No summary available.
ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሣ አዳነ ንጉሴ አመልካች፡- አቶ ሳምሶን መንግሰቱ ቀረቡ ተጠሪ፡- የፍድራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ያቃቤ ህግ ወኪል መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፍደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ስላመለከቱ ነው። ጉዳዩ የውጭ ምንዛሬ ያለፈቃድ ከአገር የማስወጣት ወንጀልን የሚመለከት ሲሆን በመጀመሪያ የታያው በፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሳሽ አመልካች ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
የክርክሩ መነሻ አመልካች ለስር ፍርድ ቤት ያቀረበው የወንጀል ክስ ነው። ተጠሪ አመልካች በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 99 እና የኢትዮጵያ ብሕራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጸ 20 ንዑስ አንቀጽ 3 እንዲሁም መንገደኞች የውጭ ምንዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ይዘው ስለሚገቡበትና ስለሚወጡበት በብሕራዊ ባንክ ግንቦት 21 ቀን 2001 ዓ.ም የወጣውን መመሪያ አንቀጽ 3 በመተላለፍ ሰኔ 10 ቀን 2002 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡30 በቦል አየር መንገድ ከአገር ላወጣ ሲል 5000 ዩሮ /አምስት ሺህ ዩሮ/ ይዞ ላወጣ ሲል በኤክስሬይ ፍተሻ የተገኘ በመሆኑ በህገወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ (ዕቃ) ማውጣትና የመያዝ ወንጀል ፈጽመዋል።
አመልካች ወንጀሉን አልፈፀምኩም ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ተከራክሯል። ተጠሪ የወንጀል ክሱን ያስረዱልኛል በማለት ሁለት የሰው ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል። ተጠሪ ሰነድ ማስረጃውንና ከአመልካች እጅ የተገኘውን (5000 ዩሮ) በማስረጃነት አቅርቧል።
አመልካች የውጭ ምንዛሬውን ለጉምሩክ አሳውቀው ድክራላሲዮን ተሰጥቷቸው ያስገቡ መሆኑንና የውጭ ምንዛሬው ከቦርሣቸው ውስጥ ሲገኝባቸው ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የተሰጠውን ድክላራሲዮን ያልያዙ መሆኑንና ወንጀል የመፈፀም ሀሳብ ያልነበረው መሆኑን ያስረዳልኛል የሚላቸውን የመከላከያ ምስክሮች እና የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል።
የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረና ከወሰነ በኋላ አመልካች የውጭ ምንዛሬውን ይዞ ለመውጣት የተፈቀደለት የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላ የውጭ ምንዛሬውን ይዞ በመውጣት ላይ እያለ ተይዟል። ተከሳሽ ውጭ ምንዛሬውን ይዞ የገባው አሳውቆና አስመዝግቦ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬውን ይዞ ለመውጣት የተፈቀደለት የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላ የውጭ ምንዛሬ ለማውጣት ይዞ ቢገኝ የውጭ ምንዛሬውን የማውጣት መብቱን ከሚያሳጣው በስተቀር በኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ እንዲሰጠው የመጠየቅ መብቱን እንደማያሳጣው ጉዳዩ የወንጀል ኃላፊነት እንደማያስከትል የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ አስገዳጅ ትርጉም ሰጥቶበታል። እንደዚሁም ተከሳሽ በበኩል የተፈፀመው ተግባር ተከሳሽ አሳውቆና አስመዝግቦ ወደ አገር ይዞት የገባውን የውጭ ምንዛሬ ይዞ መውጣት መብት እንዳለው በመቁጠር የፈፀመውና ወንጀል የመፈፀም ሀሳብ የልለው መሆኑን የሚያሳይ ስለሆነ ከቀረበበት ወንጀል ክስ በነፃ ይሰናበታል። ከሳሽ ከተሰሳሽ እጅ የያዘውን ዩሮ /የውጭ ምንዛሬ/ በተያዘበት ቀን ባለው ምንዛሬ በማሰብ በብር ለተከሳሽ ክፍል በማለት ውሣኔ ሰጥቷል።
ተጠሪ በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።
የከፍተኛው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ መልስ ሰጭ የውጭ ምንዛሬ ይዞ ሲወጣ ሲል ተይዟል። የውጭ ምንዛሬውን ይዞ ላወጣ ሲሞክር ዲክላራሲዮኑ ከተፃፈ የስድስት ወራት ጊዜ አልፎታል። አመልካች መልስ ሰጭ የውጭ ምንዛሬ ይዞ ሲገባ የነበረው መመሪያ መልስ ሰጭ ይዞ ለመውጣት በሚሞክርበት ጊዜ የተቀየረ ሲሆን በጉዳዩ ተፈፃሚ የሚሆነው ነው መልስ ሰጭ ለማውጣት ሲሞክር ፀንቶ ስራ ላይ የነበረው መመሪያ ነው። መልስ ሰጭ የውጭ ምንዛሬው ገደብና ቁጥጥር የሚደረግበት እቃ መሆኑን ያውቃል። ህጉን በመተላለፍ የውጭ ምንዛሬ ለማውጣት ሲሞክር በኤክስሬይ ማሽን የተያዘ በመሆኑና የተከሰሰበትን ወንጀል የፈፀመ ጥፋተኛ ነው በማለት በአንድ ዓመት ከስድሰት ውር ጽኑ እስራት እንዲቀጣና በተያዘው 5000 ዩሮ እንዲወረስ ወስኗል። ከፍተኛው ፍርድ ቤት የእስራት ቅጣቱ አፈፃፀም ለሁለት አመት ተገድቦ እንዲቆይ ወስኗል።
አመልካች በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል። ይግባኝ ሰሚው ችሎት የአመልካችን ይግባኝ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 195/1/ መሰረት ሰርዞታል። አመልካች ግንቦት 24 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ ሰበር አቤቱታ በጉዳዩ የስር ፍርድ ቤት የከፍተኛ ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡትን ውሣኔ ይዘት ከዘረዘረ በኋላ እኔ የውጭ ምንዛሬውን ይዤ ለመወጣት ስሞክር ስራ ላይ የነበረው መመሪያ መጀመሪያ ዩሮውን አስመስግቤ ወደ አገር ውስጥ ሳስገባ ያልነበረ ነው።
የውጭ ምንዛሬ ይዤ በምወጣበት ጊዜ አልፏል የሚባል ከሆነም በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ብር ተመንዝሮ ከሚሰጠኝ በስተቀር ወንጀል ሰርተሀል ተብሎ ላወረሰብኝ አይገባም።
የከፍተኛው ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት ውሣኔ በተመሳሳይ ጉዳይ ይህ ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ የሰጠውን አስገዳጅ ትርጉም ያልተከተለና መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ታረምልኝ በማለት አመልክቷል።
ተጠሪ ነሐሴ 25 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካች 5000 ዩሮ ከአገር ለማውጣት የተያዙት በኤክስሬ ምርመራ ነው። ገንዘቡን ወደ አገር ውስጥ ሳስገባ አስመዝግቤአለሁ በማለት ድክላራሲዮን ያቀረቡት ገንዘቡ በፍተሻ ከተያዘ በኋላ ነው። ያቀረቡት ድክራላሲዮን ከስድስት ወራት በላይ ያለፈው ከመሆኑም በላይ አመልካች ይዞት ወደ አገር ውስጥ ያስገባቸውን ዩሮ ቁጥር የሚገልጽ አይደለም። አመልካች ወንጀል የፈፀመው ያውም ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገባ ሳይሆን ይዞ ለመውጣት በሞከረበት ቀን /ጊዜ/ በመሆኑ ለጉዳዩ ተፈፃሚ የሚሆነው ወንጀሉ ሲፈፀም ፀንቶ ሲሰራበት የነበረው ህግና መመሪያ ነው። አመልካች ሰበር ችሎት በፍ/ብሕር ጉዳይ የሰጠውን ውሣኔ ለወንጀል ጉዳይ መከራከሪያ አድርጎ ማቅረቡ የህግ መሰረት ያለውም። ስለዚህ አመልካች ጥፋተኛ መባሉና ገንዘቡም እንዲወረስ የተሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል። አመልካች መስከረም 21 ቀን 2005 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና ለሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት የጽሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ፍደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አመልካች የውጭ ምንዛሬ በህገወጥ መንገድ ይዞ ሲወጣ የተያዘ ጥፋተኛ በመሆኑ ገንዘቡ በወርስ ለመንግስት ገቢ ይሁን በማለት የሰጡት ውሣኔ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ተጠሪ 5000 ዩሮ ከአገር ለማስወጣት ሲሞክር ቦል ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በፍተሻ የተያዘው ሰኔ 10 ቀን 2002 ዓ.ም መሆኑ ተረጋግጧል። ተጠሪ አመልካች ያለ ህጋዊ እውቅናና ፈቃድ የውጭ ምንዛሬ ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ አገር ሲያወጣ ተይዟል በማለት የተከሰሰው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 25 በሚደነግገው መሰረት ወንጀሉ ተፈፀመበት ቦታና ወንጀሉ የተፈፀመበትን ጊዜ ማለትም ሰኔ 10 ቀን 2002 ዓ.ም በመጥቀስ ነው።
ይህ ከሆነ ወንጀሉ በተፈፀመበት ጊዜ ስራ ላይ የነበረው የብሕራዊ ባንኩ መመሪያ ተፈፃሚነት ይኖረዋል በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትና የፍደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት የህግ ትርጉም የህገ መንግስቱን አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 1 እና የወንጀል ህጉ አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጸ 2 መሰረት ያደረገና የህግ አተረጓጎም ስህተት የልለበት በመሆኑ አመልካች የውጭ ምንዛሬውን ወደ አገር ውስጥ ይዞ ሲገባ የነበረው መመሪያ ልላ ስለነበረ የውጭ ምንዛሬውን ይዤ ስውጣ ጸንቶ ስራ ላይ ያለው መመሪያ በእኔ ጉዳይ ተፈፃሚነትና ተጠቃሽነት ላኖረው አይገባም በማለት ያቀረበውን ክርክር አልተቀበልነውም ።
አመልካች የውጭ ምንዛሬውን በፈቃድ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ መሆኑን ከአገር ይዞ ለመውጣት የተፈቀደለት የጊዜ ገደብ ያለፈበት በመሆኑ የውጭ ምንዛሬውን ይዞ ለመውጣት እንዲፈቀድለት አሳውቆና ጥያቄ አቅርቦ ሳይሆን በቦርሳው ውስጥ በማድረግ ይዞ ሲወጣ በኤክስሬይ ፍተሻ ስለተደረገበት የተያዘ መሆኑ አላከራከረም።
ይህም የአመልካች አድራጎት ያለፈቃድ የውጭ ምንዛሬ ይዞ የመወጣት ወንጀል የሚያቋቁም ስለመሆኑ ከላይ የተገለፁት የህግ ማዕቀፎችና ከወንጀል ህጉ አንቀጽ 23/2/ ድንጋጌ ለመገንዘብ ይቻላል።
አመልካች የሚያቀርበው ክርክር በወንጀል ህጉ አንቀጽ 81 ስር የሚወድቅና የውጭ ምንዛሬውን ሳያስፈቅድ ይዞ መወጣት ወንጀል መሆኑን አላውቅም የሚል ይዘት ያለው ነው። ሆኖም ህግ አለማወቅ ይቅርታን የማያሰጥ መሆኑን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 81 ንዑስ አንቀጽ 1 የተደነገገ በመሆኑና የአመልካች አድራጎት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 81 ንዑስ አንቀጽ 3 ስር የማይሸፍን መሆኑን በስር ፍርድ ቤትና በይግባኝና በሰበር ከቀረበው ክርክር ለመገንዘብ የሚቻል በመሆኑ አመልካች በተከሰስኩበት ወንጀል ጥፋተኛ መባል የህግ ስህተት አለበት በማለት ያቀረበውን ክርክር አልተቀበልነውም።
በመሆኑም አመልካች ከህግ ውጭ የውጭ ምንዛሬ ይዞ የመውጣት ወንጀል ሲፈጽም የተያዘነው በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለበትም በማለት ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሰጡትን የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሣኔ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 195 ንዑስ አንቀጽ መሰረት ፀንቷል።
አመልካች በህገወጥ መንገድ ከአገር ሲያወጣ የተገኘው 5000 ዩሮ /አምስት ሺህ ዩሮ/ በውርስ ለመንግስት ገቢ መደረጉ ተገቢ ነው በማለት ወስነናል።
መዝገቡ ተዘግቷል። መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ።
No topics extracted.