከርካሪው ከውጪ ሀገር የገባ ከሆነ የጉምሩክ ድክላራሲዮን በሀገር ውስጥ የተሰራ ከሆነ ተገዛበትን ኢንቮይስ እንዲሁም ከቀድሞ ባለንብረት በግዥ የተላለፈለት ከሆነ ደግሞ የዝውውሩን ህጋዊነት ለማስረዳት በሚመለከተው አካል የተሰጠ ወይም ተረጋገጠ ሰነድ ማቅረብ አንደሚጠበቅበት ስለተሽከርካሪ መለያ መመርመሪያና መመዝገቢያ በወጣው አዋጅ ቁጥሩ 681/2002 በአንቀጽ 6 ስር በሚገኙ አራት ንዑሳን ቁጥሮች በዝርዝር ተመልክቷል። በተለይም አዋጁ አንቀጽ 6/3/ እና 6/4/ ድንጋጌዎች ጥምሩ ንባብ እንድ ተሽከርካሪ በቀድሞ ባለንብረት በሽያጭ ለልላ ሰው የተላለፈ መሆኑ ተረጋግጦ የባለሀብትነት ዝውውሩ ላፈፀም የሚችለው ውሉ በጽሑፍ በተደርገ ጊዜ መሆኑን መገንዘብ የሚያስችልነው። በተያዘው ጉዳይም ከሳሽ የመኪና ሽያጭ መደረጉን ለማስረዳት ማቅረብ የሚጠበቅባቸው የሽያጭ ውሉ የተደረገበትን ሰነድ ሆኖ እያለ እና የዚህ ዓይነቱን ሰነድ ደግሞ ያላቀረቡ ሆኖ እያለ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ከሳሽ የሀዋላ ሰነዱን ማቅረባቸው በቂ ነው ሲል ሰጠው ውሳኔ የክሱን እና የፍ/ሕ/ቁ 2001/1/ ድንጋጌን ይዘት ያገናዘበ ሆኖ አልተገኘም።
ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ለውሳኔው በምክንያትነት የጠቀሰው ልላኛው ነጥብ ተከሳሾቹ ገንዘቡን መቀበላቸውን አምነው ምክንያቱን ከመካድ በስተቀር ከከሳሽ የሚፈልጉት ዕዳ ስለመኖሩ ያቀረቡት የጽሑፍ ማስረጃ ሳይኖር ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ የቀረበበትን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ምስክሮቹን በመስማት እልባት ለመስጠት መሞከሩ ተገቢነት ያለው የማስረጃ ሳይኖር ከፍተኛ ፍ/ቤት ክስ የቀረበበትን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ምስክሮችን በመስማት እልባት ለመስጠት መሞከሩ ተገቢነት ያለው የማስረጃ አቀራረብ ስርዓት አይደለም የሚል ነው። በመሰረቱ ተከሳሾቹ በማስረጃነት ያቀረቡት ምስክሮችን ብቻ ሳይሆን የኤልክትሮኒክስ ዕቃዎች ንግድ ፈቃድ እና ከሳሽ ቀደም ሲል ብር 100¸000 በባንክ የላኩበትን ሰነድ ጭምር ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አከራካሪ ሆኖ ቀረበን አንድ ፍሬ ነገር ማስረዳት ስለሚቻልበት የማስረጃ ዓይነት አግባብነት ባለው ሕግ በተለይ የተቀመጠ ግልጽ ድንጋጌ እስከልለ ድረስ እንደዚህ ዓይነቱን ፍሬ ነገር በምስክር ጭምር ማስረዳት እንደሚቻል ከፍ/ሕ/ቁ 2002 ድንጋጌ ይዘት መገንዘብ የሚቻል ሲሆን በግራ ቀኙ መካከል ስለነበረው የንግድ ግንኙነት ሁኔታ እና ከግንኙነቱ ስለመነጨው የገንዘብ ዕዳ በምስክሮች ማስረዳትን የሚከለክል ድንጋጌ የለም።
ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም ምስክሮችን በመስማት ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት መሞከሩ ተገቢነት ያለው የማስረጃ አቅራረብ ስርዓት አይደለም ከማለት በስተቀር የዚህ ዓይነቱን የማስረጃ አቀራረብ ስርዓት ተገቢነት የሚያሰጠው የትኛው ሕግ ወይም ድንጋጌ እንደሆነ በውሳኔው አልገለጸም። በመሆኑም ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በዚህ ረገድ ለውሳኔ በምክንያትነት የጠቀሰው ነጥብ የህግ መሰረት ያለው ሆኖ አልተገኘም።
በመጨረሻም በዚህ መዝገብ ለክርክር የቀረበው ጉዳይ በግለሰቦች መካከል የሚደረግ የብር 750¸000 ግምት ያለው ክርክር በመሆኑ እና የዚህ ዓይነቱ ክርክር ደግሞ ተመርምሮ አልባት ማግኘት የሚገባው የጉዳዩን ዋነኛ ፍሬ ነገር መሰረት በማድረግ በግራ ቀኙ ከቀረበው ክርክርና ማስረጃ እንዲሁም ለክርክሩ መሰረታዊ ጭብጥ አግባብነት ካላቸው ህጎች አንፃር በመሆኑ ከተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/94 እና ከንግድ ፈቃድና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 686/2002 ጋር ተያይዞ በሰበር ደረጃ በተጠሪ መልስ ላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች በዚህ ውሳኔ ላይ ማስፈሩን እና መመርመሩን አስፈላጊና ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።
ሲጠቃላል የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይ/ሰሚ ችሎት የከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔን በመሻር የስር ተከሳሾች ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ከነወለዱ ለስር ከሳሽ ላከፍሉ ይገባል ሲል የሰጠው ውሳኔ ከላይ በዝርዝር በሰፈሩት ምክንያቶች ሁሉ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
ው ሣ ኔ
የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ በ22/09/04 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
የፍ/ከ/ፍ/ቤት በመ/ በ08/03/04 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 348/1/ መሰረት ፀንቷል
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ። የስር መዝገብ ይመለስ።
ውሣኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል። ወደ መዝገብ ቤት ይምለስ።
No topics extracted.