No summary available.
ጥቅምት 22 ቀን 2005 ዓ.ም ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- ወ/ሮ ዋሪቴ ሱቡሳ ቀረቡ ተጠሪ፡- 1ኛ. የጎልጆታ ከተማ አስተዳደር ተወካይ አቶ ቡርቃ ፈጂሶ - ቀረቡ 2ኛ. ወ/ሮ አየለች ሞሲሳ ቀረቡ መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ሲሆን ፤ መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የቀረበው ለዚህ የሰበር ክርክር ምክንያት የሆነውን የመጨረሻ ፍርድ የሰጠው የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በግራ ቀኙ መካከል የተነሣው ክርክር በፍርድ ላያልቅ የሚችል አይደለም በሚል የሰጠውን ዳኝነት ካከራከረው የጉዳይ ይዘት አንፃር ተመልክቶ አግባብነቱን ለማየት በሚል ነው።
የጉዳዩ መነሻ የአሁን አመልካች በአርሲ ነገል ወረዳ ፍ/ቤት ያቀረቡት ክስ ሲሆን ፤ ይዘቱም የግል ንብረቴ በሆነው ቤቴ ላይ 1ኛ ተጠሪ የጎልጆታ ከተማ አስተዳደር የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታና ኘላን አዘጋጅቶ ለ2ኛዋ ተጠሪ የሰጣት ስለሆነ ይኸው ካርታና ኘላን ላሰረዝ ይገባል የሚል ነው።
የአሁን 1ኛ ተጠሪ ክርክር ባስነሳው ቤት ላይ በ2ኛ ተጠሪ ስም ካርታና ኘላን አዘጋጅቶ ለመስጠት የሚያስችል ማስረጃ በ2ኛ ተጠሪ መቅረቡንና ይህንኑ መሰረት አድርገን የሰጠን ስለሆነ የከሣሽ ጥያቄ ተቀባይነት እንደልለው ገልፆ ተከራክሯል።
የአሁን 2ኛ ተጠሪም በበኩላቸው ይህ ክስ የቀረበበትን ቤት ባለቤታቸው አቶ አንኮ ሐዊያ በ1981 ዓ.ም ገዝቶታል። ከዚህ በኋላም ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ሚስትነቴንና የወራሽነት መብት በፍ/ቤት በማረጋገጤ ምክንያት የከተማው አስተዳደር ቤቱን ወደ ስሜ ያዞረው ስለሆነ የንብረቱ ባለመብት እኔ ነኝ የሚል ክርክር አቅርባለች።
ፍ/ቤቱም ከግራ ቀኙ ክርክር በመነሳት ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ቤት የማን ነው? የሚለውን ነጥብ ለመለየት በሁለቱም ወገኖች የቀረበውን የቤት ግዥ የፅሑፍ ውል ሰነድ ፤ ግብር የተከፈለበትን ደረሰኝ እና የሰው ማስረጃዎችን ቃል ከተመለከተና ከሰማ በኋላ ሁሉም ተከራካሪ ወገኖች በየፊናቸው ያቀረቧቸው ማስረጃዎችን የማስረዳት ጥንካሬውን መርምሮና የተሻለ ማስረጃ ማን አቅርቧል የሚለውን ለመለየት ማስረጃውን መዝኖ ይኸው ቤት የአሁን አመልካች በሥር ፍ/ቤት ከሣሽ የሆኑት የወ/ሮ ዋሪቴ ሱቡሳ መሆኑን አረጋግጧል። ይህ ቤት የወ/ሮ ዋሪቶ መሆኑ እየታወቀ የከተማው አስተዳደር ያለአንዳች ማስረጃ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታና ኘላን አዘጋጅቶ ለ2ኛ ተጠሪ በመስጠቱ ምክንያት 2ኛ ተጠሪ ያለአግባብ የንብረቱ ባለቤት እንድትሆን ያደረጋት በመሆኑ የሰጠው ካርታና ኘላን ላሰረዝ ይገባል በማለት ወስኗል።
ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተውም የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ማስረጃ በመመዘን ረገድ ተመሳሳይ ትንታኔ ተከትሎ የወረዳውን ፍ/ቤት ውሣኔ አፅንቷል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ በከተማው ውስጥ የሚገኙ መሬቶችን ቤቶችን ማስተዳደርና መቆጣጠር የባለይዞታነትና የባለቤትነት ማስረጃ መስጠት የከተማው አስተዳዳር ሥልጣን ነው። የከተማው አስተዳደርም ይህንኑ ክርክር የተነሣበትን ካርታና ኘላን አዘጋጅቶ የሰጠው በዚሁ ሥልጣኑ መሰረት በመሆኑ ይህ ካርታና ኘላን የተሰጠው በስህተት ፣ አግባብ ባልሆነ መንገድ ነው የሚባል ከሆነ እራሱ ይሰርዘው ዘንድ ጥያቄው ለከተማው አስተዳደር ከሚቀርብ በቀር በፍ/ቤቶች ሥልጣን ሥር ላወድቅ የሚችል ጉዳይ አይደለም ስለሆነም በገልጆታ ከተማ አስተዳደር የተሰጠው ካርታና ኘላን በመደበኛ ፍ/ቤት ላሰረዝ አይገባም በማለት የበታች ፍ/ቤቶችን ውሣኔ ሽሮታል።
ግራ ቀኙ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ስለጉዳዩ በፅሑፍ ያቀረቡት ክርክር ከዚህ በላይ እንደተገለፀው በሥር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያቀረቡትን የክርክር ይዘት ተከትለው የሚያብራራ በመሆኑ በድጋሚ ማስፈሩ አስፈላጊ ሆኖ አልተገኝም።
እንግዲህ የጉዳዩ አነሳስ እና አመጣጥ ከላይ በአጭር በአጭሩ የተመለከተው ሲሆን ፤ እኛም ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምረናል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በውሣኔው እንደገለፀው በአንድ ከተማ ውስጥ የሚገኝን መሬት የማስተዳደር የመሬትን ስሪትን እና በስሪቱ መሰረት የተገነቡ መሆኑን በማረጋገጥ የተገነባው ንብረት /ቤት/ የባለቤት ማረጋገጫ ካርታና ኘላን የመስጠት የከተማው አስተዳደር በአስተዳደር ረገድ ለከተማው አስተዳደር የተሰጠ ተግባርና ሥልጣን ስለመሆኑ ይህ የፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም የሚስማማበት ጉዳይ ነው።
ይሁን እንጂ ይህ በዚህ ጉዳይ የጎልጀታ ከተማ አስተዳደር አከናወነ የተባለው ተግባር ከዚህ በላይ የከተማው አስተዳደር የአስተዳደር ሥልጣን ነው በተባለው ሥር ላወድቅ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ነጥብ ግን ላታይ የሚገባው ነው። በከተማ አስተዳደር ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ የማይንቀሳቀስ ንብረት የሆነ የቤት የባለቤትነት መብት ከአንዱ ወደ ልላው በሚተላለፍበት ጊዜ ንብረቱን ለማስተላለፍ የሚያስችል ህጋዊ ተግባር የተከናወነ መሆኑን በማረጋገጥ የዚሁ ንብረት የባለቤትነት መብት ከአንድ ወደ ልላው የተላለፈ መሆኑን የሚያረጋግጠውን የንብረት ምዝገባ ተግባር ማከናወን ነው። በዚህ አኳኋን አረጋግጦ የምዝገባ ሥርዓቱን አከናውኖ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታና ኘላኑን ንብረቱ በተላለፈለት ሰው ስም አዘጋጅቶ በሰጠ ጊዜ በስሙ ካርታና ኘላን ተዘጋጅቶ የተሰጠው ሰው የዚሁ ንብረት ባለቤት እንደሆነ በህጉ ግምት እንደተወሰደ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 1195 ተደንግጓል። ይሁን እንጂ በዚሁ መሰረት በህጉ የሚወሰደውን የግምት አይነት ተከታይ በሆነው ድንጋጌ በተቃራኒ ማስረጃ ማስተባበል እንደሚቻል ተመልክቷል።
ከዚህ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ 1196 ጋር በተያያዘ ተቃራኒ ማስረጃ በማቅረብ አስቀድሞ በከተማው አስተዳደር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1195 የተሰጠውን የባለቤትነት የምስክር ወረቀት ልላ ተቃራኒ ማስረጃ በማቅረብ የማስተባበል ሥራ የሚከናወነውና ፤ በህጉ ተሰጥቶ የነበረው የባለቤትነት ግምት ቀሪ የመሆኑና ያለመሆኑ ጉዳይ የሚረጋገጠው በፍ/ቤት የዳኝነት ተግባር ጭምር ነው።
ከዚህ አንፃር አሁን በዚህ ሰበር ችሎት ደረጃ የተነሣውን ጉዳይ ለአመልካች ክርክር ያስነሳው ቤት ባለቤት የአሁን አመልካች እንደሆኑ የሥር የወረዳ እና የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤቶች በሰጡት ውሣኔ እንደተረጋገጠ ገልፆዋል። እንዲሁም የከተማው አስተዳደር በዚሁ የአመልካች መሆኑ በተረጋገጠው ቤት ላይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታና ኘላን በ2ኛ ተጠሪ ስም አዘጋጅቶ ላሰጥ የቻለው 2ኛ ተጠሪ ስለጠየቀችው እንጂ የዚህን ቤት ባለቤትነት መብት ከንብረቱ ባለቤት ወደ 2ኛ ተጠሪ የተላለፈ መሆኑን የሚያሳይ ህጋዊ ተግባር /juridical act/ መቅረቡን አረጋግጦ እንዳልሆነ በግራ ቀኙ ክርክር በፍሬ ነገር ረገድ በማስረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።
ይህም ከሆነ ምንም እንኳ ማዘጋጃ ቤቱ በእራሱ እምነት የዚሁ ንብረት ባለበት 2ኛ ተጠሪ መሆኗን አረጋግጫለሁ በማለት የባለቤትነት የምስክር ወረቀት የሰጠ መሆኑ ቢታወቅም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1196 እንደተደነገገው የአሁን አመልካች ይህ የባለቤትነት የምስክር ወረቀት ላሰጥ የቻለው የንብረት ባለሀብትነት መብት ከአንዱ ወገን ወደ ልላው እንድት መተላለፍ እንዳለበት በህጉ የተመለከተውን ደንብና ሥርዓት ሳይከተል ስለሆነ የንብረቱ ባለሀብት ስለመሆኑ የህግ ግምት መውሰጃ የሆነው የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ቀሪ ነው ፤ ላሰረዝ ይገባል በማለት ያቀረቡት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1195 ፣ 1196 እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 33/2/ እና 231/1/ሀ/ በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሰረት በፍ/ቤት ላረጋገጥ የሚችል የዳኝነት ጥያቄ እንጂ ጉዳዩ በፍርድ ላያልቅ የሚችል ጉዳይ አይደለም ለማለት የሚያበቃ አይደለም ከዚህ አንፃር የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በጉዳዩ ላይ የሰጠው የመጨረሻ ፍርድ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ በማግኘታችን የሚከተለውን ውሣኔ ሰጥተናል።
ው ሣ ኔ
የኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ በቀን 16/04/2004 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል።
ግራ ቀኙን ያከራከረው ጉዳይ በፍርድ ላያልቅ የሚችል ጉዳይ በመሆኑ ይኸው የክልሉ ሰበር ሰሚው ችሎት በሰበር ሥልጣኑ ጉዳዩን ተመልክቶ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 343/1/ እንደተመለከለተው አስፈላጊውን ዳኝነት ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩን መልሰናል።
የዚህ የፍደራል ሰበር ሰሚ የሰበር ክርክር ላስከተለው ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኝ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
ቤ/ዮ የሰ/መ/ ህዳር 17 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች አልማው ወል ዓላ መሐመድ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አልቀረቡም ተጠሪ፡- አቶ በላይ ሀሰን አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ስላመለከቱ ነው። ጉዳዩ በመንገድ ሥራ ምክንያት ለጠፋ ንብረት /የባህርዛፍ አትክልት/ የሚከፈልን የካሣ የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ አመልካች መንገድ ሲሰራ፣ ቁጥሩ 4500 የሆነ የባህርዛፍ አትክልት ላይ ውድመት ያደረሰበት መሆኑን ገልፆ ብር 165‚000 /አንድ መቶ ስልሣ አምስት ሺህ ብር/ ካሣ ተከሣሹ (አመልካች) እንዲከፍል ይወሰንልኝ በማለት ያቀረበው ክስ ነው። አመልካች በተከሣሽነት ቀርቦ ተጠሪ ባህርዛፍ የተከለው ከመንገዱ መጠበቅ የሚገባውን ርቀት ሣይጠብቅ በመሆኑ በደንብ ቁ. 6/1936 መሰረት ካሣ የመክፈል ኃላፊነት የለብኝም። የተጠየቀው የካሣ መጠን የተጋነነ ነው በማለት ተከራክሯል። የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የባህርዛፍ አትክልቱ የተተከለበትን ሁኔታ፣ በመንገድ ሥራው ምክንያት የወደመው ባህርዛፍ ዋጋ በባለሙያ ተገምበቶ እንዲቀርብለት በማድረግ አመልካች ለተጠሪ ብር 17,942.00 /አስራ ሰባት ሺህ ዘጠኝ መቶ አርባ ሁለት ብር/ እንዲከፍል ውሣኔ ሰጥቷል። አመልካች ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቧል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአመልካችን ይግባኝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል።
አመልካች ተጠሪ ባህርዛፍ ወደመብኝ የሚለው ከዋና መንገድ መሐል መስመር ወደግራና ወደ ቀኝ አስራ አምስት ሜትር ስፋት ያለው መንገድ ነው። ስለዚህ አስራ አምስት ሜትር ወደ ግራና ቀኝ አትክልት እንዳይተከል አዋጅ ቁጥር 65/36 የሚከለክል በመሆኑና ተጠሪ ይህንን የህግ ክልከላ በመተላለፍ፣ መጠበቅ የሚገባውን እርቀት ሣይጠበቅ ለተከለው ባህርዛፍ ግምት የመክፍል ኃላፊነት የልለበት መሆኑን በመግለጽ ያቀረበው ክርክር አላግባብ ውድቅ ተደርጓል።
አመልካች እንዲከፍል የተወሰነው የካሣ መጠን የተጋነነ ነው በማለት የሰበር አቤቱታ አቀርበዋል። አመልካች መጋቢት 10 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ መልስ፣ እኔ ባህርዛፍ ስተክል ከመንገዱ መጠበቅ የሚገባኝን ርቀት በመጠበቅ ነው የተከልኩት። አመልካች በመንገድ ሥራ ለወደመው ባህርዛፍ በተሟላ ሁኔታ ካሣ እንዲከፍል አልተወሰነበትም። ስለዚህ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም አመልካች በሰበር አቤቱታው ያቀረበውን ክርክር በማጠናከር ሚያዚያ 16 ቀን 2004 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሣኔ አግባብነት ካላቸው የህግ ማእቀፎች ጋር በማገናዘብ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ተጠሪ ባህርዛፉን በሚተክልበት ወቅት በተጠሪ የይዞታ መሬት አዋሣኝ የነበረው መንገድ የተንታ ወረዳን ከዞኑ ከተማ ደሴ ጋር ለማገናኘት ታስቦ የተገነባ መንገድ እንደነበርና መንገዱ የተንታ ወረዳን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኝ መንገድ እንዳልነበር ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል። አመልካች የዚህን መንገድ ደረጃ ከፍ በማድረግ ተንታን ከአዲስ አበባ ጋር ለማገናኘት የሚችል መንገድ ለመገንባት ባደረገው እንቅስቃሴ ተጠሪ የመንገዱ አዋሣኝ በሆነው የይዞታ መሬት ላይ የተከለውን የባህርዛፍ አትክልት የወደመበት መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል።
አመልካች ተጠሪ ቢያንስ አስራ ሁለት ሜትር ርቀት ሣይጠብቅ ባርህዛፍ የተከለ በመሆኑ ካሣ የመክፈል ኃላፊነት የለብኝም በማለት ያቀረበው የሰበር ክርክር አከራካሪው መንገድ በመጀመሪያ አውራ ጎዳና ያልነበረና መካከለኛ መንገድ የነበረ መሆኑን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡትን ፍሬ ጉዳይ መሰረት ያደረገ ነው።
መንገዱ መጀመሪያ ወረዳን ከዞኑ ዋና ከተማ የሚያገናኝ የነበረ መሆኑንና አመልካች መንገዱን በማስፋትና ደረጃውን ከፍ በማድረግ ወረዳውን ከአዲስ አበባ ጋር ለማገናኘት የሚችል መንገድ ሲገነባ ለተጠሪ በይዞታው በተከለው ባህርዛፍ ላይ ጉዳት ማድረሱ ተረጋግጧል። ስለዚህ አመልካች ለጉዳቱ ኃላፊነት የለብኝም በማለት ያቀረበው ክርክር ስለመገንዶችና ድልድዮች አጠባበቅ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 65/1936 አንቀጽ 2(ሀ) እና የጎዳናዎችና መንገዶች አከፋፈል አዋጅ ቁጥር 66/1936 አንቀጽ 1(ለ) ድንጋጌዎች ይዘት መንፈስና ዓላማ ያላገናዘበና የህግ መሰረት የልለው በመሆኑ አልተቀበልነውም።
ው ሣ ኔ
የአማራ ክልለ የደቡብ ወል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ ፀንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት ሰኔ 19 ቀን 2004 ዓ.ም የተሰጠው የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል።
ይፃፍ።
No topics extracted.